“ከሰማይ ከወረደው የሰው ልጅ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለም” (ዮሐ.፫፥፲፫)
በቀሲስ ኃይለሚካኤል ብርሃኑ
ቃሉን የተናገረው ለስም አጠራሩ ክብር ምስጋና ይድረሰውና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ አንዳንዶች ይህንን ቃል ለምን እንደተነገረና ምን ማለት እንደሆነ ባለመረዳት ሲሰነካከሉበት ይስተዋላል፡፡ ለስህተታቸውም እንደ ማስረጃ ለመጠቀም ይሞክራሉ፡፡ በተለይ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ዕርገት ሲነሣ የሚረብሻቸው የዲያብሎስ የግብር ልጆች ከሞት አልተነሣችም አላረገችም ለማለት ሲጠቀሙበት ይታያል፡፡ ነገር ግን ይህ ቃል እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እና ሌሎችም ቅዱሳን ስለ ማረጋቸው የሚያስረዳ እንጂ አለማረጋቸውን የሚገልጽ አይደለም፡፡ ነገር ግን የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ዕርገት ከሌሎቹ የሚለይ መሆኑን የሚያስገነዝብ ነው፡፡
ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ፡- “ዐርገ እግዚአብሔር በይባቤ፣ወእግዚእነ በቃለ ቀርን፣ ዘምሩ ለአምላክነ ዘምሩ፤ እግዚአብሔር በዕልልታ ጌታችንም በመለከት ድምፅ ዐረገ ዘምሩ ለአምላካችን ዘምሩ”(መዝ፵፮፥፭)፡፡ በማለት በምን ሁኔታ እንዳረገ በመግለጽ ተቀኝቶለታል፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢሱስ ክርስቶስ ከትንሣኤው በኋላ የደቀ መዛሙርቱን ልብ እያጸና ተስፋቸውን እየነገረ ትንሣኤውን በግልጽ እንዲረዱ በአካል እየተገለጠላቸው በመካከላቸውም እየተገኘ አስተማራቸው፡፡ ግብረ ሐዋርያት በተባለው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል እንደተጻፈው፡- “ሕማማትን ከተቀበለ በኋላ ብዙ ተአምራት በማሳየት ዐርባ ቀን ሙሉ እየተገለጠላቸው ስለ እግዚአብሔር መንግሥትም እየነገራቸውና እያስተማራቸው ሕያው ሆኖ ራሱን ገለጠላቸው” (ሐዋ.፩፥፫) ይላል፡፡
ከማረጉም አስቀድሞ እንደነገራቸው የሚያጸናቸውን የመንፈስ ቅዱስን ኃይል እስኪቀበሉ ድረስ በኢየሩሳሌም እንዲቆዩ ነግሮአቸዋል፡፡ ይህንንም ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ ሲገልጽ ‘እነሆ እኔ የአባቴን ተስፋ ለእናንተ እልካለሁ እናንተ ግን ከአርያም ኃይልን እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ተቀመጡ’’( ሉቃ.፳፬፥፵፱) በማለት እንደነገራቸው ጽፎልናል፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከአርያም ኃይልን እስኪለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም እንዲቆዩ ማዘዙ ዳግም ወደ ምርኮ እንዳይመለሱ ነው፡፡ ምክንያቱም አጽናኙን መንፈስ ቅዱስን ካልተቀበሉ መፍራት፣ መጠራጠር፣ መጨነቅ ሊመጣ ስለሚችል ከዚህ ሁሉ ፍርሃትና ጭንቀት የሚታደጋቸውን የመንፈስ ቅዱስን ኃይል መልበስ ስለሚኖርባቸው ነው፡፡
ይህን ካላቸው በኋላ በንፍሐተ ቀርን እጁን ጭኖ ባረካቸው፡፡ እያዩትም ከፍ ከፍ አለ ከዐይናቸውም በርቀት ሳይሆን በርኅቀት ተሠወረ፡፡ የክብሩ መገለጫ የሆነችው ደመና ተቀበለችው፡፡ የመላእክትም ምስጋና እና የመለከት ድምጽ ይሰማ ነበር። ደቀ መዛሙርቱም ሲያርግ በአንክሮ ይመለከቱት ነበር፡፡ ነጫጭ ልብስ የለበሱ ሁለት መላእክትም እንዲህ አሏቸው፡፡ “እናንተ የገሊላ ሰዎች ሆይ ወደ ሰማይ እያያችሁ ለምን ቆማችኋል? ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ ያረገው ኢየሱስ ከእናንተ ወደ ሰማይ ሲያርግ እንዳያችሁት እንዲሁ ዳግመኛ ይመጣል አሏቸው” (ሐዋ.፩፥፲፩)፡፡
በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ የነገረ ሥጋዌው ምሥጢር በልደቱ ይጀምርና በዳግም ምጽአቱ ይጠናቀቃል፡፡ ይኸውም ተወለደ፤ ተጠመቀ፤ ተሰቀለ፤ ሞተ፤ ተቀበረ፤ ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፤ በክብር በምስጋና ዐረገ፤ ዳግመኛም ለፍርድ ይመጣል፤ የሚለው ነው፡፡ ለዚህም ነው በኪዳን ጸሎታችን መጀመሪያ ላይ “ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል ቅዱስ ሕያው ዘኢይመውት ዘተወልደ እማርያም እምቅድስት ድንግል ተሣሃለነ እግዚኦ፣ ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል ቅዱስ ሕያው ዘኢይመውት ዘተጠምቀ በዮርዳኖስ ወተሰቅለ ዲበ ዕፀ መስቀል ተሣሃለነ እግዚኦ፣ ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል ቅዱስ ሕያው ዘኢይመውት ዘተንሥአ እሙታን አመሣልስት ዕለት በከመ ጽሑፍ ውስተ ቅዱሳት መጻሕፍት ዐርገ በስብሐት ውስተ ሰማያት ወነበረ በየማነ አቡሁ ዳግመ ይመጽእ በስብሐት ይኮንን ሕያዋነ ወሙታነ ተሣሃለነ እግዚኦ” (ጸሎተ ኪዳን)፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ተወለደ ብለን ተጠመቀ ማለትን፣ ተሰቀለ ብለን ሞተ ማለትን፣ ተቀበረ ብለን ተነሣ ማለት፣ ዐረገ ብለን ዳግመኛ በሕያዋንና በሙታን ይፈርድ ዘንድ ይመጣል በማለት የዚህን ዓለም ሥርዓት እንጠቀልላለን፡፡
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ዕርገቱ ከሌሎች ቅዱሳን ዕርገት ይለያል፡፡ ለዚህም ነው በወንጌሉ “ከሰማይ ከወረደው ከሰው ልጅ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለም እርሱም በሰማይ የሚኖረው ነው” በማለት የነገረን (ዮሐ.፫፥፲፫)፡፡
በመጽሐፍ ቅዱስ ከምድር ወደ ሰማይ የተወሰዱ ቅዱሳን፣ ከሰማይም ለምሕረትም ሆነ ለመዓት ወደ ምድር የተላኩ ቅዱሳን መላእክት አሉ፡፡ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ዕርገት ከእነዚህ ሁሉ ቅዱሳን ልዩ የሚያደርገው ምንድን ነው? ብለን ከጠየቅን በዝርዝር ማየት ያሻልና ለአብነት ያህል ጥቂቶችን እንመልከት፡-
፩ኛ. ከሰማይ ከወረደው በቀር ሲል፡- አካላዊ ቃል ወደዚህ ዓለም ከመምጣቱ አስቀድሞ የነበረበት አምላካዊ አነዋወር እና የቅዱሳን መላእክት አነዋወር ይለያያል፡፡ እርሱ በፈጣሪነቱ የሚመለክ እነርሱ ደግሞ በፍጡርነታቸው የሚያመሰግኑ፣ የሚያገለግሉ፣ የሚገዙ ናቸው፡፡ የእርሱ በከበረ ዙፋኑ ከፍከፍ ብሎ የሚኖር የልዑላን ልዑል፣ የጌቶች ጌታ፣ የአማልክት አምላክ፣ የነገሥታት ንጉሥ ሲሆን ሰውን ለማዳን ከሰማያት ወርዶ ወደዚህ ዓለም መምጣቱ “ከሰማይ የወረደ” ያሰኘዋል፡፡
ለሰማያውያን ሰማያቸው ወይም ሀገራቸው የሆነ አምላክ በሥጋ ማርያም ተገልጦ መታየቱ ልዩ ነውና ከእርሱ ወደ ምድር መምጣት(መውረድ) እና ወደ ሰማይ ከማረግ ጋር የቅዱሳን መላእክት ለምሕረትም ሆነ ለመዓት ወደዚህ ምድር መላካቸው የሚነጻጸር አይደለም፡፡ በመሆኑም “ከሰማይ ከወረደው ከሰው ልጅ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለም” አለ ፡፡
፪ኛ. ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደና የማዳኑን ሥራ ሁሉ ፈጽሞ ሰውንም ወደ ቀደመ ክብሩ መልሶ ወደ ሰማያት ዐርጎ በአባቱ ቀኝ የተቀመጠ እርሱ ብቻ ነውና ፡፡
፫ኛ. በሕይወተ በሥጋ እያሉ ያረጉ ቅዱሳን፡- በመጽሐፍ ቅዱስ በሕይወተ ሥጋ እያሉ ያረጉ ቅዱሳን መኖራቸው ተጽፎአል፡፡ ከእነርሱም ውስጥ ሄኖክና ኤልያስ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ቅዱሳን ማረጋቸው እውነት ቢሆንም ዕርገታቸው ግን ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ዕርገት ጋር አይነጻጸርም፡፡ ምክንያቱም የእነርሱ አሳራጊ እርሱ ስለሆነ እርሱ ግን በሥልጣኑ ዐረገ፡፡
ሊቀ ነቢያት ሙሴ ስለ ሄኖክ ሲጽፍልን “ሄኖክም እግዚአብሔርን ደስ ስላሰኘው አልተገኘም እግዚአብሔር ሠውሮታልና” (ዘፍ.፭፥፳፬) ይላል፡፡ ሄኖክን እግዚአብሔር ሠውሮታል ይላል እንጂ በሥልጣኑ ተሠወረ አይልም፡፡
እንደዚሁም ኤልያስም በምን መልኩ እንዳረገ ስንመለከት “ከተሻገሩም በኋላ ኤልያስ ኤልሳዕን ከአንተ ሳልወሰድ አደርግልህ ዘንድ የምትሻውን ለምን አለው” (፪ኛነገ.፪፥፱) ይላል፡፡ ኤልያስ እንደተናገረው ሳልወሰድ ማለቱ የሚወስደው ኃይል እንዳለ የሚያሳይ ነው፡፡ ስለዚህ ዕርገቱ በእግዚአብሔር እንጂ በራሱ ሥልጣን እንዳልሆነ በግልጽ የሚያስረዳ ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ዐረገ ስንል ያረገው በሥልጣኑ ነው፡፡ ከላይ እንደተመለከትነው ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ፡- “እግዚአብሔር በእልልታ፣ ጌታችንም በመለከት ድምጽ ዐረገ” በማለት የተቀኘለት ነውና ዕርገቱ ልዩ ነው፡፡
፬ኛ. ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያረገው ወደ ሰማየ ሰማያት ወደ መንበረ ክብሩ ነው፡፡ ሄኖክና ኤልያስ ግን ያረጉት ወደ ብሔረ ሕያዋን ነውና የጌታችን የምድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ዕርገቱ ከቅዱሳን ዕርገት ጋር ሊነጻጸር አይችልም ፡፡ እርሱ በመለከት ድምጽ በመላእክት ምስጋና በክብር ያረገ፤ በአባቱም ቀኝ የተቀመጠ፤ የዘለዓለም ንጉሥ ነው፡፡ ወነበረ በየማነ አቡሁ ዳግመ ይመጽዕ በስብሐት ይኮንን ሕያዋነ ወሙታነ ወአልቦ ማኅለቅት ለመንግሥቱ’’ (ጸሎተ ሃይማኖት) እንዲል፡፡
በመሆኑም “ከሰማይ ከውረደው በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለም’” ተብሎ የተጻፈው የወረደው ሌላ የወጣው(ያረገው) ደግሞ ሌላ ነው የሚሉ መናፍቃን ስለ ነበሩ የሰው ሥጋን በመዋሐድ አዳምና ልጆቹን ለማዳን የወረደው አካላዊ ቃል የመጣበትን የማዳን ሥራ ፈጽሞ “አባ ወአቡየ ግብረ ዘወሀብከኒ ፈጸምኩ ፤አባት ሆይ የሰጠኸኝን ሥራ ፈጽሜአለሁ” በማለት ያረገው ያው ሥጋን ተዋሕዶ ሰው የሆነው አካላዊ ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን ለማጠየቅ እንደሆነ ሊቃውንት ያስረዳሉ ፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!