“ወብዙኃን ይትፌሥሑ በልደቱ፤ በመወለዱም ብዙዎች ደስ ይላቸዋል” (ሉቃ. ፩፥፲፬)

መ/ር እንዳልካቸው ንዋይ

ይህን ቃል የተናገረው የእግዚአብሔር መልአክ ለካህኑ ዘካርያስ ነው፡፡ የጻፈልንም ከአራቱ ወንጌላውያን አንዱ የሆነው ቅዱስ ሉቃስ ነው፡፡ ይህ ቃል የተነገረለትም የካህኑ ዘካርያስና የኤልሳቤጥ ልጅ የሆነው መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ነው፡፡ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ አባቱ ዘካርያስ እናቱ ኤልሳቤጥ ይባላሉ፡፡ ቅዱስ ዮሐንስን እስኪወልዱ ድረስ በመካንነት (ያለ ልጅ) ኖረዋል፡፡

ጻድቃን መካን ሆነው የሚቆዩበት ጊዜ አለ፤ ኃጥአን መክነው የሚቀሩበት ሁኔታ አለ፡፡ እግዚአብሔር ባወቀ መክነው የሚቀሩም አሉ፡፡ በቅዱሳት መጻሕፍት እንደተገለጠው ምክነት (ልጅ መውለድ አለመቻል) በሦስት ዋና ዋና ምክንያቶች ሊመጣ ይችላል፡፡

. በኃጢአት፡

የሰው ልጅ ሕገ እግዚአብሔርን ሲተላለፍ፣ እግዚአብሔርን በሕይወቱ ማክበር ሲያቅተው፣ የቅዱሳንንም ክብር አልጠብቅ ሲል እግዚአብሔር ከቸርነቱ ብዛት የተነሣ ለሰው የሚሰጠውን ጸጋ ይነሳዋል፡፡ “ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታዎች ናቸው”ና፡፡ (መዝ.፻፳፯፥፫)  ልጅ ጸጋ ስጦታ ወይም ሀብት ነው፡፡ ጸጋ የሚሰጠው ደግሞ ለሚገባው ነው፡፡ ኃጢአት ደግሞ ጸጋን ያሳጣል፡፡ በኃጢአት ምክንያትም እግዚአብሔር ማሕፀናቸውን የዘጋባቸው እና ያለ ልጅ ያስቀራቸው ሰዎች አሉ፡፡ ከእነዚህም ሰዎች አንዷ የእስራኤል የመጀመሪያው ንጉሥ የሳዖል ልጅ እና በኋላም የነቢየ እግዚአብሔር የዳዊት ሚስት የሆነቸው ሜልኮል ናት፡፡

ዳዊት ታቦተ ጽዮን ከምርኮ በምትመለስበት ጊዜ ለታቦተ ጽዮን በዘመረ ጊዜ ሚስቱ ናቀችው፤ በዚህ ምክንያት እግዚአብሔር የሜልኮልን ማሕፀን ዘጋ፡፡ “ኢወለደት ሜልኮል እስከ አመ ሞተት፤ ሜልኮል እስከ ሞተችበት ቀን ድረስ ልጅ አልወለደችም፡፡” (፪ኛሳሙ. ፮፥፳፫) በማለት ይገልጻታል፡፡ በኃጢአት ከሚመጣው ምክነት ለመዳን ንስሓ መግባትና ወደ ፈሪሃ እግዚአብሔር መመለስ ይገባል፡፡

. ለሰዎች ጥቅም፡-

እግዚአብሔር የማይጠቅም ጸጋ አይሰጥም (፩ኛቆሮ. ፲፪፥፯) የቅዱሱ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት እናት እግዚእ ኃረያ እግዚአብሔርን ልጅ እንዲሰጣት በለመነችው ጊዜ አንድ ቃል ተናግራ ነበር፡፡ “የምትሰጠኝ ልጅ አንተን የሚፈራ የሚያገለግል ሰውን የሚያፍር ሃይማኖቱን የሚያከብር ይሁንልኝ ካልሆነ ግን ማህፀኔን ዝጋው” በማለት ነበር የተማጸነችው፡፡ (ገድለ ተ/ሃይማኖት፤ ገጽ ፳፰፤ ምዕ. ፰፥፶-፶፫) እግዚአብሔርም ጸሎቷን ሰምቶ አቡነ ተክለ ሃይማኖትን የመሰለ ልጅ ሰጥቷታል፡፡ የማይጠቅም ልጅ ቢሆን ግን እግዚአብሔር አይሰጥም፡፡

. የሚወለደው ልጅ የተለየ ቅዱስ ከሆነ፡-

እግዚአብሔር ስለሚሰጠን ልዩ ስጦታ ብሎ ስጦታውን ሊያዘገየው ይችላል፤ ይህም የሚሆንበት ምክንያት ውድ ስጦታ ስለሆነ በደጅ ጥናት፣ በጸሎት፣ በሱባኤ እንዲሆን ሁለተኛም አክብረን እንድንይዘው ነው፡፡ በዚህ ምክንያት በቅዱሳት መጻሕፍት እንደተነገረው ስለሚሰጣቸው በጎ ስጦታ በምክነት ያቆያቸው ቅዱሳን ሰዎች አሉ፡፡

ለምሳሌ፡-  ሣራ የአብርሃም ሚስት ለ፺ ዓመት ያህል በምክነት የቆየችው ይስሐቅን የመሰለ በጎ ስጦታ እግዚአብሔር ስላዘጋጀላት ነው፡፡ ሐና እና ኢያቄምም ያለ ልጅ የቆዩት የአምላክ እናት የምትሆን ድንግል ማርያምን ሊሰጣቸው ስለሆነ ነው፡፡ ዛሬም በዓለ ልደቱን የምናከብርለት ቅዱስ ዮሐንስ ወላጆቹ በእግዚአብሔር ፊት ያለ ነውርና ያለ ነቀፋ የሚሄዱ ጻድቃን ሲሆኑ ያለ ልጅ በምክነት የቆዩት ክርስቶስን በዮርዳኖስ ባሕር ለማጥመቅ የሚበቃውን ደግ ሰው ስለሚወልዱ ነበር፡፡

ለዚህም ነበር መልአኩ የቅዱሱን ልደት አስመልክቶ “በመወለዱም ብዙዎች ደስ ይላቸዋል” ሲል የተናገረው፡፡ ልደቱ ከእናትና አባቱ ጀምሮ የክርስቶስን መምጣት ለሚጠባበቁ ሁሉ ደስታ ነበር፤ ለዚህም ነው መልአኩ ስሙ ዮሐንስ ይባላል ያለው፡፡ ዮሐንስ ማለትም ፍስሓ ወሐሴት ፍቅር ወሰላም ማለት ነው፡፡ ከፅንሰቱ ጀምሮ እስከ ልደቱ በመላ ሕይወቱም ሁለንተናው በተአምር የተመላ ልጅ በማግኘታቸው ወላጆቹ ደስታን አግኝተዋል፡፡ ሲፀነስ የአባቱ አንደበት የመልአኩን ቃል ባለመቀበሉ ሲዘጋ ሲወለድ ደግሞ የአባቱን አንደበት ከፍቶ ቤቱን በደስታ የመላ ቅዱስ ሕፃን ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቅዱስ ዮሐንስን ልደት በየዓመቱ በታላቅ ክብር ታከብረዋለች፡፡

በዚህ አንጻር የእኛ ልደት እንዴት ነው እየተከበረ ያለው? በእኛ ልደት ቤተሰቦቻችን፣ ቤተ ክርስቲያንና ሀገራችን ምን ተጠቀሙ? በየዓመቱስ ልደታችን የምናከብርበት መንገድ ኦርቶዶክሳዊ የቅዱሳንን መንገድ የተከተለ ነው? የሚለውን ጥያቄ ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ግን በልደቱ ብዙዎች ደስ ተሰኝተዋል፡፡ ምክንያቱም በትምህርቱ በተአምራቱ ብዙዎች ተጠቅመዋልና “የጌታን መንገድ አዘጋጁ” እያለ በትምህርቱ ሰዎችን ወደ ክርስቶስ ያቀርብ ነበር፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ በውኃ ለንስሓ በዮርዳኖስ ባሕር እያጠመቀ ለአማናዊ ጥምቀት ሰዎችን ያዘጋጅ ነበርና ብዙዎች በመወለዱ ተጠቅመዋል፡፡ እኛስ በመወለዳችን ማን ተጠቀመ? በቅዱስ ዮሐንስ መወለድ ግን ብዙ ድንቆች ሆነዋልና ደስ ይለናል፡፡ አስቀድመን እንዳነሣነው ስለ ክርስቶስ እያስተማረ፣ በበረሐ በመኖሩና ጌታን በማጥመቁ ቅድስናውን ማድነቅ፣ በቃል ኪዳኑም መጠቀም ከእኛ ይጠበቃል፡፡

ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ይህን ሲያስረዳ እንዲህ አለ።-

ሰባኬ ወንጌል በጥዑም ልሳኑ፣

ርስነ መለኮት ገሠሠት የማኑ፣

ፀጕረ ገመል ተከድነ ዘባኑ፣

ለዮሐንስ ሂሩቶ ንዜኑ ንዜኑ፡፡

ትርጉሙም

በጣፋጭ አንደበቱ ወንጌልን የሚሰብክ፤ የሚያቃጥል መለኮትን የዳሰሰች ቀን እጅ፤ ጀርባው በግመል ፀጕር የተሸፈነ የዮሐንስን ደግነት ፈጽመን እንናገራለን በማለት አመስግኖታል፡፡

በአጠቃላይ የዮሐንስ ልደት ለብዙዎች ደስታ ነው የተባለው ሰውን ሁሉ በንስሓ ወደ ጌታው የሚመልስ በመሆኑ ነው፡፡ ስለሆነም እኛም መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ የጌታ መንገድ ጠራጊ ነውና በልደቱ ደስ ሊለን ይገባል፡፡

አምላከ ዮሐንስ ይርዳን፣ በበረከተ ልደቱም ይባርከን፡፡

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *