“የምናመልከው አምላክ ከሚነድደው ከእሳቱ እቶን ያድነን ዘንድ ይችላል” (ዳን. ፫፥፲፯)
ገብርኤል ማለት “እግዚእ ወገብር፤ የእግአብሔር አገልጋይ” ማለት ነው። እግዚአብሔር ሥነ ፍጥረት መፍጠር በጀመረበት በዕለተ እሑድ ስምንት ፍጥረታትን ፈጥሯል፡፡ ከእነዚህም መካከል ቅዱሳን መላእክት ተፈጥረዋል፡፡ አገልግሎታቸውም ሳያቋርጡ እግዚአብሔርን “ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ” እያሉ ማመስገን ነው፡፡ እግዚአብሔርም መላእክትን ከፈጠራቸው በኋላም ተሰወራቸው፡፡
በመላእክቱም ከተማ “መኑ ፈጠረነ፡ ማን ፈጠረን?” እያሉ ፈጣሪያቸውን ፍለጋ ጥረት አደረጉ፡፡ ነገር ግን ምላሽ ማግኘት ባለመቻላቸው ከመላእክቱ መካከል ሳጥናኤል በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት ማጋረጃውን የመክፈትና የመዝጋት ክብር ተሰጥቶታልና ወደ ላይ ቢያይ ከእርሱ በላይ ምንም እንደሌለ ተመለከተ፤ ወደ ታች ሲያይ ግን ፍጥረታት መላእክቱን ጨምሮ በመመልከቱ “እኔ ፈጠርኳችሁ” ሲል ተመጻደቀ፤ ፈጣሪነትንም ተመኘ፡፡ ከመላእክቱ መካከል ግን ሊቀ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል የተረበሸውን የመላእክቱን ከተማ በማረጋጋት “የፈጠረንን አምላካችን እስክናገኝ በያለንበት ጸንተን እንቁም!” በማለት አረጋጋቸው። እግዚአብሔር ቀናተኛ አምላክ ነውና አምላክነትን የተመኘውን ሳጥናልን ከሥልጣኑ ሽሮ ወደ ገሃነመ እሳት አወረደው፡፡
መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልም መላእክቱን አረጋግቶ አምላካቸው እግዚአብሔር እስኪገለጥላቸው ድረስ ይጠብቁ ዘንድ አረጋግቷቸዋልና ነቢያት ይወርዳል ይለዳል እያሉ ትንቢት እንደተናገሩለት አምስት ሺህ አምስት መቶው ዘመን ሲፈጸም “ድንግል በድንግልና ፀንሳ በድንግልና ትወልዳለች” ብሎ የተናገረውን የነቢዩ ኢሳያስ ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እንደሚወለድ በቤተ መቅደስ ሐርና ወርቁን አስማምታ እየፈተለች ሳለ ያበስራት ዘንድ እግዚአብሔር ፈቃዱ ሆኗል፡፡ በዚህም መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል “ብስራታዊ መልአክ” እየተባለ ይጠራል፤ የጌታን መወለድ አብስሯልና፡፡
መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ከሰባቱ ሊቃነ መላእክት አንዱና ለካህኑ ዘካርያስ “እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ” ሲል በእርጅናቸው ወራት ወንድ ልጅ እንደሚወልድ አብስሮታል፡፡ (ሉቃ. ፩፥፲፱) ቅዱስ ገብርኤል በተረዳኢነቱና በአማላጅነቱ በክርስቲያኖች ዘንድ እጅግ ይወደዳል፡፡ ምክንያቱም ያዘኑትን ለማጽናናት የምሥራች ለመንገር ከእግዚአብሔር ወደ ምእመናን ይላካልና፡፡
በታኅሣሥ ፲፱ ቅ የእግዚአብሔር አገልጋይ የሆኑትን አናንያ አዛርያ ሚሳኤልን በባቢሎን በምርኮ ሳሉ ናቡከደነፆር ላቆመው የወርቅ ምስል እንዲሰግዱ ሲያስገድዳቸው “ንጉሥ ሆይ እኛ የምናመልከው አምላክ በሰማይ አለ፤ ከሚነድደው ከእሳቱ እቶን ያድነን ዘንድ ይችላል፤ ከእጅህም ያድነናል፡፡ ንጉሥ ሆይ ይህም ባይሆን አማልክትህን እንዳናመልክ ላቆምኸውም ለወርቁ ምስል እንዳንሰግድለት ዕወቅ” አሉት፡፡ (ዳን. ፫፥፲፯-፲፰) የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ገብርኤልም ከእግዚአብሔር ተልኮ ወደሚነደው እሳት ወርዶ እሳቱን አጥፍቷል፤ አንዲት የጸጉራቸው ዘለላ እንኳን አልተነካም፡፡ ይህን የተመለከተው ናቡከደነፆርም ከተጣሉበት ይወጡ ዘንድ ተናገራቸው፡፡ በፊታቸውም ለእግዚአብሔር ሰገደ፡፡ በባቢሎን አውራጃዎችም ሾማቸው፤ ከፍ ከፍም አደረጋቸው፤ በግዛቱ ያሉትን አይሁድንም አስገዛላቸው፡፡
ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችንም ይህንን መሠረት አድርጋ ታኅሣሥ ፲፱ ቀን መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ሠለስቱ ደቂቅን ከሚነደው እሳት ያዳነበትን ቀን ምክንያት በማድረግ በየዓመቱ በድምቀት ታከብረዋለች፡፡
ከመልአኩ ቅዱስ ገብርኤል እና ከሠለስቱ ደቂቅ በረከት ያሳትፈን፡፡ አሜን፡፡
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!