ውጣ ውረድ

በእንዳለ ደምስስ

ከአርሲ ነገሌ አምስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከሚገኘው የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን መጠለያ ውስጥ ከአንድ መቶ ያልበለጥን ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ሰሞኑን “መንደራችንን ከክርስቲያኖች የማጽዳት ዘመቻ” በሚል በጽንፈኛ አክራሪ ሙስሊሞች በተከሠተ ወረራ መሰል ዘመቻ ተፈናቅለን ተጠልለናል፡፡ መኖሪያ ቤቶቻችን ተቃጥለዋል፣ ንብረቶቻችን ወድመዋል፣ ከጥቂት አባወራዎች በስተቀር አባቶቻችን ታርደዋል፡፡ በእግዚአብሔር ቸርነት የተረፍነው ቤት ንብረታችንን ጥለን ራሳችንን ለማዳን ቤተ ክርስቲያንን መጠጊያ አድርገናል፡፡

አባቴ በሰማዕትነት ካለፉት ውስጥ አንዱ ነው፡፡ እኔንና እናቴን ደብድበው ሲጥሉን፣ አባቴ እኛንና ቤት ንብረታችንን ለመከላከል ሲል ባደረገው ተጋድሎ እንደ በግ እጅና እግሩን አስረው በፊት ለፊታችን አርደውታል፣ ቤታችንን ከነከብቶቻንና ንብረቶቻችን ሁሉ እሳት ለቀውበታል፡፡

ሰፈሩ በለቅሶና በዋይታ ተሞልቶ ሁሉም ራሱን ለማዳን ማቄን ጨርቄን ሳይል ነፍሱን ለማዳን ይሯሯጣል፡፡ እንደምንም እናቴን ከወደቀችበት አንስቼ ወደ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ነፍሳችንን ለማዳን ሮጠን ከክርስቲያን ወገኖቻችን ጋር ተቀላቀልን፡፡

ተወልጄ ያደግሁት እዚያው መንደር ውስጥ ነው፡፡ የ፳፯ ዓመት ወጣት ስሆን ሰላማዊት ዋለልኝ እባላለሁ፡፡ እኔና ቤተሰቦቼ በመንደሩ በጣት ከሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች መካከል ነን፡፡ በርካታ የእስልምና እምነት ተከታዮች የሚገኙባት ሲሆን በየአራት ወይም አምስት መቶ ሜትሮች ከግዙፍና ዘመናዊ እስከ ቆርቆሮ ለበስ አነስተኛ መስጊዶች ከቁመታቸው ገዝፈው ይታዩባታል፡፡ ፺፭ በመቶ የሚሆነው የአካባቢው ነዋሪ የእስልምና ተከታይ ሲሆን፣ ወንዶቹን ነጭ ጀለቢያ ሴቶቹን ደግሞ ጥቁር ሂጃብ ለብሰው በየመንገዱ ማየት የተለመደ ትእይንት ነው፡፡

በአቅራቢያችን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታዮች የምንገለገልበት የፃድቁ አባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ብቸኛው ነው፡፡ መላው ቤተሰባችን በእምነታችን በጣም ጠንካራ ከሚባሉት ውስጥ እንመደባለን፡፡ በተለይም አባቴ ይህ ቤተ ክርስቲያን በአያቴ ከፍተኛ ጥረት የተተከለ ነው ብሎ ስለሚያምን ልዩ ፍቅር አለው፡፡ ባለው ጊዜ ሁሉ ዘወትር ቤተ ክርስቲያን የጎደላትን በማሟላት ደከመኝ ሰለቸኝ የማይል ስለሆነ ከእናታችን ጀምሮ ቤተሰቡ ሁሉ የእርሱን ፍኖት ተከትለን አድገናል፡፡ በየቀኑ አስገዳጅ ችግር ካልገጠመን በስተቀር ቤተ ክርስቲያን ሄደን ሳንሳለምና የኪዳን ጸሎት ሳናደርስ አንውልም፡፡ የኪዳን ጸሎት ባይታጎልም የአገልጋይ እጥረት ስላለ በሰንበተ ክርስቲያንና በዓመት አራት ጊዜያት ከሚከበሩ የፃድቁ መታሰቢያ ክብረ በዓላት፣ በተጨማሪ የዘመን መለወጫ፣ የልደት፣ የትንሣኤ እና የደብረ ታቦር በዓላት ብቻ ይቀደስበታል፡፡

በቀድሞው ዘመን ክርስትና ከተስፋፋባቸው አካባቢዎች አንዱ የነበረ ቢሆንም ቀስ በቀስ ግን እስልምናው አይሎ ኦርቶዶክሳውያን አረጋውያን ዐረፍተ ዘመን እየገታቸው በማረፋቸው፣ የእስልምናው ተጽእኖ መቋቋም ተስኗቸው ወደ ከተማ የገቡ በርካቶች ናቸው፡፡ ክርስቲያን የነበሩ ልጃገረዶችንም በጠለፋም ይሁን በሀብት የበላይነትና በማስፈራራት በማስለም ስለሚያገቧቸው የክርስቲያኑ ቁጥር ተመናምኗል፡፡ በዚህም ምክንያት የአብዛኛው ነዋሪ መሠረት ክርስትና ቢሆንም ዛሬ ግን ተለውጧል፡፡

ለመስፋፋታቸው ዋነኛው ምክንያት ከአስገዳጅነታቸው በተጨማሪ የክርስቲያኖች ቸልተኝነት፣ ክርስቲያን ወንዶች በሥራ ምክንያት በሚያደርጉት እንቅስቃሴ የትዳር አጋሮቻቸውን ከከተማ ይዘው ስለሚመጡ የአካባቢው ተወላጅ የሆንን ልጃገረዶች ወደ ዩኒቨርሲቲ የመግባት ዕድል ካለገኘን ወይም ወደ ከተማ ካልኮበለልን በስተቀር ትዳር ሳንይዝ ዕድሜአችን እያለፈ በዕድላችን ስናማርር እንኖራለን፡፡

ሁለቱ ታላቅ እኅቴና ታናሼ በዚህ ምክንያት በሙስሊም ወጣቶች ገንዘብ ተደልለው ምድራዊ ሕይታቸውን ለማሳመር ሲሉ የእግዚአብሔር ልጅነታቸውን ክደው፣ የአባቴን ልፋትና መሠረታቸውን ጥለው ሰልመዋል፡፡ ሁለቱ ወንድሞቼም የከተማ ነጋዴ ስለሆኑ እንደ ሌሎቹ የአካባቢያችን ወጣቶች በከተማ ኑሯቸውን መሥርተው፣ በከተማው ያገኟቸውን ሴቶች አግብተው ይኖራሉ፡፡ አባቴ እኅቶቼን ለማስመለስ ያደረገው ጥረት ስላልተሳከለት በኀዘን እንደተኖር ነበር፡፡

በትምህርቴ እስከ ፲፪ኛ ክፍል ልድረስ እንጂ ውጤት ስላልመጣልኝ እቤት ቀርቻለሁ፡፡ የቤተሰቦቼን እጅ ከመጠበቅ እያልኩ ያልሞከርኩት ሥራ የለም፤ ግን አልተሳካልኝም፡፡ በቅርቡ ግን ሰፈራችን ከሚገኝ ጉልት ድንች፣ ቲማቲምና የመሳሰሉትን እየቸረቸርኩ ከራሴ አልፌ ለቤተሰቦቼ መርዳት ባልችልም ለራሴ መሆን አላቃተኝም፡፡ አንድ ነገር ግን ይጎድለኛል፤ በዚህም እጨነቃለሁ፡፡ ትዳር መያዝ አለመቻሌ፡፡

ራሴን ዕድለ ቢስ አድርጌ እቆጥረዋለሁ፡፡ ነፍሷን ይማርና አያቴ “አንዲት የገጠር ሴት ትዳር ይዛ ራሷን ካልተካች እንዴት ሴት ተብላ ትጠራለች?” እያለች ስትናገር የምሰማው ድምጽ ሁልጊዜ ዕረፍት ይነሳኛል፡፡

ያገቡም ያላገቡም ሙስሊም ወንዶች እኔን ከመጠየቅ ወደ ኋላ ያሉበት ጊዜ የለም፡፡ በተለያዩ መደለያዎችን ስጦታዎች እጅ እንድሰጥ ከማድረግ እስከ ዛቻና ማስፈራሪያ ይደርስብኛል፡፡ አንዳንዶቹ ሦስትና አራት ሚስት ያላቸው ናቸው መውጫ የሚከለክሉኝ፡፡ ነገር ግን በያዝኩት እውነተኛና ቀጥተኛ በሆነው በክርስትና መንገዴ ከማንም ጋር አልደራደርም፤ የትናንት፣ የዛሬም፣ የወደፊትም አቋሜ ነው፡፡ ከአካባቢው ልማድ አንጻር ዕድሜዬ እየገፋ እንደሆነ ይታወቀኛል፣ ነገር ግን እግዚአብሔር አምላኬን፣ የአምላኬን እናት ቅድስት ድንግል ማርያምን፣ ቅዱሳን ጻድቃን፣ ሰማዕታትን፣ ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖትን ትቼ ከምኮበልል ሞቴን እመርጣለሁ፡፡

ማግባት እንዳለብኝ ውስጤ ያስገድደኛል፡፡ ግን ማንን ላግባ? ፈላጊ እንደሌላት ጋለሞታ ራሴን እቆጥራለሁ፡፡ መልሼ ደግሞ እግዚአብሔር ለእኔ ያዘጋጀው ይኖራል፣ ለምን አጉረመርማለሁ እያልኩ ራሴን ለማጽናናት ጥረት አደርጋለሁ፡፡ ውስጤ ደስታ ርቆታል፡፡ በከፋኝ ሰዓት መሸሸጊዬ ፃድቁ ናቸው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ሔጄ ዕንባዬን እያፈሰስኩ እቆያለሁ፡፡

እኅቶቼን ጨምሮ የቅርብ ጓደኟቼ ብዙዎቹ “ደረቴ ይቅላ፣ የዚህ ዓለም ኑሮን ላጣጥማት” በሚል ፈሊጥ በተኩላዎች ተነጥቀው ጓደኛ የምለው የለኝም፡፡ በየቀኑ “እከሊት እኮ ሰለመች፣ እከሌን እኮ አገባችው” መባል የተለመደ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ቀስ በቀስ የክርስቲያኖች ቁጥር ተመናምኗል፡፡ ያም ቢሆን ግን በሰላም ተከባብሮ ከመኖር ውጪ አንዱ በአንዱ ላይ ተነሥቶ ግጭት ተከስቶ አያውቅም ነበር፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን መልኩን ቀይሮ “ክርስቲያኖችን ከአካባቢው ማጽዳት” በሚል እንቅስቀሴያቸው በየጊዜው ግጭት ማስተናገድ የተለመደ ሆኗል፡፡

ቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ብንጠለልም አባቴን መርሳት አልቻልኩም፡፡ ሕይወቱ ቢያልፍ እንኳን አስከሬኑ የአውሬ ሲሳይ እንዳይሆን መቅበር አለብኝ በሚል ስሜት ተነሣሥቼ ግርግሩ ጋብ ሲል አመሻሽ ላይ ወደ ሰፈራችን ሮጥኩ፡፡ አካባቢው ምድረበዳ መስሏል፣ ያስፈራል፣ ቤት ንብረታችን ወድሞ ጭሱ ብቻ አልጠፋም፡፡ አባቴን ከታረደበት ለማንሣት አስከሬኑን ዞር እያልኩ ፈለግሁ፣ ማግኘት ግን አልቻልኩም፡፡ በታረደበት ቦታ የፈሰሰውን ደሙን ብቻ አገኘሁ፡፡ ቁጭ ብዬ አለቀስኩ፡፡

“ልጄ አታልቅሺ፡፡ አባትሽ የጀነት ሰው ነው፡፡ ልጆቻችን እምቢ ብለው አብረን በፍቅር ከኖርናቸው ሰዎች ለዩን፣ ምን እናድርግ ልጄ አቅም አጣን፣ እንደ እናንተው ዕንባችን እናፈስሳለን፡፡ በይ ደሙ እንዳይዞርብሽ ተነሺ” አሉ ጎረቤታችን ሐጂ ሙስጠፋ እነሣ ዘንድ በደከመ ጉልበታቸው እየጣሩ፡፡

“ሐጂ ተዉኝ፡፡ አባቴ ካረፈበት፣ ሰማዕትነት ከተቀበለበት ሆኜ ላልቅስ” ብዬ ሣሩ ላይ ተደፋሁ፡፡

“ልጄ እያደረግሽ ያለው ነገር በጎ አይደለም፣ እባክሽ ልጄ ካገኙሽ ይገድሉሻል፡፡ የአባትሽንና የሌሎችን ጎረቤቶቻችን አስከሬን የአካባቢው ሚሊሺያዎች አንስተው የት እንደወሰዷቸው እኛም አናቅንም፡፡ ለእናትሽ አንቺ እንኳን ትረፊላት” ብለው ካነሡኝ በኋላ  አብረውኝ አለቀሱ፡፡

ተስፋ ቆርጬ በመጣሁበት ፍጥነት እየሮጥኩ የቀረችኝ እናቴና ሌሎች ወደተጠለሉበት የጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን በረርኩ፡፡

ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከተጠለልን ሦስተኛ ቀናችን ነው፡፡ ነፍስን ለማቆየት የሚበላ የሚቀመስ ባለመኖሩ የሕፃናት ዋይታ፣ የደካማ እናቶች ጣር፣ ከፍተኛ ድብደባ የደረሰባቸው፣ የተደፈሩ ወጣችና እናቶች ሥቃይ ያስጨንቃል፡፡ የትኛውን አጽናንተን የትኛውን እንተው? የሰቆቃ ዕንባ ከእናቶችና ሕፃናት እንደ ጎርፍ ይፈሳ’ል፣ ካህናቱ ነፍሳቸውን ለማትረፍ ሲሉ ጽላቱን ይዘው ሸሽተዋል፣ አንድም ጠያቂ ሆነ አጽናኝ አካል ብቅ አላለም፡፡

አመሻሽ ላይ ከዐሥር የሚበልጡ የአካባቢው ሚሊሺያዎችና ሦስት የአስተዳደር አካላት በአንድ አይሱዙ መኪና ምግብና ብርድ ልብስ ይዘው መጡ፡፡ በተፈጠረው ነገር ማዘናቸውን፣ ችግሩን የፈጠሩት ፀረ ሰላም ኃይሎች እንደሆኑ በመግለጽ አሰልቺ ዲስኩራቸውን ከደሰኮሩ በኋላ ለተጎዱት ሰዎች ነገ የጤና ባለሙያዎችን ይዘው እንደሚመጡና ለጊዜው ለሕፃናትና ለእናቶች እንዲሁም ለሌሎቻችን የሚሆኑ የታሸጉ ምግቦችን፣ የሚጠጣ ውኃ እና ብርድ ልብሶችን አከፋፍለው ሄዱ፡፡

እናቴ ጭካኔን በተላሞሉ ጎረምሶች በደረሰባት ድብደባ ከተጎዱት ሰዎች አንዷ ናት፡፡ እኔን ግን ከማንገላታት ያለፈ ብዙም ጉዳት አልደረሰብኝም፡፡ ብዙዎቹ የማውቃቸው ልጆች ተደፍረዋል፣ እኔን ግን አምላከ ተክለ ሃይማኖት ከልሎኛል፡፡ ለእናቴና ለእኔ የሚያስፈልገውን ምግብና ብርድ ልብስ ተቀብዬ እናቴን ለመንከባከብ ሞከርኩ፡፡ ረኃብና ጥማችንንም ካስታገሥን በኋላ የተጎዱትን ለመንከባከብ የተወሰንን ሰዎች ተሰባበስን ተሯሯጥን፡፡ ነገር ግን ከፍተኛ ሕክምና የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ሁኔታ ከአቅማችን በላይ ሆነ፡፡ ያለን አማራጭ ነገ ይመጣሉ የተባሉትን የጤና ባለሙያዎች መጠበቅ ግዴታ ሆነብን፡፡

አባቴን አሰብኩት፡፡ እኛን ለማሳደግ የከፈለው መሥዋዕትነት፣ ለእምነቱ ያለው ጽናትና ለቤተሰቡ እንዲሁም ለሀገሩ ያለው ፍቅር በቀላሉ መግለጽ አይቻልም፡፡ “እባካችሁ አትግደሉኝ” እያለ እየለመናቸው ፊት ለፊቴ እንደ በግ አረዱት፡፡ ያሰማው የሲቃ ድምፅ እረፍት ነሳኝ፡፡ ምንም መፍጠር ሳልችል፣ ለአባቴ አለሁልህ ሳልለው በፊቴ ታረደ፡፡ ከማልቀስና ከማንባት በስተቀር ሐይወቱን ከግፈኞች እጅ ማዳን የምችልበት መሣሪያ አልነበረኝም፡፡

አንድ ቀን በጠዋት ከቤተ ከርስቲያን ስመለስ በአካባቢያችን በሀብቱ የሚታወቅ ጎልማሳ ጀለቢያውን ለብሶ፣ በረጅም ወፍራም መፋቂያ ጥርሱን እየፋቀ ፊት ለፊቴ ተደቅኖ ያዘኝ፡፡ ከዚህ በፊት በአካል ከማውቀውና ሌሎች ስለ ሀብቱ ሲያወሩለት መስማት ካልሆነ በስተቀር ምንም አይነት ግንኙነት የለንም፡፡ እጄን ለማስለቀቅ ሞከርኩ፡፡ አልተሳካልኝም፡፡

“ምንድነው የምትፈልገው?” በማለት በቁጣ ጠየቅሁት፡፡

“ረጋ በይ፣ ምን ያፈናጥርሻል? ሴት ልጅ አደብ ሲኖራት ነው የሚያምርባት፣ አደብ ግዢ” አለኝ፡፡

በንዴት ገፍትሬው ለመሔድ ጥረት ባደርግም በፈረጠመው ጡንቻው ይዞ አስቀረኝ፡፡

“ለምን አትለቀኝም፡፡ እኔና አንተን የሚያገኛኘን ምንም ነገር የለም” አልኩት እየተጠየፍኩት፡፡

እየሳቀ “ያገናኘናል እንጂ፡፡ እኅቶችሽ እንዴት ተንደላቀው እንደሚኖሩ አታውቂም? የአጎቶቼ ልጆች ናቸው ያገቧቸው” አለኝ፡፡

“እና?”

“እናማ እኔም አንቺን አገባለሁ” አለኝ ሳያመነታ፡፡

“ገድል ግባ፡፡ እኔና አንተ ምን ኅብረት አለን? ዞር በልልኝ ልሂድበት፡፡”

“እኔን ተራምደሽማ አትሔጂም፡፡ ለጥያቄዬ መልስ እፈልጋለሁ” አለ ቁጣው እያገረሸ፡፡

“አልችልም፡፡ ሂድና በገንዘብ የምትደልላትን ፈልግ፡፡ እኔ ክርስቲያን ነኝ” አልኩት ከራስ ፀጉሩ እስከ እግር ጥፈሩ በመጠየፍ እየተመለከትኩት፡፡

“እንደ ሦስቱም ሚስቶቼ ምንም ሳላጓድል ነው አንቀባርሬ ነው የማኖርሽ” አለ እየሳቀ፡፡

ያለኝን ኃይል አጠራቅሜ ገፍትሬው መንገዴን ቀጠልኩ፡፡ ባለበት እንደቆመ የፌዝ ሳቁ ብቻ ተከተለኝ፡፡

እቤት እንደተመለስኩ እያለቀስኩ ለአባትና እናቴ ነገርኳቸው፡፡ “እኛ ለአንቺ መሆን አያቅተንም፡፡ በክርስትና ሕይወትሽ ጠንክሪ፣ የእግዚአብሔርንም ጊዜ ጠብቂ፡፡ እንደ እኅቶችሽ እንዳናዝንብሽ ተጠንቀቂ” በማለት አባቴ አቅፎ አጽናናኝ፡፡

እናቴም “ዕድሜዬ ገፋ፣ ቆሜ ቀረሁ እያልሽ አትጨነቂ፤ እግዚአብሔር ምን እንዳዘጋጀልሽ አታውቂም፡፡ ልመናሽ ወደ እግዚአብሔር ይሁን፣ በገንዘብና ብልጭልጭ ነገር አትታለዪ፣ እኅቶችሽን አጥተናልና አንቺንም እንዳናጣ አደራሽን” አለችኝ፡፡

በዐራተኛው ቀን ጠዋት ከወረዳው የሕክምና ባለሙያዎች መጥተው ጎበኙን፡፡ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸውን እየለዩ ወደ መኪናዎቻቸው ወስደው በሆስፒታል ደረጃ ሕክምና እንደሚያስፈልጋቸው ከገለጹ በኋላ ለሌሎቹ አስፈላጊውን የመጀመሪያ ሕክምና ዕርዳታ አደረጉላቸው፡፡

ከነርሶቹ መካከል አንገቷ ላይ ወፈር ያለ ክር ያሰረችው ነርስ ሁላችንንም ሰብስባ “አሁን አካባቢው እየተረጋጋ ነው፡፡ ክፉ አድራጊዎች ለሰው ባይቻለው ከእግዚአብሔር ፍርድ አያመልጡም፡፡ ለዚህም ነው አካባቢውን የጦር ቀጠና አድርገው፣ የሚገድሉትን ገድለው፣ የሚዘርፉትን ዘርፈው በአይሱዙ መኪና ተጭነው ሲሔዱ ተገልብጦ ለወሬ ነጋሪ እንኳን ሳይተርፉ ጥልቅ ገደል ውስጥ ገብተው አልቀዋል፡፡ እናንተ ልትረጋጉ ይገባል፡፡ አይዟችሁ” በማለት አጽናናችን፡፡

ክፉን በክፉ መቃወም ተገቢ ባይሆንም ለደረሰብን የመንፈስና የአካል ስብራት ባይጠግንልም፣ በሰማዕትነት ያረፉ ቤተሰቦቻችንን በአካል ባይመለሱልንም ክፉ አድራጊዎቹ ሳይውል ሳያድር መቀሰፋቸው አስደሰተን፡፡

በአምስተኛው ቀን ከአርሲ ሀገረ ስብከት የተውጣጡ ልዑካን አልባሳትና ምግብ ይዘው በመምጣት እስከ አሁን ያልመጡት መላው አርሲ አለመረጋጋት እንደነበር በመግለጽ ቶሎ ባለመድረሳቸው ይቅርታ ጠየቁን፡፡ የወንጌል ትምህርት በመስጠት እያበረታቱን ለሦስት ቀናት አብረውን ቆይተው ተመለሱ፡፡

ለአሥራ አምስት ቀን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከጠጠለልን በኋላ አካባቢው በመረጋጋቱ ወደመጣንበት እንድንመለስ ተደረገ፡፡ ያ ውጣ ውረድ የበዛበት፣ እንግልትና ሞት የበዛበት ሕይወት በእግዚአብሔር ቸርነት አልፏል፡፡ ከደቂቃዎች በኋላ ምን እንደሚፈጠር አናውቅም፣ ዛሬን በተጠንቀቅ፣ ነገን ደግሞ እግዚአብሔርን ተስፋ በማድረግ ኑሮአችንን እንደገና “ሀ” ብለን ጀመርን፡፡

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *