ዐርብ ዕለተ ስቅለት
ከመምህር አዲሱ በዛብህ
ዕለተ ዓርብ በቤተክርስቲያን ልዩ ቀን ነው፡፡ የማይታመመው ታሞ የዋለበት፣ የወደቁ ከተረሱበት ከትቢያ የሚያነሳ እሱ ሲወድቅ ሲነሳ የዋለበት፣ ሕመምተኞችን የሚፈውስ እሱ ሲያቃስት የዋለበት፣ ከሲኦል የዲያብሎስ ግብር ነፃ የሚያወጣ ሲገረፍ የዋለበት፣ ወልደ እግዚአብሔር ለወዳጆቹ ድኅነት በመሥዋዕትነት ሙሽራ የሆነበት የደስታ ቀን፤ አሳዳጅ አሳሪያችን ዲያብሎስ ከነወጥመዱ ድል የተነሳበት ቀን ነው። ከዚህም የተነሳ በቤተክርስቲያን የተለያየ ምሥጢራዊ ስያሜዎች ተሰጥቶታል፡፡
የስቅለት ዓርብ ይባላል።
የዓለም ሁሉ መድኃኒት የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአዳምና ለልጆቹ ሁሉ ቤዛ ሆኖ በመልዕልተ መስቀል ላይ ተሰቅሎ ለዓለም ድኅነት መሥዋዕት ሆኖ የዋለበት ዕለት በመሆኑ የስቅለት ዓርብ ተብሏል። (ማቴ ፳፯፥፴፭)
መልካሙ ዓርብ ይባላል።
ይህም የሚያስገነዝበን ከስቅለተ ክርስቶስ በፊት ማንም ሰው ሲያጠፋ በመስቀል ተሰቅሎ እንዲሞት ይደረግ ነበር፤ በተለይ በሮማውያንና በፈሪሳውያን ሕግ መስቀል የወንጀለኞች መቅጫ ነበረ። በዚህ ዕለት ግን ታሪክን የሚቀይር ነገርን የሚገለብጠው አምላክ የወንጀለኞች መቅጫ ምልክት የነበረውን መስቀል በደሙ ቀድሶ የምሕረት ምልክት፣ የሕይወት አርአያ፣ የዲያብሎስ ድል መንሻ ፣ የቤተክርስቲያን ጌጥ የገዳማት ዘውድ ስላደረገው እንዲሁም በዕለተ ዓርብ በሞቱ ሕይወትን ስላገኘን መልካሙ ዓርብ ተብሏል፡፡
➣ ጌታችን ከ፮-፱ ሰዓት በመስቀል ላይ ሳለ የተናገራቸው ፯ቱ ቃላት
፩ኛ. ኤሎሄ ኤሎሄ ኤልማስ ላማ ሰበቅታኒ፤ አምላኬ አምላኬ ለምን ተውከኝ። (ማቴ. ፳፯፥፵፮)
፪ኛ. እውነት እውነት እልሃለሁ ዛሬ በገነት ከእኔ ጋር ትኖራለህ፡፡ (ሉቃ. ፳፫፥፵፫)
፫ኛ. አባት ሆይ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ፡፡ (ሉቃ. ፳፫፥፵፮)
፬ኛ. አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው። (ሉቃ. ፳፫፥፴፬)
፭ኛ. እናትህ እነኋት፤ እነሆ ልጅሽ፤ (ዮሐ. ፲፱፥፳፮-፳፯)
፮ኛ. ተጠማሁ። (ዮሐ. ፲፱፥፴)
፯ኛ. ተፈጸመ ። (ዮሐ. ፲፱፥፴)
➣ ጌታችን ከ ፮-፱ ሰዓት በመስቀል ላይ ሳለ የተፈጸሙ ፯ቱ ተአምራት፤
፩ኛ. ፀሐይ ጨለመች።
፪ኛ. ጨረቃ ደም ሆነች።
፫ኛ. ከዋክብት ረገፉ።
፬ኛ. የቤተመቅደስ መጋረጃ ለሁለት ተከፈለ።
፭ኛ. ዐለቶች ተሰነጣጠቁ።
፮ኛ. መቃብራት ተከፈቱ።
፯ኛ. የሞቱት ተነሡ። (ማቴ. ፳፯፥፵፭-፵፮)
፭ቱ ቅንዋተ መስቀል ችንክሮች ሳዶር፣ አላዶር፣ ዳናት፣ አዴራ እና ሮዳስ ይባላሉ።
➣ ሞትን ይሽረው ዘንድ የማይሞተው ሞተ፤ መከራንም ታገሰ።
➣ ሁሉን የያዘውን እርሱን ያዙት።
➣ ሁሉን የሚገዛውን እርሱን አምላካችንን እጅ አሰሩት።
➣ ሐጢአትን ይቅር የሚል እርሱን ሐጢአተኛ አሉት።
➣ የማይገረፍ አምላክ እርሱን የሰውን ሥጋ በመዋሐዱ ገረፉት።
➣ እንደ መብረቅ የሚያንፀባርቀውን ነጭ ልብስ የሚያለብስ አምላክ እርሱን ቀይ ግምጃ አለበሱት።
➣በእሳት በተጋረዱ ዙፋን ላይ የሚቀመጥ እርሱን በመዘባበቻ ወንበር ላይ አስቀመጡት።
➣እንደ ድንኳን ሰማይን የዘረጋ እርሱን በመስቀል ላይ ሰቀሉት።
➣የመላእክትን አለቆች በፊቱ በመፍራት የሚቆሙለት እርሱን በጲላጦስ ፊት አቆሙት።
➣በሕያዋንና በሙታን ላይ የሚፈርድ እርሱን እንደበደለኛ ተፈረደበት።
➣አለምን ሁሉ በቅፅበት የፈጠረ እርሱ በመለኮቱ ሕያው ሆኖ በሥጋው ሞተ።
ጌታችን፣ መድኃኒታችን፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቶ በሦስተኛው ቀን ሞትን ድል አድርጎ ተነስቶ ከኃጢአት ቁራኝነት፣ ከዲያብሎስ ባርነት ነፃ አውጥቶናል። እኛስ በሞቱ የዳንን ልጆቹ መንግሥቱን ለመውረስ ምን ልናደርግ ይገባናል?
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለእኛ መሞቱና መነሳቱ የመዳን መንገድን ከፍቶልናል፤ ነገር ግን የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ እኛም እርሱን አብነት ድርገን ያዘዘንን ሁሉ መፈጸም ይገባናል።
➣ ልናደርጋቸው የሚያስፈልጉን ነገሮች ፦
1.እምነት እና ንስሐ
በእግዚአብሔር በሙሉ ልብ ታምነን ከኃጢአታችን ልንጸጸትና ልንመለስ ይገባል። መጽሐፍ እንዲህ ይላልና፤ “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሓ ግቡ”። (ማቴ. ፫፥፩)
2. ቅዱስ ሥጋውን ክቢር ደሙን መቀበል
በጥምቀት (ከውኃና ከመንፈስ/ከአብራከ መንፈስ ቅዱስና ከማኅጸነ ዮርዳኖስ) መወለድ “ዳግመኛ ያልተወለደ ሰው የእግዚአብሔርን መንግሥት ማየት አይችለም” (ዮሐ. ፫፥፫) እንዲል።
ቅዱስ ቁርባንን (ቅዱስ ሥጋናውን፣ ክቡር ደሙን) መቀበል ያስፈልጋል። “ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘለዓለም ሕይወት አለው” (ዮሐ. ፮፥፶፬) እንዲል።
3. ትእዛዛትን መጠበቅ
➣ እግዚአብሔርን በሙሉ ልብ መውደድ፤ “እግዚአብሔር አምላክህን በፍጹም ልብህ፥ በፍጹም ሰውነትህ፥ በፍጹም ኀይልህ፥ በፍጹም ዐሳብህ ውደደው፤” ። (ሉቃ. ፲፥፳፯ ፣ ዘሌዋ. ፲፱፥፲፰)
➣ ሰውን እንደ ራስ መውደድ፤ “ባልንጀራህን እንደራስህ ውደድ፤” (ዘሌዋ. ፲፱፥፲፰)
➣ ዐሥርቱ ትእዛዛትን መጠበቅ፤ “ብትወዱኝ ትእዛዛቴን ጠብቁ፤” (ዮሐ. ፲፭፥፲፬)
4. መጾምና መጸለይ
” ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ፤ መንፈስ ይሻልና፤ ሥጋ ግን ደካማ ነው” (ማቴ. ፳፮፥፵፩)
ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉን ያስተማረን፣ አብነት የሆነን አምላክ ነውና በሁሉ ነገር እርሱን ልንመስለው ይገባናል። ̏ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁና˝ (ዮሐ. ፲፫፥፲፭)
5. መልካም ሥራ መሥራት
በቅዱስ ወንጌል የተጻፈልንን በሕይወት መኖር አለብን።
ድሆችን መርዳት፣ የተራቡትን ማብላት፣ የተጠሙትን ማጠጣት ፣ የታረዙትን ማልበስ፣ … እነዚህንና የመሳሰሉትን የትሩፋት ሥራዎችን ልንተገብራቸው ያስፈልጋል። (ማቴ. ፳፭፥፥፴፩-፵፮)
➣ ምሕረትና ትሕትና መልበስ
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፤ የእጆቹ ፍጥረቶች አይሁድ ያን ሁሉ መከራ ሲያደርሱበት ጊዜ እፍ ብሎ ማጥፋት እየቻለ በዝምታ መከራውን ተቀብሏል፤ እንዲሁም በግፍ ለሰቀሉት አባት ሆይ የሚያደርጉትን ያውቁምና ይቅር በላቸው። (ዮሐ. ፲፱፥፩-፳፪) ፣ (ሉቃ. ፳፫፥፴፬)
6. ትዕግሥት እና ቅድስና
ፈተናን በእምነት መቋቋምና ራስን ከኃጢአት ማራቅ ያስፈልጋል።
“እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ቅዱስ ነኝና እናንተ ቅዱሳን ሁኑ” (ዘሌዋ. ፲፱፥፪፣ ፩ኛ ጴጥ. ፩፥፲፭) እንዲል በቅድስና መንገድ ልንመላለስ ያስፈልጋል።
➣ በአጭሩ መንግሥተ ሰማያት በእምነት ብቻ ሳይሆን እምነት + ሥራ + ጸጋ የሚወረስ ነውና እምነትን ከምግባር ጋር አስተባብረን ልንይዘው ያስፈልጋል።
ስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር

Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!