ወጣትነት እና እጮኝነት

በዲ/ን ኢያሱ መስፍን

 ክፍል ሁለት

እጮኝነት ከማን ጋር?

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለዚህ ጥያቄ የምትሰጠውን መልስ አለመረዳት በሥጋም በነፍስም ብዙ ዋጋ የሚያስከፍል ስሕተት ውስጥ ሊያስገባ ይችላል። የትዳር አጋር አልያም እጮኛ ለመምረጥ የሃይማኖት አንድነት፣ ዝምድና፣ ዕድሜ፣ ወዘተ ያሉት  ቅድሚያ የምንሰጣቸው መሥፈርቶች በመሆናቸው ትልቅ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። ያስቀደምናቸው መሥፈርቶች ጊዜያዊ እና ሥጋዊ ብቻ ከሆኑ ግን የጋብቻን መንፈሳዊ ዓላማ ለማሳካት እንቅፋት ከመሆናቸውም ባሻገር እስከ ፍጽሜ የሚጸና ጥምረት ለመፍጠርም አዳጋች ይሆናሉ። ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ልጆቿ ቅድሚያ እንዲሰጧቸው አጥብቃ ከምታዝዛቸው መሥፈርቶች መካከል ሃይማኖት እና መንፈሳዊ ሕይወት የመጀመሪያዎቹ ናቸው።

በብሉይ ኪዳንም ሆነ በሐዲስ ኪዳን በሃይማኖት ከማይመስሉን ሰዎች ጋር በትዳር መጣመር የተነቀፈ ምግባር ነው፡፡ አብርሃም ለልጁ ይስሐቅ ሚስትን ፍለጋ ሎሌውን ሲልክ ከአሕዛብ እና ከከነዓናውያን እንዳያጋባው አስምሎ እግዚአብሔርን ከሚያውቁ ከዘመዶቹ አገር ሚስት እንዲያመጣለት የላከው በዚሁ ምክንያት ነው። (ዘፍ 24) እንዲህ ዓይነት ታሪኮችን በመጽሐፍ ቅዱስ ማግኘት የተለመደ ነው። በሐዲስ ኪዳን ያለን አማኞችም ከማይመስሉን ሰዎች ጋር የሚኖረንን ግንኙነት በተመለከተ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶናል። “ከማያምኑ ጋር በማይሆን አካሔድ አትጠመዱ፤ ጽድቅ ከዐመፅ ጋር ምን ተካፋይነት አለውና? ብርሃንም ከጨለማ ጋር ምን ኅብረት አለውና?” (2ቆሮ6፡14)። እስከ ሕይወት ፍጻሜ ከሚቀጥል በመንፈስ ብቻ ሳይሆን በአካል አንድ ከሚያደርግ ከጋብቻ በላይ ልንጠነቀቅለት የሚገባ አካሔድ ወይም ጉዞ ምን አለ?

ብዙዎች ለዚህ ስሑት ሐሳብ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃ አድርገው የሚያቀርቡት አንድ ጥቅስ አለ፡፡ ይህም ቅዱስ ጳውሎስ “ሌሎችንም እኔ እላለሁ ጌታ አይደለም፣ ከወንድሞች ወገን ያላመነች ሚስት ያለችው ቢኖር እርስዋም ከእርሱ ጋር ልትቀመጥ ብትስማማ አይተዋት…” የሚለው ነው፡፡ (1ቆሮ. ፯፥፲፪) የገዛ ፈቃዱን ለማስፈጸም ሳይሆን የእግዚአብሔርን ቃል በእውነት ለመረዳት ለሚያስብ ሰው ይህ ኃይለ ቃል ካላመኑ ሰዎች ጋር ለመጋባት መብት የሚሰጥ አይደለም። ቅዱስ ጳውሎስ “የማታምን ሴት ለማግባት የፈለገ ሰው ቢኖር” ብሎ አላስተማረም፤ ይልቁንም  ክርስትና ባልተስፋፋበት በዚያ ዘመን ተጋብተው ከሚኖሩ መካከል ባል ወይ ሚስት በወንጌሉ ቢያምኑ የትዳር አጋሬ አላመነም ብለው የገነቡትን ቤት እንዳያፈርሱ ልጆች እንዳይበተኑ እና ክርስትና የጸብ እና የመለያየት ምክንያት እንዳይሆን የተሰጠ ትእዛዝ ነው። መልእክቱ አግብተው የሚኖሩትን እንጂ ገና ያላገቡትን አይመለከትም።

ሐዋርያው ዝቅ ብሎ ይህ ያላመነ አጋር ለማመን አልያም ከክርስቲያን አጋሩ ጋር አብሮ ለመኖር ፈቃደኛ ባይሆን መተው ወይም መፍታት እንደሚቻል በመናገር ጌታችን ከዝሙት ውጭ አትፋቱ ብሎ ካስቀመጠው ሥርዓት በተጨማሪ የሃይማኖት ልዩነት ሌላ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ገልጿል። እጮኛ የሚይዝ ኦርቶዶክሳዊ ወጣት እየመረጠ ያለው የትዳር አጋሩን በመሆኑ እና ከጋብቻ ውጪም እጮኛ የሚያዝበት ሌላ አንዳች ዓላማ ስለማይኖረው እስካልተጋባን ምን ችግር አለው ሊል አይችልም።

ከማያምኑ ጋር ብንጋባ ችግሩ ምንድን ነው?

ቅዱሳት መጻሕፍት እንዳዘዙን ቢቻለንስ ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ልንኖር ይገባናል (ሮሜ. ፲፪፥፲፰)። ይህ ማለት ግን ጥላቻን እና አለመግባባትን ማስወገድ መቻል ማለት እንጂ ትዳርን በሚያህል የተቀደሰ ትስስር ወስጥ መግባት ማለት አይደለም። የተቀደሰውን ለውሾች እንዳንሰጥ ጌታችን አስጠንቅቆናል (ማቴ 7፡6)። በክርስቶስ ኢየሱስ ደም የከበረ ከውኃ እና ከመንፈስ ተወልዶ የሥላሴን ልጅነት ያገኘ እና የእግዚአብሔር መቅደስ ተብሎ የተጠራ ሰውነታችን የተቀደሰ አይደለምን?  ይህንን ሳናስተውል ቀርተን በእምነት የማይመስለን እጮኛ ብንይዝ ከሚገጥሙን እንከኖች መካከል የተወሰኑትን እናንሣ።

. የትዳርን ዓላማ ማሳካት አንችልም

ክርስቲያኖች ወደ ምንኩስናም ሆነ ወደ ጋብቻ የሚገቡበት ዓላማ አንድ ዓይነት ነው። እርሱም ቅድስና! የድንግልናን ሕይወት የመረጠ ሰው ራስን መግዛትን ገንዘብ አድርጎ ፍትወታቱን ለፈቃደ ነፍሱ አስገዝቶ ለመኖር እንደሚችል አምኖና ወስኖ ነው። የዚህ ጉዞ ዓላማውም ኃጢአትን አሸንፎ በምድር መላእክትን መስሎ መኖር ነው። በሌላ በኩል ራስን መግዛትን እና ድንግልናን መጠበቅን ገንዘብ ማድረግ ያልቻለ ሰው ስለ ዝሙት ጠንቅ እንዲያገባ ተፈቅዶለታል (1ቆሮ 7፡2)። የዚህም ሰው ጉዞ በዝሙት ተፈትኖ ሳይወድቅ በትዳር ንጽሕናውን ጠብቆ የእግዚአብሔርን መንግሥት መውረስ ነው። ስለዚህም የትዳር አንዱ ዓላማ መረዳዳት ነው። መረዳዳት ማለትም ብዙዎች እንደሚያስቡት በሥራ እና በኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን በዋናነት በመንፈሳዊ ሕይወት ነው። ጠቢቡ ሰሎሞን “አንድ ብቻ ከመሆን ሁለት መሆን ይሻላል ቢወድቁ አንዱ ሁለተኛውን ያነሣዋልና” (መክ 4፡9) እንዳለ አንዱ ወድቆ ከእግዚአብሔር መንግሥት እንዳይርቅ ሌላኛው አጋዥ ሊሆነው፣ ቢዝል ሊያበረታው፣ ተስፋ ቢቆርጥ ሊያጽናናው ይችላልና ተረዳድተው እና ተደጋግፈው የእግዚአብሔርን መንግሥት መውረስ የትዳር ዋነኛ ዓላማ ነው። ለዚህም ነው ምዕራባውያን ሊቃውንት “the goal of marriage is not happiness; it is holiness” “የጋብቻ ግቡ ደስታ፣ ተድላ አይደለም ቅድስና ነው” የሚሉት።

የማያምን የትዳር አጋር ያለው ሰው ይህንን ዓላማ ሊያሳካ አይቻለውም። ከማያምን ሰው ጋር ተረዳድቶ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በጋራ መግባት የማይሆን ነገር ነው ምክንያቱም ጌታችን እንዳለ “የማያምን ሰው በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል” (ዮሐ 3፡18)። ከማያምኑ ጋር መኖር ለመንፈሳዊ ዝለት መንስኤ እንጂ መፍትሔ ሊሆን አይችልም። ስለዚህ ጋብቻችን እንኳ እጅግ መልካም ቢሆን ከተድላ ሥጋ ያለፈ ለነፍሳችን የሚረባ ነገር አይኖረውም። ክርስቲያኖች ደግሞ እንኳን እንዲህ ያለውን ትልቅ ነገር ቀርቶ ጥቃቅኑን ጉዳይ እንኳ የእግዚአብሔርን ፍቅር እያሰብን ለእርሱ እንድናደርገው ታዝዘናል። “መብላትም ቢሆን መጠጣትም ቢሆን ማንኛውንም ነገር ስታደርጉ ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት” (1ቆሮ 10፡31) እንዳለ።

. በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ ያለው ኦርቶዶክሳዊ ጋብቻ መፈጸም አንችልም

ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ልጆቿን በእግዚአብሔር እና በሰዎች ፊት በክብር የምትድርበት ሥርዓተ ተክሊል የሚባል የጋብቻ ሥርዓት አላት። ለደናግል በሚደረገው የተክሊል ጋብቻም ሆነ ለመዓስባን (ደግመው ለሚያገቡ አልያም ድንግልናቸውን ላጡ) ሰዎች በምታደርገው የመዓስባን ጋብቻ (የቁርባን ጋብቻ) መሳተፍ የሚችሉት ምሥጢራተ ቤተክርስቲያንን መፈጸም የተፈቀደላቸው፣ ልጅነትን ያገኙ ክርስቲያኖች ብቻ ናቸው። እግዚአብሔር አምላክ የሚቀበለው ጋብቻ እርሱ ምስክር ሆኖ የተጠራበትን ቅዱስ ጳውሎስ “ሁሉን ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት” እንዳለ እርሱ የሚከብርበትን ጋብቻ ብቻ ነው።

የሰው ልጅ የእግዚአብሔር መንፈስ አልያም የጠላት ዲያብሎስ መንፈስ ያድርበታል። እስራኤል የያዕቆብ አምላክ፣ የእግዚአብሔር ማደሪያ (ሐዋ.፯፥፲፮) እንደ ተባሉ ሁሉ ባቢሎናውያን ደግሞ የአጋንንት ማደሪያ ተብለው ተጠርተዋል (ራእ. ፲፰፥፪)። እያንዳንዱ ሰው የሚያድርበትን መንፈስ የሚመርጠው ራሱ ነው። እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን የሚያቀርብ ሥራ እና ምግባር ያለው ሰው የእግዚአብሔር ማደሪያ ይሆናል፡፡ ሐሳቡን እና ድርጊቱን ያልቀደሰ ሰው ደግሞ ለጠላት ማደሪያነት እንደ ተወለወለ ቤት ራሱን ያዘጋጃል (ሉቃ. ፲፩፥፳፭)። በሠርጋችን ቀን የሚኖረን ምግባር በዕለቱ የምንጠራውን የክብር እንግዳ የሚጋብዝ ነው። ወዳጄ ሆይ! በሰርግዎት ቀን የትኛው መንፈስ እንዲገኝ ይሆን የሚፈልጉት? ማንም ጤነኛ አእምሮ ያለው ክርስቲያን ከእግዚአብሔር ቅዱስ መንፈስ ውጭ ሌላ መልስ እንደሌለው ግልጥ ነው። እግዚአብሔር በማይከብርበት ብዙ መብላት፣ ብዙ መጠጣት፣ ዘፈን፣ ጭፈራ፣ መዳራት እና የመሳሰሉት ኃጢአቶች ባሉበት ቦታ እግዚአብሔር በረድኤት አይገኝም። ኃጢአት የደስታው ምንጭ የሆነለት ዲያብሎስ ግን ሳይጠራ የሚመጣበት ዓለሙ ነው። እነዚህ ሁሉ ኃጢአቶች ባይኖሩ እንኳ ስለ እግዚአብሔር ክብር እንደ እርሱ ፈቃድ አልተደረገምና እግዚአብሔር አይገኝበትም።

በተቃራኒው ቤተ ክርስቲያን በአምልኮተ እግዚአብሔር በሚደረግ ጋብቻ ላይ ጌታችን እንደ ቃና ዘገሊላ ቤት ይገኝበታል። ዛሬም ሠርጉ በሚደረግበት ቤተ ክርስቲያን በሚፈጸመው ቅዳሴ ላይ የጌታችን እውነተኛ ሥጋው እና ደሙን በቤተ ክርስቲያን  ይቀበላሉ፡፡ በዚህ የቅዳሴ ጸሎት ቅዱሳንም በሠርጋችን ይገኛሉ። ንጉሣቸው ባለበት ሁሉ የማይታጡ ሠራዊተ መላእክት ባሉበት መሞሸር የማይፈልግ ማነው? ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ይህንን በመሰለ ጋብቻ እንዳንከብር ከምትከለክልባቸው ምክንያቶች አንዱ ከማያምኑ ጋር የሚደረግ ጋብቻ ነው።

. በልጆች አስተዳደግ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ አለው 

ከላይ የዘረዘርናቸው መንፈሳዊ ጉዳዮች አያሳስቡኝም የሚል እንኳ ቢኖር የተለያየ እምነት ያላቸው ሰዎች የሚፈጽሙት ጋብቻ ይዞት የሚመጣው ማኅበራዊ ቀውስ ብዙ ነው። ከእነዚህም ወስጥ የልጆች አስተዳደግ ትልቁን ድርሻ ይወስዳል። ወላጆች ልጆቻቸውን ወደየራሳቸው እምነት ለመሳብ የሚያደርጉት ጥረት የልጆችን አእምሮ በብዙ መልኩ የሚጎዳ ሲሆን ይህንን ጉዳት ለመሸሽ ልጆችን ወደ እምነት ተቋማት አለመውሰድ ደግሞ የባሰ ፈጣሪን የማያውቁ እና ከአምልኮተ እግዚአብሔር የራቁ ሆነው እንዲያድጉ ያደርጋል። ሌላኛው ወላጅ ባይቃወምና ልጆች አማኝ ሆነው ቢያድጉ እንኳ ከወላጆቻቸው አንዱ ለእግዚአብሔር መንግሥት ያልታጨ ለዘላለም ፍርድ የተጋለጠ መሆኑን እያሰቡ እንዲኖሩ ይገደዳሉ።

እነዚህና መሰል ጉዳዮች በእምነት ከማይመስሉን ሰዎች ጋር በዚህ መልኩ መጠመድ እንደማይገባን የሚያሳስቡ ናቸው። ከዚህም ባሻገር በአንድ ሃይማኖት ጥላ ሥር መጠለል ብቻውን በትዳር ለመጣመር በቂ ምክንያት አይደለም። ምንም እንኳ በእምነት የሚመስሉንን ሰዎች እንዳናገባ ክልከላ ባይኖርብንም መምህራችን ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለ የተፈቀዱልን ነገሮች ሁሉ የሚጠቅሙን እና የሚያንጹን አይደሉም (፩ቆሮ. ፮፥፲፪ እና ፩ቆሮ. ፲፥፳፫)። ዓላማቸው ከዓላማችን፣ ፈቃዳቸው ከፈቃዳችን መግጠሙን ማስተዋል ያስፈልጋል። በሃይማኖት እንመሳሰላለን ካልን በኋላ አንዳችን ለፈቃደ እግዚአብሔር መገዛትን ስንሻ፣ ሌላኛው ይህ የማያሳስበው ከሆነ ግንኙነቱ ዘላቂነት የሌለው ቢዘልቅም አንዱን አካል አልያም ሁለቱንም የሚጎዳ መሆኑ አይቀርም። ስለሆነምወደ ትዳር ከመግባት በፊት ከሃይማኖት ባሻገር መንፈሳዊ ሕይወታችን ተቀራራቢ ደረጃ ላይ መሆኑን እና እርስ በርስ መደጋገፍ መቻላችንን ማወቅ ይገባል። መደጋገፍ አልን እንጂ መደገፍ ብቻ አላልንም። እለውጠዋለሁ፣ አሻሽላታለሁ ተብሎ ወደ ጾታዊ ግንኙነት መግባት ትዕቢትንም ጭምር የሚያሳይ ነው።

መተው የምንፈልገውን ኃጢአት ለመተው፣ መልመድ የምንፈልገውን በጎ ምግባር ለመልመድ ራሳችንን ማሻሻል እና መለወጥ ያልቻልን ሰዎች ሌላ ሰው እለውጣለሁ ብሎ ማሰብ ከትዕቢት ውጭ ምን ሊሆን ይችላል? ስለዚህ ከእኛ ጋር ተቀራራቢ፣ ከተቻለም የተሻለ መንፈሳዊ ሕይወት ያለውን ሰው መምረጥ ያስፈልጋል። ብዙዎች ሰዎችን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በማግኘታቸው ብቻ መንፈሳዊ ሰዎች እንደሆኑ አስበው ሳይጠነቀቁ ወደዚህ ሕይወት ይገባሉ ከዚያም ነገሮች እንዳሰቡት ባልሆኑላቸው ጊዜ ቤተክርስቲያን ውስጥ ያሉት ሰዎች ሁሉ እንደዚያ እንደሆኑ በማሰብ መንፈሳዊ ሕይወትን እና ቤተ ክርስቲያንን ይሸሻሉ። ሐኪም ቤት ውስጥ የተገኘ ታማሚ ሁሉ ተሽሎት እንደማይወጣ እንዲሁም ቤተክርስቲያን ወስጥ ያገኘናቸው ሰዎች ሁሉ ከድካማቸው የተፈወሱ አይደሉምና መጠንቀቅ ያስፈልጋል።

ይቆየን

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *