“ዓላማዬ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎችን በዕውቀት ማነጽ ነው” (ሄኖክ ግዛው)
ሄኖክ ግዛው በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የ፳፻፲፯ ዓ.ም ተመራቂ ነው፡፡ በሒሳብ ትምህርት ክፍል አጠቃላይ ውጤት የትምህርት ክፍሉ ሜዳልያና በዩኒቨርሲቲው አጠቃላይ ውጤት ደግሞ 3.99 በማስመዝገብ በከፍተኛ ውጤት የዋንጫ ተሸላሚ ሆኗል፡፡ ዩኒቨርሲቲውም በመደበኛ መምህርነት በመቅጥር የሁለተኛ ዲግሪውንም ስፖንሰር በማድረግ እንዲማር ዕደል ሰጥቶታል፡፡
ሄኖክ ይህንን ውጤት እንዴት ማምጣት ቻለ? የቤተሰቦቹና የመምህራኑ ድርሻ ምን ነበር? አስተዳደጉና ለትምህርት የሰጠውን ትኩረት አስመልክተን ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡ እንዲህ ተዘጋጅቷል፡፡
ስለ አስተዳደግህ በመግለጽ ውይይታችንን ብንጀምር?
ሄኖክ፡- የተወለድኩት ከወልቂጤ ከተማ 42 ኪሎ ሜትር ርቀት በምትገኘውና ከአበሽጌ ወረዳ ወጣ ብላ በምትገኝ በምዕራብ ሸዋ ዞን ገጠር ቀበሌ ውስጥ ነው፡፡ እንደማንኛውም የገጠር ልጅ ለቤተሰብ እየታዘዝኩ፣ ከብቶች እየጠበቅሁና እያሰማራሁ ነው እስከ ዘጠኝ ዓመቴ ያደግሁት፡፡ ትምህርቴንም በሚመለከት አባቴ እስከ ስምንተኛ ክፍል ተምሮ የነበረ ቢሆንም ቤተሰብን ለመርዳትና ራሱንም ለመቻል ወደ ግብርናው ተሰማርቶና ትዳር ይዞ ኖረ፡፡ ነገር ግን ከፍተኛ ቁጭት ስለነበረው የትምህርት እልሁን በእኛ በልጆቹ መወጣት ይፈልግ ነበር፡፡ በአካባቢያችን ጥሩ ትምህርት ቤት ስላልነበረ ታላቅ ወንድሜን አስቀድሞ ወደ ወደ አበሽጌ ከተማ ልኮ ያስተምረው ስለነበር እኔንም ከወንድሜ ጋር ትምህርቴን እንድከታተል ወደ አበሽጌ ላከኝ፡፡ በየሳምንቱ ዓርብ ለሳምንት የሚሆነን ምግብ ይላክልናል፤ የእኛ ድርሻ መማር ብቻ ነበር፡፡

ለትምህርት የነበረህ ፍላጎትና ውጤትህ ቤተሰቦችህ ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ አልነበረም?
ሄኖክ፡- ለታናናሾቼ አርአያ ሆኛለሁ ማለት እችላለሁ፤ እኔን ተከትለው እነርሱም ከፍተኛ የትምህርት ፍቅር አላቸው፡፡ እኔ ደግሞ የታላቅ ወንድሜ ውጤታማነት አግዞኛል፤ እኔም በተፈጥሮ የነገሩኝን ነገር ያለመርሳት፣ በትምህርቴም ክፍል ውስጥ አስተማሪዎቼ ሲያስረዱ የመቀበል አቅም ነበረኝ፡፡ በውጤቴም እስከ መጨረሻው ድረስ የደረጃ ተማሪ ነበርኩ፡፡ ስምንተኛ ክፍልንም 100 ውጤት አምጥቼ ዘጠነኛ ክፍልን ለመማር ወደ ወልቂጤ ከተማ መጣሁ፡፡ ወልቂጤም ብዙ አልተቸገርኩም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ተከታትዬ በጥሩ ውጤት ነው ያለፍኩት፡፡ እናትና አባቴ አንዲት እኅትና አራት ወንድ ልጆችን ነው የወለዱት፡፡ ታላቅ ወንድሜ ከኮሌጅ ተመርቆ አዲስ አባባ ሥራ ላይ ነው፣ እኔ እግዚአብሔር ፈቅዶ ዘንድሮ ተመርቄያለሁ፣ ታናሽ ወንድሜ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሦስተኛ ዓመት አርክቴክቸር ተማሪ ሲሆን ትንሹም በትምህርት ላይ ይገኛል፡፡ አንዲት ታላቅ እኅት ነበረችን እርሷም ትታመም ስለነበር ጸበል በሄደችበት ነው ያረፈችውና ከባድ ኀዘን ነበር በቤታችን ውስጥ የተፈጠረው፡፡
ከቤተሰቦቼ ጋር በጣም የጠበቀ ቅርበት ስለነበረኝ አቅማቸው በፈቀደ መጠን ከማበረታታት ወደኋላ አላሉም፡፡ በተለይ አባታችን ተምራችሁ አንድ ደረጃ ላይ መድረስ አለባችሁ እያለ ስለሚመክረን የቅርብ ክትትሉ አልተለየንም፡፡
በሰንበት ትምህርት ቤት ስለነበረህ ተሳትፎ ብትገልጽልን?
ሄኖክ፡- ቤተ ክርስቲያን ከጓደኞቼ ጋር እሄዳለሁ፣ በሰንበት ትምህርት ቤትም በአባልነት ወጣ ገባ ያለ ተሳትፎ ብቻ ነበር የነበረኝ፡፡ እንደ ወጣት ዓለም ስባ እንድታስቀረኝ ዕድሉን አልሰጠኋትም፤ እምነቴን ለመጠበቅ ጥረት እያደረግሁ ነው ያደግሁት፡፡ መውደቅ መነሣቱ ቢኖርም በእምነት ጸንቼ ለመኖር የምችለውን ሁሉ ሳደርግ ነበር፡፡ ወደ አገልግሎት የመግባት ዕድሉን ግን አላገኘሁም፡፡ በተፈጥሮ ዝምታን ስለማበዛ ራሴን ለመማር እንጂ ለማገልገል አላዘጋጀሁትም፡፡
ከፍተኛ ትምህርት ተቋም (ዩኒቨርሲቲ) ስትገባ መንፈሳዊ ሕይወትህን እንዴት ትመራ ነበር?
ሄኖክ፡- በግቢ ጉባኤ ውስጥ በአባልነት ስሳተፍ ነበር፣ ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄድ፣ መጸለይ አዘወትራለሁ፡፡ አገልግሎትን በተመለከተ ግን ኮርስ መከታተልና በልዩ ዝግጅት ከመሳተፍ ውጪ ወደ አገልግሎት አልገባሁም፡፡
ቤተሰብ ውጤታማ ሆነህ እንድትወጣ ከመጓጓትና ለትምህርትህ ልዩ ትኩረት እንድትሰጥ ከመፈለግ አንጻር ወደ ግቢ ጉባኤ እንዳትሄድ አልተከለከልክም?
ሄኖክ፡- ቤተሰቦቼ ለትምህርት ልዩ ትኩረት እንደምሰጥ ስለሚያውቁ ወደ ቤተ ክርስቲንና ግቢ ጉባኤ እንዳልገባ ያደረጉት ጫና አልነበረም፡፡ እኔም ይህንን ስለምረዳ መቼ ቤተ ክርስቲያን መሄድ፣ መቼ ግቢ ጉባኤ መሄድ እንዳለብኝ ስለማውቅ ሁሉንም አጣጥሜ ለመጓዝ ጥረት አድርጌያለሁ፡፡

የትምህርት ክፍሌ (የሒሳብ ትምህርት) ልዩ ትኩረት የሚሻ የትምህርት ዓይነት በመሆኑ ከመምህራን ከማገኘው ዕውቀት በተጨማሪ በራሴም ከፍተኛ ጥረት ሳደርግ ነበር፡፡ የመምህራኖቼም ጥሩ ድጋፍና አይዞህ ባይነት አልተለየኝም ነበር፡፡
የውጤታማነትህ ምሥጢር ምንድነው?
ሄኖክ፡- የመጀመሪያው ውሳኔ ነው፡፡ በዩኒቨርሲቲ ቆይታዬ ከተሰጡት 50 የትምህርት ዓይነቶች 43A+ ነውያመጣሁት፣ ከአንድ ትምህርት A-ውጪቀሪዎቹ A ነው ያስመዘገብኩት፡፡ማንኛውም ቤተሰብ ልጆቹ ተምረው ዶክተር እንዲሆኑ ነው የሚመኘው፡፡ ልጆችም ብንሆን ከልጅነት ጀምሮ ዶክተር ወይም አውሮፕላን አብራሪ እንድንሆን እንመኛለን፡፡ እኔ ግን መምህርነትን ከልጅነቴ ጀምሮ ነው ስመኘው የኖርኩት፤ ቤተሰብም ሲጠይቀኝ መምህር ነው የምሆነው ስለምላቸው በውሳኔዬ ነው የጸናሁት፡፡ የመጀመሪያ ዓመት ውጤቴም ከፍተኛ ስለነበረ ለምን ሕክምና አታጠናም የሚሉኝ ብዙዎች ነበሩ፡፡ እኔ ግን ፍላጎቴ ስላልነበር ተማሪዎች የትምህርት ክፍላቸውን ሲመርጡ እኔ ግን ሐሳቤን እንዳልቀይር ግቢውን ትቼ በመውጣት ወደ ቤተ ክርስቲያን ነው የሄድኩት፡፡
ከግቢው ከፍተኛ ውጤት ማምጣት አለብኝ ብዬ አልነበረም የማጠናው፡፡ ነገር ግን በሂደት ጥሩ ውጤት እያመጣሁ መሆኔን ስረዳ ነው በጥሩ ውጤት ተመርቆ የመውጣት ፍላጎቴ ከፍ ያለውና ቢያንስ ሜዳልያ ማግኘት አለብኝ የሚለው ፍላጎት ያደረብኝ፡፡ የጓደኛ ግፊት፣ ሌሎች ሱሶች የሚያጠቁኝ ሰው አይደለሁም፤ ከዓላማዬ የሚያዘናጋኝም የተለየ ችግር ስላልነበር ሙሉ ትኩረቴን ትምህርቴ ላይ ነበር የማሳርፈው፡፡
ፈተና ሲኖርም ጠለቅ ያለ ጥናቴን በሦስት ቀን ውስጥ አጠናቅቃለሁ፤ ክፍል ውስጥ የሚሰጠውን ትምህርት በትኩረት እከታተላለሁ፤ አንድ ጊዜ ከተረዳሁ ደግሞ አልረሳም፣ በዚህ ላይ የሒሳብ ትምህርት ክፍል መምህራኖቼ ድጋፍ ስለማይለየኝ በውጤት መዋዠቅ ውስጥ ሳልገባ እስከ መጨረሻው መዝለቅ ችያለሁ፡፡
ለጥናት የትኛውን ጊዜ ትመርጥ ነበር?
ሄኖክ፡- ከሰኞ እስከ ዓርብ ጠዋትና ከሰዓት በኋላ ትምህርት ስለሚኖረን ለጥናት ያለኝ ጊዜ ማታ ነው፡፡ ስለዚህ ከራት በኋላ ያለውን ጊዜ ነው የምጠቀመው፡፡ ራት ከበላሁ በኋላ ቢበዛ እስከ ሌሊቱ ሰባትና ስምንት ሰዓት እያጠናሁ ልቆይ እችላለሁ፡፡ ይህ ሰዓት ለእኔ ልዩ ምቾት የሚሰጠኝ ጊዜ ነው፡፡
ጊዜህን ለትምህርትህ እንደሰጠህ ሁሉ በትርፍ ሰዓትህ በምን ትዝናና ነበር?
ሄኖክ፡- ትርፍ ሰዓት ሲኖረኝ ቀድሞ ሙዚቃ ነበር የማደምጠው ግቢ ከገባሁ በኋላ ግን ከቀድሞ ይልቅ ይበልጥ ቤተ ክርስቲያንን እያወቅኋት በመምጣቴ መዝሙር በመስማት፣ ቤተ ክርስቲያን በመሄድ ነው የማሳልፈው፡፡
በትምህርትህ ውጤታማ እንድትሆን የቤተሰብ ድጋፍ እንዴት ነበር?
ሄኖክ፡- ቤተሰቦቼ በመካከለኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ ናቸው፡፡ ገንዘብም ቢሆን የሚያስፈልገኝን ሁሉ በማሟላት ሲደጉሙኝ ቆይተዋል፡፡ አባቴ ለትምህርት ከተባለ ያለምንም ቅሬታ የቻለውን መሥዋዕትነት ይከፍላል፣ የጠየቅነውን ሳያሟላ ዕረፍት አይኖረውም፡፡ ስለዚህ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ውስጥ ሆኜ ቤተሰቦቼ የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ከማድረግ ወደ ኋላ አላሉም፡፡ እኔም አደራቸውን ለመወጣት የቻልኩትን ሁሉ ለማድረግ ጥረት አድርጌያለሁ፡፡
አባቴ ለትምህርት ያለው ፍቅር ከፍተኛ ስለሆነና እርሱ ያጣውን በልጆቹ መበቀል ስለሚፈልግ “ከእኔ ምንም አትጠብቁ፣ የማወርሳችሁም ነገር የለኝም፤ ስለዚህ ጠንክራችሁ ተማሩ” በማለት ከፍተኛ ግፊት ስለሚያደርግ ለትምህርት ከሆነ ማንኛውንም መሥዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ የሆነ ቆራጥ አባት ነበር፡፡ ወላጅ እናቴም ከአባቴ የተለየ አመለካከት አልነበራትም፡፡ ለራሳቸው እያስፈለጋቸው አጉድለው ለእኛ ለልጆቻቸው የሚያደረጉት ነገር ያስገርመኛል፡፡ ሁል ጊዜም ከራሳቸው ይልቅ እኛን ያስቀድማሉ፡፡ እዚህ ደረጃ ላይ ለመድረሴ የወላጆቼ ክትትልና ድጋፍ ከፍተኛ ድርሻ ነበረው፡፡
በግቢ ቆይታህ ከጓደኞችህ ጋር ምን ዓይነት ግንኙነት ነበረህ?
ሄኖክ፡- እኔ ጓደኛ ከማያበዙት ወገን ነኝ፡፡ በማደሪያ ክፍላችን ውስጥ አብረን ስላለን አንዳንድ ነገሮችን ልንነጋገር፣ ልንደጋገፍ እንችላለን፡፡ ያ ግንኙነት ጓደኝነት ነው ማለት አይደለም፡፡ ክፍል ውስጥም እንዲሁ፡፡ ነገር ግን ትምህርቴን ጨርሼ ከግቢ እስክወጣ ድረስ አንድ ጓደኛ ብቻ ነበረኝ፡፡ ከእርሱም ጋር ትርፍ ሰዓት ካለን ነው የምንገናኘው፤ በተለይ ቅዳሜ ከቅዳሴ በኋላ ጊዜ ስለሚኖረን አብረን እንሆናለን፣ ሻይ ቡና እንላለን፡፡ በግል ሕይወታችን ዙሪያም እንመካከራለን፡፡ በተረፈ ቀሪውን ሰዓት ደግሞ ዕረፍት አደርጋለሁ፡፡
ከክፍል ልጆች ጋር ደግሞ ፈተና ከመድረሱ በፊት አስረዳን ስለሚሉኝ ባዶ ክፍል ፈልገን አስረዳቸዋለሁ፣ እኔም እያስረዳሁ አብሬ እማር ነበር ማለት እችላለሁ፡፡
በግቢ የነበረህ ቆይታ በድል ተወጥተኸዋልና የወደፊት ዓላማህ ምንድነው?
ሄኖክ፡- ተቋሙ የመምህርነት ዕድሉን ሰጥቶኛል፣ በዚህ ላይ ደግሞ ሁለተኛ ዲግሪዬን እንድማር ስፖንሰር ሆኖኛል፡፡ የወደፊት ዕቅዴ በመምህርነቱ የመቀጠል ፍላጎት ቢኖረኝም ግቢ ውስጥ ለረጅም ጊዜ የመቆየት ፍላጎት የለኝም፡፡ ከታች ወርጄ አንደኛ ወይም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ ለማስተማር ነው የማስበው፡፡ ዓላማዬ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎችን በዕውቀት ማናጽ ነው፤የትምህርት መሠረት የሚገነባው ከሕፃንነት ጀምሮ ነውና ውጤታማ ሆነው እንዲወጡ የድርሻዬን መወጣት አለብኝ፡፡ በማኅበረሰብ አገልግሎትም የመሳተፍ ፍላጎት ስላለኝ ይህንን ሕልሜን ለማሳካት ጥረት አደርጋለሁ፡፡ ልጆቹን መንገድ ማሳየት፣ መምራት ላይ ትኩረት አደርጋለሁ፡፡ እዚሁ ወልቂጤ እያስተማርኩም ታናናሽ ሁለቱን ወንድሞቼን ማስተማር፣ አብሬአቸው መኖርና ውጤታማ ይሆኑ ዘንድ መርዳት እንዳለብኝ ራሴን አሳምኜዋለሁ፡፡
በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እና በመንፈሳዊ ሕይወት ጸንቶ ለመኖር የምታደርገው ጥረት ምን ይመስላል?
ሄኖክ፡- ከልጅነቴ ጀምሮ ከተሳታፊነት ባለፈ ደፍሮ ወደ አገልግሎት የመግባት ልምዱ የለኝም፡፡ ጸጋውም ያለኝ አይመስለኝም፡፡ ነገር ግን ያለ መንፈሳዊ ሕይወት ትርጉም አይኖረውምና ጥሩ ክርስቲያን መሆን፣ ቤተሰቤንም የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ ተገንዝበው በመልካም መንገድ ላይ እንዲጓዙ አርአያ መሆን እፈልጋለሁ፡፡
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ተማሪዎች በመደበኛ ትምህርታቸውም ሆነ በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ውጤታማ ሆነው እንዲወጡ ከተሞክሮህ በመነሣት ልምድህን ብታካፍል?
ሄኖክ፡- የገጠር ወይም የከተማ ልጅ ብሎ መከፋፈሉ አስፈላጊ ባይሆንም እስከሚለምዱት ድረስ ጫናው በገጠር ልጆች ላይ የሚበረታ ይመስለኛል፡፡ እኔም የተገኘሁት ከገጠር ስለሆነ ስሜታቸውን እጋራለሁ፡፡ ማንኛውም ተማሪ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሲገባ ግር ሊለው ይችላል፡፡ የመደናገጥ፣ ፍርሃት ውስጥ የመግባት ችግር ሊገጥመው ይችላል፡፡ ነገር ግን ይህንን በመቋቋም ከማንም እንደማያንስና የተሻለ ብቃት እንዳለው በማመን ተስፋ ሳይቆርጥ መማር ይገባዋል፡፡
ትምህርት ጊዜን ይፈልጋል፣ ለፈተና ብቻ ብለን የምናጠናው ሳይሆን ዕውቀታችን ለማስፋት፣ ወደፊት ለሚጠብቀን የሕይወት ምዕራፍ እንደሚረዳን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ከማኅበራዊ ሚዲያ ጋር ያላቸውን ቁርኝት መቀነስ፣ ሞባይላቸውን ለትምህርት አጋዥ ለሚሆኑ አገልግሎቶች ብቻ ማዋል ይጠበቅባቸዋል፡፡ ማኅበራዊ ሚዲያው ብዙዎችን ከዓላማቸው እያዘናጋ ያሰቡበት እንዳይደርሱ እንቅፋት ስለሚሆን ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡
ተሞክሮህን ስላካፈልከን በእግዚአብሔር ስም እናመሰግናለን፡፡
ሄኖክ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
ስብሐት ለእግዚአብሔር
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!