“ከተራ”

በመ/ር ኃይለ ሚካኤል ብርሃኑ

የከተራ በዓል የሚከበረው ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ የጥምቀት በዓል አንድ ቀን ሲቀረው በዋዜማው ነው፡፡ ይህም ከጌታችን መድኀኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የጥምቀት በዓል አከባበር የሚጀምረው ሁል ጊዜ ጥር ፲ ቀን የከተራን በዓል ከማክበር ነው፡፡ በዚህ ዕለት ታቦታቱ ወደ ተዘጋጀላቸው የማደሪያ ቦታ በልዩ ድምቀት በዝማሬ ታጅበው ይወጣሉ፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለመጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ የመሄዱም ምሳሌ ነው፡፡

“ያን ጊዜ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ በዮሐንስ ሊጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መጣ ዮሐንስ ግን እኔ በአንተ ልጠመቅ እሻለሁ አንተ ወደ እኔ ትመጣለህን? ብሎ አይሆንም አለው፡፡ ጌታችን ኢየሱስም መልሶ አሁንስ ተው እንዲህ ጽድቅን ሁሉ ልንፈጽም ይገባናልና አለው …”(ማቴ፫፥፲፫) በማለት የኢየሱስ ክርስቶስን ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መሄድ ይገልጻል፡፡ በመሆኑም የበዓሉ ዋዜማ ከተራ በዓል ተብሎ በጾም ታስቦ የታቦታቱን መውጣትና ወደ ማደሪያቸው የመሄድ ሥርዓት በድምቀት የሚከበርበት ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ሥርዓት ነው፡፡

“ከተራ” የሚለው ቃል “ከተረ ከበበ ካለው የግዕዝ ግስ የወጣ ሲሆን ፍቺው ውኃ መከተር፣  መገደብ ማቆም፣ ማገድ፣ መከልከል” ማለት ነው፡፡ ከላይ እንደገለጽነው የጥምቀት ዋዜማ ታቦተ ሕጉ ከቤተ መቅደስ ወጥቶ ውኃ ባለበት አካባቢ ስለሚያድር የየአጥቢያው ሕዝብ እየተሰበሰበ በወንዝ ዳር ወይም በምንጭ አካባቢ ድንኳን ይተከላል፡፡  ድንኳንም  ከሌለ  ዳስ  ሲጥል  ይውላል፡፡  የምንጮች  ውኃ  ደካማ  በመሆኑ እንዲጠራቀም ይከተራል፡፡

ይህም በየዓመቱ ጥር ፲ ቀን የምእመናኑ አብዛኛው ሥራ ውኃውን መከተርና መገደብ በመሆኑ ዕለቱ ከተራ የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ ውኃው የሚከተረው በማግሥቱ ጥር ፲፩ ቀን የጥምቀት በዓል ስለሚከበር ለሕዝቡ መጠመቂያ እንዲሆን ነው፡፡ በየሰበካው ቦታ ተለይቶና ተከልሎ ታቦታቱ በዳስ ወይም በድንኳን የሚያድሩበት፣ የተለያዩ የውኃ አካላት ተጠርገው የሚከተሩበት ወይም ሰው ሠራሽ የግድብ ውኃ የሚበጅበት ስፍራ ‹‹ባሕረ ጥምቀት››፣ ‹‹የታቦት ማደርያ›› እየተባለ ይጠራልና ለዚህ ሥርዓት መፈጸም አስቀድሞ በዋዜማ የሚደረግ ዝግጅት ነው፡፡ ከበዓለ ጥምቀቱ ረድዔት በረከት ይክፈለን አሜን፡፡

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *