የነቢያት ሀገራቸው ቤተ ልሔም ደስ ይበልሽ

ክፍል ሁለት

በዲ/ን ዐቢይ ሙሉቀን

ደስ ይበልሽ የተባለች ማን ናት?

ቤተ ልሔም

ደስ ይበልሽ፡ለሀገሪቱ ነው፡፡ በሀገሪቱ ሰዎችን መናገር ነው፡፡ ሰው በሀገሩ፣ ሀገሩ ደግሞ በሰው ይጠራል፡፡ ስለዚህ ቤተ ልሔም ሆይ ደስ ይበልሽ ፡፡ ምክንያቱም እስራኤልን የሚጠብቃቸው ንጉሥ ክርስቶስ ባንቺ ይወለዳልና፡፡ ሀገር ደግ ሰው ሲወለድበት፣ ደግ ሰው ሲወጣበት  ያስደስታል፡፡ አንዳንዴ “ሀገር ይባረክ” ተብሎ ይመረቃል፡፡ ሰው ይውጣበት ማለት ነው፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ሀገርም በሰው ክፋት የተነሣ ሰው አይውጣብሽ ተብላ ልትረገም ትችላለች፡፡ በአዳም ምክንያት ምድር ተረግማለች፡፡ “እግዚአብሔር አምላክም አዳምን አለው የሚስትህን ቃል ሰምተሃልና ከእርሱ እንዳትበላ ካዘዝኩህ ከዚያ ዛፍም በልተሃልና ምድር በሥራህ የተረገመች ትሁን፤ በሕይወት ዘመንህም ሁሉ በድካም ከእርስዋ ትበላለህ እሾኽንና አሜከላን ታበቅልብሃለች፤ የምድርንም ቡቃያ ትበላለህ፡፡” (ዘፍ.፫፥፲፯-፲፰፡፡) ነገር ግን ከዚህ መርገም ድኖ ደግ ሰው ማስገኘት ያስደስታል፡፡ ይልቁንም ቤተ ልሔም እስራኤልን የሚያድናቸው አምላክ፣ የሚጠብቃቸው እውነተኛ እረኛ፣ እነሆ “እስራኤልን የሚጠብቀው አይተኛም፣ አያንቀላፋምም”  (መዝ.፻፳፥፬) እንዲል፤ የሚታደጋቸው መሓሪ አምላክ ነው የተወለደባትና፣ ደስ ይበልሽ ተብላለች፡፡

ቤተ ልሔም ሀገሮሙ ለነቢያት ተብላለች፡፡ ነቢያት ትንቢት ተናግረውባታልና፡፡ የተናገሩት ትንቢት፣ የቆጠሩት ሱባኤ ሲፈጸም ትንቢቱ ለተነገረባት ለሀገሪቱም፣ ትንቢቱን ለተናገሩት ነቢያትም ታላቅ ደስታ ነውና ሀገሮሙ ለነቢያት ተብላለች፡፡ ደግ ነገር በተፈጸመት ሀገር ኖሮ ሀገሪቱ የእነገሌ ናት ሲባል ሰዎችን ያስደስታል፡፡ ሀገሪቱንም የእነገሌ ሀገር ማስባል እጅግ ኩራትን ያሰጣልና ሀገሮሙ ለነቢያት ተብላ ተጠራች፡፡ ሀገሮሙ ለነቢያት ከተባለላቸው ከእነዚህ ነቢያት መካከል ዳዊትና ሚክያስ ይገኙበታል፡፡

ዳዊት ቤተ መቅደሱን ለመሥራት ሲሻ ለነቢዩ ናታን እንዲህ ብሎ ነገረው፡፡ “እኔ ከዝግባ በተሠራ ቤት ተቀምጫለሁ፤ የእግዚአብሔር ታቦት ግን በድንኳን ውስጥ ተቀምጣለች” አለው፡፡ ናታንም ንጉሡን “እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነውና ሂድና በልብህ ያሰብኸውን ሁሉ አድርግ” አለው፡፡ በዚያም ሌሊት የእግዚአብሔር ቃል ወደ ናታን እንዲህ ሲል መጣ፤ እንዲህም አለው፡- “ሒድ ለባሪያዬ ለዳዊት ንገረው እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ አንተ የምኖርበትን ቤት አትሠራልኝም፡፡” (፪ሳሙ.፯፥፪-፭) አለው፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ለዳዊት ድንቅ የሆነው የደገኛው ነገር የነገረ ድኅነት ምሥጢር ተገልጾለት “ናሁ ሰማዕናሁ በኤፍራታ ወረከብናሁ ውስተ ዖመ ገዳም፤ እነሆ በኤፍራታ ሰማነው፣ ዛፍ በበዛበትም ቦታ አገኘነው፡፡” (መዝ.፻፴፩፥፯) በማለት ተናገረ፡፡ ስለዚህ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት የምሥጢረ ሥጋዌ ነገር ተገልጾለት ትንቢት የተናገረባት ቦታ ስለሆነች ሀገሮሙ ለነቢያት ተብላለች፡፡

ሁለተኛው ደግሞ ሚክያስ ነው፡፡ ይህ ነቢይ ሲያስተምር ውሎ ማታ በዚህች በቤተ ልሔም በኩል ሲመለስ እስራኤላውያን በባቢሎናውያን ተማርከው ቤተ ልሔም ምድረ በዳ ሆና ተመለከታት፡፡ በዚህ ጊዜ “እነሆ የጽዮንን ሴት ልጅ ከበው ያጥሯታል፤ የእስራኤልንም ወገኖች ጉንጫቸውን በበትር ይመታሉ፡፡ አንቺም የኤፍራታ ምድር ቤተ ልሔም ሆይ አንቺ በይሁዳ አእላፋት መካከል ትሆኚ ዘንድ ታናሽ ነሽ፤ ነገር ግን አወጣጡ ከቀድሞ ጀምሮ ከዘለዓለም የሆነ በእስራኤል ላይ ገዥ የሚሆን ከአንቺ ይወጣልኛል፡፡ ስለዚህ ወላዲቱ እስከምትወልድበት ጊዜ ድረስ አሳልፎ ይሰጣቸዋል፤ የቀሩትም ወንድሞቻቸው ወደ እስራኤል ልጆች ይመለሳሉ፡፡” (ሚክ.፭፥፩-፬) በማለት ለጊዜው እስራኤላውያን ተማርከው እንደማይቀሩ በዘሩባቤል መሪነት በእግዚአብሔር ቸርነት ተመልሰው ወደ ርስታቸው እንደሚገቡ ተናግሯል፡፡

ነቢየ እግዚአብሔር ሚክያስ ለጊዜው እስራኤል ዘሥጋን ያጣች ቤተ ልሔም ምድረ በዳ እንደሆነች፡፡ በዚህ ምድረ በዳነቷም እንደማትቀጥል እስራኤል ከምርኮ ተመልሰው እንደሚሰፍሩባት፣ እንደሚደሰቱባት፣ ንጉሥ ዘሩባቤል እንደሚነግሥባት ተናገረ፡፡ እንዲሁም ሆነ፡፡ እስራኤል ከምርኮ ተመለሱ፤ ተደስተውም ዘመሩባት፡፡ ፍጻሜው ግን እስራኤል ዘነፍስን ያጣች ገነት የሚገባባት አጥታ ባዶ እንደሆነች፣ ነገር ግን እስራኤልን የሚጠብቅ ንጉሥ ክርስቶስ ከጠላት የሚያድን አምላክ እንደሚወለድባት ያስረዳል፡፡ በመሆኑም ቤተ ልሔም ንጉሠ ሰማያት ወምድር አምላክ ተወልዶባት መላእክት ዘመሩባት፤ ሰውና መላእክት ታረቁባት፤ የእስራኤል ነጻነት ታወጀባት፡፡ “እነሆ ለእናንተና ለሕዝቡ ሁሉ ደስታ የሚሆን ታላቅ የምሥራችን እነግራችኋለሁና አትፍሩ አላቸው፡፡” (ሉቃ.፪፥፲) ተብሎ ተነገረባት፡፡

ለዚህም ነው ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም “ስለ ክርስቶስ ባንድ መንፈስ ቅዱስ ትንቢት የተናገሩት የእነዚህ የሚክያስና የዳዊት ነገር ምን ይደንቅ” (ውዳሴ ማርያም ዘሐሙስ) በማለት የተናገረው፡፡ እውነት ነው የተነገረው ትንቢት በመንፈስ ቅዱስ መሆኑን እንድንረዳ አንድ ዐይነት ትንቢት ግን በተለያየ ጊዜ በተለያዩ ሰዎች ተነገረ፡፡ ደግሞ የተነገረው ትንቢት፣ የተቆጠረው ሱባኤ ሲፈጽም የአናገረው መንፈስ ቅዱስ መሆኑን የተናገሩት ነቢያት ደግሞ ደጋግ መሆናቸውን የሚያስረዳ ነውና የእነሱም ነገር ምን ይደንቅ ተባለ፣ ሀገሪቱም ከዚህ የበለጠ ደስታ ስለሌለ ደስ ይበልሽ ተባለች፡፡

እመቤታችን

ድንግል ማርያም የነቢያት ሀገራቸው ደስ ይበልሽ ተብላለች ፡፡ ለምን የነቢያት ሀገራቸው ተባለች ከተባለ የአበው ሱባኤና ተስፋ፣ የነቢያት ትንቢት በእርሷ ስለተፈጸመ ነው፡፡ ለዚህም ነው “ትንቢቶሙ ለነቢያት፣ እሞሙ ለሰማዕት፣ ወእህቶሙ ለመላእክት” የምትባለው፡፡  የነቢያት ትንቢት በእርሷ ስለ ተፈጸመ “ትንቢቶሙ ሀገሮሙ ለነቢያት” ተብላለች፡፡ በተጋድሎ፣ በስደት፣ በመከራ ወዘተ ስለምትመስላቸው “እሞሙ ለሰማዕት፣ የሰማዕት እናታቸው” ተብላለች፡፡ በንጽሕና፣ በቅድስና ስለምትመስላቸው ደግሞ “እህቶሙ ለመላእክት፣ የመላእክት እህታቸው” ተብላለች፡፡ ቤተ ልሔምን እና ድንግል ማርያምን የሚያመሳስላቸው ነገር ምንድን ነው? ቢባል የቤተ ልሔምን ከላይ በገለጽነው መንገድ መረዳት ይቻላል የድንግል ማርያምን ደግሞ እንደሚከተለው እንመልከት፡፡

“ኦ ከርሥ ዘተጽሕፈ ውስቴታ መጽሐፈ ግእዛን እምግብርናት ለኩሉ ሰብእ፤ ኦ ከርሥ  ዘተረጸውረ ውስቴታ ንዋየ ሐቅል ዘይትቃወሞ ለሞት በእንቲኣነ፤ ለሰው ሁሉ ከመገዛት የነጻነት መጽሐፍ የተጻፈባት ማሕፀን እንደምን ያለች ናት፣ ስለኛ ሞትን የሚቃወም ክርስቶስን የተሸከመች ማኅፀን ወዮ እንደምን ያለች ናት፡፡” (ሃ/አበ.፵፰፥፲፭) በማለት ሊቁ ቅዱስ ኤራቅሊስ በሃይማኖተ አበው ነገረ ሥጋዌን በተናገረበት አንቀጹ ተናገረ፡፡

ይህ ለሁሉ የነጻነት መጽሐፍ የተጻፈባት የተባለች ጥንት በትንቢተ ኢሳይያስ እንዲህ ተብላ ተገልጻለች፡፡ “ደከሙ፤ ደነገጡ፤ ሰከሩም፤ በወይን አይደለም፤ በጠጅም አይደለም፡፡ እግዚአብሔር የእንቅልፍ መንፈስን አፍሶባቸዋል፤ ዐይኖቻቸውን የነቢያትንም ዐይን የተሰወረውንም የሚያዩ የአለቆቻቸውን ዐይን ጨፍኖባቸዋል፡፡ ይህም ሁሉ ነገር እንደታተመ መጽሐፍ ቃል ሆኖባቸዋል፤ ማንበብንም ለሚያውቅ “ይህን አንብብ” ብለው በሰጡት ጊዜ እርሱ ታትሟልና “ማንበብ አልችልም” ይላቸዋል፤ ደግሞም መጽሐፉን ማንበብ ለማያውቅ “ይህን አንብብ” ብለው በሰጡት ጊዜ “ማንበብ አላውቅም” ይላቸዋል፡፡ (ኢሳ.፳፱፥፱)፡፡

ከላይ በተገለጸው ምንባብ በርካታ ሐተታዎች ቢኖሩትም ከዚህ ርእስ ጋር የሚሄደውን ብቻ ለማየት እንሞክራለን፡፡ የታተመ መጽሐፍ የተባለች ድንግል ማርያም፣ ማንበብ የማይችል  የተባለ ዮሴፍ፣ ማንበብ የሚችል የተባለው ሚስቱን በግብር የሚያውቅ ማለት ነው፡፡ ማንበብ የማይችል የተባለ ደግሞ ድንግል ማርያምን በግብር የማያውቅ ማለት ነው፡፡ በድንግልና ፀንሳ በድንግልና መውለዷ ጭንቅ ይሆኖበታል፡፡ “ኢያእመራ ዮሴፍ እስከ አመ ወለደት ወልደ ዘበኲራ፤ የበኲር ልጇን እስከ ወለደች ድረስ አላወቃትም” እንዲል፡፡ እስከ የሚለውንም ቃል ፍጻሜ የሌለው እስከ እንደሆነ ልብ ይሏል፡፡ ሜልኮል እስከ ሞተችበት ጊዜ ድረስ አልወለደችም ይላል፤ ከሞተች በኋላ ወለደች ማለት አይደለም ፍጻሜ የሌለው እስከ ነው እንጂ፡፡ ኖኅ የላከው ቁራም የጥፋት ውኃ እስከ ጎደለ ድረስ አልተመለሰም ይላል፤ ከዚያ በኋላ ተመለሰ የሚል ታሪክ አልተጻፈም ፍጻሜ የሌለው እስከ ነው እንጂ፡፡

እንዲሁም መጽሐፍ ማንበብ የሚያውቅ የተባለ ዮሴፍ ሚስቱን በግብረ ሥጋ የሚያውቅ፣ መጽሐፍ እንደታተመ ሰጡት፣ አልተገለጠምና ማንበብ አልቻለም፡፡ መጽሐፍ የተባለች ድንግል ማርያም እንደ ታተመች ሰጡት ማንበብ አልቻለም፡፡ አይሁድ በቅንዓት ከቤተ መቅደስ ሲያስወጧት ከእግዚአብሔር አግኝተን እንደ ሰጠንህ ከእግዚአብሔር አግኘንተን እስክንቀበልህ ድረስ ጠብቅ ተብሎ ተሰጥቷልና፡፡ እንደ ታተመ ሰጡት ግን ማንበብ አልቻለም ተባለ፡፡ ማኅተመ ድንግልናዋን እንደ ጠበቀች እንድትኖር እንጂ በግብር ሊያውቃት አይደለምና፡፡

ማንበብ ለማይችለው የተዘረጋ መጽሐፍ ሰጡት ግን ማንበብ አልቻለም፡፡ ማንበብ ስለማይችል ነገረ ሥጋዌ በአበው ምሳሌ፣ በነቢያት ትንቢት ሲነገር የኖረና በተስፋ ሲጠበቅ የኖረ ነው፡፡ ግን ማንበብ ለማይችል ሰጡት አለ፡፡ ይህ ትንቢት የተነገረው ለማን እንደሆነ ላላወቀው ዮሴፍ ሰጡት ማንበብ አልቻለም፡፡ ድንግል የተባለች እርሷ፣ ወልድ የተባለ ከእርሷ የሚወለደው ነቢያት ትንቢት የተናገሩለት፣ አበው ምሳሌ የመሰሉለት እርሱ እንደሆነ አላወቀም ነበር፡፡ ስለዚህ ማንበብ አልቻለም ተባለ፡፡

ይህም ነገር ዮሴፍን እጅግ አስጨነቀው ሊቁ ኤራቅሊስ እንደሚነግረን “የድንግል ሆዷ ገፋ፣ ያለ ዘር የፀነሰች የድንግልን የሆድዋን መግፋት ባየ ጊዜ የዮሴፍ ልቡ አዘነ፤ የንጽሕት እመቤታችንን ምሥጢሯን ፈጽሞ መረመረና በማያውቀው ምሥጢር ፀንሳ ቢያገኛት በጽኑእ ሐሳብ በማውጣት በማውረድ ተያዘ” (ሃ/አበ.፵፰፥፴፫) እንዲል፡፡ ነገሩ አምላካዊ ነውና ዮሴፍ ማወቅ አልቻለም፡፡ ባለማወቁም ተጨነቀ፡፡ ለዚህ ነው ማንበብ ለማያውቅ መጽሐፍ ሰጡት ግን ማንበብ አልቻለም፣ ያልተማረ ማንበብ የማያውቅ ነውና የተባለው፡፡

ሌላው መጽሐፍ የተባለ መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ማንበብ የሚችል፣ ማንበብ የማይችል የተባሉ አይሁድ ናቸው፡፡ ማንበብ የሚችል ማለት ትንቢት የተነገረላቸው፣ ሱባኤ የተቆጠረላቸው በሕገ ኦሪት የሚመሩ የመሢሁን መምጣት የሚጠባበቁ ስለሆኑ ነው፡፡ ማንበብ የማይችል የተባሉት ሲጠባበቁት የነበረው መሢህ ትንቢቱን ሊፈጽም እነሱን ሊያድን ቢመጣ አልተቀበሉትም፡፡ ያ ትንቢት የተነገረለት፣ ሱባኤ የተቆጠረለት እርሱ እንደሆነ አምኖ መቀበል አለመቻላቸው ነው፡፡ ማንበብ ለሚችል የታጠፈ መጽሐፍ ሰጡት የተባለ ትንቢቱ የተነገረልን፣ ሱባኤው የተቆጠረልን እኛ ነን ለሚሉት ግን የታተመ መጽሐፍ ተሰጣቸው እነሱ በሚያስቡት መንገድ አለመገለጡን ሲያስረዳ ነው፡፡ እነሱ የሚያስቡት ብዙ ሠራዊት አስከትሎ፣ የጦር መሣሪያ አስይዞ ከሮማውያን ግዛት ነጻ የሚያወጣ ነበርና፡፡

ማንበብ ለማይችለው የተገለጠ መጽሐፍ ተሰጠው ግን ማንበብ ስለማይችል አላነበበውም የተባለው ደግሞ አምላክነቱን የሚያስረዱ በርካታ ተአምራትን እያደረገ ሕሙማንን እየፈወሰ፣ ሙታንን እያስነሳ ዕዉራንን እያበራ እኔ አምላክ ነኝ ቢላቸው አላመኑበትም፡፡ ምክንያቱም ማንበብ አይችሉምና፣ ማለት ሃይማኖት የላቸውምና፡፡ እርሱ ደግሞ የሚታወቅ በሃይማኖት ስለሆነ፡፡ “በሃይማኖት ነአምር ከመ ተፈጥረ ዓለም በቃለ እግዚአብሔር፤ ዓለም በእግዚአብሔር ቃል እንደ ተፈጠረ በሃይማኖት እናውቃለን፡፡” በማለት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንደ ተናገረው ነው፡፡

ለምን ደስ ይበልሽ አላት

የዚህ ሁሉ ምሥጢር መፈጸሚያ መዝገብ ሆናለችና ተፈሥሒ፤ ደስ ይበልሽ አላት፡፡ ከመልአኩ ከቅዱስ ገብርኤል እንደተረዳው እንዲህ በማለት “እስመ እምኔኪ ይትወለድ ክርስቶስ ዘይርዕዮሙ ለሕዝብየ እስራኤል፤ ሕዝቤን እስራኤልን የሚጠብቃቸው ክርስቶስ ከአንቺ ይወለዳልና፡፡” ሰዎች በተለይም እናቶች ልጅ ወልዶ እንደ ማሳደግ ደስ የሚላቸው ነገር የለም፡፡ ስለዚህም አንዲት እናት ልጅ ስትወልድ እንኳን ደስ አለሽ፣ እንኳን ማርያም ማረችሽ ትባላለች፡፡ ሴቶች ልጅ ትወልዳላችሁ ሲባሉ ደስ ይላቸዋል፤ ይልቁንም ወንድ ልጅ ትወልዳላችሁ ሲባሉ  እጅግ ደስ ይላቸዋል፡፡ ድንግል ማርያም በብሥራተ መልአክ የተነገረችው የዓለሙን መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስን ነውና መልአኩም ደስ ይበልሽ ብሏታል፡፡ ጻድቃንን፣ ሰማዕታትን፣ ሐዋርያትን የወለዱ እናቶችም ደጋግ ልጆች በመውለዳቸው ይከበራሉ፤ ይመሰገናሉ፡፡ ቅድስት ድንግል ማርያም ደግሞ የወለደችው ዓለሙን ያዳነውን ጌታ ነውና ደስ ይበልሽ ልትባል ይገባታል፡፡

ለምን ተወለደ?

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው የሆነበት ሁለት መሠረታዊ ዓላማዎች አሉት፡፡ አንደኛውና ዋነኛው ሰውን ለማዳን ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ለአርአያነት ነው፡፡ አርአያነቱንም የደቀ መዛሙርቱን እግር አጥቦ ትሕትናን፣ ለሚያሰቃዩት ጸልዮ ፍቅርን፣ ወዘተ በመግለጽ አሳይቷል፡፡ ሰውን ለማዳን እንደመጣም ሊቁ ሰው የሆነበትን ምክንያት ሲገልጥ “ልቡ የአዘነና የተከዘ አዳምን ወደቀደመ ቦታው ይመልሰው ዘንድ ወደደ” ነው ያለን፡፡  ወደ ቀድሞ ክብሩ ልጅነት፣ ወደ ቀድሞ ቦታው ገነት ይመልሰው ዘንድእስመ በኀቤኪ ተወልደ ክርስቶስ ዳግማይ አዳም ከመ ያግብኦ ለአዳም ቀዳሚ ብእሲ እምድር ውሰተ ገነት፤ ዳግማዊ አዳም ክርስቶስ አዳምን ከሲኦል ወደ ገነት ይመልሰው ዘንድ በአንቺ ተወልዷልና ደስ ይበልሽ” አለ፡፡

አዳም ከገነት ተባሮ ስደተኛ ሆኖ ነበርና ባለ ርስት ባለ ጉልት ሊያደርገው ሰው ሆኖ በሥጋ አዳም ተገለጠ፡፡ በመሆኑም በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት የመንግሥቱ ወራሾች ሆን፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “እምይእዜሰ ኢኮንክሙ ነግደ ወፈላሴ አላ ሰብአ ሀገሪቶሙ ለቅዱሳን ወሰብአ ቤቱ ለእግዚአብሔር፤ እንግዲህስ ወዲህ እናንተ ከቅዱሳን ጋር ባለ ሀገሮችና የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እንጂ እንግዶችና መጻተኞች አይደላችሁም፡፡” (ኤፌ.፪፥፲፱) በማለት እንደገለጸልን ወደ ርስቱ ይመልሰው ዘንድ ሰው ሆነ፡፡ ስለዚህ ንጉሥ ክርስቶስ ሰውን ወደ ርስቱ ይመልሰው ዘንድ ካንቺ ተወልዷልና ደስ ይበልሽ ተባለች፡፡

በአጠቃላይ ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም ተፈሥሒ ኦ ቤተ ልሔም ሀገሮሙ ለነቢያት ያላት ለጊዜው ነቢያት ያመሰገኗትን ቤተ ልሔምን ሲሆን፤ ፍጻሜው ግን የነቢያት ትንቢትም ፍጻሜውን ያገኘው በድንግል ማርያም ስለሆነ ድንግል ማርያም ሆይ ደስ ይበልሽ እያለ አመሰገናት፡፡ ለምን አመሰገናት ከተባለ ደግሞ የአምላክ እናት ስለሆነች፡፡ እኛም እንደ ሊቃውንቱ ድንግል ማርያምን አመስግነን ከድንግል ማርያም በረከት እንድናገኝ የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የመላእክት ጥበቃ፣ የቅዱሳን ሁሉ ተራዳኢነት አይለየን አሜን፡፡

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *