“የእግዚአብሔር ልጅ የመሆን ሥልጣን (ዮሐ.፩፥፲፪)
መ/ር ኃይለ ሚካኤል ብርሃኑ
የእግዚአብሔር ልጅ የመሆን ሥልጣን የሚገኘው በእግዚአብሔር ቸርነት እንጂ በራስ ጥረትና በሹሙኝ ቅስቀሳ አይደለም፡፡ ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ እንደገለጸው “ለተቀበሉት ሁሉ ግን በስሙ ለሚያምኑ የእግዚአብሔር ልጆች እንዲሆኑ ሥልጣንን ሰጣቸው”(ዮሐ.፩.፲፪) በማለት ለተቀበሉት እና ላመኑት በጸጋ የሚሰጥ መሆኑን አስረድቷል፡፡ ይህም የሚገኘው ዳግም ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከማሕፀነ ዮርዳኖስ በመወለድ ነው፡፡
ዳግም ልደት ማለት ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ማለትም ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ፣ ከማኅፀነ ዮርዳኖስ መወለድ ሲሆን፣ የሥላሴ ልጅነትን ያስገኛል፡፡ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ወንዱ በተወለደ በዐርባኛው ቀን፣ ሴቷ በተወለደች በሰማንያ ቀኗ ዳግም ከውኃና ከመንፈስ እንዲወለዱ ታደርጋለች፡፡ ለዚህም መነሻዋ መጽሐፍ ቅዱስን አስረጅ በማድረግ አዋልድ መጻሕፍትን እና ትውፊታዊ አስተምህሮዋን ተከትላ ነው(ኩፋ.፬፥፱)፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሌሊት ወደ እርሱ እየመጣ ይማር ለነበረው ለኒቆዲሞስ ስለ ዳግም ልደት ሲያስተምረው እንዲህ አለው፡፡ “እውነት እውነት እልሃለሁ ዳግመኛ ያልተወለደ ሰው የእግዚብሔርን መንግሥት ለማየት አይችልም” ካለው በኋላ ኒቆዲሞስ ስላልገባው በነገሩ ግራ በመጋባቱ ሰው ዳግመኛ እንዴት መወለድ ይችላል? ሲል ጠየቀው፡፡ ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፡፡ “እውነት እውነት እልሃለሁ ዳግመኛ ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ያልተወለደ ሰው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም፡፡ ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነውና፤ ከመንፈስ የተወለደ መንፈስ ነውና” (ዮሐ.፫፥፫-፮) በማለት አስረዳው፡፡
የሰው ልጅ ዳግም ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ሲወለድ የእግዚአብሔር ልጅ ይሆናል፡፡ መንፈስ ቅዱስም ስለሚያድርበት የእግዚአብሔር ማደሪያ፣ ለእግዚአብሔር የተለየ ዙፋን፣ የእግዚብሔር ቤተ መቅደስ ይባላል፡፡ በዘመነ አበውም ሆነ በዘመነ ኦሪት ራሳቸውን ከርኩሰትና ከኃጢአት ለይተው ለእግዚአብሔር ክብር ከተለዩ ምእመናን ጋር እግዚአብሔር በረድኤት ነበረ፡፡
በሐዲስ ኪዳንም የእግዚአብሐር ልጅ የመሆን ሥልጣንን ያገኘ ሰው አካሉ የመንፈስ ቅዱስ ቤት ማደሪያ ይሆናል፡፡ ይህንን የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ የሆነ አካል በንጽሕና በቅድስና መያዝ የሚያድርበትን እግዚአብሔርን ማክበር ነው፡፡ እግዚአብሔር ንጹሐ ባሕርይ ነውና ያድርበት ዘንድ ንጹሕ ነገርን ይወዳል፡፡ በኃጢአትና በበደል በተጐሳቆለ አካል ላይ እግዚአብሔር አያድርም፡፡ የእርሱ ማደሪያ፣ ለመሆን በኃጢአት ያደፈውን ማንነት በንስሓ ማጠብና ማንጻት ያስፈልጋል፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በላከላቸው መልእክቱ “ሥጋችሁ ከእግዚአብሔር ለተቀበላችሁት በእናንተ አድሮ ላለ ለመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደ ሆነ አታውቁምን? ለራሳችሁ አይደላችሁም በዋጋ ተገዝታችኋልና ስለዚህም እግዚአብሔርን በሥጋችሁ አክብሩት” (፩ኛቆሮ ፮፥፲፱) ይላልና፡፡
ሐዋርያው እንደገለጸው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ የተሰቀለውና ደሙን ያፈሰሰው በዲያብሎስ ግዛት ሥር ወድቆ የነበረውን፤ የሰው ልጅ ነጻ ለማውጣት ነው፡፡ በሲኦል የነፍስ መገዛትን፤ በመቃብር የሥጋን መበስበስ፣ አስወግዶ በፊቱ ሕያዋን አድርጎ ሊያቆመን ስለ በደላችን የደሙን ዋጋ ከፍሎ ገዝቶናልና የራሳችን አይደለንም፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ በመሆን የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ መሆናችን እያስተዋልን ከኃጢአት ልንርቅና ከበደል ልንነጻ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም ነው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ፡-
“እናንተ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደሆናችሁ የእግዚአብሔር መንፈስም በእናንተ ላይ አድሮ እንደሚኖር አታውቁምን? የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ የሚያፈርሰውን ግን እርሱን ደግሞ እግዚአብሔር ያፈርሰዋል፤ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ነውና፤ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስም እናንተ ራሳችሁ ናችሁ፤ እንግዲያስ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ አታርክሱ” (፩ኛቆሮ.፫፥፲፮)ያለን፡፡
የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መሆን እጅግ የከበረ ማንነት ነው፡፡ ይህም የሚያሳየው እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ምን ያህል እንዳከበረውና እንደወደደው ነው፡፡ ለሰው ልጅ ወደር የሌለው ፍቅሩን የገለጠበትም ታላቅ ምሥጢር ነው፡፡ እግዚአብሔርን ያህል በባሕርዩ ቅዱስ የሆነ ጌታ በእኛ በደካሞችና፣ በበደለኞች አካል ማደሩ እጅግ የሚያስደንቅ ቸርነት ነው፡፡ ይህንን ስንረዳ እግዚአብሔር ለእኛ ያደረገውን ምሕረት እናደንቃለን፡፡
በወንጌል እንደ ተጻፈው በእርሱ ሕይወት ይሆንልን ዘንድ የሚወደውን አንድያ ልጁን ወደ ጎስቋላዋ ዓለም ልኮታል፡፡ “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለም ሕይወት እንዲያገኝ እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ቤዛ አድርጎ እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲህ ወዶታልና”(ዮሐ.፫፥፲፮)፡፡
እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍጹም ፍቅሩን ማስተዋል ከቻልን የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ የሆነ አካላችንን የኃጢአት መሣሪያ ለማድረግ አንደፍርም፡፡ ምክንያቱም ቀደም ብለን እንዳየነው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “በዋጋ ተገዝታችኋልና የራሳችሁ አይደላችሁም” በማለት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዋጋ የገዛን ገንዘቡ እንደሆንን አስገንዝቦናል፡፡
የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ከተረዳን የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ እንደሆንን መገንዘብ አለብን፡፡ ይህንን ከተረዳን ደግሞ አካላችን በኃጢአት ማቆሸሽ እንደሌለብን፤ በንጽሕና በቅድስና መኖር እንደሚገባን አውቀን ራሳችንን በንስሓ ታጥበን ንጹሓን መሆን ይገባናል፡፡ የእግዚአብሔር ልጆች ነንና ስለ ኃጢአታችን እንዳይፈረድብን አካሎቻችንን ሁሉ ለእግዚአብሔር አገልግሎት ልናውላቸው ያስፈልጋል፡፡
አንዳንድ ሰዎች ግን ይህንን ባለ መረዳት ሰውነታቸውን ሲያረክሱና ሲያቆሽሹ ራሳቸውን ከእንስሳት በታች ሲያደርጉ ይታያሉ፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት የሰው ልጅ ቢያውቅበት ምንኛ ታላቅ እንደሆነ በመዝሙሩ ሲገልጽ፡- “ሰው ግን ክቡር ሆኖ ሳለ አላወቀም፣ ልብ እንደሌላቸው እንስሶችም ሆነ፣ መሰላቸውም” (መዝ.፵፰፥፲፪)ይላል፡፡
የሰው ልጅ ክብሩ(የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑ) እውን የሚሆነው ያከበረውን እግዚአብሔርን በሰውነቱ ማክበርና፣ አካሉ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መሆኑን ተረድቶ ከኃጢአት ሲለይ ብቻ ነው፡፡ ሰው በጥምቀት የእግዚአብሔር ልጅ የመሆን ሥልጣንን ስለሚያገኝ ከእግዚአብሔር ቸርነት የተነሣ የተቀደሰና የተከበረ ነው፡፡ ለዚህም ነው ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌሉ “ለተቀበሉት ሁሉ ግን በስሙ ለሚያምኑ የእግዚአብሔር ልጆች እንዲሆኑ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከሥጋዊና ከደማዊ ግብር ወይም ከወንድና ከሴት ፈቃድ አልተወለዱም” (ዮሐ.፩፥፲፪)ያለው፡፡
የእግዚአብሔር ልጅ የመሆንን ሥልጣን የተሰጣቸው ሁሉ ድካም ገጥሟቸው ኃጢአትን በመሥራት የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ የሆነ አካላቸውን በሚያሳድፉበት ወቅት ወዲያውኑ ንስሓ በመግባት ከኃጢአት መንጻት አለባቸው፡፡ ንስሓ ኃጥኡን ጻድቅ፣ ዘማዊውን ድንግል ያደርጋልና፡፡ ኃጢአትን የሠሩ ምእመናን ንስሓ በገቡ ጊዜ ከኃጢአታቸው ይነጻሉ፡፡ በሚነጹበትም ጊዜ ንጹሓን የእግዚአብሔር ማደሪያዎች ናቸውና ቅዱሳን ይባላሉ፡፡
የእግዚአብሔር ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን፡፡ አሜን፡፡
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!