ወጣትነትና ታማኝ አገልጋይነት

ወጣትነትና ታማኝ አገልጋይነት

ክፍል ሁለት

በዲ/ን ወልደ ቂርቆስ ደሳለኝ

   . አልችልም/አይገባኝም ማለት

ትሕትና ራስን ዝቅ ማድረግ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው በተግባር ሠርቶ፣ በቃል አብራርቶ፣ በምሳሌ አጉልቶ ያስተማረን፤ አባቶችም በመንፈሳዊ ክብር ከፍ ከፍ ያሉበት ታላቅ ጸጋ ነው፡፡ ስለዚህም ነው ቅዱሳት መጻሕፍት ደግመው ደጋግመው ስለ ትሕትናና ራስን ዝቅ ስለማድረግ በአጽንዖት የሚነግሩን፡፡ “ትሕትናና እግዚአብሔርን መፍራት ባለጠግነት፣ ክብር፣ ሕይወትም ነው” እንዲል (ምሳ. ፳፪፥፬)፡፡ በመንፈሳዊ አገልግሎት ራስን ዝቅ አድርጎ ቅድሚያ ለሌሎች መስጠት የተገባ እንደሆነ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ “እያንደንዱ ባልንጀራው ከርሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቁጠር” (ፊልጵ. ፪፥፫) ሲል ይነግራል፡፡

ነገር ግን ትሕትናችን፣ ራስን ዝቅ ማድረጋችን ለእይታ እታይ ባይነትና ከንቱ ውዳሴ ሰለባ የሚያደርገን ከሆነ በልቡናችን አንዳች የትሕትና ፍሬ ሳይኖር ውስጣችን በትዕቢት ወደ ላይ ተወጥሮ ውጫዊ አካላችን ለብቻው የሚያጎነብስ ከሆነ ትሕትናችን ለምድራዊ ክብር መሻት፣ ዓለማዊ ሀብትን በማየት አለዚያም ራሳችንን ከኃላፊነት ከአገልግሎትና መታዘዝ ለመሸሽ የመደበቂያ ምሽግ ሆኖ ካገለገለ በውኑ ይህንን በቅዱሳት መጻሕፍት ሚዛንነት ትሕትና ነው ማለት አይቻልም፡፡ በዘመናችን ብዙ ወጣቶች ወደ ቤተ ክርስቲያን ቀርበው በአገልግሎት ተሳትፈው የበረከት ተቋዳሽ እንዳይሆኑ ትልቅ እንቅፋት እየሆነባቸው ያለ ጉዳይ ትሕትናን የሚመስል፣ ነገር ግን ትሕትና ያልሆነ የአልችልም ባይነት ስሜት፣ ራስን ዝቅ በማድረግ እየተደበቀ ከኃላፊነትና ከአገልግሎት የመሸሽ ልማድ ነው፡፡

የሰው ልጅ በአስተሳሰቡና በአመለካከቱ አልችልም፣ ደካማ ነኝ የሚል ስሜት ካሳደረ፣ የእግዚአብሔርን ረዳትነት ተማምኖ “ወደ እርሱ ቅረቡ ያበራላችሁማል፣ ፊታችሁም አያፍርም” (መዝ. ፴፫፥፭) እንዲል መዝሙረኛው ቅዱስ ዳዊት ወደ ቤተ ክርስቲያን ቀርቦ ለተግባር፣ ለድርጊት መቸም ቢሆን ውስጣዊ መነሣሣትና ቁርጠኝነት አይኖረውም፡፡ ሰው የሚያስበውን ያንኑ ይመስላል እንዲል አስተሳሰባችን ከተግባራችን ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን ይህ የአስተሳሰብ ደካማነት፣ እምነት ጎደሎነት ወይም የጥርጥር መንፈስ ተብሎ ይገለጻል፡፡ በውኃ ላይ መራመድን ሽቶ በመሐል በመጠራጠሩ ሊሰምጥ የነበረውን ቅዱስ ጴጥሮስን ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ በጥብዓት ከተጓዘ በኋላ በመሐከል ግን የጥርጠር መንፈስ ወደ እርሱ ገባና እምነተ ጎደሎ በመሆኑ እንደተገሠጸ ቅዱስ መጽሐፍ ይነግረናል (ማቴ. ፲፬፥፳፬)

በእርግጥ አበው ነቢያት፣ ሐዋርያት፣ ሊቃውንት፣ ጻድቃን ሰማዕታት ለታላቅ አገልግሎትና ተልእኮ ከፈጣሪ ጥሪ ሲደረግላቸው ከልብ በመነጨ መንፈሳዊ ትሕትና “ይህንን ጥሪ እቀበል ዘንድ እኔ ምንድን ነኝ፤ እኔ ደካማ ሰው ነኝ” ሲሉ የተሰጣቸው ተልእኮ ታላቅነትን፣ የእነርሱን ደካማነት አሳይተዋል፡፡ ነገር ግን ይህንን ብለው ከኃላፊነትና ከአገልግሎት አልሸሹም ይልቅ ሰማያዊ ተልእኳቸውን በትጋትና በብቃት ተወጡ እንጂ፡፡ ሊቀ ነቢያት ሙሴ ሕዝበ እስራኤልን ከፈርዖን ግፍና ባርነት ነጻ ያወጣ ዘንድ መመረጡን በሰማበት በዚያች ቅጽበት “እኔ ኮልታፋ ምላሴም ጸያፍ የሆነ ሰው ነኝ፤ ትናንት ከትናንተ ወዲያ ባሪያህንም ከተናገርከኝ ጀምሮ አፈ ትብ ሰው አይደለሁምን፡፡” (ዘጸ. ፬፥፲) እንዲል፡፡ ይህንን ማለቱ ተልእኮውን ከመወጣት አላስቀረውም፡፡

ከሁሉም በላይ ብዙ ወጣቶች “እኔ ገና ጀማሪ ነኝ፤ እኔ ምንም አልጠቅምም፣ እኔ ለቤተ ክርስቲያን የምሆን ሰው አይደለሁም” ሲሉ ለሰውም ለራሳቸውም ኅሊናም እየነገሩ በትሕትና ሰበብ በቅድሚያ ከአገልጋይነት፣ እየቆዩም ከጾም ጸሎት ሸሽተው የጠፉ ብዙ ሰዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ አንድ አገልጋይ “ሁል ጊዜም ስደክም ያን ጊዜ ኃይለኛ ነኝ” (፪ኛቆሮ. ፲፪፥፲) በማለት ሐዋርያው እንዳስተማረን እርሱም ለበለጠ ትጋት፣ ለበለጠ አገልግሎት መነሣሣት ይገባዋል፡፡ ምክንያቱም በእግዚአብሔር ቤት ታናሽና ታላቅ ኃላፊነት ያለበትና የሌለበት ሰው የለም፡፡ አምላካችን በሁላችንም ደጅ ቆሞ “እነሆ በደጅ ቁሜ አንኳኳለሁ፤ ማንም ድምጼን ቢሰማ ደጁንም ቢከፍትልኝ ወደ እርሱ እገባለሁ ከእርሱም ጋር ራት እበላለሁ፤ እርሱም ከእኔ ጋር ይበላል” (ራእ. ፫፥፳) እያለ ለበረከት ይጠራናል፡፡ ስለዚህ እያንዳንዳችን ይህን ጥሪ አክብረን የሚጠበቅብንን ተወጥተን የስሙ ቀዳሽ የመንግሥቱ ወራሽ እንድንሆን ልንተጋ ይገባል፡፡

. ተነሳሽነት ማጣትና ለነገ ማለት

የሰው ልጅ በአፍአ በሚታየው አካሉ ነገሮችን በትጋትና በብቃት ያከናውን ዘንድ አእምሮው ወይም መንፈሱ ለተግባር መነሳሳት ያስፈልገዋል፡፡ ተነሣሽነትን ከሚገድሉ ጉዳዮች አንዱና ዋነኛው ደግሞ ሥራን ወይም መንፈሳዊ አገልግሎትን ለነገ እያሉ በቁርጠኝነት አለመጀመር ነው፡፡ ቅዱስ መጽሐፍ “እነሆ የተመረጠችው ቀን ዛሬ ናት” (፪ኛቆሮ. ፮፥፪) እያለ ሲመክረን፤ በሌላው ክፍል ደግሞ ስለ ነገረ ምጽአቱ ሲያስተምረን “… የእግዚአብሔር ቀን ግን እንደ ሌባ ድንገት ትመጣለች” (፪ጴጥ. ፫፥፲) ማለቱ ነገሮችን ሁሉ ነገ አደርገዋለሁ፣ ነገ እፈጽመዋለሁ እያልን ወደ ኋላ ከማዝገም ይልቅ በቁርጠኝነት ወደፊት ልንገሰግስ እንደሚገባ የሚያስተምረን ነው፡፡

በዘመናችን ብዙ በክርስቶስ ክርስቲያን የተሰኙ ወጣቶችን ቀረብ ብለን ለምን በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ደጀ ሰላም ተሳልመው ለመንፈሳዊ አገልግሎት እንደማይተጉ ብንጠይቃቸው የሚሰጡን አንድ ተደጋጋሚ ምላሽ አላቸው፡፡ እርሱም፡- “እያሰብከበት ነው፣ ትምህርቴን ልጨርስና፣ ይህን ላድርግና፣ ያንን ልፈጽምና፣ ወዘተ“ በማለት ይመልሳሉ፡፡ እንደዚህ ዓይነት የማይጨበጥ ምክንያት የሚፈጥሩት እንደ ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ አገላለጽ ”እነሆኝ ጌታዬ፤ እኔን ላከኝ” (ኢሳ.፮፥፰) ማለት የማይችሉት ተነሳሽነት ከመንፈሳቸው ፈጽሞ ስለሚጠፋ ነው፡፡

በጥቅሉ በመንፈሳዊ አገልግሎት ብቻ ሳይሆን ወጣቶች በዘመናችን ለትምህርት፣ ለሥራ፣ ከፍ ሲልም ለግል እንክብካቤና ንጽሕናን ለመጠበቅ የሚሆን ተነሣሽነት ሲጎድላቸው ይስተዋላል፡፡ ይህ ተነሳሽነት ማጣት የብዙ ተወራራሽ መንስኤዎች ድምር ውጤት ነው፡፡ ከእነዚህም መካከል ለዘመናዊነት ያለን የተዛባ አመለካከት የወላጆች የልጅ አስተዳደግ ሁኔታ፣ በቴክኖሎጂ ከመበልጸግ ጋር ተያይዘው የመጡብን የማኅበራዊና ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ሱሰኝነት ትልቁን ድርሻ ይስዳሉ፡፡ ከዚያ ባለፈ ግን የሰው ልጅ ለመኖር፣ ለመሥራት፣ ለመለወጥ፣ ብሎም ለዘለዓለማዊ ሕይወት የሚያበቃውን የጽድቅ ሥራ ለመሥራት ይተጋ ዘንድ ክርስቲያናዊ ዕሴት ሊኖረው ይገባል፡፡ ያም ሲሆን ነው “በሚያስችለኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ” (ፊል. ፬፥፲፫) በማለት ፈተናና እንቅፋቱን ተራምደን ወደ ዘለዓለም ሕይወት የሚደረገውን መንፈሳዊ ሩጫ በቁርጠኝነት ጀምረን በድል የምናጠናቅቀው፡፡

. በቀላሉ ተስፋ መቁረጥ

ሌላውና በአራተኛነት የምናነሣው ወጣቶች ወደ ቤተ ክርስቲያን ቀርበው ለመንፈሳዊ አገልግሎት እንዳይተጉ እንቅፋት የሆናቸው ጉዳይ በቀላሉ ተስፋ የመቁረጥ አባዜ ነው፡፡ ብዙ ወጣቶች የሥላሴን ልጅነት በዐርባና በሰማኒያ ቀናቸው አግኝተው ስመ ክርስትናም ተሰይሞላቸው በስብከተ ወንጌል ተነቃቅተውና ልባቸው ተሰብሮ በታላቅ ተነሳሽነት ለአገልግሎት ወደ ቤተ ክርስቲያን ከመጡ በኋላ በቀላሉ በጥቃቅን ፈተናዎች ተዳክመው ተስፋ ይቆርጣሉ፡፡

እንደዚህ ዓይነት ወጣቶች የሀገራችን እናቶች በንግሥ ሰዓት በዝማሬአቸው ታቦተ ሕጉን ሲያጅቡ “አልጋ በአልጋ ነው መንገዱ” እንዲሉ መንፈሳዊ አገልግሎት ሁሌም በበረከት በድንቃ ድንቅ ተአምራት ብቻ የተሞላ፣ ሁሌም የዝማሬና የምስጋና በዓል፣ ሆሳዕና እንጂ ከሆሳዕና ማግሥት ሕማም፣ ድካም፣ መራብ፣ መጠማት፣ መገረፍ፣ መሰቀል ያለበት መሆኑን እጅግ አብዝተው ይዘነጉታል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው የዚህ ዓለም ቆይታችን በፈተና የተሞላ እንደሆነ በቃልና በምሳሌ ከማስተማሩም ባሻገር በገዳመ ቆሮንቶስ ዐርባ መዓልትና ዐርባ ሌሊት ቆይቶ በተግባር ተፈትኖ አሳይቶናል፡፡ (ማቴ. ማቴ. ፬፥፩)፡፡ ለዚህም ነው “በብዙ ድካምና መከራ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት እንገባ ዘንድ ይገባናል” (ሐዋ.  ፲፬፥፳፪)፡፡ ተብሎ የተጻፈው፡፡

የወይን ፍሬ ይሰበሰብ ዘንድ የሚሻ አንድ አትክልተኛ ያን ለዐይን ዕይታ እንኳ የሚያስጎመዥ ፍሬ ይለቅም ዘንድ የተከለውን ተክል ከለጋነት ወጥቶ አድጎና በልጽጎ ፍሬ የሚያፈራበትን ጊዜ በትዕግሥት እየጠበቀ ካልተንከባከበው ፍሬውን ይቀምስ ዘንድ እንዴት ይችላል? አንድ መንፈሳዊ አገልጋይም “በትዕግሥታችሁም ነፍሳችሁን ገንዘብ ታደርጓታላችሁ” (ሉቃ. ፳፩፥፲፱) እንደተባለ እንዲሁ አገልግሎቱ በእግዚአብሔር ፈቃድ ለፍሬ እስኪበቃ በትዕግሥትና በተስፋ መጠበቅ ይገባዋል፡፡ የቤተ ክርስቲያናችን ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ለአንድ መንፈሳዊ አገልጋይ ሊኖረው ስለሚገባው ተስፋ ማድረግና ትዕግሥት ሲያስረዳ ይላሉ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ በሦስተኛው መጽሐፋቸው “አንድ ፅንስ ምሉእ ሰው ሆኖ ይህችን ምድር ይቀላቀል ዘንድ ወራትን በእናቱ ማኅፀን መቆየት(መታገስ) ካስፈለገው፤ እንደዚሁም መንፈሳዊ ፅንሱ ሳይቋረጥ በአግባቡ ያድግ ዘንድ አንድ አገልጋይ በትዕግሥት ሊጠብቅ ይገባዋል፡፡’ ይላሉ (Spiritual Ministry: HH. Pope Shenoda III) ስለሆነም እግዚአብሔር በአንድም በሌላም መንገድ ወደ ደጀ ሰላሙ ጠርቶን አገልግሎት የጀመርን ወጣቶች ነገሮችን ሁሉ ከውጪ በርቀት ስንመለከታቸው እንደነበር ባይሆኑ እንኳን ድካማችን ለፍሬ ይበቃ ዘንድ ብዙ ዘመናትን ቢጠይቅም “መከራ በተቀበልሁ ጊዜ ወዲያውኑ እበረታለሁና” (፪ኛቆሮ. ፲፪፥፲) እንዲል ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በእግዚአብሔር ኃይል ልንተጋ ይገባል እንጂ ተስፋችንን አቀዝቅዘን ለጠላት ዲያብሎስ እጅ መስጠት አይገባም፡፡

ይቆየን፡፡

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *