ወጣትነትና ታማኝ አገልጋይነት

ክፍል አንድ

በዲ/ን ወልደ ቂርቆስ ደሳለኝ

የሰው ልጅ በዚህች ምድር ላይ በሚኖረው ቆይታ ብዙ ኃይልና መነሳሳት የተሞላበት ዘመኑ የወጣትነት ዘመን ነው፡፡ የሰው ልጅ ከሌላው ጊዜ በተለየ አዳዲስ ግኝቶችን ለማበርከት፣ እጅግ ከባድና ውስብስብ የሚመስሉ ጉዳዮችን በድፍረት ለመጀመርና ለመሞከር ታላቅ ወኔና ድፍረት የታጠቀበት ዘመን ቢኖር የወጣትነት ዘመን ነው፡፡ የመመራመር ጉጉት፣ የማወቅ፣ የማገልገል ልዩ ትጋትና ቁርጠኝነትን የተላበሰ ዘመንም የሚታየው በወጣትነት ዘመን ነው፡፡ አካላዊ ማኅበራዊ፣ መንፈሳዊ ብሎም ምጣኔ ሀብታዊ ለውጦች በስፋት የሚስተናገዱበት፣ ውስብስብ ፈተናዎች የሚገጥሙበት ዘመን ቢኖር የወጣትነት ዘመን ነው፡፡ ችኩልነት፣ እብሪተኝነት፣ አልታዘዝ ባይነት የሚፈታተኑት በወጣትነት ዘመን ነው፡፡ ለሉላዊነት አስተሳሰብ፣ ለረቀቀ የቴክኖሎጂ አቅርቦት፣ ለባህል ብረዛ፣ ለሥራ አጥነት፣ ለቤተሰብ ጫና የሚጋለጠውም በወጣትነት ዘመን ላይ ነው፡፡

ይህንን ወጣትነት ብዙዎች እንደተጠቀሙበት ሁሉ ብዙዎችም መልካም ፍሬ የማያፈራ ዛፍ ተብለው “እንግዲህስ ምድራችንን እንዳታቦዝን ቁረጣት” (ሉቃ. ፲፫፥፮) እንደተባለች እንደዚያች በለስ የመቆረጥ ፍርድ ተፈርዶባቸዋል፡፡ በዚህ የወጣትነት ዘመን አቤል የፈጣሪውን ንጽሐ ባህሪይነት ተረድቶ ቀንዱ ያልከረከረውን፣ ጥፍሩ ያልዘረዘረውን፣ ጸጉሩ ያላረረውን ንጹሕ የመሥዋዕት ጠቦት በንጽሕና አቅርቦ ከእግዚአብሔር ዘንድ አትርፏል፡፡ ወንድሙ ቃየልም በንዝህላልነትና ግድየለሽነት ከሕይወት መስመር ወጥቶ ተቅበዝባዥነትን ተከናንቧል፡፡ (ዘፍ.፬፥፫-፲፭)፡፡ በወጣትነት ዮሴፍ እንደ ወርቅ በእሳት ተፈትኖ ንጽሕናውን አሳይቶበታል፤ በዚህ በወጣትነት ራሱን ለታይታና ለይሰሙላ ባልሆነ ፍጹም ትሕትና ከወንድሞቹ ሁሉ በታች ራሱን ዝቅ አድርጎ በንግሥና ከፍ ከፍ ብሎበታል፡፡ (ዘፍ.፴፱፥፩)፡፡ በዚያም በምድርና በሰማይ ሠላሳ፣ ስድሳ፣ መቶም ያማረ ፍሬ አፍርቶ ዝገት የማይበላውን፣ ሌቦች የማይሰርቁትን መዝገብ አከማችቶበታል፡፡

በዚሁ የወጣትነት ዘመን እንደ ጢሞቴዎስ ያሉት ትጉሃን ደቀ መዛሙርት በትጋት የመምህራቸውን ፈለግ ተከትለው ለክርስቲያን ወገኖቻቸው ተርፈውበታል፤ በመምህራቸውም እንዲህ ተወድሰዋል”በአንተ ያለው ግብዝነት የሌለበትን እምነትህን አስባለሁ” (፪ጢሞ. ፩፥፲፭)፡፡ በወጣትነት ከሰማያዊው ክብር ይልቅ ወደ ምድራዊው ድሎት የመጡ እነዴማስም እንዲህ ተብለዋል”ዴማስ ይህንን የዛሬውን ዓለም ወድዶ እኔን ተወኝ፤ ወደ ተሰሎንቄም ሄደ” (፪ጢሞ.፬፥፲)፡፡ በዚሁ የወጣትነት ዘመን ነው እንደ ሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ ያሉት መከራና ግፍን ሳይፈሩ በጥብአትና በእምነት ለታላቅ ድልና መንፈሳዊ አክሊል የበቁት፡፡ እንዲያው በጥቅሉ ይህንን የወጣትነት ዘመን ፈቃደ ሥጋን ለፈቃደ ነፍስ አስገዝተው ለክብር ሞት፣ ለዘለዓለም ሕይወት የበቁ ብዙዎች እንደሆኑ ቅዱሳት መጻሕፍት ይመሰክራሉ፤ አበው ሊቃውንትም ያስተምራሉ፡፡

በውኑ የእኛስ የወጣትነት ዘመን የትጋት ነውን? ከላይ እንደተጠቀሱት ደጋግ አበው ቅዱሳን የተሰጠንን መክሊት ሠርተን፣ ደክመን፣ ወጥተን ወርደን ለማትረፍ የጣርንበት ነው? ወይስ የተሰጠንን ጸጋና መክሊት ቀብረን ያው ያለን እንኳ ተወስዶብን ለቅሶና ጥርስ ማፋጨት ወዳለት ወደማይጠፋ እሳት ለመጣል እየጠበቅን ነው? በውኑ በወጣትነቱ ደግና ታማኝ አገልጋይ (ገብር ሔር) ማን ነው? ወጣቶች ወደ መንፈሳዊ አገልግሎት እንዳይቀርቡስ እንቅፋት የሆናቸው ምንድን ነው? ተግተው ለአገልግሎት የመጡት ወጣቶችስ እየገጠማቸው ያለው ፈተናና ተግዳሮት ምንድነው? በወጣትነት ታማኝ መንፈሳዊ አገልጋይ ለመሆንስ ምን ማድረግ አለባቸው? የሚሉትን ነጥቦች በዚህ ጽሑፍ ለመዳሰስ እንሞክራለን፡፡ በቅድሚያ ግን ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዳንቀርብ፣ ለማገልገል ዝግጁ እንዳንሆን እንቅፋት የሆኑን ምክንያቶችን በጥቂቱ እንመልከት፡-

የመንፈሳዊ አገልግሎት እንቅፋቶች

በዘመናችን አብዛኛዎቹ ወጣቶች ከእግዚአብሔር ቤት እየሸሹ ውሎና አዳራቸው በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ወደማይጠቀሙበት አቅጣጫ በማምራት ከዓላማቸው ተሰናክለው ለጤና መታወክ በሚያበቋቸው አልባሌ ቦታዎች ይሆናሉ፡፡ ድምጿን ከፍ አድርጋ ለምትጣራ ቤተ ክርስቲያን ልባቸውን ከመስጠት ይዘገያሉ፡፡ ወጣቶች ወደ አገልግሎት እንዳይገቡ እንቅፋት ከሚሆኑ ነገሮች መካከል የሚከተሉትን ጠቅለል አድርገን እንመልከት፡-

፩. ቤተ ክርስቲያንን አለማወቅ

፪. አልችልም/አይገባኝም ማለት

፫.ተነሳሽነት ማጣትና ለነገ ማለት

 ፬. በቀላሉ ተስፋ መቁረጥ

፩. ቤተ ክርስቲያንን አለማወቅ

ብዙ ወጣቶች ስብከተ ወንጌልን ልብ ሰጥቶ ከመታደም፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን ጊዜ ሰጥቶ በተመስጦና በጥልቀት አንብቦ ከመረዳት፣ ሊቃውንትን፣ መምህራነ ወንጌልንና ካህናትን ቀርቦ ከመጠየቅ ይልቅ በተለያየ ሰበብና ምክንያት ራሳቸውን ስላሸሹ ቤተ ክርስቲያንን በውል ማወቅ፣ መረዳት ሲከብዳቸው ይስተዋላል፡፡ ቤተ ክርስቲያንን እናውቃለን ብለው የሚያስቡት እንኳን ዓለም ከምታቀርብላቸው ሥጋዊ ፍላጎትን ከሚያነሣሱ ከማኅበራዊ ትስስር ገጾች በለቃቀሟቸውና በቃረሟቸው የተቆራረጡና ምሉእ ያልሆኑ ሕጸጽና ግድፈት ያለባቸውን መረጃዎች በመሰብሰብ ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ ተልእኮዋን በውል ተረድተዋል ለማለት ይቸግራል፡፡

በዚህ ጽሑፍ ቤተ ክርስቲያንን አለማወቅ ስንል እግዚአብሔርንና የእግዚአብሔር ፈቃድ፣ የቤተ ክርስቲያንን ዶግማዊና ቀኖናዊ ድንጋጌዎች፣ አካሄዷንና አሠራሯን አለማወቅን ለመግለጽ ነው፡፡

ወጣቶች ቤተ ክርስቲያን ምንድን ናት? ተልእኮዋስ ምንደነው? ቤተ ክርሴቲያን ከእኔ ምን ትፈልጋለች? እኔስ ከቤተ ክርስቲያን የማገኘው ጥቅም ምንድነው? እነዚህን ለመሰሉ መሠረታዊ ጥያቄዎች ለኅሊናቸው በውል ምላሽ መስጠት ሲቸግራቸው ይስተዋላል፡፡ ለአንዳንድ ወጣቶች ቤተ ክርስቲያን የእነ አቡነ እገሌ፣ አባ እገሌ፣ ሰባኪ (ዘማሪ) እገሌ ናቸው፡፡ እነዚህ ዓይኑንና ተስፋውን የጣለባቸው ሰዎች ፈተና አድክሟቸው የዓለም አንጸባራቂ ውበት ስቦ አታሏቸው እንደ  ዴማስ (፪ጢሞ.፬፥፲) ወደ ኃላ መጓዝ፣ መሰናከል በጀመሩ ጊዜ ቀድሞውኑ ቤተ ክርስቲያንን በእነዚህ ሰዎች ትከሻ ላይ ወስነዋት ነበርና የእነርሱን ድካምና ጥፋት ከቤተ ክርሰቲያን ለይቶ ማየት ያቅታቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ከሕወት መንገድ ተደናቅፈው ይወድቃሉ፡፡

ለዚህም ነው በየአድባራቱ፣ ማኅበራትና ሰንበት ትምህርት ቤቶች “የእገሌ መዝሙር ካልተዘመረ፣ እገሌ የተባለ ሰባኪ ካልመጣ፣ አባ እገሌ ካልተሾሙ፣ አቡነ እገሌ ካልተሻሩ አላገለግልም፣ አልመጣም …” ወዘተ በማለት ቀስ በቀስ ከቤተ ክርስቲያን እቅፍ የወጡና እየወጡ ያሉ ምእመናን ቁጥራቸው እየበዛ የመጣው፡፡ ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን ከእነዚህ ነገሮች በላይ የሆነች አንዲት፣ ቅድስት፣ ሐዋርያዊትና ኩላዊት (ዓለም አቀፋዊት) ናት፡፡ (ሊቀ ጉባኤ አባ አበራ፤ ትምህርተ ሃይማኖትና ክርስቲያናዊ ሕይወት)፡፡ ለዚህም ነው አበው በሃይማኖት ጸሎት ደግመን ደጋግመን እንዘክረው ዘንድ “ከሁሉ በላይ በምትሆን ሐዋርያት በሰበሰቧት በአንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እናምናለን” ብለው ያስቀመጡልን፡፡

 ቤተ ክርስቲያንን አለማወቅ በሦስት ክፍሎች ከፍለን ልናየው እንችላለን፡፡

የመጀመሪያው ስለ ቤተ ክርስቲያን ምንም ዓይነት ዕውቀትና ግንዛቤ አለመኖር ነው፡፡ አንዳንድ ወጣቶች ወላጆቻቸው በልጅነታቸው ካመላለሷቸው በኋላ እግሮቻቸው ደጀ ሰላምን አልረገጡም፡፡ ነገር ግን በአንገታቸው ማዕተብ አጥልቀው፣ በስማቸውም ክርስቲያን፣ የክርስቶስ ወገን ተሰኝተዋል፡፡ እንደነዚህ ዓይነት ሰዎች ቤተ ክርስቲያን ምን እንደሆነች፣ ተልእኮዋ ምን እንደሆነ፣ በዚህ ወቅት ቤተ ክርስቲያን ምን ሁኔታ ላይ እንደምትገኝ አያውቁም፤ የማወቅ ፍላጎታቸውም የደከመ ነው፡፡ እናም መቼም ቢሆን ውስጣቸው በቤቱ ቅናት ተቃጥሎ “እስመ ቅንዐተ ቤትከ በልዐኒ፤ የቤተህ ቅናት በልቶኛልና” (መዝ.፷፰፥፱) ብለው ለአገልግሎት ይነሡ ዘንድ፣ የሀገር፣ የቤተ ክርስቲያን መጥፋት አሳዝኗቸው ወደ መንፈሳዊ ቁጭት ውስጥ ይገቡ ዘንድ “ኢታርእየነ ሙስናሃ ለኢየሩሳሌም፤ የኢየሩሳሌምን ጥፋት አታሳየን” ሊሉ አይችሉም፡፡

በሁለተኛ ደረጃ የበቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮዋን፣ ዶግማዋንና ቀኖናዋን በግል ምልከታቸው በሥጋዊ ድካማቸው ደረጃ ዝቅ አድርገው “ምን አለበት፣ ምን ችግር አለው፣ ብዙ ባናካብድ” በሚሉ ሰበቦች ታስረው ቤተ ክርስቲያንን ያወቁ የሚመስላቸው ነገር ግን ያላወቁ ወጣቶች ናቸው፡፡ ለእነዚህ ዓይነቶቹ ምእመናን ቤተ ክርስቲያን የምታስፈልጋቸው ሥጋዊ ፈተናዎች (ሥራ ማጣት፣ ከወዳጃቸው ጋር መጋጨት፣ ሥጋዊ ደዌ፣ የኑሮ መክበድ፣ የትምህርት ጉዳይ፣ …) ሲያስጨንቃቸው ብቻ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን የሰማያዊና የዘለዓለማዊ ሕይወት ሰጪነት፣ የቤተ ክርስቲያን የነፍስ መጋቢነት አይታያቸውም፡፡

ሩጫቸው ምድራዊ ስኬት እስከ ማግኘትና መጎናጸፍ ድረስ ብቻ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ አሳስቧቸው ሳይሆን ለአገልግሎት የሚመጡት ለሥጋዊ ዓላማ ብቻ ነውና ጥያቄአቸው መልስ ሲያገኝ (ሥራ ወይም ትዳር ሲይዙ፣ …) ከቤተ ክርስቲያንም ይኮበልላሉ፡፡

በሦስተኛ ደረጃ ቤተ ክርስቲያንን ባልተረጋገጠና በተምታታ መረጃ በአላዋቂዎች ትምህርት ተመርኩዘው እናውቃለን የሚሉት ናቸው፡፡ በዚህኛው የዕውቀት ደረጃ ብዙ ወጣት ምእመናን ቤተ ክርስቲያን ለዘመናዊነት፣ ሠርቶ ለመለወጥ፣ ራስን ለማሳደግ ጠላት አድረገው ይስሏታል፡፡ መንፈሳዊነትንና ለቤተ ክርስቲያን አሳቢነትን ራስን ካለመንከባከብ፣ ንጽሕናን ካለመጠበቅ እና ሥራና ትምህርትን እርግፍ አድርጎ ትቶ የብህትውና ኑሮ ከመኖር ጋር የሚያዛምዱ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ እግዚአብሔርን በፈራጅነቱ፣ በቀጪነቱ ፈርተው ያመልኩታል እንጂ ከፍቅር የመነጨ ፈሪሃ እግዚአብሔር አይኖራቸውም፡፡ የእንደዚህ ዓይነት ሰዎች ሌላው መለያ ባሕርያቸው በመንፈሳዊ መንገዳቸው ፊት ለፊት የሚታያቸው የክርስቶስ ሕይወት፣ አልያም የአበው ቅዱሳን ተጋድሎ አይደለም። ከዚያ ይልቅ በቅርብ የሚያገኙትን አገልጋይ የፍጹምነት ምሳሌ አድርገው ይስሉታል፡፡ እነዚህ ወጣቶች ከቤተ ክርስቲያን ይልቅ እነዚህን ሰዎች ከማምለክ ባልተናነሰ ሲያዳምጡ ይስተዋላል፡፡ በአጠቃላይ ሦስቱም ትክክለኛ መንገዶች አይደሉም፡፡

ይቆየን፡፡

ምንጭ፡- ሐመር መጽሔት ፳፯ ዓመት ቁጥር ፪ ሰኔ ፳፻፲፩ ዓ.ም

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *