ወጣትነትና ታማኝ አገልጋይነት

ወጣትነትና ታማኝ አገልጋይነት

በዲ/ን ወልደ ቂርቆስ ደሳለኝ

ክፍል ሦስት

በወጣቶች አገልግሎት ላይ የሚታዩ ክፍተቶች

እስከ አሁን የተመለከትናቸው አራት መሠረታዊ ነጥቦች ወጣቶች ወደ መንፈሳዊ አገልግሎት እንዳይቀርቡና ከቤተ ክርስቲያን እንዲሸሹ እያደረጉ ያሉ እንቅፋቶችን ነበር፡፡ ነገር ግን እነዚህ እንቅፋቶች በእግዚአብሔር ቸርነት፣ በደጋግ ካህናትና መምህራነ ወንጌል አበረታችነት ተቋቁመው ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በተሰጣቸው ጸጋ ለማገልገል በደጇ የሚመላለሱ ወጣቶች ብዙዎች ናቸው፡፡ በወጣትነት (በጉብዝና ወራት) ፈጣሪን እያሰቡ በቤተ ክርስቲያን እቅፍ ተከልሎ ማለፍ፣ በመንፈሳዊም ይሁን በሥጋዊ ሕይወታችን ከውድቀትና ከኃጢአት ተጠበቀን ለራሳችን፣ ለቤተሰባችን፣ ለቤተ ክርስቲያንና ለሀገራችን ጠቃሚዎች ከመሆን አልፈን ለሰማያዊ ክብር እንበቃ ዘንድ በትጋት ለማገልገል መሠረት የምንጥልበት ወቅት ነው፡፡

ይህ ማለት ግን በቁርጠኝነት ወደ ቤተ ክርስቲያን ከቀረቡ በኋላ ፈተና የለም ማለት አይደለም፡፡ በመንፈሳዊ አገልግሎት ላይ ያሉ ወጣቶችም ብዙ ፈታኝና አስቸጋሪ ሁኔታዎች እየገጠሟቸው እንመለከታለን፡፡ ከዚህ በታች አጠር ባለ መንገድ በዘመናችን በወጣቶች መንፈሳዊ አገልግሎት ላይ እየታዩ ያሉ ፈታኝ ጉዳዮችን (ችግሮችን) እንመለከታለን፡፡

የልምድ ተመላላሽ መሆን

አገልግሎት መቼም ቢሆን መንግሥተ ሰማያትን (ሰማያዊ ሕይወትን) ዕሴት ያደረገ ግብ ሊኖረው ያስፈልጋል፡፡ ስለሆነም ወደ እግዚአብሔር ቤት መመላለሳችን በዓላማ የታጠረ፣ በዕቅድ የተወጠነ መሆኑ ቀርቶ እንዲሁ በዘልማድ ብቻ ከሆነ ለራሳችንም፣ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያንም የማንጠቅም ከንቱዎች መሆናችን እሙን ነው፡፡ ብዙ ወጣቶች ወደ ሰንበት ትምህርት ቤቶች፣ ወደ መንፈሳውያን ማኅበራት ለምን እንደሚሄዱ እንኳን ግራ እስኪገባቸው ድረስ ያለ ዓለማ በዘልማድ ይመላለሳሉ፡፡ ግብና ዓላማ የሌለው አገልጋይ ለመንፈሳዊ ሱታፌና ፈተናን ድል ለማድረግ የነቃና የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ ፈጽሞ አይቻለውም፡፡ ከዚያ ይልቅ “በራድ ወይም ትኩስ ብትሆንስ መልካም ነበር፤ እንዲሁ ለብ ስላልህ በራድም ወይም ትኩስ ስላልሆንህ ከአፌ ልተፋህ ነው” (ራእ. ፫፥፲፭-፲፮) እየተባለ በመኖርና ባለመኖር መካከል እንደባከነ ዘመኑን ይጨርሳል፡፡

ስለዚህ እኛ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልጆች በትምህርት፣ በሥራ፣ ብሎም በማኅበራዊ ሕይወታችንም “እግዚአብሔር ቢፈቅድ ብንኖር ይህን ወይም ያን እናደርጋለን” እያልን ምን ለማድረግ፣ ምን ለመሥራት፣ መቼና እስከ መቼ በምን ያህል ፍጥነት የሚለውን ጥያቄ በንቃት እያሰብን ከዘልማዳዊ ምልልስ መውጣት አለብን፡፡ (ያዕ. ፬፥፲፭)፡፡ ነገር ግን አገልጋዮች በተለይም ወጣቶች የትንሣኤ ልቡና ንቃተ ኅሊና ሳይኖራቸው እንዲሁ ከተመላለሱ ከማትርፍ ይልቅ ይጎዳሉ፡ በዚህም “ስለ በረከት ፈንታ መርገምን፣ ስለሥርየተ ኃጢአት ፈንታ ገሃነመ እሳትን ይቀበላል” እንዲል ሥርዓተ ቅዳሴአችን ልፋትና ድካማችን ለውድቀት ይሆንብናል፡፡

መንፈሳዊነት የሌለበት ስሜታዊ አገልገሎት

በእርግጥ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ተቆርቁሮ በእልህ፣ በመንፈሳዊ ወኔና በስሜት “የቤትህ ቅናት በልቶኛልና፣ የሚሰድቡህም ስድብ በላዬ ወድቋልና” (መዝ. ፷፰፧፱) ብሎ ለመንፈሳዊ አገልግሎት በቁርጠኝነት መነሣት የተገባ በጎ ተግባር ነው፡፡ አንድ መንፈሳዊ አገልጋይ ከዓለማውያን ሠራተኞች የሚለየው ከመንፈሳዊ ስሜትና ቁጭት ጋር መንፈሳዊ ብስለትና ፈቃደ እግዚአብሔርን አስተባብሮ መጓዝ ሲችል ነው፡፡

በዘመናችን ብዙ ወጣቶች ልቡናቸውን በቃለ እግዚአብሔር ሳይሰብሩ በሥጋዊ አስተሳሰብ፣ በእልህ፣ በቁጣና በስሜት ብቻ ለአገልግሎት ሲመላለሱ ይስተዋላል፡፡ በዚህም ምክንያት በመንፈሳዊ አገልግሎት ላይ ጠብ፣ ክርክርና ንትርክ ሲበዛ እንመለከታለን፡፡ ማንኛውም መንፈሳዊ አገልግሎት ግቡን የሚመታውና ውጤታማ የሚሆነው አገልግሎቱን የሚፈጽመው ሰው መንፈሳዊ ብስለትን ሲጎናጸፍ ብቻ ነው፡፡ ይህ ካልሆነ ግን በሥጋዊ አስተሳሰብ መንፈሳዊ ጉዳይን ለማራመድ መሞከር ከንቱ ድካም ነው፡፡

ወደ ቤተ ክርስቲያን በመንፈሳዊ ብስለት ሳይሆን በሥጋዊ ስሜት ብቻ የምንመላለስ ከሆነ ድካማችን ለፍሬ የማይበቃ ነው የሚሆነው፡፡ ከዚያም አልፎ ስኬትን በሥጋ ሚዛን እየመዘንን በቀላሉ ተስፋ የምንቆርጥና ችኩሎች ሆነን ከምናለማው ይልቅ የምናጠፋው የሚገዝፍ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ታማኝ አገልጋይ ተብለን በጌታችን እንመሰገን ዘንድ ራሳችንን ከስሜታዊነት አላቅቀን በፍጹም መንፈሳዊ ትዕግሥትና ትሕትና በእግዚአብሔር ቤት በቀናነት ልንመላለስ ይገባል፡፡ ይህንን ስናደርግ ነው እንደ ጎልያድ የገዘፈውን የዓለም ፈተና እንደ ነቢዩ ዳዊት “እኔ ግን ዛሬ በተገዳዳርኸው በእስራኤል ጭፍሮች አምላክ ስም በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ስም እመጣብሃለሁ” (፩ሳሙ. ፲፯፥፵፭) በማለት ድልን የምንጎናጸፈው፡፡

ራስን ማታለል (ለራስ ኅሊና መዋሸት)

አቡሃ ለሐሰት፣ የሐሰት አባት የተባለ ጥንተ ጠላታችን ዲያብሎስ “ሞትን አትሞቱም፤ ከእርስዋ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንዲከፈቱ እንደ እግዚአብሔርም እንደምትሆኑ መልካምንና ክፉን እንደምታውቁ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው እንጂ” (ዘፍ. ፫፥፬) ብሎ ሔዋንን በማታለል ሐሰትን እንደ ጀመረ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡ መዋሸት በሁለት መንገድ ሊፈጸም ይችላል፡፡ በቀዳሚነት በተለመደው መንገድ አንድ ሰው ለሌላ ሁለተኛ ወገን እውነትን አዛብቶ፣ አልያም ያለተደረገውን ተደረገ ብሎ ቢናገርበት የሚፈጸመው ሲሆን፣ በሌላ በኩል ግን አንድ ሰው ይህንኑ ጉዳይ ሌላ ሁለተኛ አካል ሳያስፈልግ ከራሱ ጋር ሊፈጽመው ይችላል፡፡ ራስን መዋሸት ወይም ማታለል ማለት እውነታውን እያወቁ ከኅሊና መደበቅ ማለት ነው፡፡ በዘመናችን ብዙ ወጣቶች በመንፈሳዊ አገልግሎት ራሳቸውን ሲያታልሉ ይስተዋላል፡፡

አበ ብዙኃን የተባለው አባታችን አብርሃም ያስጨነቀውና እውነትን ወደ መምርመር የወሰደው ኅሊናውን ማታለልና ለራሱ መዋሸት ከባድ ስለሆነበት ነው፡፡ ከእንጨት ተጠርቦ የተሠራውን ጣዖት ምስል ፈጣሪ፣ መጋቢ፣ አምላክ፣ ወዘተ ነው ብሎ አምኖ ለመቀበልና ለኅሊናው ውሸትን ይነግር ዘንድ አልቻለም፡፡ በዚህም የተነሣ “የፀሐይ አምላክ ተናገረኝ” በማለት በትጋት አምላኩን ፈልጎ አገኘ፡፡ ነገር ግን የሰው ልጅ ራሱን እያታለለ ከእውነት ሲሸሽ በጉልህ ይስተዋላል፡፡ በርእሳችን መነሻ ያነሣነውን የመክሊቱን ምሳሌ መለስ ብለን ብንመለከት ያ ሰነፍና ልግመኛ አገልጋይ (ገብር ሐካይ) ኅሊናው ሥራ፣ ድከም፣ መክሊትህን አትቅበር እያለ እንዳይወቅሰው ለራሱ ማታለያ ይሆነው ዘንድ ምክንያት አስቀምጦ ነበር፡፡ ይኸውም “አቤቱ አንተ ካልዘራህበት የምታጭድ፣ ካልበተንህበትም የምትሰበስብ እንደሆንህ አውቃለሁ” የሚል ነው፡፡ ይህም ምክንያት ለስንፍናው ማደላደያ ያቀረበው የሐሰት ማስረጃ እንደሆነ ከጌታው ምላሽ በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡ “ጌታውም መልሶ አለው፤ አንተ ክፉና ሰነፍ አገልጋይ እኔ ካልዘራሁበት የማጭድ፣ ካልበተንሁበት የምሰበስብ ጨካኝ ሰው እንደሆንሁ ታውቃለህን?” በማለት የተሰጠውን መክሊት በታማኝነት ሳይጠቀምበት በመቅረቱ ለቅጣት እንደተዳረገ እንመለከታለን፡፡ (ማቴ. ፳፭፥፳፬-፳፮)፡፡

ብዙ ወጣቶች ለመንፈሳዊ አገልግሎት ወደ ቤተ ክርስቲያን ከመጡ በኋላ ቅዱሳት መጻሕፍት የመዘገቡትን፣ አበው ሊቃውንት የሚያስተምሩትን ከመሥራትና የሕይወታቸው መመሪያ ከማድረግ ይልቅ “እናንተ ሰነፎች የገላትያ ሰዎች ሆይ፤ ለዐይን በሚታየው እውነት እንዳታምኑ ማን አታለላችሁ?’ (ገላ. ፫፥፩) እንዳለ ከእውነት ርቀው ራሳቸውን በማታለል ለፈቃደ ሥጋቸው አድልተው ፈቃደ ነፍሳቸውን የሚያከስም ተግባርና አካሄድ ላይ ይጠመዳሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ነው በመንፈሳዊው ዐውደ ምሕረት በአገልግሎት ስም ዓለማዊ ጭፈራ በሚመስል አላስፈላጊ እንቅስቃሴ ዋና አጋፋሪዎች የሆኑ ብዙ አገልጋዮችን የምንታዘበው፡፡ በዚህም ራስን በማታለል ኩነኔውን ጽድቅ፣ የጽድቁን ሥራ ልማዳዊ አድርጎ የማሰብ አባዜ የተነሣ በሥርዓተ ዑደቱ በዝማሬና እልልታ የቤተ ክርስቲያን ቅጽር በምእመናን ተሞልቶ በሥርዓተ ቅዳሴውና በምሥጢረ ቁርባን ግን በጣት የሚቆጠሩ ምእመናን ብቻ የምንመለከተው፡፡ በዚህ ራስን የማታለል ልማድ ምክንያት ለመላው ምእመናን በዐዋጅ ቤተ ክርስቲያን ያስቀመጠቻቸውን ሰባቱ አጽዋማት እንኳን ያለ ምንም መነሻ ይህ የአረጋውያን፣ ይህ ደግሞ የካህናት፣ ይህኛው የሕፃናት የሚል ያልተገባ ክፍፍል ሲያደርጉ እንመለከታለን፡፡ ሌሎችም ከቤተ ክርስቲያን ሳይርቁ ከጾም፣ ከጸሎትና ከስግደት ርቀው የጠፋውን ድሪም ሆነዋል፡፡

ድክመቶቻችንን በሌሎች እያሳበብን በደላችንን አምነን ለንስሓ ሳንዘጋጅ፣ የሌሎችን ሕይወት በመንፈሳዊ አገልግሎት ለመሥራት የምንጥር፣ በምድራዊ ታይታና ከንቱ ውዳሴ ብቻ እየተመራን እግዚአብሔርን ሳይሆን ሰዎችን ብቻ በሚያስደስት የይሰሙላና ከንቱ አገልግሎት የምንጠመድ ሆነን እንቀራለን፡፡ ስለሆነም ራስን ከማታለል ተቆጥበን፣ ድካማችንን እያሰብን ሥርየተ ኃጢአትን ለማግኘት ወደ አበው ሊቃውንትና ወደ መምህራነ ንስሓ ቀርበን በደላችንን በመናዘዝ ለመለወጥ እየተጋን የምናገለግል ከሆነ ያኔ ትጉህና ታማኝ አገልጋይ እንሆናለን፤ አገልግሎታችንም “በውኃ ፈሳሾች ዳር እንደተተከለች፣ ፍሬዋን በየጊዜዋ እንደምትሰጥ፣ ቅጠልዋም እንደማረግፍ ዛፍ ይሆናል” (መዝ. ፩፥፫)

የአገልግሎት ጸጋን ለይቶ አለማወቅ

ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ “መንፈስ ቅዱስ አንድ ሲሆን ስጦታው ልዩ ልዩ ነው፡፡ ጌታም አንድ ሲሆን ልዩ ልዩ አገልግሎቶች አሉ፡፡ ሁሉን በሁሉ የሚያደርግ እግዚአብሔርም አንድ ሲሆን ልዩ ልዩ አሠራር አለ፡፡ ለሁሉም ጌታ እየረዳ በዕድሉ እንደሚገባውና እንደሚጠቅመው ለእያንዳንዱ በግልጥ ይሰጠዋል፡፡” (፩ቆሮ. ፲፪፥፬-፲፩) እንዲል የምናገለግለው ለአንድ ሰማያዊ ዓለማ ቢሆንም ያንን የምናደርግበት ልዩ ልዩ ጸጋ ከእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ተሰጥቶናል፡፡ የሰው ልጅ በተሰጠው ጸጋና መክሊት እግዚአብሔርን ያገለገለ እንደሆነ አገልግሎቱ ሠላሳ፣ ሥሳና መቶ ያማረ ፍሬ ያፈራ ዘንድ ጊዜ አይወስድበትም፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን በብዙ ወጣቶች አገልግሎት ላይ የሚስተዋለው ፈተናና ተግዳሮት ይኸው የመንፈሳዊ አገልግሎት ጸጋን ለይቶ አለማወቅ ችግር ነው፡፡

አንዳንድ ወጣቶች በዐውደ ምሕረት ላይ በኵራት ቁመው ድምጽ ማጉያውን ጨብጠው ለስብከተ ወንጌል ካልተሰማሩ ያገለገሉ አይመስላቸውም፡፡ ሌሎቹም እንዲሁ መንፈሳዊ አገልግሎት ዝማሬ ከመዘመር ጋር ብቻ ሁኖ ይታያቸዋል፡፡ በዚህ ጸጋን ለይቶ አለማወቅ ድካም ብዙ ወጣቶች ከሌሎች በሚደርስባቸው ተግሣፅና ነቀፋ በመሸማቀቅ እንደ ሎጥ ሚስት (ዘፍ. ፲፱፥፪) ወደ ኋላ ሲመለከቱ በዓለም እየቀለጡ ቀርተዋል፡፡ ወጣትና ታማኝ አገልጋይ ሆነን አትርፈን እንገኝ ዘንድ ከንቱ ውዳሴንና እየኝ ማለትን ብሎም ምድራዊ ክብርን ትተን አንተ ሰይጣን ከፊቴ ወግድ ብለን አሽቀንጥረን በመጣል በተሰጠን ጸጋ በተለያየ የአገልግሎት ዘርፍ ተግተን በመሳተፍ በሰማይ ያለ መዝገባችንን ልናካብት ይገባል፡፡

ማጠቃለያ

ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ “ጎልማሳ መንገዱን በምን ያቀናል፤ ቃልህን በመጠበቅ ነው” (መዝ. ፲፰፥፱) እንዳለ የቃሉን ወተት በትጋት እየተመገበ ስሜቱን በቅዱስ መንፈስ እየገዛ በእውነትና ለእውነት በመመላለስ የሚተጋ ወጣት አገልጋይ ለመሆን እንበቃ ዘንድ ከሁሉም በፊት ከላይ የተጠቀሱትን ክፍተቶች እንደ ሰንኮፍ አውልቀን እንጣል፡፡ ስለሆነም በጉብዝናችን ወራት ፈጣሪን በማሰብ እናልፍ ዘንድ አገልግሎት ለምርጫ የምናስቀምጠው ጉዳይ ሳይሆን መንፈሳዊ ግዴታ እንደሆነ ልብ ልንለው ይገባል፡፡ “በጎ ነገር ማድረግን የሚያውቅ፣ የማይሠራትም ኃጢአት ትሆንበታለች” (ያዕ. ፬፥፲፯) እንደተባለ በመንፈሳዊ አገልግሎት አለመሳተፍ ኃጢአት ነው፡፡ ከጥፋት ለመዳን ብሎም በዘለዓለማዊ ፍሥሐ ስሙን ለመቀደስ፣ ዘለዓለማዊ ክብርን ለመውረስ “የኢየሩሳሌምን ጥፋት አታሳየን” (ኤር. ፱፥፩-፴) እያልን ለአገልግሎት ዛሬ እንነሣ፣ የመዳን ቀን አሁን ነውና፡፡ ይህንንም በትጋት እንዳንፈጽም እንቅፋት የሚሆኑንን ፈተናዎች ሁሉ በጾም፣ በጸሎት፣ በስግደት፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን በማንበብና መምህራንን በመጠየቅ አስወግደን፣ ራሳችንን በመንፈሳዊ አገልግሎት አትግተን፣ የኋላውን እየተውን ወደፊት እንገሰግስ ዘንድ የአበው ቅዱሳን ረድኤት አይለየን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *