የእግዚአብሔር ስጦታ

በእንዳለ ደምስስ

ጋብቻ በእግዚአብሔር ፈቃድ ለሰው ልጅ የተሰጠ ስጦታ ነው፡፡ እግዚአብሔር “ሰውን እንደ መልካችንና ምሳሌአችን እንፍጠር” ብሎ አዳምን ከምድር አፈር ሲያበጀው፣ ሔዋንንም ከአዳም ግራ ጎን አጥንት ወስዶ ሲሠራት/ሲያስገኛት ዓላማ ነበረው፡፡ ዘወትር እርሱን እያመሰገኑ እንዲኖሩ፣ እንደ ቃሉም ይጓዙ ዘንድ፣ በምድር ያለውን ሁሉ ይገዙ ዘንድ፣ … ከዓላማዎቹ ውስጥ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ እግዚአብሔር ለአዳምና ለሔዋን ባርኮ ከሰጣቸው በረከቶች ውስጥ ደግሞ አንዱ ጋብቻ ነው፡፡ “እግዚአብሔርም ባረካቸው፣ እንዲህም አላቸው፡- ብዙ፣ ተባዙ ምድርንም ሙሉአት፣ ግዙአትም”(ዘፍ.፩፥፳፰) እንዲል፡፡ ስለዚህ ጋብቻ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች የሠራው ሕግ ነው፡፡ ከሰው የሚጠበቀው ከእግዚአብሔር የተሰጠውን ስጦታ አክብሮ በሕግና ሥርዓት እንዲሁም በፍቅር ተንከባክቦ መኖር ነው፡፡

እግዚአብሔር ለአዳም ሔዋንን እንደሰጠ ሰዎችም የትዳር አጋራቸውን እንዲሰጣቸው እግዚአብሔርን አጋሬ ማን ናት/ማነው? ብሎ መጠየቅ ይገባል፡፡ እግዚአብሔር ለአዳም ሔዋንን ሲሰጠው የሠራላቸውን ሕግ ጠብቀው ቢኖሩ በረከትን፣ ከፈቃዱም ቢወጡ ደግሞ መርገምን እንደሚያገኙ አስጠንቅቋቸዋል፡፡ አትብሉ የተባሉትን ዕፀ በለስን እንዳይበሉ፣ በበሉም ጊዜ የሞት ሞትን እንደሚሞቱ አምላካዊ ውሳኔውን አስተላልፏል፡፡ እነርሱ ግን ከሰባት ዓመታት በላይ ይህንን ሕግ ጠብቆ መኖር ተስኗቸዋል፡፡ ወደተከለከሉትም ፍሬ ዓይኖቻቸው አተኮሩ፣ ማተኮር ብቻም ሳይሆን ቀጥፈው እስከ መብላት በመድረሳቸው የእግዚአብሔርን ሕግ ተላልፈዋልና መሸሸግን ምርጫቸው አደረጉ፡፡ መሸሸጋቸው ግን ሊያድናቸው አልቻለም፡፡ በዚህም ምክንያት አዳምም ሆነ ሔዋን ከመረገም አላመለጡም፡፡ “ምድር በሥራህ የተረገመች ትሁን፣ በሕይወት ዘመንህም ሁሉ በድካም ከእርስዋ ትበላለህ፣ እሾህና አሜከላ ታበቅልብሃለች” ሔዋንንም “ጭንቅሽን እጅግ አበዛለሁ፣ በጭንቅ ትወልጃለሽ” ተብላ ለእርግማን በቁ፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው ሕግን በመተላለፋቸው ነው፡፡(ዘፍ.፫፥፲፬-፲6)፡፡

እግዚአብሔር ጋብቻን ሲመሠርት አንድ ወንድ ለአንዲት ሴት አድርጎ ነው፡፡ ስለዚህ ባልና ሚስት ለመተሳሰብና በፍቅር በመኖር፣ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለመፈጸም የቆረጡ፣ ከኃጢአት ሥራ በመከልከል የእግዚአብሔርን ስጦታ አክብረው በፍቅር መኖርን መመሪያቸው ሊያደርጉ ይገባል፡፡ አብርሃም ሚስቱ ሣራን “እኅቴ” ይላት እንደነበር፣ እንዲሁም ሣራ አብርሃምን “ጌታዬ” እያለች ሁለቱም በመከባበር ይኖሩ እንደነበር ቅዱሳት መጻሕፍት ይመሰክራሉ፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንም በምልአትና በስፋት ያስተምራሉ፡፡ በዚህ ዘመን ያለን ክርስቲያኖችም ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ፣ እንደ ቀደሙት አባቶቻችንና እናቶቻችን የትዳር አጋርን ለማግኘት ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት ማጠንከር ያስፈልጋል፡፡

ስለዚህ ስለዚህ ያለን ክርስቲያኖች ወደ ጋብቻ ከመድረሳችን በፊት ልናደርጋቸው የሚገቡን ጥንቃቄዎች እንዳሉ ከላይ የቀረበው ማብራሪያ ያስረዳናል ማለት ነው፡፡ ከጥንቃቄዎቹም ውስጥ፡-

ፈቃደ እግዚአብሔርን መጠየቅ፡- ወጣትነት በቤተ ክርስቲያናችን ትምህርት በእሳት ይመሰላልና ችኩልነት፣ ይህንንም ያንንም ካልጨበጥኩ የምንልበት ዘመን ነው፡፡ በዚህ ወቅት ወንድ ለአቅመ አዳም ሴት ደግሞ ለአቅመ ሔዋን ከደረሰችበት ዕድሜ ጀምሮ የተቃራኒ ጾታ ፍላጎት መኖር ተፈጥሯዊ ነው፡፡ ነገር ግን “ካለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉም” ብሏልና አምላካችን እግዚአብሔር እንደ ፈቃዱ ልንጓዝ ያስፈልጋል፡፡ ዘወትር በእግዚአብሔር ፊት ተንበርክኮ፣ በጸሎት መጠየቅ ይገባል፡፡ ወጣትነት በሚያመጣው ችኩል አስተሳሰብና ፍላጎት ተስቦ ወደማይፈለግ ሕይወት መግባት አይገባም፡፡ ለሁሉም ጊዜ አለውና የእግዚአብሔርን ጊዜ መጠበቅ ከውድቀት ያድናል፡፡ ወንዱ ግራ ጎኔ ማን ናት? ሴቷም የእኔ አዳም ማነው? ብላ መጠየቅ ብልህነት ነው፡፡ ከእግዚአብሔር እስኪሰጥ ድረስም በትዕግሥት መጠበቅ ከኦርቶዶክሳውያን ወጣቶች የሚጠበቅ ነው፡፡ በትዕግሥት ሆነን በማስተዋል የምንጠይቀው ጥያቄ መጨረሻው ያማረ ነውና ለፈቃደ እግዚአብሔር ቅድሚያ መስጠት ያስፈልጋል፡፡

አካላዊና ሥነ ልቡናዊ ዝግጅት ማድረግ፡- አንድ ኦርቶዶክሳዊ ፈቃደ እግዚአብሔርን እየጠየቀ ለጠየቀው ጉዳይ ደግሞ ራሱን ምን ያህል ዝግጁ እንዳደረገ መረዳትና ማወቅ ይጠበቅበታል፡፡ አካላዊ ብቃት ብቻ ወደ ጋብቻ ሕይወት አያደርስም፡፡ ለአቅመ አዳም ወይም ለአቅመ ሔዋን ደርሻለሁና ማግባት አለብኝ ተብሎ ብቻ ወደ ትዳር ዘው ተብሎ አይገባም፡፡ እግዚአብሔር በሰጠው አቅምና ችሎታ የሚገነባውን ቤተሰብ መምራትና ማስተዳደር እንደሚችል መረዳት፣ በኢኮኖሚም ሆነ ከሌሎች ጋር ያለውን ግንኙነት ጤናማ ማድረግ፣ በሥነ ልቡና ረገድም እግዚአብሔር ፈቅዶ የሰጠውን የትዳር አጋሩን የሚወድ፣ መቀበልን ብቻ ሳይሆን ለመስጠትም የተዘጋጀ፣ ፍቅርን የተላበሰ፣ ቤቱን መምራት የሚችል፣ ደስታን፣ ሐዘንን፣ ችግርና ውጣ ውረድን  በጋራ መቋቋም የሚችል ሥነ ልቡና መገንባት ይጠበቅበታል፡፡

በንስሓ ሕይወት መመላለስ፡- እግዚአብሔር አምላካችን ደካማነታችንን ስለሚያውቅ፣ በመውጣት በመውረድ ውስጥ ኃጢአት መሥራታችንን ያውቃልና ንስሓን አዘጋጅቶልናል፡፡ ዘወትር በማሰብ፣ በመናገርና በማድረግ የምንፈጽመውን ኃጢአት ቆጥሮ መጨረስ አይቻልም፣ ለመደበቅም ብንሞክር ከእግዚአብሔር ዘንድ የተሰወረ አይደለምና ንስሓ መግባት ለሰው ልጆች ሁሉ የተሰጠ ነው፡፡ እንዳልተገራ ፈረስ መሮጥ፣ በደልና ኃጢአትን መሥራት፣ የሥጋ ፈቃድን ለመፈጸም መባከን አይገባም፡፡ እንደ አዳምና ሔዋን ከውድቀትና ከበደል በኋላ በንስሓ፣ በጸጸትና በዕንባ ወደ እግዚአብሔር መመለስ ያስፈልጋል፡፡ አዳም በመበደሉ አዘነ፣ ተጸጸተ፡፡ በዚህ ብቻ አላበቃም በአምላኬ፣ በፈጣሪዬ ፊት ልቆም አይገባኝም ብሎ ተሸሸገ፡፡ እግዚአብሔርም የአዳምን ከልብ መጸጸት ተረድቶያድነው ዘንድ ቃል ኪዳን ገባለት፡፡

ስለዚህ ስለ በደልና ኃጢአት እየተጸጸቱና እያለቀሱ ምሕረትን መለመን፣ እንዲሁም የምንሻውን መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ እዚህም እዚያም እያሉ የትዳር ጓደኛ የምትሆነኝን እየፈለግሁ ነው ማለት አይቻልም፡፡ በትዕግሥት እንደሚከናወንልን ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ያዕቆብ በላባ ቤት ስለ ራሔል ዐሥራ አራት ዓመታት ማገልገሉን መረዳት ተገቢ ነው፡፡ ስለዚህ የትዳር አጋራችንን እግዚአብሔር እንዲሰጠን በንስሓ ራሳችንን በመግዛት፣ በትሕትና በቅንነት እንዲሁም በትዕግሥት መለመንና እግዚአብሔርን ደጅ መጥናት ያስፈልጋል፡፡

የትዳር ጓደኛን እንዴት እንምረጥ?

የትዳር ጓደኛን ለመምረጥ በምናደርገው ሩጫ ውስጥ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ውጫዊውን ማንነት ላይ ብቻ ትኩረት ማድረግ ከጥቅሙ ጉዳቱ ስለሚያመዝን በማስተዋልና በተረጋጋ መንፈስ ከስሜታዊነት በመራቅ እግዚአብሔር ያዘጋጀልንን ለመቀበል መትጋት ይገባል፡፡ የትዳር ጓደኛን ለመምረጥ ብዙዎች ሲቸገሩ እንመለከታለን፡፡ ከራሳቸው አልፈውም በቅርባቸው ያሉትን ጓደኞቻቸውን ማግባት እፈልጋለሁ፣ ነገር ግን ማንን ላግባ? እስቲ እባክህ/ሽ ፈልጊልኝ በማለት ከራሳችን አልፈን ምርጫችንን ለሌላ ሰው አሳልፈን እንሰጣለን፡፡ መመካከር መልካም እንደሆነ ቢታመንም ያማከሩት ሁሉ ትክክለኛ መንገድ ይመራል ብሎ ማሰብ ደግሞ የዋህነት ነው፡፡ ስለዚህ አንድ ኦርቶዶክሳዊ ወጣት የትዳር ጓደኛዬን እንዴት ልምረጥ ሲል ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገባ መሠረታዊ መስፈርቶች ሊኖሩት ይገባል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ጥቂቶቹን ብንመለከት፡-

ለኦርቶዶክሳዊነት ቅድሚያ መስጠት፡- ወንድም ሆነ ሴት የትዳር ጓደኛን ለመምረጥ የራሳቸው የሆነ መስፈርት ሲያወጡ መመልከት የተለመደ ነው፡፡ አንዱ ውጫዊ አቋም ላይ ሲያተኩር ሌላው ደግሞ ውስጣዊ ውበት ላይ ትኩረት ያደርጋል፡፡ ለአንድ ትዳር መሳካት ውጫዊም ሆነ ውስጣዊ ማንነት አስፈላጊ ቢሆኑም ለኦርቶዶክስ ሃይማኖት ቅድሚያ መስጠትን ከፍተኛ ትኩረት ሊያደርጉበት ይገባል፡፡ ሁለቱም ኦርቶዶክሳውያን መሆናቸውን ካረጋገጡ ፈቃደ እግዚአብሔርን ጠይቀው እስከተገናኙ ድረስ ከውጫዊ ማንነት ይልቅ ለውስጣዊ ማንነት/ውበት ይበልጥ ሊጨነቁ ያስፈልጋል፡፡ ውጪዊ ማንነቱን አስጊጦ ውስጡ የመረረ ብዙ አለና፡፡ ብዙዎች ምርጫቸው ለውጫዊ ማንነት፣ ለሀብትና ንብረት፣ እንዲሁም ዕውቀት ቅድሚያ ስለሚሰጡ መስፈርታቸው ውስጥ ለኦርቶዶክስ ሃይማኖት የሚኖራቸው ግምት እጅግ ዝቅተኛ ነው፡፡ ተመሣሣይ ሃይማኖት ሳይኖራቸው በስሜታዊነት ተነድተው የዓለሙን ሀብት፣ ንብረትና ውበትን ብቻ በማየት ወደ ትዳር ከተገባ በኋላ ሕይወት ምስቅልቅል ያለ ይሆናል፡፡ በሃይማኖት መለያየታቸው በልጆች ሕይወት ላይ የሚፈጥረው ጫና ከፍተኛ በመሆኑ ቤተሰብን እስከመበተን ሊያደርስ ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ የሚያስከትለው ማኅበራዊ ቀውስ እጅግ የከፋ ያደርገዋል፡፡ ይህንንም ለማስተካከል እጅግ ፈታኝ በመሆኑ ከመነሻው በማሰብ ችግሩ ከመፈጠሩ በፊት ለለኦርቶዶክስ ሃይማኖት ሁለቱም ቅድሚያ ሰጥተው ምርጫቸውን ማስተካከል ይጠበቅባቸዋል፡፡

የዓላማ አንድነት መኖር፡- ጋብቻ ስለ ሦስት መሠረታዊ ዓላማዎች (ለመረዳዳት፣ ከዝሙት ለመዳን፣ ዘር ለመተካት) ከእግዚአብሔር መሰጠቱን ማመን ያስፈልጋል፡፡ ዓላማ የሌለው ትዳር ትርፉ ሕይወትን በማክበድ ለጭቅጭቅና ለጸብ የሚዳርግ ነው፡፡ በቅድሚያ ሁለቱም ለምን እንደሚጋቡ መረዳት፣ ራሳቸውንም በእግዚአብሔር ቃል እያነጹ፣ እንደ ቃሉም እየተመላለሱ በመረዳዳትና በመተሳሰብ መንፈስ ለመኖር የቆረጡ መሆን አለባቸው፡፡ በደስታቸውም ሆነ በችግር ጊዜ በመደጋገፍና ለሌሎች ምሳሌ በመሆን ከእግዚአብሔር የተሰጣቸውን በረከት ተጠቃሚ መሆን ከኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች የሚጠበቅ ነው፡፡

ከፍተኛ የዕድሜ ልዩነት የሌላቸው:- በትዳር ጓደኞች መካከል ከፍተኛ የዕድሜ ልዩነት እንዳይኖር ይመከራል፡፡ ብዙውን ጊዜ በሀገራችን በተለይም ከተማ እና ከተማ ቀመስ በሆኑ አካባቢዎች በሁለቱ ባለትዳሮች መካከል ከፍተኛ የዕድሜ ልዩነት ብዙም አይታይም፡፡ ይህ ማለት ግን በፍጹም የለም ማለት ሳይሆን ከገጠሪቱ ኢትዮጵያ አንጻር ስንመለከተው ዝቅተኛ ነው ለማለት ያህል ነው፡፡ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የወንዱ ዕድሜ ከፍተኛ ሆኖ የሴቷ ደግሞ በዐሥራዎቹ መጀመሪያ ላይ ተገድቦ ለትዳር ሲበቁ መመልከት የተለመደ ነው፡፡ በተለይም ሴቷ ላይ የሚደርሰው ጫናና አካላዊ አቅም ዝቅተኛ መሆን፣ ለተለያዩ ማኅበራዊ፣ አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ቀውሶች ይዳርጋል፡፡ ስለዚህ ከአካላዊ እስከ አመለካከት መራራቅ የሚያመጣው ችግር እጅግ የከፋ ነው፡፡

ከሕይወት ልምድ አንጻር ስንመለከተውም ሰፊ ልዩነቶች እንዲኖሩ ያደርጋል፡፡ ይህም አብረው በሚኖሩበት ዘመን ወንዱ በሴቷ ላይ ተጽእኖ የመፍጠር ዕድሉ ከፍተኛ ያደርገዋል፡፡ ገና በለጋ ዕድሜ ልጆችን በመውለድና በማሳደግ ረገድ ከወንዱ ይልቅ ሴቷ ላይ ያለው ኃላፊነትና ጫና ትልቁን ድርሻ ይወስዳል፡፡ ስለዚህ ከጋብቻ በፊት በዕድሜ መራራቅ የሚያስከትለውን ችግር በመረዳት ምርጫን ማስተካከል ያስፈልጋል፡፡

እንግዲህ በወጣትነት ዘመን ወደ ትዳር ከመግባታችን በፊት ከላይ ለተዘረዘሩትና ሌሎቹም ጉዳዮች ትኩረት መስጠት የወደፊት ሕይወትን ከማስተካከል አንጻር የሚኖራቸው ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት ምርጫን ማስተካከል ይገባል፡፡ በተለይም ኦርቶዶክሳውያን ወጣቶችና የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች ከምረቃ በኋላ ሥራ የሚፈልጉበት፣ ከቤተሰብ ጥገኝነት የሚወጡበትና የትዳር አጋርን በመፈለግ የሚባዝኑበት ጊዜ በመሆኑ ከስሜታዊነት ወጥተው ቆም ብለው ግራ ቀኙን በማየትና በማስተዋል መጓዝ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ትዳር ከእግዚአብሔር የሚሰጥ ስጦታ ነውና የተሰጠንን ስጦታ ደግሞ በትዕግሥትና በማስተዋል መቀበል የወደፊት የሕይወት አቅጣጫን የሰመረ ያደርጋል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *