ከማያምነው ጸጉር አስተካካይ ጋር የተደረገ ውይይት
አንድ ሰው ጸጉሩንና ጺሙን ለመስተካከል ወደ አንድ ጸጉር ቤት ይሄዳል፡፡ ጸጉር አስተካካዩም ሥራውን መሥረት ከጀመረ በኋላ ከደንበኛው ጋር ጥሩ የሆነ ውይይት ይጀምራሉ፡፡
ብዙ ጉዳዮችን እያነሡ ከተወያዩ በኋላ “ነገርን ነገር ያነሣዋል” እንዲሉ ውይይታቸው ነገረ እግዚአብሔር ጋር ይደርሳል፡፡ በዚህ ጊዜ ጸጉር አስተካካዩ “እኔ እግዚአብሔር አለ ብዬ አላምንም::” በማለት ይናገራል፡፡ ደንበኛውም በመገረም “እንዴት እንዲህ ልትል ቻልክ?” በማለት ይጠይቀዋል፡፡ “እንግዲህ እግዚአብሔር እንደሌለ (አለመኖሩን) ለማረጋገጥ ወደ ጎዳና ወጥተህ ነገሮችን ማየት ይኖርብሃል፡፡ እስኪ ንገረኝ እግዚአብሔር ቢኖር በየመንገዱ የምታያቸው ብዙ የታመሙ ሰዎች ይኖሩ ነበር? በየጎዳናው የምታያቸው ወላጅ የሌላቸው ሕጻናት ይኖሩ ነበር? እግዚአብሔር ቢኖር ኖሮ መከራም ሆነ ስቃይ የሚባል ነገር ባልኖረ ነበር፡፡ እነዚህን ሁሉ ክፉ ነገሮች የሚፈቅድ ደግሞ ፍጥረቱን የሚወድ አምላክ ነው በዪ ማሰብ አልችልም፤ ይከብደኛል፡፡” ደንበኛውም ትንሽ አሰብ ካደረገ በኋላ እንደገና ጉንጭ አልፋ ክርክር መክፈት ስላልፈለገ ምንም ነገር ሳይመልስ ዝም አለ፡፡
ከዚህ በኋላ አስተካካዩ ሥራውን ጨርሶ ደንበኛው ጸጉር ቤቱን ለቆ ወጣ፡፡ ከቤቱ እንደወጣም በጎዳናው ላይ አንድ ጸጉሩ ረጅም፣ የተንጨባረረና የቆሸሸ እንዲሁም ጺሙ አድጎ ያልተስተካከለ ሰው ተመለከተ፡፡ ወዲያውም ወደ ጸጉር ቤቱ ተመለሰና አስተካካዩን “ታውቃለህ? ጸጉር አስተካካይ የሚባል ነገር የለም::” አለው፡፡ ጸጉር አስተካካዩም “እንዴት እንዲህ ልትል ቻልክ?” በማለት በመገረም ጠየቀው፡፡ “ይኸው እኔ አለሁ፤ እኔ ጸጉር አስተካካይ ነኝ፤ አንተንም አሁን አስተካክዬሃለሁ፡፡” አለ፡፡
“አይ! ጸጉር አስተካካይ የሚባል ነገር የለም፡፡ ምክንያቱም ጸጉር አስተካካይ ቢኖር ኖሮ እዛ ውጪ እንደምታየው ያለ ጸጉሩ የረዘመና የተንጨባረረ ጺሙም ያልተስተካከለ ሰው አይኖርም ነበር፡፡”
“አሀ! ጸጉር አስተካካይማ አለ፡፡ እንዲህ ያለ ነገር ሊሆን የሚችለው እኮ ሰዎች ወደ እኔ እስካልመጡ ድረስ ነው፡፡”
“በትክክል! ይህ ነው ነጥቡ! እግዚአብሔርም አለ፡፡ ሰዎች ወደ አስተካካዩ መጥተው ጸጉራቸውን አለመስተካከላቸው ጸጉር አስተካካይ የሚባል ነገር የለም እንደማያስብል ሁሉ በዓለም ላይ በመከራና በስቃይ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች መኖራቸው እግዚአብሔር የለም አያስብልም፡፡ ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር በእውነት ብንቀርብ ከመከራና ከስቃይ ሊያድነን የታመነ ነው፡፡ ወደ እርሱ እስከቀረብን ድረስ ለጊዜው በመከራና ስቃይ ውስጥ ቢተወን እንኳ መከራውን የምንታገሥበትን አስደናቂ የሆነውን የውስጥ ሰላምና እውነተኛ ደስታ ይሰጠናል፡፡ እርሱ እስከ መስቀል ሞት በደረሰ የልጁ መሥዋዕትነት መከራችንንና ስቃያችንን ተካፍሏል፡፡ የትንሣኤና የዘላለም ሕይወት ተስፋም አለን፡፡”
አንዳንድ ሰዎች ወደ እግዚአብሔር ባለመቅረባቸው ምክንያት ፈተና ሲገጥማቸው እግዚአብሔር የለም እያሉ በኃጢአት ላይ ሐኃአትን ይሠራሉ፡፡ ጸጉራም ሰው የጸጉር አስተካካይን መኖር የሚያውቀው ጸጉር ቤት ሲሔድ እንደመሆኑ መጠን ፣ እግዚአብሔርንም ማግኘት የሚቻለው ወደ ቤተ እግዚአብሔር በመሔድ ነው፡፡ ቅዱስ ዳዊት “ተፈሣሕኩ እስመ ይቤሉኒ ቤተ እግዚአብሔር ነሐውር” መዝ 121፡1 ወደ እግዚአብሔር ቤት እንሒድ ባሉኝ ጊዜ ደስ አለኝ ያለው ወደ ቤቱ በመገስገሱ ሰላምን፣ እውነትን፣ ስላገኘ ነው፡፡ እግዚአብሔርን ፈልገን ስንጓዝ ቸርነቱ ትጐበኘናለች፤ መሐሪነቱ ትማርከናለች፡፡ ከእርሱ ስንርቅ ደግሞ ሥቃይ፣ መከራ፣ ድቀት ያገኘናል፡፡ አባታችን አዳም ወደ እግዚአብሔር ሲጓዝ ሰላምን አግኝቷል፡፡ የእግዚአብሔርን አምላክነት ቸል ብሎ አምላክ መሆንን ሲሻ ግን መከራ አግኝቶታል፡፡ በመሆኑም እንደ ጸጉር አስተካካዩ ወደ ባለቤቱ እንቅረብ፤ የባለቤቱን መኖርም እናረጋግጣለን፡፡