ክርስቶስ ተከፍሎአልን? (፩.ቆሮ.፩፥፲፪)

ዲ\ን ታደለ ፈንታው( ዶ/ር)

ክፍል አንድ

የምንኖርበት ዓለም በቅራኔዎች እና በግጭቶች የተሞላ ነው፡፡ ጥናቶች እንደሚያረጋግጡት ግማሽ የሚሆነው የዓለም ሕዝብ በግጭት ቀጠና ውስጥ የሚኖር ነው፡፡ አሁን አሁን ይህ ግጭት አድማሱን አስፍቶ በአንድ ወቅት የተረጋጉ የሚባሉ የምዕራብ አውሮፓ ሀገሮች ሳይቀሩ የግጭት ሰለባ እየሆኑ መጥተዋል፡፡

ግጭቶች የሚነሡበት በርካታ ምክንያቶች ይኖራሉ፡፡ ለአብነት ያህል የ፳ኛውን መቶ ክፍለ ዘመን ብቻ አንስተን ብንመለከት በአንድ ሀገር ግጭት ከሚነሣባቸው እና ውጤቱም አውዳሚ ከሆነባቸው ምክንያቶች አንዱ በዘር ምክንያት የሚከሠተው ችግር ነው፡፡ ለመሆኑ ዘር ምንድነው? የሰው ልጆች ስለ ምን በዘር ምክንያት ይጣላሉ? ስለ ምንስ የከፋ ግጭት ሰለባ ይሆናሉ? በክርስትና አስተምህሮ አንጻር እንዴት ይታያል? የሚለውን መሠረታዊ እሳቤን መመልከት ይጠይቃል፡፡

ማኅበራዊ ቅራኔን እና ግጭትን በተመለከተ ትኩረትን የሚሹ ሁለት እውነታዎች አሉ፡፡ የመጀመሪያው በማደግ ላይ ባሉ ሀገሮች በሚነሡ ግጭቶች ግማሹ የሞት ሰለባ የሚሆነው ሕዝብ ቁጥር የሚሸፍነው መንሥኤው በዘር ምክንያት የሚነሣ ነው፡፡ ለሁለተኛው የዓለም ጦርነት ምክንያቱ አዶልፍ ሂትለር የእኔ ዘር ከሰው ዘር በላይ ነው፡፡ የጀርመን ዘር ከፀሐይ በታች ምርጥ ዘር ነው የሚለው ልፈፋውና እብደቱ የወለደው ውድመት ነው፡፡ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ ፳፪ በሚሆኑ ሀገሮች ውስጥ የተከሠቱ ግጭቶች ነበሩ፡፡ በእነዚህ ግጭቶች የሞተው ሰው ልጅች ቁጥር ከ፫-፰ ሚሊዮን እንደሚደርስ ጥናቶች ያረጋግጣሉ፡፡ የድል ነጋሪት የተጎሰመባቸው፣ ሰፊ የሕዝብ ቁጥር ያሰለፉ ጥፋቶች ደግሞ ከዚህ ላቅ ያለውን ቁጥር ይይዛሉ፡፡ በሀገሮች መካከል በተደረገ ዘርን መሠረት ያደረገ ጦርነት ወደ ፳፭ ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ በቀጥታ የሞት ሰለባ ሆኗል፡፡

ዘር ምንድነው?

አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ዘርን፣ ዘርዕ በቁሙ፡- ዘር ቅንጣት ፍሬ የሚበቅል ማለት ነው፡፡ የሰውን ዘር ልጅ፣ ወገን ነገድ ትውልድ በማለት ይፈቱታል፡፡ በዘመናዊው ዓለም ዘር የሚለው ቃል ከጥንት ጀምሮ የነበረ ቢሆንም በአውሮፓውያን የቋንቋ ጥናት መጀመሪያ የተከሠተው በ፲፮ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው፡፡ በ፲፯ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የፈረንሳይ ተመራማሪዎች ዘርን፣ እንዲሁም ቤተሰብን ለመግለጥ ተጠቅመውበታል፡፡ ጀርመኖች ቃሉን በ፲፰ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የቆዳ ቀለማቸው እና አካላዊ ቅርጻቸው የተለያዩ ወገኖችን (የሰው ልጆችን) ለመግለጽ ተጠቅመውበታል፡፡ ሌላ ተመራማሪ ዘርን ነጭ፣ ቢጫ፣ ጥቁር፣ እና ቀይ በማለት የቆዳ ቀለምን ለመለየት ተጠቅሞበታል፡፡ አሁን አሁን ደግሞ ቋንቋ ያለ ቦታው ገብቶ ዘርን ለመግለጥ ጥቅም ላይ ውሎ የመለያየት እና የመበታተን አደጋ ሲሆን እንመለከታለን፡፡

ዘረኝነት ምንድነው?

ዘረኝነት የሰው ልጆችን የሚነጣጥል፤ ደረጃ የሚሰጥ እና እኛ እና እነርሱ በሚል ጎራ የሚከፋፍል ነው፡፡ ይህንንም ሁኔታ ተከትሎ የሰው ልጆችን ወደማያባራ ውስብስብ ጥላቻ ውስጥ የሚከት የማኅበረሰብ ስብራት ነው፡፡ ዘረኝነት የሰው ልጆችን ከዚህ የክፍፍል አጥር ውጭ አድርጎ አይመለከታቸውም፡፡

ሰዎችን ወደ አንድነት ወይም ወደ ልዩነት የሚመራ አውዳሚ እሳት ነው፡፡ በዘረኝነት የታወሩ ሰዎች ደግሞ ሲመሩት ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም፡፡ ይህ አመለካከት ከክርስትና አስምህሮ ምሰሶዎች ጋር አብሮ የሚሄድ አይደለም፡፡ እርሱም የሰው ልጆችን አንድነት “ሁሉም የአንድ አዳም እና አንድ የሔዋን ልጆች እንጂ ሌላ አይደሉም” ከሚለው አስተምህሮ፣ ከሰው ልጅ ክቡር ባሕርይ እና ከክርስቲያናዊ መንፈሳዊነት እሳቤ አንጻር ዘረኝነት ስፍራ የለውም፡፡ ሰው ሠራሽ እና ጨካኞች የወለዱት ከፋፋይ እና አውዳሚ አስተሳሰብ ነው፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዘረኝነትን የምትቃወምበት መጽሐፍ ቅዱሳዊና ትውፊታዊ አስተምህሮ መነሻ አላት፡፡

ስለ ሰው ልጆች አንድነት ክርስትና የሚያስተምረው

አስቀድሞ በአይሁድ እምነት ዘንድ የነበረው የተስፋ ቃልም ይሁን ወንጌል ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻው የሰው ልጆችን ፍጹም አንድነት የሚቀበል ነው፡፡ ይህም ትምህርት እግዚአብሔር አንድ ነው ከሚለው ይጀምራል፡፡ እግዚአብሔር የመጀመሪያም የመጨረሻም (አልፋ እና ኦሜጋ) እርሱ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ድኅነት አንድነት እና ዓለም አቀፋዊነት መነሻ ሲናገር መነሻው ቅድስት ሥላሴን ማእከል ያደረገ ነው፡፡ የእነርሱን የማትከፈል አንድነት ለሰው ልጆች አንድነት መሠረት አድርጎ ተናግሯል፡፡

የዘረኝነት ድምዳሜ የሚያመራው ደግሞ በተግባር እግዚአብሔርንና መንግሥቱን በመካድ ነው፡፡ የእስራኤል ነቢያት ራሳቸውን በዘር ብቻ ሳይሆን በተለያየ የየራሳቸው አማልክት ከፋፍለው ምድርን ዕረፍት ነሥተው የነበሩት በተሳሳተ ዕሳቤ ላይ በመቆማቸው ነበር፡፡ እውነተኞቹ ነቢያት የቀደሙ ሰዎችን ሲገሥፁ የተናገሩት “እግዚአብሔር የሁሉም በሁሉም ያለ፤ ሁሉን ቻይ ጌታ ነው” የሚል አስተምህሮን ወደ ዓለም በማምጣት ነው፡፡ አበው ኦሪት ዘፍጥረትን መነሻ አድርገው የሰው ልጆችን አንድነት አምልተው አስፍተው አስተምረዋል፡፡

ሔዋን ከአዳም ግራ ጎን ተገኘች፤ ሕያዋን የሆኑ የሰው ልጆችንም በሩካቤ አስገኘች ማለት ሌላ አይደለም የሰው ልጆች ግንድ አንድ ነው ማለት ነው፡፡ የሃይማኖት ድንጋጌዎች፣ ቀኖናዎች ሕግጋት ሁሉ የሰው ልጆችን መገኛ ግንድ አንድ አዳምን ማድረጋቸው (the absolute homogeneity of human nature) ፍጹም የሰው ልጆችን ፍጹማዊ አንድነት የሚያረጋግጥ እንጂ ሌላ አይደለም፡፡

ሔዋን (የሕያዋን ሁሉ እናት) ሌላ ፍጥረት ሳትሆን ከአዳም ከግራ ጎን መገኘቷ ከአንዱ አዳም ጎን የተከፈለች እንጂ ሌላ ልዩ አካል አለመሆኗን እናውቃለን፤ እናምናለንም፡፡

እግዚአብሔር “ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር” ሲል እግዚአብሔር የሰው ልጆች አንድነት እየተገለጠ ነው፡፡ እግዚአብሔር በአካል ሦስት እንደሆነ እናምናለን፡፡ ነገር ግን በባሕርይ፣ በአገዛዝ፣ በመለኮት፣ በሥልጣን፣ በእግዚአብሔርነት፣ በዘላለማዊነት፣ ዓለምን በመፍጠር አንድ አምላክ ነው፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ሰው አንድም ብዙም ነው፡፡ የአንበሳ ዘር አንድ፣ የነብር ዘርም አንድ ነው፡፡ የሰው ዘርም እንዲሁ ሰው ነው፡፡

የትም ይወለድ የትም ይደግ የሰው ልጅ ሰው ነው፡፡ መርጦ የሚያገባውም ጃፓናዊት ትሁን ኮርያዊት እስያም ትሁን አውስትራሊያ ሰው በመሆኗ ነው የባሕርይ አንድነቱን ተመልክቶ ገንዘብ የሚያደርጋት፡፡ ሰው በሚኖርበት አካባቢም በቆዳ ቀለሙ አንዱ ከአንዱ ሊለያይ ይችላል፡፡ በቋንቋ፣ በባህልም እንዲሁ ነው፡፡ ይህ ግን የሰው ዘር መሆኑን ሰውነቱን ሊቀይር የሚችል አይደለም፡፡ የሰው ልጆችም አማራ ይሁኑ ኦሮሞ አፋር ይሁኑ አርጎባ፤ ፈረንሳዊ ይሁኑ እንግሊዛዊ ሰው ተብለው ይጠራሉ እንጂ ሌላ ከሰውነት ተራ ወጥተው የሚጠሩበት መጠሪያ የላቸውም፡፡

ይቆየን

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *