“የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ” (፩ኛዮሐ. ፫፥፰)
ክፍል አራት
በመ/ር ኃይለሚካኤል ብርሃኑ
እግዚአብሔር ሰውን መውደዱ በባሕርይ ልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ መገለጥ ፍጹም መሆንን ተረዳን፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ በማለት ቅዱስ ዮሐንስ በመልእክቱ የመሰከረው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ እርሱም ቅድመ ዓለም የነበረ ዛሬም ያለ ወደፊትም ዓለምን አሳልፎ የሚኖር አልፋና ዖሜጋ ነው፡፡ ዓለምንም ለማዳን ሲል ከዘመን በኋላ ጊዜውና ሰዓቱ ሲደርስ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም መወለዱ ፍጹም ፍቅሩ የታየበት መገለጥ ነው፡፡ የማይወሰነው አምላክ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ ሕግ ጠባይዓዊንና ሕግ መጽሐፋዊን በትክክል ሲፈጽም የታየበት ስለ ሆነ የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ በማለት ቅዱስ ዮሐንስ ስለርሱ መስክሯል፡፡ የመገለጡ ዋና ዓላማም ምን እንደሆነ በጥቂቱ ለማየት ቀደም ብለን የተመለከትናቸው እንዳሉ ሆነው በዚሁ ክፍልም የሚከተለውን እናያለን፡፡
ከጨለማ ወደ ብርሃን ሊያወጣን
ከበደል በኋላ የሰው ልጅ በጨለማና በሞት ጥላ ሥር በመሆን እረኛ እንደሌለው መንጋ ሲቅበዘበዝ ይኖር ነበር፡፡ መቅበዝበዛችንን አይቶ በፍቅሩ ይሰበስበን ዘንድ በጨለማ መኖራችንን አርቆ በብርሃኑ እንድንመላለስ ያደርገን ዘንድ አማናዊው ብርሃን በሥጋ ተገለጠ፡፡ በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ የጨለማው አበጋዝ ዲያብሎስ ፈራ ደነገጠ፡፡ እንዲህ አይነት የእግዚአብሔር መገለጥ ጥንተ ጠላታችን ዲያብሎስን ያስደነገጠ መገለጥ ነው፡፡ ምክንያቱም ሰይጣን እንኳን አይቶት የማያውቀውን ትሕትና ያሳየበት፣ለሰው ያለው ፍቅር እስከ ምን ድረስ እንደሆነ እንድናስተውል በሥጋ መገለጡንም ዕፁብ ዕፁብ ብለን ትሕትናውን እና ለሰው ልጅ ያለውን ፍቅር እንድናደንቅ አድርጎናል፡፡
ሕይወታችን በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ በሞት ጥላ ሥር ሆኖ በባርነት ተይዘን ነበር፡፡ የእርሱ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከቅድስት ድንግል ማርያም መወለድ ያንን አስጨናቂ የጨለማ ኑሮ አርቆ በብርሃን እንድንመላለስ አደረገን፡፡ ለዚህም ነው ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ኢሳይያስ፡- “በጨለማ የሄደ ሕዝብ ታላቅ ብርሃን አየ በሞት ጥላና በጨለማ ሀገርም ለነበሩ ብርሃን ወጣላቸው”(ኢሳ.፱፥፪) በማለት ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ መገለጥ አስቀድሞ የሰው ልጅ ኑሮው በጨለማ ውስጥ እንደነበረና በኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ብርሃን እንደ ወጣልን መስክሯል፡፡
ቅዱስ ኢሳይያስ ታላቅ ብርሃን በማለት የገለጸው ኢየሱስ ክርስቶስን ነው፡፡ እርሱ የብርሃናት ብርሃናቸው ነውና ከእርሱ ብርሃንነት ቅንጣት ሰጥቷቸው በዓለም ላይ እንዲያበሩ ፀሐይን በቀን፣ጨረቃና ከዋክብትን በሌሊት እንዲሠለጥኑ ያደረገ የዓለማት ዓለማቸው ኢየሱስ ክርስቶስ
ታላቅ ብርሃን ነውና፡፡ ብርሃናውያን ቅዱሳን መላእክትን በኀልዮ የፈጠረ የመላእክት አስገኚ፤ ሰማይንና ሰማያውያንን ምድርንና ምድራውያንን በቃሉ የፈጠረ የሁሉ አስገኚ ስለ ሆነ ታላቅ ብርሃን ተብሏል፡፡
ለዚህም ነው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል፡- “ እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃንን ያገኛል እንጂ በጨለማ አይመላለስም” (ዮሐ.፰፥፲፪ በማለት እርሱን በመንገዱ ሁሉ የሚከተል የሕይወት ብርሃን እንደሚሆንለት ከጨለማ ኑሮ ወጥቶ በብርሃን እንደሚመላለስ ያስተማረን፡፡
ብርሃን ጨለማን አርቆ ማየት የምንችለውን ሁሉ እንድናይ ዕድል እንደሚፈጥርልን ሁሉ አማናዊውን ብርሃናችንን ኢየሱስ ክርስቶስን መከተል ስንችል ከጨለማው ዓለም ወጥተን በዘላለም ብርሃን ውስጥ ያለውን ክብር ማስተዋል እንችላለን፡፡ ይህም ማለት የምድሩን ሳይሆን የሰማዩን፣ቁሳዊውን ሳይሆን መንፈሳዊውን፣ ጊዜያዊውን ሳይሆን ዘላለማዊውን፣ታይቶ የሚጠፋውን ሳይሆን ለዘለዓለም የሚኖረውን፣ ከሰው የሆነውን ሳይሆን ከእግዚአብሔር የሆነውን በእምነት መመልከት እንችላለን ማለት ነው፡፡
ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊትም በመዝሙሩ “የሕይወት ምንጭ ከአንተ ዘንድ ነውና በብርሃንህ ብርሃንን እናያለን”(መዝ.፴፭፥፱) በማለት የተቀኘለት መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጨለማውን ዓለም ወደ ብርሃን እንደሚያወጣው በትንቢት መነጽር በመመልከቱ ነው፡፡ በጨለማ ውስጥ መኖር ትርፉ ኀዘን፣ልቅሶ፣ዋይታ፣ሞት፣ፍርሀት፣ጭንቀት፣ጉስቁልና ወ.ዘ.ተ ነው፡፡
ከዚህ ጨለማ ከነገሠበት መራራ ሕይወት ተላቆ ብርሃን በሆነ በደስታ፣በሰላም፣በዕረፍት፣በሕይወት፣በክብር በነፃነት መኖር ምን ያህል ከፍታ እንደሆነ ሲገባን የሚያስፈራውን ድቅድቁን ጨለማ በሚደነቀው ብርሃኑ ለውጦ ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ከሞት ወደ ሕይወት፣ከባርነት ወደ ነፃነት ከፍርሃት ወደ ሰላም ከመቅበዝበዝ ወደ መረጋጋት ወደ ዕረፍት ያሸጋገረን አምላካችን ልዑል እግዚአብሔርን በነገር ሁሉ እናመሰግናለን፡፡ ልባችንም በፍቅሩ የተማረከ፣አንደበታችን ለምስጋና የተከፈተ ይሆናል፡፡
ጠቢቡ ሰሎሞን እንደተናገረው የሰው ሰላሙ የሚረጋገጠው በብርሃን ነው፡፡ በጨለማ ውስጥ ሰላም የለም ምክንያቱም ጨለማ በራሱ በሞትና በፍርሃት እንዲሁም በባርነት ውስጥ መኖር ነው፡፡ ለዚህም ጠቢቡ ሰሎሞን የጨለማን አስከፊነትና የብርሃንን መልካምነት በገለጸበት ክፍል፡-“ብርሃን ጣፋጭ ነው ፀሐይንም ማየት ለዐይን መልካም ነው ሰው ብዙ ዘመን በሕይወት ቢኖር በሁሉም ደስ ቢለው የጨለማውን ዘመን ያስብ ብዙ ቀን ይሆናልና የሚመጣውም ነገር ሁሉ ከንቱ ነው፡፡ ”(መክ.፲፩፥፯) በማለት የጨለማ ኑሮ መራራ እንደሆነ ገልጾልናል፡፡ ከዚህ ጨለማ ከነገሠበት ዓለም የጨለማውን ሥልጣን ሽሮ ወደ ብርሃን የመለሰን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ ማርያም ተገልጦ ነው፡፡
ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን በዓለም ሲገለጥ ጨለማው ተወገደ፣ሞት ደነገጠ፣ ፍርሃትም ነግሦ የነበረበትን የሰው ሕይወት ለቀቀ፡፡ ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም በውዳሴው እንደገለጸው፡-“ ብርሃን ዘበአማን ዘያበርህ ለኲሉ ሰብእ ለእለ ይነብሩ ውስተ ዓለም በእንተ ፍቅረ ሰብእ መጻእከ ውስተ ዓለም ወኲሉ ፍጥረት ተፈሥሐ በምጽአትከ እስመ አድኃንኮ ለአዳም እምስሕተት ወረሰይካ ለሔዋን አግዓዚተ እምፃዕረ ሞት ወወሀብከነ መንፈስ ልደት ባረክናከ ምስለ መላእክቲከ፤በዚህ ዓለም ለሚኖሩ ሰዎች ሁሉ የምታበራ እውነተኛ ብርሃን ስለሰው ፍቅር ወደ ዓለም የመጣው ፍጥረት ሁሉ በመምጣትህ ደስ አለው አዳምን ከስህተት አድነኸዋልና ሔዋንንም ከሞት ፃዕረኝነት ነፃ አድርገኻታልና የምንወለድበትን መንፈስ (ረቂቁን ልደት) ሰጠኸን ከመላእክት ጋርም አመሰገንህ፡፡”(ውዳሴ ማርያም ዘሰኑይ) በማለት ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለም የተገለጠው ጨለማ በነገሠበት ዓለም ለምንኖር ለሰው ሁሉ የሚያበራ እውነተኛ ብርሃን ሆኖ እንደሆነ ገልጾታል፡፡
አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር ወደ ተናቀው ዓለም የመጣው ስለሰው ፍቅር በመሆኑ የአዳምን በደል ይቅር በማለት ሔዋንንም የሞት ተገዢ ከመሆን ነፃ በማውጣት ዳግመኛም ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ የምንወለድበትን ረቂቁን ልደት መሠረተልን፡፡ በዳግም ልደትም ሰማያዊውን ዜግነት አንድናገኝ የእግዚአብሔር ልጆች የመሆን ሥልጣን ሰጠን፡፡
ለዚህ ክብር በመብቃታችንም ደስ ብሎን እንድናመሰግነው ከቅዱሳን መላእክት ጋር በምስጋና እንድንተባበር አደረገን፡፡ ይህም እግዚአብሔር ለሰው ያለውን ፍጹም ፍቅሩን የገለጠበት የማዳን ሥራው ነው፡፡ እኛም እንዲህ የወደደን እግዚአብሔርን በሁሉ ነገር ልናመሰግነው ይገባናል፡፡ ጨለማውን አርቆ በብርሃን እንድንመላለስ ብርሃን ሆኖ ተገልጦልናልና የብርሃንን ጋሻ ጦር እንልበስ፡፡
ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ፡- “ከእንቅልፍ የምትነቁበት ጊዜ እንደደረሰ ዕወቁ ካመንበት ጊዜ ይልቅ መዳናችን ዛሬ ወደ እኛ ደርሳለችና ሌሊቱ አልፎአል ቀኑም ቀርቦአል እንግዲህ የጨለማን ሥራ ከእኛ እናርቅ የብርሃንንም ጋሻ ጦር እንልበስ በቀን እንደሚሆን በጽድቅ ሥራ እንመላለስ በዘፈንና በስካር በዝሙትና በመዳራትም አይሁን በክርክርና በቅናትም አይሁን ነገር ግን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ልበሱት የሥጋችሁንም ምኞት አታስቡ፡፡”(ሮሜ ፲፫፥፲፩) በማለት የገለጸው መዳናችን ወደ እኛ ደርሳለችና የጨለማ ሥራ የተባለው ኃጢአትን አስወግደን በጽድቅ ሥራ አጊጠን መገኘት እንደሚገባን ሲያስገነዝበን ነው፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ልበሱት እንደተባልን ክርስቲያናዊ ሕይወታችንን በምግባር አስጊጠን ልንገኝ ይገባናል፡፡ ሕይወታችንን በቀናው ጎዳና መርቶ በብርሃኑ እንድንመላለስ አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር በቸርነቱ ይርዳን፡፡ ይቆየን…
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!