ከኦርቶዶክሳዊ ወጣት ምን እንጠብቅ?

ዲ/ን ታደለ ፈንታው(ዶ/ር)

ክፍል አንድ

 

ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖታችን የደም ዋጋ ተከፍሎበት፤ ተፈትኖ፣ ነጥሮ፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ ተሸጋግሮ በቅብብሎሽ የመጣ እውነተኛ ሃይማኖት ነው፡፡ የዓለማውያን ፍልስፍና፣ ተረት ተረት፣ ድርሰትም፣ የታዋቂ ሰዎች ድንገተኛ ፈጠራም አይደለም፡፡

ቤተ ክርስቲያን በክርስቶስ ደም ላይ ተመሥርታለች እና ተጠብቃ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንድትሸጋገርም ወጣቶች የከፈሉት ዋጋ ደማቅ በሆነ በደም ቀለም በቤተ ክርስቲያናችን ቅዱሳት መጻሕፍት የተመዘገበ ነወ፡፡ እንደ ምሳሌም ሊቀ ዲያቆናት ቅዱስ እስጢፋኖስን ማንሣት እንችላለን፡፡ ራሱን ለእግዚአብሔር አሳልፎ በመስጠቱ አይሁድ በድንጋይ ሲወግሩት ሰማያት ተከፍተው የእግዚአብሔርን ዙፋን እስከ ማየት አድርሶታል፤ ምሥጢርም ተገልጦለታልና አቤቱ ይህን ኃጢአት አትቁጠርባቸው” እስከ ማለት አደረሰው፡፡ የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም ወጣቶች አርአያ ሊያደርጉት ይገባል፡፡ (ሐዋ. ፯፥፶፬-፷)

ከአባቶቻችን፣ ከእናቶቻችን  የተቀበልነውን ይህንን የደም ዋጋ የተከፈለበትን  እውነተኛ ሃይማኖት እንደ ወጣት በምንኖርበት ዘመን የመጠበቅ፣ የመከላከል፣ የብዙዎች መዳንን የሚሹ፣ በእውነተኛው መንገድ ለመጓዝ የፈቀዱ ሰዎችን እንዲያውቁት፣ እንዲገነዘቡት፣ በሥጋቸውም በነፍሳቸውም እንዲጠቀሙበት ማድረግ የአንድ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ተከታይ ወጣት የሃይማኖት ግዴታ ነው፡፡ እምነታችንም የሚገለጠው ዕለት ዕለት በማኅበረሰቡ መካከል ስንመላለስ በምናሳየው የማይለዋወጥ ባህርይጥሩ ሥነ ምግባር አማካኝነት ነው፡፡ የእኛ ጽናት፣ አቋም፣ ጥንካሬ፣ መንፈሳዊ ሕይወት የሃይማኖታችንን እውነተኛነት ይገልጣል፡፡ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታይ የክርስቶስ መልክ የሚታይበት ሰው ነው፡፡ በክርስቶስም የእግዚአብሔር መልክ በእርሱ ላይ ታትሟልና፡፡

በምንኖርበት ሉላዊ ምድር በዓለም ላይ እንደሚኖር ሰው ተግዳሮቶች አሉብን፡፡ እኒህ ተግዳሮቶች ታስበው ታቅደው እንደሚሠሩ ሁሉ ሰው በመሆናችን፣ ሉላዊውን ዓለም በመጋራታችን  ጭምር የሚመጡ እንጂ ክርስቲያን በመሆናችን ምክንያት ብቻ ተለይተው የሚመጡ አይደሉም፡፡ ክርስትናን ለመቃወም ታስበውም ሆነ ሳይታሰቡ የሚወጡ አፋኝ ሕጎች፤ የሉላዊነት ተጽእኖ፣ ኤችአይቪ ኤድስና ሌሎች ተላላፊ በሽታዎች፤ ድህነት፣ የደኅንነት ስጋት፣ ዘረኝነት፣ ያልተስተካከለ እና ሕይወትን የማያሻሽል መሠረቱን አገር በቀል እውቀትን ያላደረገ የተኮረጀ ትምህርት እና የመሳሰሉት ተግዳሮቶች ለአብነት ይጠቀሳሉ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ በገላትያ መልእክቱ ሲያስተምር እንዲህ ብሏል፡- “እናንተ ለአርነት ተጠርታችኋልና ፤ ብቻ አርነታችሁ ለሥጋ ምክንያትን አይስጥ፤ ነገር ግን በፍቅር እርስ በርሳችሁ እንደ ባሪያዎች ሁኑ፤ ሕግ ሁሉ በአንድ ቃል ይፈጸማልና እርሱም ባልንጀራህን እንደራስህ አድርገህ ውደድ የሚል ነው፡፡  ነገር ግን እርስ በርሳችሁ ብትነካከሱና  ብትበላሉ እርስ በርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተጠንቀቁ፡፡” እንዲል(ገላ 5፡13)

ፍቅር የእምነታችን እና ጽናታችን መሠረት

እንደ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አማኝ ተከታይ የእምነታችን ታላቅነት የሚገለጠው ለሌሎች በሚኖረን ፍቅር እና አክብሮት ላይ ነው፡፡ ሕግ ሁሉ በሁለት ምሰሶዎች ላይ የቆመ ነው፡፡ እነርሱም ፍቅረ እግዚአብሔር እና ፍቅረ ቢጽ(የወንድም ፍቅር) ናቸው፡፡ ሰው የሚመለከተውን ወንድሙን፣ የሚመለከታትን እኅቱን የማይወድ ከሆነ የማይመለከተውንና ያላየውን እግዚአብሔርን መውደድ እንደምን ይቻለዋል? ስለዚህ ፍቅራችን በሰው እና በእግዚአብሔር መካከል የቆመች እውነተኛ የሃይማኖታችን መገለጫ ምልክት ናት፡፡ እኛም እውነተኛ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደመሆናችን፤ በቅዱሳት መጻሕፍትም መሠረትነት ላይ ልንጓዝ ግድ ይለናል፡፡

የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መገለጫው ፍቅር ደስታ፣ ሰላም፣ ቸርነት በጎነት  የዋህት፣ ራስን መግዛት(ገላ. ፭፥፳፪) እንጂ ዝሙት ርኩሰት ፣ መዳራት፣፣ ጣዖትን ማምለክ ምዋርት፣ ጥል፣ ክርክር፣ ቅንዓት፣ ቁጣ አድመኛነት፣ መለያየት፣ መናፍቅነት፣ ምቀኝነት መግደል ስካር ዘፋኝነት (ገላ. ፭፥፳) አይደለምና በቀደሙ በአባቶቻችን የፍቅር መንገድ እንጓዝ፡፡

መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “መልካሙን ሥራችሁን ተመልክተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን ያመሰግኑ ዘንድ ብርሃናችሁ በሰው ሁሉ እንዲሁ ይብራ” እንዳለ(ማቴ ፭፥፲፫) ከውኃና ከመንፈስ ዳግም ስንወለድ ሀብተ ጸጋ ሀብተ ልጅነት ሆነው የተሰጡን መንፈሳውያን ሀብቶቻችን ይገለጡ ዘንድ ብርሃናችን  በዓለሙ ሁሉ ይብራ፡፡ እነዚህም አስቀድመን የገለጥናቸው ናቸው፡፡ ፍቅር የእግዚአብሔር ገንዘብ ነው፡፡ ፍቅር እግዚአብሔርን የምናውቅበት ፍኖት ነው፡፡

ፍቅር እግዚአብሔር የፈጠረውን ፍጥረት፣ ሰው፣ እንስሳ ሳንል የምንወድበት መሳሪያ ነው፡፡ ፍቅር ተፈጥሮአችንን የምናድስበት ነው፡፡ ፍቅር ጉድለታችንን የምንሞላበት መዝገብ ነው፡፡ ፍቅር የተጣመመን ሰብእና የምናርቅበት መዶሻ ነው፡፡ ፍቅርን ተከትለው የሚመጡ ሌሎች ሀብታት አሉ እንጂ ፍቅር ብቻውን የሚመጣ አይደለም፡፡ ፍቅር፡– ሰላምን፣ ደስታን ያስከትላል፡፡ ርኅራኄ እና ለጋስነት ያጅቡታል፡፡ ፍቅር ማደሪያውን ትሕትናን እና ራስን መግዛትን ያደርጋል፡፡

እንደ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት አማኝ የሚጠበቅብን ብዙ ነገር አለ፡- አስቀድመን በገለጽናቸው መንፈሳዊ ሀብታት መኖር እና ማደግ ዕድገታችንም ዕለት በዕለት ያለ ድካም፣ ያለ ፍርሃት፣ የሚጨምር ሊሆን ይገባዋል፡፡ እነዚህን ሀብታት ሳንታክት ገንዘብ ልናደርጋቸው የሚገቡ ጠቃሚ ሀብታት ናቸው፡፡ በእነዚህ ሀብታት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንደተናገረ ክርስቶስን እንለብሰዋለን፡፡ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደሶችም ተብለን በእውነት ልንጠራ የተገባን እንሆናለን፡፡

ሌሎች ሊኖሩን የሚገቡ ዕሤተ ምግባራት

እንደ ክርስቲያን በሕዝብ እና በአሕዛብ መካከል የምንመላስ የክርስቶስን እውነት የምንመሰክር ደምቀን የምንታይ አጥቢያ ኮከቦች ነን፡፡ አጥቢያ ኮከብ ደምቆ፣ ፈክቶ እና አብርቶ ስለሚኖር ለሁሉ እንደሚታይ እውነተኛ ክርስቲያንም በሰው ሁሉ ፊት የተገለጠ ነው፡፡ የበለጠ ደምቀን እንድንታይ የሚያደርጉን ኦርቶዶክሳዊ ዕሤተ ምግባራት አሉ፡ እነርሱም፡- አርምሞ፣ ሥርዓት፣ ሰላማዊ ኑሮ፣ ዕውቀት፣ ማስተዋል፤ በሕዝብ ተገብቶ ራስን አሳልፎ መስጠት፣ ከግለኝነት መጽዳት፣ በሰዎች ጉዳይ ጣልቃ አለመግባት፣ እና እኒህን የመሳሰሉ ናቸው፡፡ ልንታገሳቸው የማይገቡንም ነገሮች አሉ፡፡ እነርሱም፡- ሞራል ማጣት፣ የነፍስን ቅድስና ገንዘብ አለማድረግ፤ ጣዖትን ማምለክ፣ ጥንቆላ እና ተያያዥ ተግባራትን መውደድ፣ ምቀኝነትን አለመጥላት፣ ጠብንና አምባጓሮን መውደድ፣ ከቁጣ ነጻ አለመሆን፣ በተሰጠን ነገር አለመርካት፣ ራሳችንን ከሌሎች ጋር ማነጻጸር እና የመሳሰሉት ናቸው፡፡ አስቀድመን የዘረዘርናቸውን ነገሮች የምንጠላቸው በሥጋችን ሥቃይን የሚጨምሩብን በነፍሳችንም የሚያስጎዱን እንጂ የሚጠቅሙን ባለመሆናቸው ነው፡፡

በእውነት  መንገድ የሚኖር ኦርቶዶክሳዊ ወጣት፡-

በምንመራው ኦርቶዶክሳዊ እውነተኛ ኑሮ ሕይወትን በተወሳሰበ እና ለዓለም በሚመች መልኩ ማድረግ ጣጣው ብዙ ነው፡፡ እኛ እንድንኖር የተፈቀደልን ሕይወት ጸሎት ያጀበው ሕይወት፣ የፍቅር ሕይወት፣ ለጎረቤቶቻችን ለወንድሞቻችንና እኅቶቻችን መልካም ነገርን የማድረግ ሕይወት ከምንም በላይ ለነፍሳችን ድኅነት የሚጠቅመንን ሥራ የመሥራት ሕይወት ነው፡፡ ንቁ ሆነን፣ አለባሰሳችን እንደ ሃይማታችን ሥርዓት ሆኖ፣ ለጸሎት የነቃን፣ የታጠቅን መሆን ይኖርብናል፡፡ እግዚአብሔር አምላክን በቃልም ቢሆን በተግባርም ቢሆን በኀልዮም ቢሆን የሠራነውን ኃጢአት ይቅር ይለን ዘንድ መትጋት ይጠበቅብናል፡፡ እግዚአብሔር ዘወትር በሥራው ከእኛ ጋር ይሆን ዘንድ ይህ የአንድ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ተከታይ የዘወትር ጸሎት ነው፡፡ መሻቱም፣ ፈቃዱም ፣ ውዱም ሁሉም ተጠቅሎ ያለው በዚያ ውስጥ ነው፡፡ መነሻውም መድረሻውም የጸሎት እና የምስጋና ሕይወት ነው፡፡

በዚህ መንገድ የሚኖር ኦርቶዶክሳዊ ወጣት፡- ሕይወቱ ለአንድ የተስተካከለ እና ጤናማ ሕብረተሰብ መኖር ምሰሶ ነው፡፡ የማኅበረሰብ ፍትኅ፣ ደስታ እና ሰላም የሚጠበቀውም በእንዲህ ዓይነት መንገድ አልፈው ማኅበረሰቡን በሚያገለግሉ ወጣቶች እንጂ አፈ ጮሌዎች ፣ ስግብግቦች እና ነገር አዋቂዎች አይደለም፡፡ እንዲህ ዓይነት እዩኝ እዩኝ የሚሉ ከንቱ ሰዎች  ማኅበረሰብን መርተው ወደሚፈልገው ዕድገት  አያሻግሩም፡፡

ሀብት አስፈላጊ ቢሆንም ኦርቶዶክስ ክርስቲያን የሚኖረው ሀብት ለማግበስበስ፣ ሌሎችን ለመቀማት ወይም ለማስቀናት አይደለም፡፡ ሀብትን ከፈለግነው በአባቶቻችን በእናቶቻችን መንገድ በርግጥ በእውነት እና በቅንነት ብንመላለስ   የሚመጣ እንጂ የሚርቅ ነገር አይደለም፡፡ ቅዱስ መጽሐፍ በመጀመሪያ ጽድቁን እና መንግሥቱን ሹ፤ ሥጋን ለሥጋ ነገር ማለማመድ ለአሁኑ ጊዜ ይጠቅማል፤ ሥጋን ለመንፈሳዊ ነገር ማለማመድ ለአሁኑ ጊዜ ለሚመጣውም ጊዜ ይጠቅማል ይላል፡፡

የሚገጥመን ተግዳሮት

         በመንፈሳዊ ልምምድ ሳለን የሚገጥመን ተግዳሮት ቀላል አይደለም፡፡ ጠላታችን ዙሪያችንን ይዞራል፡፡ ወጥመዱን ይዘረጋል፡፡ የአጋንንትን ትምህርት በሚያስተምሩ ሰዎች ልባችንን ለመክፈል እንዲሠሩ ያደርጋል፡፡ ነገሮች ለእነርሱ አልጋ በአልጋ ሲሆኑ ለጊዜው ሁሉም ነገረ የተሳካላቸው አስመስሎ፤ የሌለ ነገር እንዳለ አድርጎ ማሣየት የአጋንንት ተግባር ነው፡፡ ከእውነተኛው ሃይማኖታችን ለማስወጣት የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም፡፡ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታይ በመሆናችን ሃይማኖታችንን የድኅነት ምንጭ፣ ስብከታችንንም ከንቱ አድርጎ ሊስል ይዳዳዋል፡፡ በእምነት የቀደሙንን ቅዱሳን፤ አሠረ ፍኖት ትተውልን የሄዱ ዋኖቻችንን ድካም ከንቱ ድካም አድርጎ ለመሳል የማይሄድበት ርቀት የለም፡፡ ረብህ የሌላቸውም ምናምንቴ ሰዎች በገበያ እና በፕሮሞሽን ወደፊት አውጥቶ ሰዎች እንዲከተሏቸው ያደርጋል፡፡ የዲያብሎስ ወጥመዱ ብዙ ነው፡፡

የቅዱስ ጳውሎስ ምክር “በቃልና በኑሮ በፍቅርም  በእምነትም በንጽሕናም ለሚያምኑት ምሳሌ ሁን እንጂ  ማንም ታናሽነትህን አይናቀው፤ እስክመጣ ድረስ ለማንበብና ለመምከር ለማስተማርም ተጠንቀቅ፡፤( ፩ኛ ጢሞ. ፬፥፲፪) የሚል ነው፡፡ ፍቅራችን፣ ራስን መግዛታችን   በቃልም በኑሮም ከተገለጠ የወጣትነት ሕይወታችን እጅግ ጣፋጭ፣ ተወዳጅ እና ፍሬ የሚያፈራ ይሆናል፡፡ በእንዲህ ዓይነት የተቀደሰ ሕይወት ስንመላለስ ፈተና ቢገጥመን  ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እኛ ሲል የተቀበላቸው በርከት ያሉ መከራዎችን እናስብ፡፡ እርሱን በመልበሳችን ምክንያት ወደ እኛ የመጡ መከራዎች መሆናቸውን በማሰብ ዕለት ዕለት በፈተና እንጸና ዘንድ ሳናቋርጥ እንጸልይ፡፡  ጸሎታችንም መንፈሳዊ  ድፍረትን፣ ጥበብን ፣ ማስተዋልን፣ ሰላምን፣ ትዕግሥትን፣ ፍቅርን፣ ትሕትናን በጎ ጤንነትን፣ ሀብትን፣ ረጅም የአገልግሎት ዕድሜን ይሰጠን ዘንድ ነው፡፡ ይቆየን፡፡

 

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *