ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በዓመት ሁለት ጊዜያት እንዲሆን በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ ፭ ቁጥር ፻፷፬ በተደነገገው መሠረት ምልዓተ ጉባኤው የመክፈቻው ሥርዓተ ጸሎት ከተፈጸመበት ከግንቦት ፲፯ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ግንቦት ፳ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. ድረስ የተለመደውን ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባ ሲያካሂድ ሰንብቶ ለቤተ ክርስቲያናችንና ለሀገራችን የሚበጁ ማህበራዊና መንፈሳዊ ውሳኔዎችን አሳልፎአል፡፡
በዚሁ መሠረት፡-
፩. የ፳፻፲፫ ዓ.ም. ግንቦት ርክበ ካህናት የጉባኤ መክፈቻ በአገራችን ወቅታዊ ሁኔታዎች ማለትም፡-
ስለ አገር ደኅንነትና ስለ ሕዝቦች አንድነት፣
ከቄያቸው ስለተፈናቀሉና ለስደት ስለተዳረጉ ወገኖች፣
በተለያዩ አካባቢዎች እየታዩ ስለአሉ አለመግባባቶች የሚያመላክት እና ይህንንም በመግባባት በውይይት በይቅርታ መፍታት እንደሚገባ ከሁሉም በላይ ወደ እግዚአብሔር በመጸለይ ምሕረት መጠየቅ እንደሚያስፈልግ የሚገልጽ በመሆኑ ጉባኤው ተቀብሎ በተግባር ላይ እንዲውል ተስማምቷል፡፡
፪. አገራዊ ሰላምን አስመልክቶ ጉባኤው በስፋት ከተነጋገረ በኋላ በአገራችን በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠሩ ግጭቶች ምክንያት የጠፋው የሰው ሕይወት የታረዱና ከቄያቸው የተፈናቀሉ ወገኖች በችግሩ ምክንያት የወደመ ንብረት በዓይነትና በቁጥር ተለይቶ በየአህጉረ ስብከቱ ተጣርቶ እንዲቀርብ ተወስኗል፡፡
፫. የቤተ ክርስቲያን የአምልኮ ሥፍራ ስምና እስከዛሬ ተጠብቆ የቆየ ክብሯ እንዲሁም በካህናትና በምእመናን ላይ እየደረሰ ያለ ሞት፣ ስደት የመሳሰለው ከየአህጉረ ስብከቱ ተጣርቶ ሪፖሪት እንዲቀርብ መንግሥትም አስፈላጊውን ጥበቃ እንዲያደርግ ጉባኤው አሳስቧል፡፡
፬. ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በአገራችን የነበረውንና የቆየውን ታሪካዊ ሂደት ለመቀየር በዚህም አጋጣሚ የኖረውንና ዓለም የሚያውቀውን በዓለም አቀፍ ደረጃ በዩኒስኮ የተመዘገበ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመስቀል አደባባይና የባሕረ ጥምቀት ቦታዎች እንዲሁም የአምልኮ ሥፍራዎችን ምክንያት በመፍጠር አንዳንድ ወገኖች የግጭትና የትንኮሳ ተግባር እየፈጸሙ መሆኑ ጉባኤውን በእጅጉ አሳዝኗል፡፡
በመሆኑም ይህ በቤተ ክርስቲያናችን ስም የቆየው የዘመናት ታሪክ አገራዊ ታሪክ ተደርጐ ልዩ ጥበቃና ክብካቤ ሊደረግለት ስለሚገባ አሁንም መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት የኖረው የቤተ ክርስቲያኒቱና የአገሪቱ ታሪክ ክብሩ ከነማንነቱ ተጠብቆ እንዲኖር የበኩሉን እንዲወጣ ቅዱስ ሲኖዶስ በአጽንኦት አሳስቧል፡፡
፭. አገራችን ኢትዮጵያ በዘመናት ታሪኳ እንደሚታወቀው ዳር ድንበሯን ጠብቃና አስጠብቃ ያለ ቅኝ ግዛት ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት በአገር ወዳድ መሪዎቿ አንድነቷን ጠብቃ የቆየች መሆኗ አለም የሚያውቀው ነው፡፡ ይሁን እንጂ በአሁኑ ጊዜ አንዳንድ የውጭ አገራት ከሩቅና ከቅርብ ግንባር በመፍጠር በአገራችን ሕልውና ላይ እያደረጉት ያለው ጣልቃ ገብነት፣
– አገራዊ የመልማት ፍላጐታችንን ለመግታት
– ዳር ድንበራችንን ለመድፈር እያደረጉ ያለውን ሙከራ ጐረቤት አገራት ጭምር በጠላትነት እንዲነሳሱብን እያደረጉ ያለው ቅስቀሳ ተዘዋዋሪ ቅኝ ግዛት በመሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስ ተቃውሞአል፡፡ ሕዝባችንም ከምንጊዜውም በተለየ መልኩ አገራዊ አንድነቱን በመጠበቅ አገሪቱን ከውጭ ወራሪ በመከላከል አገራዊ ልማትን በማፋጠን የበኩሉን እንዲወጣ ጉባኤው ጥሪውን አቅርቧል፡፡
፮. አገራችን ኢትዮጵያ በልማት እንድታድግ ሌሎች አገራት ከደረሱበት ደረጃ ለማድረስ በዚህም ዜጐችን ከጨለማ ወደ ብርሃን ለማውጣት ታስቦ እየተገነባ ያለው ህዳሴ ግድባችን ወደ መጨረሻው ምዕራፍ እየተቃረበ እና ለኢትዮጵያውያን ሁሉ የአንድነታችን ማሳያ እየሆነ በመምጣቱ አሁንም ለግንባታው ፍጻሜ መላው ኢትዮጵያ እንዲረባረብ ጉባኤው ጥሪውን አቅርቧል፡፡
፯. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዘመናት ታሪኳ የአብያተ ክርስቲያናትን አፀድ በመትከል አረንጓዴ ልምላሜን በማስፋፋት ጠብቃ የቆየች ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ደግሞ መንግሥታችን በየዓመቱ በቢሊየን የሚቆጠር ችግኝ ተከላ መርሐ-ግብር ማዘጋጀቱ ለአየር ጥበቃና በምግብ ራስን ለመቻል እየተደረገ ያለው አገራዊ ጥረት የሚደገፍ በመሆኑ በዘንድሮውም የችግኝ ተከላ መርሐ-ግብር መላው ዜጋ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጉባኤው አሳስቧል፡፡
፰. ከአንድ ዓመት በፊት በመላው ዓለም ተከስቶ ብዙዎችን ለሕልፈተ ሕይወት የዳረገው ኮቪድ 19 ተላላፊ በሽታ በአሁኑ ጊዜ በአገራችን በመስፋፋቱ ብዙዎች ወገኖቻችን ለሞት እየዳረገ የሚገኝ በመሆኑ መላው ሕዝባችን ከምንግዜውም በበለጠ በአሁኑ ጊዜ ከጤና ባለሙያዎች የሚሰጠውን ምክረ ሐሳብ በመቀበል ራሱን ከወረርሽኑ እንዲጠብቅ ጉባኤው አሳስቧል፣
፱. በአገራችን በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠረው አለመግባባት ምክንያት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ያለመጠለያ የሚገኙ እና በዚሁ ተላላፊ በሽታ ምክንያት ችግር ላይ የወደቁ ወገኖቻችንን በተለመደውና በኖረው የመረዳዳትና የመተሳሰብ ባሕላችን ከምንግዜው በላይ አሁን ለችግራቸው እንድንደርስላቸው ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪውን አቅርቧል፡፡
፲. አገራችን ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ በሽግግር ላይ የምትገኝ በቀጣይም ሕዝባዊ ምርጫ ለማካሄድ በከፍተኛ ዝግጅት ላይ መሆኗ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም ገዥው ፓርቲም ሆነ ተፎካካሪዎች ለአገራችንና ለሕዝባችን የሚጠቅመውን ሰላማዊ መንገድ እንዲከተሉ መላው ሕዝባችንም ለአገርና ለወገን ይጠቅማሉ የሚባሉትን በመምረጥ ሁሉም አካል ውጤቱን በፀጋ በመቀበል ኢትዮጵያዊ ጨዋነትን የምናስመሰክርበት ምርጫ እንዲሆን ጉባኤው የሰላም ጥሪውን አቅርቧል፡፡
፲፩. በምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት በጐንቻ ሲሶ እነሴ ወረዳ በምስካበ ቅዱሳን ቆጋ ኪዳነምሕረት በሕገ-ወጥ መንገድ ዶግማና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን በጣሰ መልኩ ራሳቸውን በራሳቸው ጳጳስና ፓትርያርክ አድርገው የሾሙ፡-
፩. መምህር ሄኖክ ፈንታ
፪. መምህር አባ ኪዳነማርያም
፫. መሪጌታ ሙሉ
ከግንቦት ፲፱ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. ጀምሮ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ተወግዘዋል፡፡ የገዳሙንም ሀብትና ንብረት አስረክበው ከገዳሙ እንዲወጡ ተወስኗል፡፡ የዚህ ተባባሪ የነበሩ መነኮሳት ካህናትና ዲያቆናትም የተወገዙ ሲሆን በዚህ የዶግማና የቀኖና ጥሰት ምክንያት በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ተሳስተው ድጋፍ ሲሰጡና ሲከተሏቸው የነበሩ ምእመናን ንስሐ እየገቡ ይቅርታ እንዲደረግላቸው ጉባኤው ወስኗል፡፡
፲፪. በአሁኑ ጊዜ በአገራችን ኢትዮጵያ እየታየ ያለው፡-
– የርስ በርስ አለመግባባት እንዲቆም፣
– ሞትና ስደት እንዲያበቃ ፣
– ተላላፊ በሽታ ከምድራችን ጠፍቶ ሰዎች በጤንነት እንዲኖሩ፣
– መጪው አገራዊ ምርጫ በኢትዮጵያ ጨዋነት በአንድነትና በሰላም እንዲጠናቀቅ፣
ለዚሁ ሁሉን ቻይና ሁሉን አድራጊ የሰላም አምላክ እግዚአብሔር አገራችንና ሕዝባችንን በሰላምና በምሕረቱ እንዲጐበኝ ሁላችንንም ይቅር እንዲለን ከአሁን ጀምሮ በግልም ሆነ በማኅበር ጸሎት በማድረግና ችግረኞችን በመርዳት እንድንተባበር ሆኖ ከምርጫው ሰኔ ፲፬ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ሐምሌ ፬ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. ድረስ በመላው አገራችንና በውጭም ባለችው ቤተ ክርስቲያን ጸሎተ ምሕላ እንዲደረግ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡
በመጨረሻም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ከግንቦት ፲፯ እስከ ግንቦት ፳፫ ለስድስት ቀናት ሲያካሂድ የቆየውን ጉባኤ አጠናቆ በጸሎት ዘግቷል፡፡
እግዚአብሔር አገራችንን ኢትዮጵያንና ሕዝባችንን ይጠብቅ፡፡
ግንቦት ፳፫ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም.
አዲስ አበባ
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!