“ከሰማይ ከወረደው የሰው ልጅ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለም፡፡” (ዮሐ. ፫፥፲፫)
በዳዊት
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ድኅነት በራሱ ፈቃድ፣ በአባቱም ፈቃድ፣ በመንፈስ ቅዱስም ፈቃድ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም የነሣውን የሰውን ልጅ ሥጋ ተዋሕዶ(አምላክነቱ ሳይለወጥ ፍጹም ሰው ሆኖ) በምድር ተመላልሷል። በሥጋ ማርያም ተገልጦ በምድር በነበረበት ጊዜ እውነተኛውን መንገድ አስተምሯል፣ መርቷል፤ ድውያነ ሥጋን በተአምራቱ፣ ድውያነ ነፍስን በትምህርቱ ፈውሷል፤ ዓይነ ሥውራንን አብርቷል፤ ሽባውን ተርትሯል፤ ጎባጣውን አቅንቷል፤ ሥርዓተ ወንጌልን ሠርቷል፤ ከኃጢአት በቀር ፍጹም ሰው ሆኖ ተመላልሷል።
ጌታችን ወደ ምድር የመጣበትና በምድር ላይ ይመላለስ በነበረበት ወቅት የነበሩ መሠረታዊ ዓላማዎች የጠፉትን የአዳምን ልጆች ፈልጎ ወደ እቅፉ ማስገባት፣ በበደል ምክንያት ከእግዚአብሔር ተለይቶ የነበረን የሰውን ማንነት ከእግዚአብሔር(ከራሱ) ጋር ማስታረቅ፣ በበደል ምክንያት ወደ ዓለም የገባውን የዲያብሎስ ማሰሪያ ለዘለዓለሙ ቆርጦ መጣል፣ በሔዋን ምክንያት ተዘግቶ የነበረን የገነት በር መክፈት፣ በሰው ልጆች ሁሉ ተፈርዶ የነበረን ሞት በሞቱ ድል አድርጎ መሻር፣ በሲዖል ተግዘው በጨለማ የነበሩትን በነፍሱ ወደ ሲዖል በመውረድ በርብሮ ማውጣት ዋነኞቹ ነበሩ። እነዚህንም ሁሉ ፍቅር ስቦት በመዋዕለ ሥጋዌው በአምላክነቱ ሥልጣን ሁሉንም ፈጽሟቸዋል።

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአምላክነቱ ሞትን ድል አድርጎ በሦስተኛው ቀን ከሙታን መካከል በኵር ሆኖ ከተነሣ በኋላ ለሐዋርያቱና ለሚወዱት ሁሉ እየተገለጠ ትንሣኤውን በገሃድ ሲያስረዳ፣ መጽሐፈ ኪዳንን፣ የመጻሕፍትን ምሥጢር፣ ሕግጋትንና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ሲያስተምራቸው ለ፵ ቀናት በምድር ቆይቷል። ከዚህም በኋላ ደቀ መዛሙርቱን “እስከ ቢታንያም ወደ ውጭ አወጣቸው፤ እጁንም አንሥቶ በላያቸውም ጭኖ ባረካቸው። እየባረካቸውም ራቃቸው፤ ወደ ሰማይም ዐረገ።”(ሉቃ. ፳፬፥፶-፶፩)
ዕርገት “ዐርገ፣ ከፍ ከፍ አለ፣ ከታች ወደ ላይ ወጣ፣ ዐረገ” ካለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ሲሆን “ዕርገት፣ መውጣት፣ ከፍ ከፍ ማለት፣ ማረግ” ማለት ነው።(መዝገበ ቃላት ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ገጽ ፯፻፰) ዕርገት ለጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲነገር ምሥጢሩ ብዙ ነው፤ በተወዳጅ ሐዋርያው ከሰማይ የወረደው ተብሎ የተነገረለት መድኃኔዓለም ማንም ሳያየው ከሰማይ ወርዶ ብዙዎች እያዩት ከትንሣኤው በኋላ በ፵ኛው ቀን ወደ ቀደመ ክብሩ በርቀት ያይደለ በርኅቀት ዐርጓል። ወደ ሰማይ መውጣቱ ማረጉ የታመነ የሆነው ጌታ አስቀድሞ ስለመውረዱ የተነገረለት፣ የታወቀለት ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም “…ወደ ሰማይ የወጣው የወረደው እንደሆነ ዕወቅ…” በማለት በሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ የተነገረውን ያጠነክራል።(ዮሐ አፈ. ክፍ ፳፫፥፳፯)
ጌታችን ከሰማይ የወረደው ንጽሐ ባሕርይው በበደል ምክንያት አድፎበት በግድ ከገነት ወደ ምድር የወረደውን አዳምን ከወደቀበት ሊያነሣው ከወጣበት ሊመልሰው ነው፤ ለዚህም የሰውን ሥጋ ተዋሕዶ ከኃጢአት በቀር ፍጹም ሰው ሆነ፤ ያለመቀላቀል ያለመጠፋት ሥጋና ለመለኮትበመዋሐዳቸው ምክንያት ዐረገ ተብሎ ተነገረለት እንጂ መለኮትስ በሁሉ የሚገኝ በሁሉ የመላ(ምልዑ) ነው። ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት “እግዚአብሔር በእልልታ ጌታችንም በመለከት ድምፅ ዐረገ” (መዝ. ፵፮፥፯) በማለት ያረገው መለኮት በሥጋ ተዋሕዶ አንድ ባሕርይ የሆነ እግዚአብሔር ወልድ እንደሆነ ይመሰክራል።
ቅዱስ ሉቃስም በወንጌሉ “እየባረካቸውም ራቃቸው፤ ወደ ሰማይም ዐረገ።” በማለት የገለጠው በኃጢአት ምክንያት ድቀት አጋጥሞት የነበረ ሥጋ በተዋሕዶተ ቃል ማረጉን ሲናገር “ራቃቸው” አለ፤ ራሱ እግዚአብሔር መሆኑን ሲገልጥም እንደ ሌሎቹ መላእክት እንዳሳረገቸው ሳይሆን ራሱ በሥልጣኑ “ዐረገ” በማለት ያረገው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ የሆነ እንደሆነ ገለጠ፡፡ ክብር ምስጋና ይግባውና የዮሴፍ ልጅ ነው ብለው ለካዱት ለአይሁድም የእግዚአብሔር ልጅ እግዚአብሔር መሆኑን በመመስከር “ከሰማይ ከወረደው የሰው ልጅ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለም” ካለው ከሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ጋር ተባበረ።
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመጣጡ ወደ ምድር መውረዱ በትሕትና ነበር፤ ሲያርግ ግን በልዕልና ነበርና “ዐርገ በስብሐት፤ በምስጋና ዐረገ” እንላለን። መውረዱን በትሕትና ባደረገባት ገሊላ ዕርገቱንም ከሠላሳ ሦስት ዓመታት በኋላ በዚሁ በገሊላ በልዕልና፣ በስብሐት፣ በዕልልታ አድርጎባታልና።
ስለዚህ እኛም ዕርገቱን መሠረተ ሃይማኖታችን በሆነው ጸሎተ ሃይማኖት ”በክብር በምስጋና ወደ ሰማይ ዐረገ በአባቱም ቀኝ ተቀመጠ” ብለን ዘወትር እንጸልያለን፤ እንመሰክራለንም። አሁንም ከሊቁ ከአባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ጋር “አሁንም ከኛ ጋር በዓልን እንዲያደርጉ አባቶችን እንጥራቸው። ከሁሉ በፊት አዳምን እንጥራው፤ እነሆ እግዚአብሔር ከገነት በወጣህ ጊዜ ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ ያለው ተፈጸመ፤ እግዚአብሔር ሥጋን ከሴት ልጅህ ለበሰ፤ በአባቱም ቀኝ በሰማያት ተቀመጠ፤ ይህን የወደድኸውን አምላክነት ከሴት ልጅህ በተወለደ በመለኮት ሰው መሆን አገኘኸው እንበለው። የሕያዋን እናታቸው ስለሆንሽ ሕይወት የተባልሽ ሔዋን ሆይ በሴትልጅሽ ደስ ትሰኚ ዘንድ ነዪ፤ ሕይወትን አምጥተሻልና፤ በታተመ አፈ ማኅፀኗ የወለደችው እርሱ በረከትን ካገኙደቀ መዛሙርቱ ጋር ቆማ እያየችው ወደ ሰማያዊው አባቱ ዐረገ” (መጽሐፈ ምሥ. ፳፰፥፲፬) እያልን እናክብር እናመስግን! ከበዓለ ዕርገቱ ረድኤት በረከት ያሳትፈን!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!
ምንጭ፦ መጽሐፍ ቅዱስ፤ መጽሐፈ ምሥጢር፤ ተንከተም (በሊቀ ሊቃውንት ስምዐ ኮነ)
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!