“የሕይወት ቀን” በግቢ ጉባኤያት
ወርቃማው የወጣትነት ዘመናችን በተስፋ፣ በመልካም ምኞትና በትጋት የተሞላ፣ ዕውቀትንና አቅምን ያማከለ ማንነታችን የሚታነጽበት፣ መንፈሳዊነታችን የሚገለጽበት የዕድሜ ክልል እንደመሆኑ የሕይወታችን መሠረት ነው፡፡ መንፈሳዊ ፍሬን አፍርተን ርስተ መንግሥተ ሰማያት ለምንወርስብትም የሕይወት ስንቅ የምንሰንቅበት የተጋድሎ ዘመን ስለመሆኑ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ከልጅነታችን ጀምሮ አበክራ ታስተምረናለች፡፡ በሰንበት ትምህርት ቤቶቿም ኮትኩታ አሳድጋ መንፈሳዊ ፍሬ ለማፍራት ታበቃናለች፡፡ ለዚህ የመሸጋገሪያ ዕድሜ በደረስንበት ጊዜም የሕይወታችን መርሕ የሆነው ትምህርተ ወንጌል እንዳይጓደልብን በዐውደ ምሕረቷ ላይ ጉባኤ ዘርግታ ሰማያዊ ኅብስትን አዘጋጅታ ትመግበናለች፡፡
በጉባኤያት የሚሰበኩ ትምህርቶች ለክርስቲያናዊ ሕይወት እንድንበቃ የሚረዱንና ለዘለዓለማዊ ሕይወት የሚያበቁን ናቸው፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን የምትመግበን ምግበ ሕይወት ግን በዚህ ብቻ አይወሰንም፡፡ ዘወትር መንፈሳዊ ዝለት አጋጥሞን ከቤቷ እንዳንርቅና በዓለም እንዳንጠፋ ዓለም ባፈራቻቸው የመገናኛ ብዙኀን በየቤታችን፣ በትምህርት ቤታችንና በየአካባቢያችን የሕይወትን ምግብ እየመገበች ታኖረናለች፡፡ ቅዱስ ቃሉን ሰምትንም ለሥጋ ወደሙ እንድንበቃ ምሥጢራቷን ታካፍለናለች፡፡
ለዚህም ተልእኮ ተደራሽነት በሀገራችን የመንፈሳዊ አገልግሎት ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ስፍራ የሚሰጠው ማኅበረ ቅዱሳን በግቢ ጉባኤ አገልግሎቱ ውስጥ ለኦርቶዶክሳዊያን ወጣት ተማሪዎች ከሚሰጠው ሥርዓተ ትምህርት በተጨማሪ ከምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ይካፈሉ ዘንድ ዘወትር እሑድ የሚቀርበው “የሕይወት ቀን” ተጠቃሽ ነው፡፡ በዓመት በሁለቱ የአጽዋማት ወቅት በነቢያትና በዐቢይ ጾም የሚካሄደው ይህ አገልግሎት በአብዛኛው የከፍተኛ ተቋማት ተማሪዎች የሚሳተፉበት ነው፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎችን መሠረታዊ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ከማስተማር ባሻገር በንጽሕና ሕይወት ኖረው ለቅዱስ ቁርባን እንዲበቁ ለማድረግ ባለው ቁርጠኛ ሐሳብ በጀመረው በዚህ መርሐ ግብር በተለይም በአዳማ፣ በሐሮማያ፣ በጎንደር እና በሌሎች ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚገኙ የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎችን የንስሓ አባት ከማስያዝ ጀምሮ ሥጋ ወደሙ እንዲቀበሉ ይረዳቸዋል፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ሥጋዬን የበላ ደሜን የጠጣ የዘለዓለም ሕይወት አለው” በማለት እንደተናገረው እኛ ክርስቲያኖች በንስሓ ሕይወት ተመላልሰን ለሥጋ ወደሙ እንድንበቃ የአምላካችን ቅዱስ ቃል ይገልጻልና የተማርነው ትምህርትም ይሁን የምንኖረው ክርስቲያናዊ ሕይወት ፍጻሜው ቅዱስ ቁርባን በመሆኑ ተማሪዎቹ ይህንን ተረድተው እንዲተገብሩት ማኅበራቸው ማኅበረ ቅዱሳን እገዛ ያደርግላቸዋል፡፡ (ዮሐ. ፮፥፶፫)
ይህን ተልእኮ ለመፈጸም በግቢ ጉባኤያት ለአገልግሎት የተመደቡ መምህራንና ሰባኬ ወንጌላውያን ተማሪዎቹን ለቅዱስ ቁርባን ዝግጁ እንዲሆኑ የእግዚአብሔርን ቃል ከማስተማር ባሻገር አስቀድመው በንስሓ አባቶቻቸው አማካይነት ንስሓን እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡ ከዚህም ቀጥሎ ለአንድ ሳምንት ያህል ሥርዓተ ንስሓን የሚፈጽሙበት “የንስሓ ሳምንት መርሐ ግብር” ይከናወናል፡፡ ተማሪዎች አስፈላጊውን ሥርዓት ተከትለውና በምክረ ካህን ታግዘውም ቅድመ ዝግጅታቸውን ሲያጠናቀቁ ሥራ አስፋጻሚ ቢሮው ከአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናቱ ጋር በመነጋገር በተለይም በዐበይት የአጽዋማት ወቅቶች ማለትም በዐቢይ ጾመና በጾመ ነቢያት ሥጋ ወደሙ ከሚቀበሉበት ዕለተ እሑድ ዋዜማ የአዳር መርሐ ግብር በማዘጋጀት ትምህርተ ወንጌልና ውይይት ያደርጋል፡፡
በመቀጠልም በቤተ ክርስቲያናቱ ተገኝተው ሥርዓተ ቁርባን እንዲካፈሉ ካደረገ በኋላ ከመምህራኑ ጋር በመተባበር ማኅበሩ የአጋፔ መርሐ ግብር አዘጋጅቶ ያቀርብላቸዋል፡፡ የአጋፔ መርሐ ግብሩንም ተከትሎ የተለያዩ መርሐ ግብራትን በማዘጋጀት የሕይወት ምግብን እንዲመገቡ ያደርጋል፡፡ ቀሪው ዘመናቸውን በሃይማኖት ጸንተው አንዲኖሩና እስከ ሕይወታቸው ፍጻሜ ድረስ ለቅዱስ ቁርባን የበቁ እንዲሆኑ ለመርዳት የድኅረ ጉባኤያት መርሐ ግብር አዘጋጅቶም የማያቋርጥ እገዛ ያደርግላቸዋል፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን በግቢ ጉባኤያት ያስመረቃቸው በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች የቀና መንፈሳዊ ሕይወትም ጉዳዬ ብሎ የያዘው ተልእኮው በመሆኑ ማኅበረ ቅዱሳን በየጊዜው ይህን ሥራውን ለማከናወን የሚረዱ መርሐ ግብራትን ያዘጋጃል፡፡ በተለይም ተልእኮውን ተደራሽ ለማድረግ የሚረዱ የዐቅም ማጎልበቻ ሥራዎችና ለአገልግሎቱ ስኬት እክል የሚሆኑ ችግሮችን የመፍታት ሥራ እየሠራ ይገኛል፡፡ ማኀበሩ ለዚህ እንደ መነሻ ያደረገው በ፳፻፲፫ የተጠናው ጥናት እንደሚያሳየው ከሆነ የመምህራን አቅም ማጎልበቻ ሥልጠናዎች እጥረት፣ የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች የመማርያ ግብአቶች አለመሟላት እንዲሁም ሌሎች ውስጣዊ እና ውጫዊ ተግዳሮቶች በመሆናቸው ይህን ችግር ለመቅረፍ የሚያግዙትን ተግባራት በመለየት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡
ስለሆነም ይህን ተግዳሮት ለማከናወን ማኅበሩ የበጎ አድራጊ ግለሰቦችም ሆነ ድርጅቶች እገዛ እንደሚያስፈልጉት በማመን በዚህ በያዝነው የግንቦት ወር ባወጣው ዕቅድ መሠረት የ፳፻፲፭ ዓ.ም የግንቦት ልደታ ለማርያምንበዓል “ግንቦት ልደታን ለግቢ ጉባኤ” በሚል ርእስ መርሐ ግብር አዘጋጅቷል፡፡ በዋናው ማእከል ደረጃ ከሚያዝያ ፳፰/ ፳፻፲፭ ዓ.ም እስከ ግንቦት ፮ /፳፻፲፭ ዓ.ም ድረስ ይህ መርሐ ግብር ይከናወናል፡፡ በዋነኛነትም የማኅበሩን የ፴፩ ዓመት አገልግሎት የግቢ ጉባኤ ፍሬዎችን አስተዋጽዖ ለቤተ ክርስቲያን፣ ለምእመናን፣ ለተማሪ ወላጆች፣ ለሀገር እና ለዓለም በማስተዋወቅ ነው፡፡
የማኅበረ ቅዱሳንን የግቢ ጉባኤያት መርሐ ግብርን መደገፍ የተማሪዎችን መንፈሳዊ ሕይወት መርዳት ብቻ ሳይሆን ጠቀሜታው ለሀገር፣ ለቤተ ክርስቲያንና ለሁላችንም ጭምር በመሆኑ ተገቢውን እገዛ የማድረግ ኃላፊነት አለብን፡፡ ለዚህም የአምላካችን የልዑል እግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃድ እንዲሆንልን በጸሎት ማሳሰብም ተገቢ ነው፡፡
ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን!
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!