እግዚአብሔርን ማመስገን

ክፍል ሦስት

በዳዊት አብርሃም

ስለ ምን እናመስግን?

ከአፈር አንስቶ ሰው ስላደረገን፡-

እግዚአብሔር ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌያችን እንፍጠር ብሎ ሰውን የሠራው ከምድር አፈር ሲሆን ዳግመኛም የሕይወት እስትንፋስን እፍ ብሎ ሰጥቶታል፤ በልጅነት ጸጋም አክብሮታል፡፡ ልጅ ሆነን ከወላጆች ስንገኝም ሰውነታችንንም ያገኘነው በእርሱ በአምላካችን ፈቃድ ነው እንጂ በራሳችን ወይም በወላጆቻችን ፈቃድ አይደለም፡፡ “እነሆ ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታ ናቸው፤ የሆድም ፍሬ የእርሱ ዋጋ ነው፡፡” (መዝ.፻፳፯፥፫) እንዲል፡፡

የሚያስፈልገንን ሁሉ አሟልቶ ስለፈጠረን፡-

እግዚአብሔር ሰውን የፈጠረው በዕለተ ዐርብ በፍጥረት መጨረሻ ቀን ነው፡፡ መጨረሻ መፍጠሩ ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ በቅድሚያ ለሰው የሚያስፈልገውን ምቹ የሆነውን ሁሉ አሟልቶና አዘጋጅቶ ነው፡፡ “እግዚአብሔርም ያ መልካም እንደሆነ አየ” በማለት በሊቀ ነቢያት ሙሴ ላይ አድሮ እንደተናገረው፡፡ (ዘፍ. ፪፥፳፭)

ስለ በጎ ስጦታዎቹ፡-

ከተአምራትና ከድንቆች በፊት ጥበብና ዕውቀት ተሰጥቶናል፡፡ (፩ኛ ቆሮ. ፲፪፥፰-፲) ልዩ ልዩ ስጠታዎችንም ሰጥቶናል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ሮሜ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ “ስጦታውም ልዩ ልዩ ነው፤ እግዚአብሔርም በሰጠን ጸጋ መጠን ልዩ ልዩ ስጦታ አለን፡፡ ትንቢት የሚናገር እንደ እምነቱ መጠን ይናገር፤ የሚያገለግልም በማገልገሉ ይትጋ፤ …” በማለት እንተናገረው፡፡

ክርስቲያን እንድንሆን ስላደረገን፡-

ብዙዎች የክርስትናን እውነት ለማግኘት አልታደሉም፤ እኛ ግን በስሙ ለመሰየም በቅተናል፡፡ ይህን ያገኘነው በራሳችን ብቃት እንዳልሆነ እናውቃለንና ስለማይነገር ስጦታው አምላክን ማመስገን ይገባናል፡፡

ሕይወት ስለሰጠን፡-

ሕይወትን የሰጠን አምላክ በሕይወተ ሥጋ ጠብቆ ለዚህች ሰዓት ስላደረሰን ልናመሰግነው ይገባል፡፡ ደግሞም ለዚህኛው ሕይወት ብቻ አይደለም፤ ከዚህኛው ሕይወት በኋላ እንድንወርሳት ስላዘጋጀልን የዘለዓለም ሕይወት ከምስጋና በቀር ምንን እንመልሳለን?

በቀጥተኛይቱ ሃይማኖት እንድንጸና ስላስቻለን፡-

ጥንታዊትና ሐዋርያዊት በሆነችው በቅድስት ቤተ ክርስቲያን፤ ከመጀመሪያው ጌታ ከመረጣቸው ሐዋርያት ጀምሮ ተያይዞ የመጣውን የክርስትናን መንገድ ሳንለቅና ሳንስት ጸንተን መኖራችን የአምላክ ቸርነት ረድቶን ነው፡፡ “የመጀመሪያ እምነታችንን እስከ መጨረሻው አጽንተን ብንጠብቅ የክርስቶስ ተካፋዮች ሆነናልና፡፡” (ዕብ. ፬፥፲፬) እንደተባለው የዚህ ጸጋ ባለቤቶች እንሆን ዘንድ ቸርነቱ እንደረዳን በማሰብ ማመስገን አለብን፡፡

እንደ ኃጢአታችን ስላልቀጣን፡-

“እግዚአብሔር መሓሪና ይቅር ባይ ነው፤ ከቁጣ የራቀ ምሕረቱም የበዛ ነው፤ ሁል ጊዜም አይቀስፍም፤ ለዘለዓለምም አይቆጣም፡፡ እንደ ኃጢአታችን አላደረገብንም፣ እንደ በደላችንም አልከፈለንም፡፡ ሰማይ ከምድር ከፍ እንደሚል እንዲሁ እግዚአብሔር ምሕረቱን በሚፈሩት ላይ አጠነከረ፡፡ ምሥራቅ ከምዕራብ እንደሚርቅ እንዲሁ ኃጢአታችንን ከእኛ አራቀ፡፡ አባት ለልጆቹ እንደሚራራ እንዲሁ እግዚአብሔር ለሚፈሩት ይራራል፤ ፍጥረታችንን እርሱ ያውቃልና አቤቱ እኛ አፈር እንደሆንን አስብ፡፡” (መዝ.፻፫፥፰-፲፬) በቅዳሴአችንም “አቤቱ እንደ ቸርነትህ እንጂ እንደ በደላችን አይሁን” የምንለው ለዚህ ነው፡፡ የእርሱ ቸርነት የእኛን ኃጢአት ይበልጣል፡፡ መሐሪነቱ ከሐሳባችን በላይ ነው፡፡ “አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልቡናችሁንና ሐሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል፡፡” እንዲል(ፊል.፬፥፯)

ስለ ርኅራሔውና አዛኝነቱ እንዲሁም ስላደረገልን እንክብካቤ፡-

ስንት ጊዜ ከመከራ ውስጥ አወጣን? በሌሎች ፊት ስንት ጊዜ መከበርን አደለን? ስንት ጊዜ ኃጢአታችንን ይቅር አለን? ስለ ጠበቀን፣ ስለ ረዳን፣ ስላቆየን፣ ስለ ተቀበለን፣ ስለራራልን፣ ስለ ደገፈን እስከዚህችም ሰዓት ስላደረሰን ብለን በቅዳሴ ጸሎታችን እንደምናመሰግነው ዘወትር የማይቆጠር መግቦቱን አስታውሰን ልናመሰግን ይገባናል፡፡

ስለ ጤንነታችን፡-

ይህንን በረከት አስበነው አናውቅም፡፡ አንዳንድ ሰዎች ግን የታመመ ዘመድ ባይኖራቸው እንኳ ወደ ሐኪም ቤት በመሄድ ሕሙማንን ይጎበኛሉ፡፡ እንዲህ ማድረጋቸው ከሚያስገኝላቸው ሰማያዊ ዋጋ በተጨማሪ ስለ ራሳቸው ጤንነት ለማመስገንም እንዲችሉ አጋጣሚው አእምሯቸውን ይከፍትላቸዋል፡፡

ስለ ሕመማችን፡-

ሕመም መጥፎ ወይም ክፉ ገጽታ ብቻ ያለው አይደለም፡፡ አልአዛር በቁስል ተመትቶ ነበር፤ ውሾች ቁስሉን እስኪልሱለት ድረስ ደርሶም ነበር፡፡ ይህ ሁኔታው ግን ከእግዚአብሔር የሚለየው አልሆነም፡፡ እንዲያውም በተቃራኒው ከእግዚአብሔር ጋር ይበልጥ የሚያቀራርበው ሆነለት፡፡ በእቅፉ ያደረገው አብርሃም እንደመሰከረለት “በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ክፉን ተቀበለ….” (ሉቃ. ፲፮፥፳፭) ታላቁ ባስልዮስ እንዲህ ተናግሯል፡፡ “ለአንተ መልካም የሆነው የቱ እንደሆነ አታውቅም፡፡ ጤና ወይም ሕመም” ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም “ስለዚህ ነገር ከእኔ እንዲለይ ሦስት ጊዜ ጌታን ለመንሁ፡፡” (፪ኛ ቆሮ. ፲፪፥፰) ሲል አስቸጋሪ የሆነበትን ሕመም እግዚአብሔር ለሥጋው መውጊያ ይሆነው ዘንድ እንደሆነ ሲያውቅ መቀበሉን ገልጧል፡፡ በተፈጥሮ ጤነኛ መሆንን እንፈልጋለን፡፡ በእርግጥም ለምድራዊ ሕይወታችን አስፈላጊው ጤንነት መሆኑ ግልጽ ቢሆንም ለመንፈሳዊ ሕይወታችን ግን አንድ ጥቅም አለው፡፡ ሕመም በአኮቴት ለሚቀበለው የኃጠአት መደምሰሻ የመንግሥተ ሰማያት መውረሻ ሊሆን ይችላል፡፡

ለምናየውና ለማናየው መልካም ነገር ሁሉ፡-

በሥጋዊ ዓይናችን ለምናየውም ሆነ በእምነት ዓይን ለምናየው የአምላክ በረከት ሁል ጊዜ ማመስገን ይገባናል፡፡ (ማቴ. ፮፥፬-፮)

በእኛ ውስጥ ስለሚሠራው የእግዘዚአብሔር ጸጋ፡-

በምስጋና ጊዜ በአንደኛ ደረጃ የምናስበው ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ነገር ግን በእግዚአብሔር ጸጋ የሆንሁ እኔ ነኝ፤ ለእኔም የተሰጠኝ ጸጋው ከንቱ አልነበረም፤ ከሁላችን ይልቅ ግን ደከምሁ፣ ዳሩ ግን ከእኔ ጋር ያለው የእግዚአብሔር ጸጋ ነው እንጂ እኔ አይደለሁም፡፡” (፩ቆሮ. ፲፭፥፲) ሲል እንደተናገረው ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል የምናውለው ልፋታችንና የሰመረው ጥረታችን ሁሉ በተሰጠን ጸጋ የተከናወነ ነው፡፡

ጌታችን ለሰጠን መዳን፡-

ከሞት ፍርድ የዳንነው በእርሱ ሞት ነው፤ ዘለዓለማዊ ሕይውትንም ያገኘነው በእርሱ የማዳን ሥራ ነው፡፡

እርሱን የማወቅ ችሎታን ስለሰጠን፡-

የምሥራቹ ወንጌል ስለተሰበከልን፣ የተሰበከውንም ስለተረዳነው፤ ይህም የሆነው በእርሱ ዕርዳታ ስለሆነ ዘወትር ልናመሰግነው ይገባል፡፡

ስለ ሰጠን ቃል ኪዳን፡-

“ታላቅም ድምጽ ከሰማይ፡- እነሆ የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ነው፤ ከእነርሱም ጋር ያድራል፤ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ፤ እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል፡፡” (ራእ.፳፩፥፫) “ሄጄም ስፍራ ባዘጋጀሁላችሁ፤ እኔ ባለሁበት እናንተ ደግሞ እንድትሆኑ ሁለተኛ እመጣለሁ፤ ወደ እኔም እወስዳችኋለሁ፡፡” (ዮሐ.፲፬፥፫) “ነገር ግን ዓይን ያላየው ጆሮም ያልሰማው በሰውም ልብ ያልታሰበው እግዚአብሔር ለሚወዱት ያዘጋጀው ተብሎ እንደተጻፈ እንዲህ እንናገራለን፡፡” (፩ኛ ቆሮ.፪፥፱)

ልጆችና ወዳጆች ብሎ ስለ ጠራን፡-

የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን ልንጠራ አብ እንዴት ያለውን ፍቅር እንደሰጠን እዩ፤ እንዲሁም ነን፡፡ ስለዚህ ምክንያት ዓለም እርሱን ስላላወቀው እኛን አያውቀንም፡፡ (፩ኛ ዮሐ. ፫፥፩) “እንግዲህ እናንተስ እንዲህ ጸልዩ፡፡ በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ” (ማቴ.፮፥፱)

የእግዚአብሔር ወዳጆቹ እንደሆንም ሲነግረን “ከእንግዲህ ወዲህ ባሮች አልላችሁም፤ ባርያ ጌታው የሚያደረገውን አያውቀውምና ወዳጆች ግን ብያችኋለሁ፤ ከአባቴ የሰማሁትን ሁሉ ለእናንተ አስታውቃችኋለሁና፡፡” (ዮሐ. ፲፭፥፲፭) ፤ “ኢየሱስም ከፋሲካ በዓል በፊት ከዚህ ዓለም ወደ አብ የሚሄድበት ሰዓት እንደ ደረሰ ዐውቆ በዚህ ዓለም ያሉትን ወገኖቹን የወደዳቸውን እስከ መጨረሻ ወደዳቸው፡፡” (ዮሐ.፲፫፥፩) ስለ እነዚህና ቆጥረን ስለማንጨርሳቸው በረከቶች ለአምላካችን ምንን እንመልሳለን? ከምስጋና በቀር ምንም ልንመልስ አንችልምና ዘወትር እናመስግነው፡፡ አምላካችንን ከማማረር ተለይተን የእርሱን መልካምነት እያሰብን እናመስግነው ዘንድ ይርዳን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *