“ከፊት ይልቅ ትጉ”(፪ኛ ጴጥ.፩፥፲)

በቀሲስ ኃይለሚካኤል ብርሃኑ

የወጣትነት የዕድሜ ክልል ብርቱ አቅማችን ተጠቅመን ከሌላው ጊዜ በተሻለ ብዙ ሥራ የምንሠራበት ወቅት  ነው፡፡  ትጋት  ለክርስቲያናዊ ሕይወት አስፈላጊ ነው፡፡  ምክንያቱም በክርስትና እምነታችን ዕለት ዕለት በጎ ተግባራትንና ትሩፋትን በመሥራት ኑኖአችን እግዚአብሔርን ማክበር ስለሚገባ ነው፡፡

በተለይም የወጣትነት ዕድሜ ክልል አብዝቶ በመጋደል መንፈሳዊ  ሩጫችንን ለማፋጠን አመቺ  ነው፡፡  በዚያው ልክ  ደግሞ  በወጣትነት ጊዜ  በራስ ሕዋሳት  መፈተንና  መጥፎ የሆነ ስሜታዊነት የሚያይልበት ወቅት ስለሆነ ፈቃደ ሥጋን ለፈቃደ  ነፍስ  በማስገዛት በሕገ   እግዚአብሔር   ተገዝቶ   መኖር   ያስልጋል፡፡ ይህ   ለሕገ እግዚአብሔር መገዛት ለሁሉም ነው፡፡ ማለትም ሕፃን፣ ወጣት፣ ሽማግሌ የማይል መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡ ነገር ግን ወጣትነት ከላይ የጠቀስናቸው ፈተናዎች የሚበረቱበት  ስለሆነ ለይተን አቀረብን እንጂ፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ  ጴጥሮስ  “ከፊት  ይልቅ  ትጉ”  ብሎ  ምክሩን  የለገሰበትን ምክንያት ዘርዝሮታል፡፡ እነሱም ለመረዳት መልእክቱን ቃል በቃል መመልከተ አስፈላጊ ነው፡፡

“እናንተ ግን በሥራ ሁሉ እየተጋችሁ በእምነት በጎነትን፣ በበጎነትም ዕውቀትን፣ ጨምሩ፣ በዕውቀትም ንጽሕናን፣ በንጽሕናም ትዕግሥትን፣ በትዕግሥትም እግዚአብሔርን ማምለክን እግዚአብሔርን በማምለክ ወንድማማችነትን፣ በወንድማማችነት ፍቅርን ጨምሩ እነዚህ ነገሮች ለእናንተ ሆነው ቢበዙ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በማወቅ ሥራ ፈቶችና ፍሬ ቢሶች እንዳትሆኑ ያደርጓችኋልና፡፡ እነዚህ ነገሮች የሌሉት ዕውር ነውና በቅርብ ያለውን ብቻ ያያል የቀደመውንም የኃጢአቱን መንጻት ረስቷል፡፡ ስለዚህ ወንድሞች ሆይ መጠራታችሁንና መመረጣችሁን ታጸኑ ዘንድ ከፊት ይልቅ ትጉ እነዚህን ብታደርጉ ከቶ አትሰናከሉም፡፡ እንዲሁ ወደ ዘለዓለሙ ወደ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መንግሥት መግባት በምልዐት ይሰጣችኋል” (፪ኛጴጥ.፩፥፭-፲፭) በማለት ሰፋ አድርጎ በመንፈሳዊ ሕይወታቸን በአገልግሎት እንተጋ ዘንድ ያስፈለገበትን ምክንያት ዘርዝሮታል፡፡

በመሆኑም ከላይ የተነሣንበትን ኃይለ ቃል ስንመለከት “እናንተ ግን በሥራ ሁሉ እየተጋችሁ “የሚል ነው፡፡ በሥራ ሁሉ ሲል መንፈሳዊ በሆነ ሥራ (አገልግሎት) መሳተፍን ይጠቁማል፡፡ ይህም መንፈሳዊ ሥራ ወይም አገልግሎት እንደተሰጠን ጸጋ መጠን የሚገለጥ ነው፡፡ የፀጋ ሥጦታ ልዩ ልዩ እንደሆነ አውቀን በተቀመጥንበት የአገልግሎት መስክ ለአእምሮ የሚመቸውን አገልግሎት  መፈጸም  ነው፡፡  ምንም  እንኳ  ወጣቶች  በውርዝውና  ዕድሜ  ላይ  እያለን ሕዋሳቶቻችን ፈቃደ ሥጋን ለመፈጸም የሚፈልጉበትወቅት  ቢሆንም  በዚህ ውብ በሆነና ለአገልግሎት ስኬት   አመቺ   በሆነው ወጣትነታችን   ሰውነታችን ለእግዚአብሔር ክብር (አገልግሎት) እንዲውል ማድረግ እጅግ ማስተዋል ነው፡፡ ለዚህም ነው፤ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ   ለሮሜ   ክርስቲያኖች   በላከላቸው   መልእከቱ   “ወንድሞቻችን   ሰውነታችሁን ለእግዚአብሔር ሕያውና ቅዱስ ደስ የሚያሰኝም መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኀራኄ እማልዳችኋለሁ፡፡ ይህም በዕውቀት የሚሆን አገልግሎታችሁ ነው፡፡ ይህን ዓለም አትምሰሉ ልባችሁንም አድሱ እግዚአብሔር የሚወደውን መልካሙንና እውነቱን መርምሩ (ሮሜ. ፲፪፥፩) እንዲል፡፡

ሐዋርያው እንደመሰከረው ሰውነትን ቅዱስና ሕያው ደስም የሚያሰኝ መሥዋዕት አድርጎ ማቅረብ ማለት እግዚአብሔር ራሱን በገለጠልን መጠን ስለ እርሱ ማወቅ ነው፡፡ ይህም በእምነት ሆነን እግዚአብሔር እኛ ከምናውቀው ከዕውቀታችን በላይ (ከአእምሮ በላይ) ምጡቅ ባሕርይው የማይመረመርና ማንም ሊደርስበት የማይችል መሆኑን ተረድተን ባወቅነው ልክ እንደ አቅማችን እሱን የምናገለግልበት አገልግሎት ነው፡፡ እሱም ሁሉም እንደ አቅሙ በተለያየ ፀጋ እግዚአብሔርን እንዲያገልግል ተጠርቷል፡፡

ይህው ሐዋርያ በጻፈው መልእክቱ “በተሰጠኝ በእግዚአብሔር ፀጋ ሁላችሁም እንዳትታበዩ እነግራችኋለሁ ራሳችሁን ከዝሙት የምታነጹበትን አስቡ እንጂ በትዕቢት አታስቡ ሁሉም እንደ እምነቱ መጠን እግዚአብሔር እንዳለው ይኑር፡፡ በአንዱ ሰውነታችን ብዙ የአካል ክፍሎች እንዳሉ ሥራውም ልዩ ልዩ እንደሆነ እንዲሁ ሁላችንም ብዙዎች ስንሆን በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ አካል ነን፡፡ እርስ በእርሳችን እያንዳንዳችን የሌላው አካሎች ነን፡፡ ስጦታውም ልዩ ልዩ ነው፡፡ እግዚአብሔርም በሰጠን ፀጋ መጠን ልዩ ልዩ ስጦታ አለን፡፡ ትንቢት የሚናገር  እንደ እምነቱ መጠን ይናገር የሚያገለግልም በማገልገሉ ይትጋ የሚያስተምርም በማስተማሩ ይትጋ የሚመክርም  በመምከሩ  ይትጋ  የሚሰጥ  በልግስና  ይስጥ  የሚገዛም  በትጋት  ይግዛ የሚመጸውትም በደስታ ይመጽውት (ሮሜ.፲፪፥፫) በማለት ሁሉም በተሰጠው ፀጋ ሊተጋ እንደሚገባ ያስረዳል፡፡

በመሆኑም የወጣትነት ጊዜ በአገለግሎት አብልጠን የምንተጋበት ወቅት ነው፡፡ ምክንያቱም ወጣትነት ጉልበቱ፣ ዕውቀቱ፣ ችግርን ተቋቁሞ ማለፍና በመሰደድም ሆነ  በብዙ  ሮጦ ማገልገል የሚቻልበት ስለሆነ ነው፡፡ ስለዚህ ልዩ ልዩ በሆነ ፀጋ ሥጦታ እግዚአብሔር እያንዳንዳችን ሾሞናል፡፡ ይህንንም ፀጋ ያገኘነው ከእርሱ በተወለድንበት ዳግም ልደት ነው፡፡

ከእርሱ ከተወለድን ዘንድ ደግሞ የእርሱ ፀጋ በእኛ ላይ አለ፡፡ ያን የጸጋ ስጦታችንን በትጋት እንድንፈጽም ያስፈልጋል፡፡ በወጣትነትም ጸጋ እግዚአብሔር በዝቶአልን ከሌላው ጊዜ በተሻለ የምናገለግልበት ወቅት በመሆኑ ራሳችንን ለቃሉ ማስገዛት ያስፈልጋል፡፡ ትጋታችንም ከሌላው ጊዜ በተሻለ ሊሆን ይገባል፡፡ ምክንያቱም ወጣትነት የሕይወታችን ዋነኛው ክፍል ስለሆነ በመንፈሳዊ ሕይወት ልንጠነክር ይገባል፡፡

ለዚህም ነው ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በመልእክቱ መግቢያ እንደተመለከትነው “እናንተ ግን በሥራው ሁሉ እየተጋችሁ” በማለት ማድረግ የሚገባንን ነገር በመጥቀስ ሲዘረዝር በመጀመሪያ በእምነት በጎነትን ጨምሩ ይላል፡፡

“በእምነት ጎነትን ጨምሩ”

እምነት የሁሉ መሠረት እንደሆነ ቅዱሳት መጻሕፍት ያስረዳሉ፡፡ ይሁን እንጂ እምነት በጎነት ሊጨምርበት ይገባል፡፡ ለዚህም ነው አብርሃም በእግዚአብሔር አምኖ በቤቱ በበጎነት እንግዶችን በመቀበል  የተራቡትን  የተጠሙትን  በመመገብ  እምነቱነ  በበጎ  ሥራ  ይገልጥ  የነበረው እምነቱም  ጽድቅ  ሆኖ  ተቆጠረለት  እንዳለው  እምነታችን  የሚታወቀው  በበጎነት  ሥራ ሲገለጥ ነው፡፡ እርሱም የመጀመሪያ የበጎ ሥራ መጀመሪያ ለእግዚአብሔር መታዘዝ ነው፡፡ “አብርሃም በእግዚአብሔር አመነ እምነቱም ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረለት (ገላ.፫፥፮) እንዲል፡፡

አብርሃም እግዚአብሔርን አምኖ ከሀገሩ ከዘመዶቹ ከቤተሰቡ መካከል ተለይቶ መውጣቱ በእግዚአብሔር መታመኑ (ማመኑ) ነው፡፡ በጎነትንም ለማሳየት የቻለው በእምነቱ ስለሆነ በእምነቱ በጎነትን ጨመረ፡፡ እኛም በእምነታችን ላይ በጎነትን ችግረኛ መርዳትን ድሆችን መመገብን  ለሰው  በጎ  ነገር  ማድረግን  ልናበዛ  ይገባል፡፡  “መልካም  ሥራ  ለራስ  ነው” እንደሚባለው ሁሉ እግዚአብሔርን የምናይበት እመነታችን(ሃይማኖታችን)   በበጎነታችን በምንሠራው መልካም ሥራ ሊገለጥ ወይም ሊታይ ያስፈልጋል፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ እንዳስተማረን ክርስቲያናዊ ሕይወታችን ከትናንትና ይልቅ ዛሬ ላይ በትጋት በምንፈጽመው አገልግሎት ማደግ ይኖርበታል የዛሬ ትጋታችንም እንዲሁ ጨምሮ እግዚአብሔር ቢፈቅድ መንፈሳዊ ፍሬአችን የተሻለ ሆኖ መታየት ይኖርበታልና በሁሉ ነገር መትጋት አለብን፡፡ አምላከ ቅዱሳን ልዑል እግዚአብሔር ትጋቱን ማስተዋሉን ለሁላችን ያድለን

አሜን፡፡ ይቆየን..

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *