የኒቆዲሞስ መንፈሳዊ ዕድገት
ኤልያስ ገ/ሥላሴ
አሐቲ፣ ቅድስት፣ ኵላዊት እና ሐዋርያዊት የሆነችው ቤተክርስቲያናችን እኛ ምእመኖቿ በዓለም ሐሳብ ድል እንዳንነሣ፣ ይልቅስ ፍትወታትን ሁሉ ድል አድርገን ራሳችንን ገዝተን (ተቈጣጥረን) በውስጣችን ፈቃደ እግዚአብሔርን አንግሠን ምድራዊውን ሳይሆን ሰማያዊውን እያሰብን እንድንኖር በዓመቱ ውስጥ በተለያዩ ወራት የሚጾሙ አጽዋማትን ሠርታልናለች፡፡ ከነዚህ አጽዋማት ውስጥ አንዱና ዋነኛው ደግሞ አሁን በዚህ ወቅት እየጾምነው ያለነው ዐቢይ ጾም ነው፡፡ ዐቢይ ጾም የኀምሳ አምስት ቀን ጾም ሲሆን፣ በውስጡም ስምንት ሳምንታት አሉ፡፡ እነዚህ ስምንት ሳምንታት ሁሉም የየራሳቸው መጠሪያ ስም ሲኖራቸው ሰባተኛው ሳምንት ኒቆዲሞስ በመባል ይታወቃል፡፡
ይህ ሰባተኛ ሳምንት ታሪኩን በዮሐንስ ወንጌል ምዕ.፫፤፩ ጀምሮ በምናገኘው በኒቆዲሞስ ስም የተሰየመ በመሆኑ ነው፡፡ ኒቆዲሞስ ከፈሪሳውያን ወገን ሲሆን የእስራኤል መምህርና የአይሁድ ሸንጎ አባል ነበር፡፡ የስሙ ትርጓሜም “የሕዝብ ገዢ” እንደ ማለት ሲሆን፣ በትውፊት እንደሚታወቀው ኒቆዲሞስ በአይሁድ ላይ አለቃ ከመሆኑ በተጨማሪ እጅግ ባለጸጋም ነበር፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፋሲካ በዓል በኢየሩሳሌም ሳለ ያደረገውን ተአምራት አይተው ብዙዎች አምነውበት ነበር፡፡ ኒቆዲሞስም ከነዚህ ምልክትን አይተው ካመኑ አማኞች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ (ዮሐ.፪፥፳፫)፡፡ ኒቆዲሞስ በሌሊት ወደ ኢየሱስ ሄዶ “መምህር ሆይ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ምልክቶች ሊያደርግ የሚችል የለምና መምህር ሆነህ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደመጣህ እናውቃለን” እንዳለውም ተጽፏል፡፡ (ዮሐ.፫፡፪)፡፡ ይሁንና ኒቆዲሞስ የኦሪት ሊቅ እንደመሆኑ መጠን በብሉይ ኪዳን ዘመን እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር በመሆኑ ምክንያት ታላላቅ ድንቆችንና ምልክቶችን ሲያደርጉ ስለነበሩ ነቢያት ያውቅ ነበርና ኢየሱስ ክርስቶስም እንደ ሙሴና ኢያሱ ሁሉ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ስለሆነ ድንቆችን የሚያደርግ እንደሆነ እንጂ ራሱ እግዚአብሔር እንደሆነ አላወቀም ነበር፡፡ (ዘፍ.፳፮፥፳፬፤ኢያ.፩፥፭)
ኒቆዲሞስ በሌሊት ወደ ጌታ መምጣቱ (ዮሐ.፫)
ኒቆዲሞስ በመጀመሪያ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ የመጣው በቀን ሳይሆን በሌሊት ነበር፡፡ ለዚህም የቤተ ክርሰቲያን አባቶች በዋናነት ሁለት ምክንያቶችን ያስቀምጣሉ፡፡ የመጀመርያው የአይሁድ መምህር ሆኖ ሳለ በቀን በሕዝብ ፊት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መማር ስላፈረ ነው የሚል ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ አይሁድ “ከእኛ ወገን በክርስቶስ ያመነ ቢኖር ከምኩራብ ይሰደድ” የሚል አዋጅ አውጀው ነበርና ያንን ፈርቶ ነው ይላሉ፡፡ ነገር ግን እነዚህ ፍራቻዎች ኒቆዲሞስን ወደ ክርስቶስ ከመምጣት አላገዱትም፡፡
ኒቆዲሞስ በርቀት በአደባባይ ድንቅ ተአምራትን ሲያደርግ ያየውን ኢየሱስ ክርስቶስን ቀርቦ መጠየቅ ፈልጓል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ካደረጋቸው ተአምራት የተረዳው ነገር ቢኖርም ቀርቦ ደግሞ ከእርሱ ከራሱ ስለማንነቱ መስማት ፈልጓል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ በኒቆዲሞስ እይታ እግዚአብሔር አብሯቸው እንደነበረ እንደቀደሙት የእስራኤል አባቶች መስሎት ነበር፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር አብሮት ካለ ሰው በስተቀር እርሱ የሚያደርጋቸውን ተአምራት ሊያደርግ የሚችል የለምና፡፡ ወደ ክርስቶስ ቀርቦም ያለው ይህንኑ ነው፡፡ “መምህር ሆይ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ምልክቶች ሊያደርግ የሚችል የለምና መምህር ሆነህ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደመጣህ እናውቃለን” አለ፡፡
ኒቆዲሞስ መጀመሪያ ወደ ክርስቶስ ሲመጣ ልክ እንደ ናትናኤል “መምህር ሆይ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ” (ዮሐ.፩፥፶) ብሎ አምላክነቱን አምኖና መስክሮ አልነበረም፡፡ በኒቆዲሞስ እይታ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእግዚአብሔር ተልኮ የመጣ መምህር መሰለው እንጂ አምላክነቱን አልተረዳም ነበር፡፡ የክርስቶስ አምላክነት እና የዓለም መድኃኒትነት ገና አልተገለጠለትም፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ይህንን ስላወቀ ለኒቆዲሞስ የሚድንበትን እና ስለ እርሱ ማንነት የሚያውቅበትን ትምህርት አስተምሮታል(ዮሐ.፫፥፲፫)፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለኒቆዲሞስ ያስተማረውን ሲያብራራ “ሰው ከውኃና ከመንፈስ ድጋሜ ካልተወለደ በስተቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ማየት አይችልም፡፡ አንተ ገና ከእግዚአብሔር አልተወለድክምና ስለ እኔ ያለህ ዕውቀት መንፈሳዊ ሳይሆን ሥጋዊና ሰዋዊ ነው፤ ግን እልሃለሁ ማንም ሰው ከእግዚአብሔር ድጋሚ ካልተወለደ በስተቀር ክብሬን ማየት አይችልም ከመንግሥቴም ውጪ ነው” እንዳለ፡፡
ኒቆዲሞስ ፈሪሳዊ ነው፡፡ ፈሪሳውያን ደግሞ የአብርሃም ልጆች በመሆናቸው እጅግ የሚመኩና ዳግም ስለመወለድ ቢነገራቸው ፈጽመው የማይቀበሉ ነበሩ (ዮሐ.፰፥፴፫)፡፡ ኒቆዲሞስ ግን ምንም ስንኳ ከፈሪሳውያን ወገን ቢሆንም ክርስቶስ ዳግም መወለድ እንዳለበት ሲነግረውና የአይሁድ መምህር ሆኖ ሳለ ክርስቶስ እየነገረው ያለውን ነገር ባለመረዳቱ ምክንያት “አንተ የእስራኤል መምህራቸው ነህ፣ ነገር ግን ይህን እንዴት አታውቅም?” ብሎ ሲገሥጸው በእምነት ተቀብሎ ተጨማሪ ጥያቄ ወደ መጠየቅ አለፈ እንጂ “የአብርሃም ዘር ሆኜ ሳለ እንዴት ድጋሚ መወለድ አለብህ ትለኛለህ?” አላለም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የአይሁድ መምህር ሆኖ ሳለ ምንም ስንኳ በቀን በሰዎች ፊት ሊያደርገው ባይደፍርም የራሱን ኩራት (ትዕቢት) አሸንፎ ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጠይቆ ለመማር ወደኋላ አላለም፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ይህን ፍላጎቱ በማየት ታላቁን ምሥጢር አስተምሮታል፡፡ “ለተቀበሉት ሁሉ ግን በስሙ ለሚያምኑ የእግዚአብሔር ልጆች እንዲሆኑ ሥልጣንን ሰጣቸው” (ዮሐ.፩፥፲፪)ተብሎ እንደተጻፈ፡፡ ይህ ልጅነት እንዴት እንደሚሰጥ በግልጥ የተነገረውም ለኒቆዲሞስ ነው (ዮሐ፫፥፭)፡፡ ይህን ታላቅ ምሥጢር የገለጸለትም ስለ ትሕትናውና ራሱን ዝቅ ስለ ማድረጉ ነው፡፡
ሰው በማንነቱና ባለው ነገር ለራሱ ከፍተኛ ግምት ሲኖረው በትዕቢት ኃጢአት ይወድቃል፡፡ ሰው በሀብቱ፣ በሥልጣኑ፣ በዘሩ፣ በዘመዶቹ፣ በዕውቀቱ፣ በመልኩ …ወዘተ ምክንያት የትዕቢት ስሜት ሊያድርበት ይችላል፡፡ ክርስቲያን የሆነ ሰው ግን እነዚህ ሁሉ አላፊና ጠፊ መሆናቸውን አውቆ ትምክህቱን ሊያድኑት ከማይችሉ ምድራዊ ነገሮች ላይ አንሥቶ በእግዚአብሔር ላይ ማድረግ አለበት(መዝ.፻፵፭፥፫፤ መዝ ፫፥፰)፡፡ ከነዚህም በተጨማሪ ትዕቢት በትሩፋት ሕይወት ላይ ያሉትን ሳይቀር ሊያጠምድ ይችላል፡፡ የሚጾመው ከማይጾመው፣ የሚጸልየው ከማይጸልየው፣ የሚያስቀድሰው ከማያስቀድሰው፣ የሚመጸውተው ከማይመጸውተው፣ ትሑቱ ከትዕቢተኛው፣ መነኩሴው ከሕጋዊው፣ ገዳማዊው ከዓለማዊው፣ ክርስቲያኑ ከአሕዛቡ … ወዘተ እሻላለሁ በሚል የትዕቢት ስሜት እንዳይወድቅ መጠንቀቅ አለበት፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሳቸውን ለሚያመጻድቁና ባልንጀራቸውን ለሚንቁ እንዲህ ብሎ መለሰላቸው “ሁለት ሰዎች ሊጸልዩ ወደ ቤተ መቅደስ ወጡ አንዱ ፈሪሳዊ ሁለተኛውም ቀራጭ ነበር፡፡ ፈሪሳዊውም ቆመና እንዲህ ብሎ ጸለየ “አቤቱ እንደ ሌሎች ሰዎች እንደ ቀማኞችና እንደ ዐመፀኞች እንደ አመንዝሮችም ወይም እንደዚህ ቀራጭ ያላደረግከኝ አመሰግንሃለሁ፡፡ እኔ በየሳምንቱ ሁለት ቀን እጾማለሁ፣ ከማገኘውም ሁሉ ከዐሥር አንድ እሰጣለሁ፡፡” ቀራጩ ግን ራቅ ብሎ ቆመ፤ ዓይኖቹንም ወደ ላይ ወደ ሰማይ ሊያነሣ አልወደደም፤ ደረቱን እየመታ “አቤቱ እኔን ኃጢአተኛውን ይቅር በለኝ” አለ፡፡ እላችኋለሁ ከዚያኛው ይልቅ ይህ ጻድቅ ሆኖ ወደ ቤቱ ተመለሰ፡፡ ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳልና፤ ራሱንም የሚያዋርድ ይከብራልና፡፡”(ሉቃ.፲፰፥፲-፲፬)፡፡ ስለዚህ ትዕቢት ወደ ኃጢአት የማይቀይረው ምንም ትሩፋት እንደሌለ ማስተዋልና እርምጃችንን ሁሉ በጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
ኒቆዲሞስ ባለ ሀብት፣ የአይሁድ መምህር እና አለቃ ሆኖ ሳለ በትዕቢት ሳይያዝ ራሱን በመንፈስ ድኃ አድርጎ ስለቀረበ “በመንፈስ ድኆች የሆኑ ብፁዓን ናቸው መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና” በሚለው ቃል መሠረት መንግሥተ ሰማያትን ገንዘብ ማድረግ የሚችልበትን ትምህርት እንዲማር ሆኗል ምሥጢሩንም ገልጾለታል፡፡(ማቴ ፭፥፫)፡፡
ዳግም መወለድ ማለት ሥጋዊ፣ ምድራዊና ጊዜያዊ የሆነውን የድሮ ማንነታችንን ትተን መንፈሳዊ፣ ሰማያዊና ዘለዓለማዊ የሆነውን አዲስ ማንነት ገንዘብ ማድረግ ማለት ነው፡፡ ይህ አዲስ ማንነትም ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ከመወለድ የሚገኝ ነው፡፡ ያጣነውንና የተወሰደብንን ጸጋ እርሱም የእግዚአብሔር ልጅነት የምናገኘው በጥምቀት ነው፡፡ “ጌታችን ከመንፈስ ቅዱስ እንድንወለድ ያዘዘን ሥጋዊው ልደት በሥጋ የወለዱንን የእናት የአባታችንን ርስት ያወርሰናል እንጂ ሰማያዊውን ርስት ሊያወርሰን አይችልምና ነው፡፡ ሰማያዊውን ርስት ልንወርስ የምንችለው መንፈሳዊውን ልደት ስንወለድ ነው፡፡ “እንኪያስ እናንተ ልጆች ናችሁ እንጂ ባሮች አይደላችሁም፤ ልጆች ከሆናችሁም በኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ወራሾች ናችሁ፡፡” (ገላ ፬፥፯) እንዲል፡፡ መንፈሳዊውን ልደት የምንወለድ ደግሞ ከመንፈስ ቅዱስ ስለሆነ ዳግመኛ ከውሃና ከመንፈስ ቅዱስ ያልተወለደ የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም በማለት አስተማረው፡፡
ጥምቀት ዳግመኛ ተወልደን ክርስቶስን የምንመስልበት ነው፡፡ “እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እኔን ምሰሉ” (1፩ኛቆሮ.፲፩፥፩) እንዳለ ሐዋርያው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ይህንን ለኒቆዲሞስ ሲያብራራ “ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው” እንዳለ ከሥጋ የተወለደ ሥጋን እንደሚመስል ከመንፈስ ቅዱስ የተወለደም መንፈስ ቅዱስን ይመስላልና፡፡(ዮሐ.፫፥፮)
ኒቆዲሞስ ስለ ጌታ ከአይሁድ ጋር መከራከሩ (ዮሐ.፯)
ኒቆዲሞስ ጌታ በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ሦስት ላይ ያስተማረውን ትምህርት ተቀብሎና አምኖ ሄዷል፡፡ ለዚህም ሁለት ማሳያዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡ የመጀመርያው የወንጌላቱ ጸሓፍያን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰዎች ጋር ያደረገውን ንግግር ሲጽፉ ሰዎቹ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ትምህርት የተቀበሉት እንደሆነ በዝምታ ያልፉታል፣ ያልተቀበሉት እንደሆነ ግን ይጽፉታል፡፡ ለምሳሌ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን “የዘላለም ሕይወት እንዳገኝ ምን መልካም ነገር ላድርግ” ብሎ የጠየቀው ሰው የክርስቶስን መልስ ከሰማ በኋላ አለመቀበሉ ተጽፏል፡፡ (ማቴ.፲፱፥፳፪፣ማር.፲፥፳፪፣ሉቃ ፲፰፥፳፫)፡፡ የኒቆዲሞስ ግን በዝምታ መታለፉ ትምህርቱን አምኖ ለመቀበሉ ማሳያ ነው፡፡ ሁለተኛው በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ፯ ላይ የምናገኘው ኒቆዲሞስ በአይሁድ ፊት ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መከራከሩ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስና በትምህርቱ ለማመኑ ማሳያ ነው፡፡
ፈሪሳውያንና የካህናት አለቆች ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሊይዙት ሎሌዎችን ልከው ነበር፡፡ ሎሌዎቹ ግን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሳይዙት ተመለሱ፡፡ የካህናት አለቆቹና ፈሪሳውያኑ በዚህ ተቈጥተው ሲገሥጹአቸው ኒቆዲሞስ ጣልቃ ገብቶ ለእውነት ቆመ፡፡ “ሕጋችን አስቀድሞ ከእርሱ ሳይሰማ ምንስ እንዳደረገ ሳያውቅ በሰው ይፈርዳልን?” ብሎ ጠየቃቸው፡፡ ያ አይሁድን በመፍራቱ ምክንያት ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቀን መሄድ ፈርቶ የነበረው ኒቆዲሞስ ጥላቻቸው እጅግ ከመጠን ያለፈ በመሆኑ ሕግ ጥሰው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሊይዙት የሚሹትንአይሁድ በግልጽ በአደባባይ ተቃወማቸው፡፡ ያን ጊዜ እምነቱ ጠንካራ ባልነበረ ጊዜ በድብቅ ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሄደው ኒቆዲሞስ አሁን ግን ላመነበት ጌታ እና ለእውነት በአደባባይ ጥብቅና ቆመ፡፡
በፍርሃት፣ በዝምድና፣ በእውቅና፣ በገንዘብ …ወዘተ ምክንያት ከእውነት ይልቅ ለሐሰት ለምንቆም፣ ለባለ ጊዜዎች በማድላት ፍርድን ለምናጣምም ይህ ጥሩ ትምህርት ነው፡፡ ኒቆዲሞስ ክርስቶስን ከሚከተሉት ከሐዋርያት ወገን አልነበረም፡፡ ቅርበቱ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ይልቅ ወገኖቹ ለነበሩት አይሁድ ነበር፡፡ ነገር ግን ኒቆዲሞስ በሐሰት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሊከሱት ለሚሹት ለወገኖቹ ለአይሁድ ሳይሆን ለእውነተኛው ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጥብቅና ቆመ፡፡ ክርስቲያንም በጠባዩ እንዲህ መሆን አለበት፡፡ ሥጋ ላይ ብቻ ሥልጣን ያላቸውን ሳይሆንበሥጋም በነፍስምላይ ሥልጣን ያለውን አምላክ መፍራት አለብን፡፡ እውነት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤ ስለ እውነት መከራ የሚደርስበትና የሚሰደድ ደግሞ በወንጌል እንደተጻፈ ዋጋውን አያጣምና (ማቴ ፭፥፲፩-፲፪፡፡) ጊዜያዊውን መገፋት እየታገሥን ተድላ መንግሥተ ሰማያትን እያሰብን በጽናት መጓዝ አለብን፡፡
ኒቆዲሞስ በጌታችን ስቅለት ጊዜ (ዮሐ.፲፱)
ጌታችን በመስቀል ላይ ነፍሱን በገዛ ፈቃዱ አሳልፎ ከሰጠ በኋላ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋ በአዲስ መቃብር ከቀበሩት ሁለት ሰዎች ውስጥ አንዱ ኒቆዲሞስ ነበር፡፡ ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስም ይህንን ሲመሰክር “ደግሞም አስቀድሞ በሌሊት ወደ ኢየሱስ መጥቶ የነበረ ኒቆዲሞስ መቶ ልጥር የሚያህል የከርቤና የእሬት ቅልቅል ይዞ መጣ የኢየሱስንም ሥጋ ወስደው እንደ አይሁድ አገናነዝ ልማድ ከሽቱ ጋር በተልባ እግር ልብስ ገነዙት፡፡ በተሰቀለበት ስፍራ አትክልት ነበረ በአትክልቱም ማንም ገና ያልተቀበረበት አዲስ መቃብር ነበረ፡፡ “ጌታችን ኢየሱስንም በዚያ ቀበሩት፡፡ ለአይሁድ የመሰናዳት ቀን ነበርና መቀብሩንም ለሰቀሉበት ቦታ ቅርብ ነበር፡፡” ብሏል፡፡
ኒቆዲሞስ ወደ ጌታችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ በድብቅ ከመምጣት በአደባባይ ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ እስከመመስከርና በኋላም ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ሙሉ ያስተማራቸው ደቀመዛሙርቱ(ከወንጌላዊው ዮሐንስ በስተቀር) ከፍርሃት የተነሣ ጥለውት በሸሹ ጊዜ እንኳ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋ ለመቅበር እስከ መብቃት ደረሰ፡፡ በትውፊት እንደሚታወቀውም ኒቆዲሞስ ከቅዱስ ጴጥሮስና ከቅዱስ ዮሐንስ እጅ የክርስትና ጥምቀትን በመጠመቅስለ ክርስቶስ ስደትን የተቀበለ ጠንካራ ክርስቲያን እስከመሆን ደርሷል፡፡ ሉችያንየተባለ የኢየሩሳሌም ቄስ “የቅዱስ እስጢፋኖስ ቀዳሜ ሰማዕት ዐፅም መገኘት” በሚለው ጽሑፉ የቅዱስ ጳውሎስ የኦሪት መምህር የነበረው ገማልያል ተገልጦ ነገረኝ ብሎ ተከታዩን አስፍሯል፡፡ “አይሁድ ኒቆዲሞስ ክርስቲያን መሆኑን ሲያውቁ ከአለቅነቱ አንሥተው፣ ንብረቱን ሁሉ ቀምተውና ክፉኛ ደብድበው ሞቷል ብለው ትተውት ሄዱ፡፡ እኔ ገማልያል በመንገድ ከወደቀበት አንሥቼ ወደቤቴ ወሰድኩት፤ እስኪሞትም ድረስ ከእኔ ጋር ኖረ፡፡ በሞተም ጊዜ ከቅዱስ እስጢፋኖስ ቀዳሜ ሰማዕት አጠገብ ቀበርኩት” ብሏል፡፡ የኒቆዲሞስ ዐፅሙም በ፬፻፳፰ ዓ.ም ከኢየሩሳሌም ወደ ቁስጥንጥንያ ፈልሶ እስከአሁን ድረስ “ቅዱስ ዲያቆን ላውረንስ” በሚሉት ቤተክርስቲያን አለ፡፡
በወንጌልና በትውፊት ከሚታወቀው የኒቆዲሞስ ታሪክ የመንፈሳዊ ሕይወት ዕድገቱን በማስተዋል እኛም የክርስትና ጉዞአችን ምን እንደሚመስል መመልከት ይገባናል፡፡ ክርስትና ጉዞ ነው፡፡ ዕለት ዕለት በእምነት እየጠነከርን በትሩፋት እየበረታን እስከ ዕለተ ሞታችን ድረስ በጽናት መቆየት ያስፈልጋል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!