የብዙኃን ማርያም
መ/ር ኃይለ ሚካኤል ብርሃኑ
ብዙኃን ማርያም የተባለበት ምክንያት በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ፫፻፲፰ቱ ሊቃውንት በንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ጥሪ መሠረት አርዮስን ለማውገዝ ሚያዚያ ፳፩ ቀን ጉዞ ጀምረው መስከረም ፳፩ ቀን በኒቂያ ስለተሰበሰቡ ብዙኃን ማርያም ተብሏል፡፡ እመ ብዙኃን የሚለውም የሊቃውንቱን ብዛት ያመለክታል፡፡ እንዲሁም እመቤታችን የብዙዎች እናት ናትና እመ ብዙኀን ተብላለች፡፡ (መድብለ ታሪክ)፡፡
ስለዚህ መስከረም ፳፩ ቀን የሚከበረው የእመቤታችን በዓል የብዙኃን ማርያም ይባላል፡፡ ይህም የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግማደ መስቀል ወደ ግሸን ደብረ ከርቤ መግባቱን ተከትሎ ብዙዎች ኦርቶዶክሳውያን ከሰሜን ከደቡብ፣ ከምሥራቅ፣ ከምዐራብ ከሁሉም የሀገራችን ክፍሎች ቅዱስ መስቀሉን ለማክበር የሚሰባሰቡበት፣ እንዲሁም በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ስም የታነፀችው ቤተ ክርስቲያን ቅዳሴ ቤት በድምቀት የተከበረበት ቀን ነው፡፡
በዕለተ ዓርብ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሳለ ከመስቀሉ ሥር የነበረችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን እናት አድርጎ በወንጌላዊው በቅዱስ ዮሐንስ አማካኝነት ሰጥቶናል፡፡ ይህች ቀን የቤታችን እና የኑሮአችን በረከት ለሕይወታችን የድኅነት ምክንያት በሆነችን በቅድስት ድንግል ማርያም ስም ተሰባስበን ዕለቱ የመስቀሉን በረከት የምንሳተፍባት ቀን በመሆኗም ከላይ እንደጠቀስነው የብዙኃን ማርያም ብለን እናከብራታለን፡፡
ይህም ዐፄ ዳዊት ቅዱስ መስቀሉ እንዲሰጣቸው ለእስክንድርያና ለኢየሩሳሌም ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቀኝ እጁ ያረፈበት ግማደ መስቀሉ ለኢትዮጵያ ተሰጠ፡፡ ዐፄ ዳዊት ግን ቅዱስ መስቀሉን ተቀብለው ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ እግዚአብሔር በመረጠው ሥፍራ ሳያስቀምጡት በድንገት ዐረፉ፡፡
ልጃቸው ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ ቅዱስ መስቀሉ ተቀብሎ በመስከረም ፲ ቀን ወደ ኢትዮጵያ እንዲገባ በማድረግ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ከሆነው በኋላ “አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል፤ መስቀሌን በመስቀልኛ ቦታ አስቀምጥ” በተባለው መሠረት መስቀለኛ መልክአ ምድራዊ አቀማመጥና አንድ መግቢያ መንገድ ብቻ ባለው በግሸን ደብረ ከርቤ መስከረም ፳፩ ቀን ፲፬፻፵፮ ዓ.ም በክብር እንዲያርፍ ተደርገል፡፡ በዚህም ምክንያት መስቀሉ በግሸን ተራራ ባረፈበት በመስከረም ፳፩ ቀን በየዓመቱ በድምቀት ይከበራል፡፡
እንዲሁም በዚህች ዕለት የተፍጻሜተ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስ ደቀ መዛሙርት ከነበሩትና በዕውቀታቸው ብዙ ከተጓዙት መካከል እለእስክንድሮስ፣ አኪላስ እና አርዮስ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ከእነዚህም መካከል በአንደበተ ርቱዕነቱና በፍልስፍናው ጎበዝ የተባለው አርዮስ በፈጠረው የክሕደትና የምንፍቅና ትምህርቱ ከራሱ አልፎ ሌሎችንም እስከማጠራጠር ደርሶ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በማወኩ የተነሣ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ በድጓው “አስተጋብኦሙ እምበሐውርት እም ጽባሕ ወእም ዓረብ ወመስዐ ወባሕር፤ ከምሥራቅ ከምዕራብ፣ ከሰሜንና ከደቡብ ከሁሉም ክፍላተ ዓለም አሰባሰባቸው” በማለት እንደተናገረው ታላቁ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ በ፫፻፳፭ ዓ.ም በልዩ ልዩ ክፍላተ በዓለም ያሉ ፫፻፲፰ የቤተ ክርስቲያን አበው ሊቃውንት በኒቂያ ሰብስቧቸዋል፡፡ በዚህም መሠረት ሊቃውንቱን በዚህ ቀን አርዮስን ለይተው በማውገዝ ሃይማኖትን አጽንተው ሥርዓት የሠሩበት ቀን በመሆኑ የሚከበር በዓል ነው፡፡ የቅዱሳን አባቶቻችን የጸናች ሃይማኖታቸው ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ በልባችን ታትማ ለዘለዓለም ትኑር አሜን፡፡
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!