ከፊት ይልቅ ትጉ (፪ኛ.ጴጥ. ፩፥፲)

በመጋቤ ሃይማኖት መ/ር  ምትኩ አበራ

ይህንን ኃይለ ቃል የተናገረው ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ ነው፡፡ ኃይለ ቃሉን የምናገኘው ደግሞ በ፪ኛ ጴጥ.፩፥፭-፲፩ ላይ ነው፡፡ ሙሉው ንባብ እንዲህ ይላል፡- “… ስለዚህ ምክንያት ትጋትን ሁሉ እያሳያችሁ በእምነታችሁ በጎነትን ጨምሩ፤ በበጎነትም ዕውቀትን፤ በዕውቀትም ራስን መግዛት፤ ራስንም በመግዛት መጽናትን፤ በመጽናትም እግዚአብሔርን መምሰል፤ እግዚአብሔርንም በመምሰል የወንድማማችን መዋደድ፤ በወንድማማችም መዋደድ ፍቅርን ጨምሩ፤ እነዚህ ነገሮች ለእናንተ ሆነው ቢበዙ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ዕውቀት ሥራ ፈቶችና ፍሬ ቢሶች እንዳትሆኑ ያድርጉአችኋልና፡፡ እነዚህ ነገሮች የሌሉት ዕውር ነውና በቅርብ ያለውን ብቻ ያያል የቀደመውንም ኃጢአቱን መንጻት ረስቷል፡፡ ስለዚህ ወንድሞች ሆይ መጠራታችሁንና መመረጣችሁን ታጸኑ ዘንድ ከፊት ይልቅ ትጉ …”

ይህንን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በጥሞናና በእርጋታ ካነበብን በኋላ መልእክቱን በጥልቀት መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ርእሱን እናስተውል “ከፊት ይልቅ ትጉ” ነው የሚለው፡፡ እንደ እግዚአብሔር መልካም ፈቃድ በዚህ ርእስ ሦስት ነገሮችን ብቻ እናያለን፡፡ እነርሱም፡-

፩. ከፊት ይልቅ ትጉ የተባሉት እነማን ናቸው?

፪. ከፊት ይልቅ ትጉ የተባልንባቸው የትጋት አቅጣጫዎች ምንድናቸው?

፫. የተባልነውን በማድረጋችን የምናገኘው ምንድነው? የሚሉት ናቸው፡፡

፩. ከፊት ይልቅ ትጉ የተባሉት እነማን ናቸው?

ኃይለ ቃሉን በአስተውሎት ስንመለከተው ትጉ ብቻ ሳይል “ከፊት ይልቅ ትጉ” ነው የሚለው፡፡ ይህ ማለት ከትጋት በአፍአ ሆነው የሚያንቀላፉትንና በስንፍና ሰንሰለት ታስረው በተስፋ መቁረጥ ምንጣፍ የተኙትን አይመለከትም ማለት ነው፡፡ ይህ ማለት በትጋት ውስጥ ሆነው የአቅማቸውን እያከናወኑ ላሉት ትጉኀን ክርስቲያኖች የተነገረ ነው ማለት ነው፡፡ ሐዋርያው ትጋታቸውን ተቀብሎና አክብሮ ነው የሚጽፍላቸው ትጋታችሁ ጥሩ ነው፣ ግን ብቻውን በቂ አይደለም ይላቸዋል፡፡ አሁን በትጋታቸው ላይ ትጋትን እንዲጨምሩ ቀድሞ ከነበራቸው ትጋት በተጨማሪ የበለጠ እንዲተጉ ሲመክራቸው “ከፊት ይልቅ ትጉ” ይላቸዋል፡፡ ይህም ማለት ቀድሞ ይጾሙ፣ ይጸልዩ፣ ያገለግሉ ከነበረበት ትጋታቸው በተጨማሪ የበለጠ እንዲተጉ ይመክራቸዋል ማለት ነው፡፡

የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እኛስ እንዴት ነን? እየጾምን ነው? በጸሎታችንስ እንዴት ነን? የማያቋርጥ የዕለት ተዕለት ጸሎት ይኖረን ይሆን? እንዲያው ለመሆኑ ከፊት ይልቅ እየተጋን ነው? ወይስ ከነአካቴው በመንፈሳዊ አገልግሎታችን ዝለናል? ምላሹ የራሳችሁ ሆኖ ለራሳችሁ ነው፡፡ ይኼኔ እኮ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ከፊት ይልቅ ትጉ እያለ እንኳንስ ከፊት ይልቅ ልንተጋ መደበኛውንና የሚጠበቅብንን ክርስቲናዊ ግዴታችንን እና የአገልግሎት ድርሻችንን በአግባቡ መወጣት የተሳነን ሞልተናል፡፡ ብቻ ፈጣሪ ለሁላችንም ልቡና ይስጠን፡፡

፪. ከፊት ይልቅ ትጉ የተባልንባቸው የትጋት አቅጣጫዎች ምንድናቸው?

እጅግ የተወደዳችሁና የተከበራችሁ አንባብያን እስቲ አንድ ጊዜ ቀና በሉና ወደ መነሻ(መሪ) ምንባባችን ተመለሱ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በቁጥር ፲ ላይ “…መጠራታችሁንና መመረጣችሁን ተጸኑ ዘንድ ከፊት ይልቅ ትጉ…” ብሎ ከመጀመሩ በፊት ከላይ እንድናነባቸውና እንድንተጋባቸው የሚያስፈልጉ ዋና ዋና ጉዳዮችን በዝርዝር አስቀምጧል፡፡ እነዚህ ጉዳዮች ስምንት ሲሆኑ፤ እነርሱም፡-

፩. እምነት                           ፭. መጽናት

፪.በጎነት                              ፮. እግዚአብሔርን መምሰል

፫. ዕውቀት                           ፯. የወንድማማች መዋደድ

፬. ራስን መግዛት                 ፰. ፍቅር ናቸው፡፡

እያንዳንዱ ክርስቲያን እነዚህን ሰፍሮና ቆጥሮ ዘወትር በሕይወቱ ውስጥ እየፈለገ ምን አለኝ? ምንስ ይቀረኛል? በማለት በትጋት እያሰላ መኖር ይገባዋል፡፡

በአርባና በሰማኒያ ቀን ከሥላሴ የጸጋ ልጅነትን ገንዘብ ያደረገ አንድ ክርስቲያን በቅድሚያ እምነት ሊኖረው ግድ ነውና ሐዋርያው በእምነት ጀመረ፡፡ እምነት ወይም ሃይማኖት ስንል ልክ እንደ አንድ ሳንቲም ሁለት አስፈላጊ ገጽታዎችን የያዘ መሆኑን ማወቅና መረዳት ያስፈልጋል፡፡ እነሱም ማመንና መታመን ይባላሉ፡፡ አንድ ክርስቲያን ሃይማኖት ወይም እምነት አለኝ ሲል በፈጣሪዬ አምናለሁ እታመንማለሁ ማለቱ ነው፡፡ ማመን ማለት ለዚህች ዓለም ሠራዒ ወመጋቢ አላት ብሎ ማመን ሲሆን መታመን ማለት ደግሞ አለ ብለን ለምናምነው አምላክ መገዛት፣ እሺ በጀ ማለት በሕጉና በትእዛዙ መጓዝ ማለት ነው፡፡ በጥቅሉ ሃማኖትና ሥነ ምግባርን ይዞ መገኘት ማለት ነው፡፡

የአንድ ክርስቲያን እምነቱ በየጊዜው ያድጋል፡፡ ይህ ማለት የማመኑና የመታመኑ ጥበብ እየተረዳው (እየገባው) ሲመጣና ራሱን ለፈጣሪና ለሕጉ ማስገዛት ሲጀምር ማመኑና መታመኑም እየጨመረ ይሄዳል ማለት ነው፡፡ ለዚህ ነው ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ “ስለዚህ ምክንያት ትጋትን ሁሉ እያሳያችሁ በእምነታችሁ በጎነትን ጨምሩ፣ …” ብሎ ከእምነት የጀመረው፡፡ ሰው አማኝ ሆኖ የበጎነት ድርቅ ካጠቃው ደግሞ ዋጋ የለውም፡፡ አንዳንድ ሰዎች ለምሳሌ በአጽዋማት ጊዜ ውሎ ቅዳሴ እያስቀደሱ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ይህ እኔ የምቆምበት ቦታዬ ነው እያሉ በቦታ የሚጣሉ ከሆነ እምነታቸው በውስጡ በጎነትና ቅንነት ይጎድለዋል ማለት ነው፡፡

አንዳንዱ ደግሞ በጎነት ይኖረውና በጎነቱ ግን ያለ ዕውቀት ሆኖ ይጎዳዋል፡፡ ለምሳሌ አንዳንድ ሰዎች በበጎነታቸው ገንዘባቸውንና ዕውቀታቸውን የቤተ ክርስቲያንን እምነትና ሥርዓት ለማፍረስ ለቆሙ መናፍቃንና የውስጥ ጠላቶች ሲያውሉ ይታያል፡፡ ባለማወቅ የረዱ እየመሰላቸው ማለት ነው፡፡ በረከታቸው ይድረሰንና በአንድ ወቅት የድሬዳዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ “ሃይማኖት ያለ ዕውቀት ጅልነት ነው፤ ዕውቀት ያለ ሃይማኖት እብደት ነው” ይሉ ነበር፡፡ ስለዚህ ነው ሐዋርያው “በእምነታችሁ ላይ ዕውቀትን ጨምሩበት” ያለው፡፡

በዕውቀት ላይ ደግሞ ራስን መግዛት እንድንጨምር ታዘናል፡፡ ምክንያቱም በራስ መግዛት መሪ ያልተዘወረ ዕውቀት የዲያብሎስ ዕውቀት ነው፤ ያስታብያል፣ ወደ እንጦሮጦስም ያስወርዳል፡፡ በራስ መግዛት ላይ መጽናትን ጨምሩበት ካላ በኋላ እንደገና በመጽናት ላይ እግዚአብሔርን መምሰል ጨምሩበት ይለናል፡፡ አንዳንድ ሰዎች “እኔ እግዚአብሔርን ብሆን ኖሮ እንዲህና እንዲያ አደርግ ነበር” እያሉ ሲዝቱ ይስተዋላል፡፡ እግዚአብሔርን መሆን ለመፍለጥና ለመቁረጥ ወይም ለማጥፋትና ለመቅሰፍ ብቻ የሚመስላቸው ናቸው፡፡ ግን እኮ እግዚአብሔርን መሆን ውስጥ በጥፊ መመታትና መሰቀል መሸከምም አለ፡፡ ኧረ እንደውም “የማያውቁትን ያደርጋሉና ይቅር በላቸው” ማለትም አለበት፡፡ እንግዲህ እግዚአብሔርን መምሰል ማለት ሆደ ሰፊ፣ ነገር አላፊ፣ ይቅር ባይ፣ ቻይና ታጋሽ መሆን ስለ ሌሎች ራስን አሳልፎ መስጠት ማለት መሆኑን ልብ ልንል ያስፈልጋል፡፡ እስኪ ቆም ብለን ራሳችንን እንመርምር፡፡

ሐዋርያው አላበቃም እግዚአብሔርን በመምሰል ላይ የወንድማማች መዋደድን ጨምሩበት ማለትም የሰፈሬ፣ የመንደሬ፣ የእናትና አባቴ … ከሚለው የወጣ የመጀመሪያውን ሰው አዳምን መሠረት ያደረገ ወንድማማችነትን ገንዘብ አድርጉ ማለቱ ነው፡፡ በዚህ የወንድማማች መዋደድ ላይ ፍቅርን ጨምሩ ይለናል፡፡ ፍቅር ምንድነው? ፍቅር እግዚአብሔር ነው፡፡ እግዚአብሔርን ምስክር ያደረገ ከሸፍጥና ከጨለማ ሥራ የጸዳ፣ ፍቅርን ያዙ ሲለን ነው፡፡ አንድም ፍቅር በቅዱስ ጳውሎስ አስተምህሮ (፩ኛቆሮ. ፲፫) የሚታገሰውን፣ የማይቀናውን፣ የማይመካውን፣ የማይታበየውን፣ የማይበሳጨውን፣ ከእውነት ጋር ደስ የሚለውን ቸርነት የሚያደርገውን፣ … ንጹሑን ፍቅር ገንዘብ አድርጉ ይለናል፡፡

የተወደዳችሁ አንባብያን እነዚህን ከላይ የተዘረዘሩትን ስምንቱን ዋና ዋና ቁም ነገሮች ሁል ጊዜ በሕይወታችን ውስጥ እንፈልጋቸው፤ ጨምሩ እየተባልን አንዱን ይዘን ለሌላው እንድንተጋ ታዘናል፡፡ እስኪ ቆም ብለን እናስብ፡፡ በእያንዳንዳችን ሕይወት ከስምንቱ ስንቱ አሉ? ስንቱን ይዘን ስንቱ ይቀረናል? እነዚህ የክርስትናችን ትጋት አቅጣጫዎች ናቸው፡፡ እነዚህ የመንፈሳዊ አገልግሎታችን ማኅቶታት(መብራቶች) ናቸው፡፡ ስለዚህ ዘወትር በትጋት እንፈልጋቸው፡፡ አንዱን በአንዱ ላይ ለመጨመር እንትጋ ፈጣሪያችን መትጋትን ያድለን ዘንድ ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን፡፡

. የተባልነውን በማደረጋችን የምናገኘው ምንድነው?

የተወደዳችሁና የተከበራችሁ አንባብያን እንግዲህ ከላይ እንዳስቀመጥነው ስምንቱን የትጋት አቅጣጫቻዎቻችንን ተከትለን ባለን የቀድሞ ትጋታችን ላይ እነዚህን ገንዘብ ለማድረግ ዘወትር በትጋት ላይ ትጋት እያሳየን ከቀጠልን ምን እንደምናተርፍ ሐዋርያው በአጭር አገላለጥ አስቀምጦልናል፡፡ እንዲህ ሲል “እነዚህ ነገሮች ለእናንተ ሆነው ቢበዙ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ዕውቀት ሥራ ፈቶችና ፍሬ ቢሶች እንዳትሆኑ ያደርጓችኋልና”(ቁ.፰)፡፡

እነዚህ ከላይ የተጠቀሱትን ስምንቱን ቁም ነገሮች እየጨመርንና እያበዛን ከሄድን ሥራ ፈቶችና ፍሬ ቢሶች እንደማንሆን በግልጽ ቋንቋ ነግሮናል፡፡ ሥራ ፈትና ፍሬ ቢስ የሚሉት ቃላቶች ሁለት ቢሆኑም ግን አንድ ናቸው፡፡ አንዱ አንዱን ይስበዋል፤ ማለትም ሰው ሥራ ፈት ሲሆን ነው ፍሬ ቢስ የሚሆነው፡፡ ፍሬ ያለ ሥራ እንደማይገኝ ሁሉ ፍሬ ቢስነትም ያለ ሥራ ፈትነት አይኖርም፡፡

ሥራ ፈትነት በሁለቱም ዓለማት ከባድ ቢሆንም በተለይ በመንፈሳዊው ዓለም ትንሽ ለየት ይላል፡፡ “ሥራ የፈታ አእምሮ የሰይጣን ቤተ ሙከራ ይሆናል” የሚል አባባል አለ፡፡ በማቴዎስ ወንጌል ምዕ.፲፪ ላይ እርኩስ መንፈስ ከሰው እንደሚወጣ (ማውጣት እንደሚቻል) ይነግረንና በዚያው ምዕራፍ ላይ “ተመልሶ ይመጣል” ይለናል፡፡ ይህንን የሐዲስ ኪዳን መተርጉማን ሲያብራሩት ከወጣ በኋላ ተመልሶ የማደር ሥልጣን የለውም ዳሩ ግን ማሰቡ አይቀርም፡፡ ሲያስብ ግን ያ ሰው ከጾም ከጸሎት በአፉ ሆኖ ከመንፈሳዊ ሕይወቱ ከመልካም ሥራው ተዘናግቶ(ተታሎ) ቢያገኘው፡- እንዲህ ይለናል፡፡ “…ወደወጣሁበት ቤቴ እመለሳለሁ ይላል ቢመጣም ባዶ ሆኖ ተጠርጎና አጊጦ ያገኘዋል፤ ከዚያ ወዲያ ይሄድና ከእርሱ የክፉትን ሰባት ሌሎችን አጋንንት ከእርሱ ጋር ይወሰዳል፤  ገብተው በዚያ ይኖራሉ፡፡ ለዚያ ሰው ከፊተኛው ይልቅ የኋለኛው ይብስበታል …” (ማቴ.፲፪፥፵፬-፵፭)፡፡

እንግዲህ ልብ አድርጉ የሥራ ፈት አእምሮ ለሰይጣን የተጠረገና ያጌጠ ቤቱ መሆኑን እየነገረን ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሥራ ፈቶች ብዙ ይነግረናል፡፡ ሥራ ፈቶች የራሳቸውን ነፍስ ከማስኮነን አልፈው ለሌሎች ሰዎችም ጭምር አዋኪዎች ናቸው፡፡ አይሁድ እንኳን በአቅማቸው የሚፈልጉትን ተንኮል ከግብ ለማድረስ ሥራ ፈቶችን ይጠቀሙባቸው ነበር፡፡ ለምሳሌ በአንድ ወቅት ሐዋርያው ጳውሎስን በተቃወሙት ጊዜ እነዚህኑ ሥራ ፈቶች እንደተጠቀሙባቸው  መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡ “… አይሁድ ግን ቀንተው ከሥራ ፈቶች ክፉ ሰዎችን አመጡ፣ ሕዝቡንም ሰብሰው ከተማውን አወኩ” (ግ.ሐዋ.፲፯፥፭)፡፡

በዚህ በሥጋዊው ዓለም እንኳን ክፉ ሰዎች የክፋታቸውን ጥግ ለመግለጥና ለማሳየት በፈለጉ ጊዜ የሚጠቀሙባቸው እነዚህኑ ሥራ ፈቶችን ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ ዓለምም ቢሆን በተቻለን መጠን ሥራ ፈት ላለመሆን መትጋት አለብን፡፡ ሥራ ማለት ከቀጣሪው አካል የምንታደለው ብቻ ግን አይደለም፡፡ ራሳችን ለራሳችን ሥራ ልንሰጠው ይገባል፡፡ ለምሳሌ ቅዱሳት መጻሕፍትን ማነበብ፣ መጠየቅ፣ ለመረዳት መጣር ገዳማትንና አድባራትን እየሄዱ እጅ መንሳት፣ ማስቀደስ፣ በሰርክና በልዩ ልዩ የቤተ ክርስቲያን ታላላቅ የስብከተ ወንጌል መርሐ ግብራት ላይ እየተገኙ መማር በሰንበት ት/ቤትና በመንፈሳዊ ማኅበራት ውስጥ ማገልገል … ወዘተ፡፡

የተወደዳችሁ አንባብያን ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ከላይ ያስቀመጣቸውን ስምንት ቁም ነገሮች በመሰብሰብ ከተጠመዳችሁ ሥራ ፈቶችና ፍሬ ቢሶች አትሆኑም ብሎናል፡፡ ሥራ ፈቶችና ፍሬ ቢሶች ካልሆንን ደግሞ የሰይጣን መፈንጫ አንሆንም ማለት ነው፡፡ እንዲህ ከሆንን ደግሞ በመጨረሻ ጊዜ በኃጥአን ሊፈርድባቸው፣ ለጻድቃን ሊፈረድላቸው የሚመጣው አምላካችን “ሑሩ እምኔየ ሳይሁን ንዑ ሀቤየ ቡሩካኑ ለአቡዬ፤ እናንት የአባቴ ቡሩካን ኑ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ያዘጋጀሁላችሁን መንግሥተ ሰማያትን ውረሱ” ይለናል፡፡ ይህ እንዲሆን ግን ከፊት ይልቅ እንትጋ፡፡

ትጉኁ አምላካችን ትጋቱን ያድለን ዘንድ ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን፡፡ አሜን፡፡

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *