ከእግዚብሔር ጋር መሆን
…በዳዊት አብርሃም…
አንድ ክርስቲያን ከሁሉ አስቀድሞ ከእግዚአብሔር ጋር ለመሆን ማቀድ ይኖርበታል፡፡ ይህም የተሳካ መንፈሳዊ ሕይወት እንዲኖረው ያስችለዋል፡፡ የተሳካ መንፈሳዊ ሕይወት ደግሞ ለስኬታማ ምድራዊ ሕይወት መሠረት ነው፡፡ ስለዚህ የሚከተሉትን ነጥቦች በመመልከት ለመተግበር መጣር ያስፈልጋል፡፡
- ጸሎት
“ወደፈተና እንዳትገቡ ተግታችሁ ጸልዩ፡፡” ተብለን በተመከርነው መሠረት በግል፣ በቤተሰብና በማኅበር በያንዳንዷ ሥራችን መጀመሪያና መጨረሻ እንዲሁም በማዕድ ስንቀመጥ ልንጸልይ ይገባል፡፡ ጸሎት ከእግዚአብሔርም ጋር የምንሆንበት ዋነኛው መንገድ ነው፡፡ እግዚብሔርም ከእኛ ጋር የሚንሆንበት ዋነኛው መንገድ ነው፡፡ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ደግሞ ሁሉም ነገር ይከናወንልናልና፡፡ ሌላው ቀርቶ እግዚአብሔር ከርሱ ጋር መሆኑን ማሳብና ማመን የቻለ ሰው ይህን በማሰቡ ብቻ ከፍርሐት ነፃ ይሆናል፡፡ ሰላማዊ መንፈስም ይኖረዋል፡፡
- ቅዱሳት መጻሕፍትን ማንበብ
አንድ የቤተ ክርስቲያን አባት እንዲህ ብሏል፡፡ “ጸሎት ስጸልይ የራሴን አሳብ ለአምላክ እነግራለሁ፤ ቅዱሳት መጻሕፍትን ሳነብ ግን እግዚአብሔር ለእኔ ሲነግረኝ እሰማለሁ፡፡” ለተሳካ ሕይወት ሰው ከሚሰጠን ምክር ይልቅ ከእግዚብሔር የምናገኘው የበለጠ አስተማማኝ ነው። እርሱ የፈጠረን ስለሆነ ለኑሯችን የሚያስፈልገንንም ከእኛ ይልቅ እርሱ ያውቃልና የእርሱን ቃል ማስተዋል ተገቢ ነው፡፡ “ሕግህ ለእግሬ መብራት ለመንገዴ ብርሃን ነው፡፡” /መዝ.118/119፥1ዐ5/ እንደተባለው የወደፊቱን ለማያውቀው የሰው ልጅ የእግዚአብሔር ቃል ብቸኛው መሪ ነው፡፡ ራሱ መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል የስኬት ቁልፍ መሆኑን ሲገልጽ እንዲህ ይላል፡፡ “የዚህን ሕግ መጽሐፍ ከአፍህ አትለይ፤ ነገር ግን የተጻፈበትን ሁሉ ትጠብቅና ታደርግ ዘንድ በቀንም በሌሊትም አስበው፤ የዚያን ጊዜም መንገድህ ይቀናልሀል ይከናወንልሀልም፡፡” (ኢያሱ.1፥8 )
- የንስሐ አባት
ለመንፈሳዊ ሕይወትህ ማደግ ከካህናት አባቶች ጋር መመካከር አስፈላጊ ነው፡፡ ስለሆነም አንድ ካህን በንስሐ አባትነት ሊኖርህና ከርሱም ጋር በቋሚነት እየተገናኝህ ምክር ልትቀበል ይገባሀል፡፡ የንስሐ አባትህ ስሕተትህን እንድታርም ከመምከር ጋር ስላለፈው በደልህ ይቅርታን ያሰጥሀል፡፡ የወደፊት ሕይወትህም የተሳካ እንዲሆን በጸሎቱ ያስብሀል፡፡
- መንፈሳዊ መርሐ ግብር መከታተል
በቤተ ክርስቲያን የሚኖሩ የጸሎት፣ የአምልኮና የትምህርት መርሐ ግብራትን ሁሌም መከታተል ከእግዚአብሔር ጋር ለሚኖር ሕይወት በጣም አስፈላጊ ስለሆነ አለማስታጎል ይመከራል፡፡
- መንፈሳዊ ንቃት
በመንፈሳዊ ሕይወት መዛል፣ ወይም በፈተና መታወክ እንደሚገጥም በማወቅ እያንዳንዱን ቀን በንቃት ማሳለፍ ሌላው አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ ፈታኛችን ዲያብሎስ ሁሌም እንደማይተኛ ማወቅ፣ ይህ ዓለምም በመከራው ብቻ ሳይሆን በምቾትም ሊያዘናጋን እንደሚችል መገንዘብ ነቅተን ለመጠበቅ የሚያነሳሱን ምክንያቶች ናቸው፡፡ እንዲሁም መንቃት በጥፋታችን ሳንሳነፍ፤ በውድቀታችን ተስፋ ሳንቆርጥ በንስሐ መመላለስንም ይጨምራል፡፡
- መንፈሳዊ ከባቢ መፍጠር
ከላይ ከተገለጹት ምክሮች በተጨማሪ በምታነበው ነገር፣ በውሎህና በጓደኞችህም ምርጫ ላይ መንፈሳዊውን መንገድ በመከተል የራስህን መንፈሳዊ ከባቢ መፍጠር ትችላለህ፡፡ ይህም አስደሳች ሕይወት ይፈጥርልሀል፡፡
- አገልግሎት
ማገልገል የስኬታማ ሰው መገለጫ ነው፡፡ እንዲሁም ማገልገል ለተሻለ ስኬት ያበቃል፡፡ በየትኛውም ደረጃ ላይ ቢሆን የማያገለግል ሰው ተሳክቶለታል ሊባል አይችልም፡፡ ምክንያቱም የስኬት መለኪያው ለሌሎች ሰዎች የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ነው፡፡ ሌሎች ካንተ ያገኙት ጥቅም፣ ደስታ፣ ሰላም መፍትሔ ያንተ የስኬታማ ሕይወት መመዘኛው ነው፡፡ ስለዚህ ራስህ ላይ ብቻ ማተኮርህን ትተህ ሌሎችን ለመርዳት በተሰጠህ ጸጋ ወደ አገልግሎት ተሠማራ፡፡ ስታገለግልም መጀመር ያለብህ ከቤተሰብህ ነው፡፡ ቀጥሎም በትምህርት ቤት በሥራ ቦታ ለሌሎች ጥሩ አርአያነት ያለው ሕይወት በማሳየት አገልግሎትህን ቀጥል፡፡ አገልግሎትህን በማስፋትም ወደ ቤተ ክርበስቲያን በመምጣት ከሌሎች ወንድሞችና እኅቶች ጋር በመተጋገዝና በመታዘዝ ማገልገልን በተግባር መለማመድ ለስኬታማ ሕይወትህ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡