ክረምትና የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች

የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች ለመደበኛው ትምህርት ራሳቸውን በማዘጋጀት በውጤት ታጅበው ለሚቀጥለው ዓመት ለመሸጋገር አቅማቸውን ሁሉ ተጠቅመው ጊዜአቸውን ሰጥተው ሲተገብሩ ማየት የተለመደ ነው፡፡ “የሚተክልም የሚያጠጣም አንድ ናቸው፤ ሁሉም እንደ ድካማቸው ዋጋቸውን ይቀበላሉ” (፩ኛ ቆሮ. ፫፥፰) ተብሎ እንደተጻፈው ድካሙ ብዙ ነው፡፡ ነገር ግን በራስ ጥረት ብቻ ሳይሆን የእግዚአብሔርም ፈቃድና ድጋፍ እንደሚያስፈልግ መረዳት ይገባል፡፡ “እኔ የወይን ግንድ ነኝ፤ ቅርንጫፎቹም እናንተ ናችሁ፤ በእኔ የሚኖር እኔም በእርሱ ብዙ ፍሬ የሚያፈራ እርሱ ነው፤ ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና፡፡” (ዮሐ. ፲፭፥፭) በማለት ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደነገረን ከእርሱ ጋር መሆን ያስፈልጋል፡፡ እግዚአብሔርን የሚፈልግ ልብ በፍሬ ይታጀባልና፡፡

በወጣትነት ለሥጋዊው ሕይወት መውጣት መውረድ እንደለ ሆኖ ለመንፈሳዊው ሕይወትም ጊዜ መስጠት፣ በጸሎት መትጋት፣ በንስሓ መመላለስ፣ ከበጎ ነገር ጋር መተባበር ከአንድ ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን የሚጠበቅ ጉዳይ ነው፡፡ ሥጋን ብቻ ለማስደሰት በመሮጥ መንፈሳዊ ምግብ የሆነውን የእግዚአብሔርን ቃል ብንዘነጋ ምን እናተርፋለን? ስለዚህ ወጣቶች (የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች) ለመንፈሳዊ ሕይወታችው ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጡና በመንገዱም ሊመላለሱ ይገባል፡፡

በወጣትነት ዘመን ስሜታዊነት የሚንጸባረቅበት ጊዜ ነው፡፡ ይህን ጊዜ በጥበብና በማስተዋል ማለፍ ካልተቻለ ለተለያዩ ክፉ ሥራዎች (ሱሶች፣ እግዚአብሔርን መርሳት፣ በጎ ነገርን አለማድረግ፣ …) መጋለጥን ያስከትላል፡፡ በተለይም እግዚአብሔርን አለማሰብ እንደ ቃሉም አለመመላስ በቀሪው ሕይወታቸው የሚያሳድረው ተጽእኖ ከፍተኛ ነው፡፡ ስለዚህ “የጭንቀት ቀን ሳይመጣ በጉብዝናህ ወራት ፈጣሪህን ዐስብ” (መክ. ፲፪፥፩) አንዲል በወጣትነት ፈጣሪን መፈለግ ይገባል፡፡ ለዚህም ነው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልጆቿን ከሕፃንነት ጀምሮ በሰንበት ት/ቤት እንዲታቀፉ፣ የእግዚአብሔርንም ቃል እየተማሩ እንዲያድጉ የምታደርገው፡፡  

ማኅበረ ቅዱሳንም አገልግሎቱን በግቢ ጉባኤት ላይ በማተኮር ኦርቶዶክሳውያን ወጣቶች ላይ በመሥራት የድርሻውን እየተወጣ ይገኛል፡፡ ለተማሪዎች ከመደበኛ ትምህርታቸው በተጓዳኝ መንፈሳዊ ትምህርትን በማስተማር፣ ሕይወታቸውን እንዲፈትሹ፣ ውጤታማም ሆነው እንዲወጡና በኦርቶዶክሳዊ እምነታቸው እንዲጸኑ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋል፡፡

የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎችም የቀሰሙትን መንፈሳዊ ዕውቀትና ሕይወት ወደ ተግባር ለመለወጥ የሚረዳቸው ጊዜ ቢኖር በክረምቱ ወራት ትምህርት ተዘግቶ ወደ ቤተሰቦቻቸው ለዕረፍት ሲሄዱ ነው፡፡ በዚህ ወቅት የዕረፍት ጊዜያቸውን በአግባቡ ሊጠቀሙበት ይገባል፡፡ ዕረፍት ላይ መሆናቸው ሊያዘናጋቸው ስለሚችል አገልግሎቱ ላይ በማተኮር ራሳቸውን እንዲጠብቁ በአጥቢያቸው በሚገኝ ሰንበት ትምህርት ቤት ውስጥ በመሳተፍ እንደተሰጣቸውም ጸጋ ማገልገል፣ ዕውቀታቸውን ማካፈል፣ ለሌችም አርአያ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡  

ሌላው በክረምት ወቅት የግቢ ጉባኤት ተማሪዎች ሊያደርጉት የሚገባው በተለያዩ በጎ አድራጎት ሥራዎች ላይ በመሳተፍ በተሰጣቸው ዕውቀት፣ ገንዘብና ጉልበት የተቸገሩትን በመደገፍ ክርስቲያናዊ ግዴታቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ዕረፍት ላይ መሆናቸው በርካታ በጎ ሥራዎችን ለመሥራት ዕድሉን ይፈጥርላቸዋል፡፡ “ለሥራ ከመትጋት አትስነፉ፤ በመንፈስ ሕያዋን ሁኑ፤ ለእግዚአብሔር ተገዙ፤ በተስፋ ደስ ይበላችሁ፤ በመከራ ታገሡ፤ ለጸሎት ትጉ፡፡ በችግራቸው ቅዱሳንን ለመርዳት ተባበሩ፤ እንግዳ መቀበልንም አዘውትሩ” (ሮሜ. ፲፪፥፲፩-፲፬) በማለት እንደተነገረና ክረምቱ ምቹ ጊዜ በመሆኑ መትጋት ይገባል፡፡

የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች ሌላው በክረምት ወቅት ሊያደረጉት የሚገባቸው ነገር ቢኖር ለአብነት ትምህርት ትኩረት ሰጥተው ይማሩ ዘንድ ነው፡፡ አንዳንድ የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች የመደበኛ ትምህርቴን በደንብ እንዳልከታተል እንቅፋት ይሆንብኛል እያሉ በግቢ ጉባኤ ውስጥ የሚሰጠውን የአብነት ትምህርት ከመማር ችላ የሚሉ አሉ፡፡ ይህ አስተሳሰብ ግን  ጊዜን መድቦ በዕቅድ ራስን ካለመምራት ጋር የሚመነጭ በመሆኑ ሲሸሹ ይታያሉ፡፡  ነገር ግን አጠገባቸው ያሉት የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች ጊዜአቸውን በአግባቡ በመጠቀም የአብነት ትምህርትን በመማር ለክህነት ሲበቁ እንመለከታለን፡፡ ስለዚህ በመንፈሳዊው ሕይወት ራስን ለማሳደግና በጎደለው ቦታ በመሙላት ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል በአጥቢያቸው በሚገኝ ቤተ ክርስቲያን ወይም አቅራቢያቸው ባለ አብነት ትምህርት ቤት ገብተው መንፈሳዊውን ትምህርት መማር ይጠበቅባቸዋል፡፡

የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች በክረምቱ ሰፊ ጊዜ ስለሚኖራቸው ሳይዘናጉ ከሌሎች በጎ አድራጎት ሥራዎችና አገልግሎት በተጓዳኝ ለሚቀጥለው ዓመት ትምህርታቸው የሚያግዟቸውን መጻሕፍት በመመርመር ለአዲሱ ዓመት ትምህርት ራሳቸውን ማዘጋጀትም ይገባቸዋል፤ ካለ ንባብ የሚያሳልፉት ቀን ሊኖር አይገባምና፡፡

በአጠቃላይ በክረምት የዕረፍት ወቅት እንደመሆኑ በመዝናናትና በስንፍና በመመላለስ የገነቡትን መንፈሳዊ ሕይወት ችላ እንዳይሉ ጥንቃቄ በማድረግ ባላቸው ጊዜ ራሳቸውንና ሌሎችን በመርዳት ከበረከቱ እንዲሳተፉ ያስፈልጋል፡፡

ስብሐት ለእግዚአብሔር

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *