እንዴት እንጸልይ?
ክፍል ፬
በእንዳለ ደምስስ
ባለፈው ዝግጅታችን “የጽድቅን ጥሩር ልበሱ” በሚል ርእስ ክፍል ሦስትን ማቅረባችን ይታወሳል፡፡ በዛሬው ዝግጅት ደግሞ ቀጣዩን ክፍል ፬ ወደ ድረ ገጻችን ተከታታዮች የምናቀርብ ይሆናል፣ ተከታተሉን፡፡
ጸሎት መለመን፣ ማመስገን፣ በንጽሕና በእግዚአብሔር ፊት መቆም፣ ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገር ማለት ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር ስንነጋገር ደግሞ ልናደርጋቸው የሚገቡ ጥንቃቄዎችና ይዘን መገኘት የሚገቡን መንፈሳዊ ምግባራትን ማወቅና መረዳት፣ በአጠቃላይ እንዴት መጸለይ እንዳለብን ጠንቅቀን መገንዘብ ይኖርብናል፡፡ እንኳን ከእግዚአብሔር ጋር በጸሎት ለመነጋገር ቀርቶ ከማንኛውም ሰው ጋር ከመነጋገራችን በፊት ምን ማለት እንዳለብን፣ በምን ጉዳይ ላይ እንደምንነጋገር ለይተን ማወቅን ይጠይቃል፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔርን በጸሎት ለመጠየቅና ለመነጋገር ስናስብ ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባን ማወቅ ተገቢ ነው፡፡ በሃይማኖት ቆመን፣ ሰማያዊውን ነገር እያሰብን ለጸሎት መዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡
በዚህም መሠረት ልናከናውናቸውና ይዘን መገኘት የሚገቡን መንፈሳዊ ምግባራት ምን ምን እንደሆኑ ማየት ያስፈልጋል፡፡ በወንጌል አምስቱ ልባም ሴቶች ያደረጉትንም ማስተዋል ይገባል፡፡ “ያን ጊዜም መንግሥተ ሰማያት መብራታቸውን ይዘው ሙሽራውን ለመቀበል የወጡ ዐሥሩን ደናግል ትመስላለች፡፡ ከእነርሱም ውስጥ አምስቱ ሰነፎች፣ አምስቱም ልባሞች ነበሩ፡፡ ሰነፎቹ መብራታቸውን ይዘው ዘይት አልያዙም ነበር፡፡ ልባሞቹ ግን ከመብራታቸው ጋር በማሰሮዎቻቸው ዘይት ይዘው ነበር” እንዲል(ማቴ.፳፭.፫)፡፡ ሃይማኖት፣ ጾም፣ ጸሎት፣ ትሕትናና ፍቅር መያዛቸውን ሲያመለክት አምስቱን ልባሞች አላቸው፡፡ ስለዚህ ከመጸለያችን በፊት እነዚህን ይዘን በመገኘት ከዚህ በታች ለተዘረዘሩት ነጥቦች ትኩረት ልንሰጥ ያስፈልጋል፡፡ እነዚህም፡-
፩. ኀጢአተኛ መሆናችንን ማሰብ፡-
ጢአት በኀልዮ(በማሰብ፣ በነቢብ(በመናገር)፣ በገቢር(በማድረግ) ሊፈጸም ይችላል፡፡ ያደረግነው ጥፋት ትክክል እንዳልበር፣ በሠራነው ኀጢአትም እግዚአብሔርን፣ ሌሎችን ሰዎች፣ እንዲሁም ራሳችንን መጉዳታችንን ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ራሳችንን እንዴት እንጎዳለን ስንል እግዚአብሔር በአርአያውና በምሳሌው ፈጥሮን፣ በሠራልን ሕግና ሥርዓት እንጓዝ ዘንድ ሲገባን ቃሉን አፍርሰናልና ሥጋችንን እናረክሳለን፡፡ ፈሪሳውያን አንዲት ሴትን ዝሙት ስትፈጽም አግኝተናታል ብለው በጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ አቅርበዋት ነበር፡፡ ኀጢአት ስትሠራ አግኝተናታልና በሙሴ ሕግ መሠረት በድንጋይ ተወግራ እንድትሞት አስበው፣ እንዲሁም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ለመፈተን ይህንን አድርገዋል፡፡ የራሳቸውን ኃጢአት ዘንግተው የሌላውን ኃጢአት ለመመልከት ፈጥነዋል፡፡ ነገር ግን የጌታችን መልስ እንደጠበቁት አልነበረም፡፡ ሊፈትኑት ቀርበዋልና ልብንና ኵላሊትን የሚመረምር አምላክ ነውና “ከእናንተ ኃጢአት የሌለበት አስቀድሞ ድንጋይ ይጣልባት” አላቸው፡፡ እነርሱም ኅሊናቸው ወቀሳቸው፡፡ “ከሽማግሌዎች እስከ ኋላኞቹ ድረስ አንዳንድ እያሉ ወጡ” እያለ ይነግረናል፡፡ ቀድሞ ከሌሎች ይልቅ የራስን ኃጢአት ማሰብ፣ ንስሓም መግባት ሲገባቸው የሌሎችን ኃጢአት ለመቁጠር ልባቸውን አስጨክነው ቀረቡ፡፡ ነገር ግን ያልጠበቁት ጥያቄ ሲቀርብላቸው ወደ ራሳቸው ኀጢአት ተመለከቱ፣ እንደበደሉም አወቁ፡፡(ዮሐ.፰.፯-9)፡፡
በደላችንን ማሰብ ከእያንዳንዳችን የሚጠበቅ ነው፡፡ ስለዚህ ለጸሎት ከመቆማችን በፊት እኛ በእግዚአብሔር ፊት መቆም የማንችልና የማይገባን እንደሆንን ማሰብና መረዳት ያስፈልጋል፡፡ በእግዚአብሔር ፊት በእኛ ሥልጣንና ፍላጎት ሳይሆን በእግዚአብሔር ቸርነት በተሰበረ ልብ መቆማችንን ልናስተውል፣ ይህንንም አምነን ተቀብለን ተግባራዊ ልናደርግ ግድ ይለናል፡፡ አይሁድ ከጌታችን ጋር እርሱ ወደሚሄድበት መሄድ እንደማይችሉ ከነገራቸው በኋላ “እኔ እሄዳለሁ፣ ትሹኛላችሁም፣ ነገር ግን አታገኙኝም በኃጢአታችሁ ትሞታላችሁ” ብሏቸዋል፡፡ ኃጢአት ወደ ሞት እንደሚወስድ አመልክቷቸዋል፤ ኃጢአተኞች ሆነው ሳለም በትዕቢት ልባቸውን በማደንደን ተፈታትነውታልና ገሰጿቸዋል፡፡(ዮሐ.፰.፳፩)፡፡
አይሁድ የአብርሃም ዘሮች ነን እያሉም ይመኩ ስለነበር ራሳቸውን ጻድቅ አድርገው የመቁጠር፣ ከፍ ከፍ ማለትንም መውደድ የተጠናወታቸው በመሆናቸው እንደ ቃሉ መኖር ሲገባቸው ጌታችንን ተፈታትነውታል፡፡ ጌታችንም የልቡናቸውን መደንደን ተመልክቶ “እውነት እውነት እላችኋለሁ ኃጢአትን የሚሠራ ሁሉ የኃጢአት ባሪያ ነው፡፡ ባሪያ ዘወትር በቤት አይኖርም፣ ልጅ ግን ለዘለዓለም ይኖራል” ሲል ከኃጢአታቸው ተመልሰው የእግዚአብሔር ልጆች ይባሉ ዘንድ፣ እንደ ልጅም በቤቱ ይኖሩ ዘንድ ነግሯቸዋል፡፡
“ኃጢአትን የሚሠራት ሁሉ እርሱ በደልን ደግሞ ያደርጋል፣ ኃጢአት በደል ናትና”(፩ኛዮሐ.፫.፬) እንዲል እኛም በደለኞች መሆናችንን እያሰብን፣ በደላችንንም ይቅር ይለን ዘንድ ለጸሎት መቆም ይገባናል፡፡
፪. የበደሉንን ይቅር ለማለት የተዘጋጀ ልብ፡-
አንድ ክርስቲያን ከእግዚአብሔር የሚፈልገው ነገር እንዳለ ሁሉ እግዚአብሔርም ከሰው ልጆች የሚፈልጋቸው ነገሮች አሉት፡፡ እነርሱም ዐሥርቱ ትእዛዛትና ስድስቱ ቃላተ ወንጌልን መፈጸም ናቸው፡፡ እነዚህም በአንድ መሠረታዊ ትእዛዝ ይጠቃለላሉ፡- ይህም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለገላትያ ሰዎች በላከው መልእክቱ “ወንድምህን እንደ ራስህ ውደድ፤ የሚለው ቃል ሕግን ሁሉ ይፈጽማልና፡፡” እንዲል(ገላ.፭.፲፬)፡፡ ወንድማችንን በመውደድ ቢበድለን እንኳን በይቅርታ በማለፍ ይቅር ባይነትን ለሌሎች ማስተማር ያስፈልጋል፤ ለነፍስም ዕረፍትን ይሰጣልና፡፡ የበደልነው ሰው ይቅር እንዲለን የምንሻ ከሆነ እኛም የበደሉንን ይቅር ለማለት የፈጠንን መሆን ይገባናል፡፡ “በምትጸልዩበትም ጊዜ በሰማያት ያለው አባታችሁ በደላችሁን ይቅር እንዲላችሁ በወንድማችሁ ያለውን በደል ይቅር በሉ፡፡ እናንተ ይቅር ባትሉ በሰማያት ያለው አባታችሁም በደላችሁን ይቅር አይላችሁም” እንዲል፡፡(ማር.፲፩.፳፭)፡፡
ልባችንን በግብዝነትና በእልከኝነት ማሠቃየት የለብንም፡፡ በዘወትር ጸሎታችን ጌታችን መድኃኒታችን ኢያሱስ ክርስቶስ እንዳስተማረን አባታችን ሆይ ብለን ዘወትር ስሙን እንጠራ ዘንድ ካዘዘን ትእዛዛት ውስጥ “. . . በደላችንን ይቅር በለን፣ እኛም የበደሉንን ይቅር እንል ዘንድ” እያልን እንጸልያለን፡፡ ይህንም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አይሁድ በመስቀል ላይ በሰቀሉት ጊዜ ከተናገራቸው “ሰባቱ አጽርሐ መስቀል” መካከል “አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” እንዳለ እኛም ለጸሎት ስንዘጋጅ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርሰቶስን አብነት አድርገን ሌሎች ይቅር እንዲሉን እኛም ይቅር ለማለት የፈጠንን መሆን አለብን፡፡ ልባችንንም ለዚህ ማዘጋጀት ከአንድ ክርስቲያን የሚጠበቅ መሆኑን ከአምላካችን ተምረናልና፡፡
፫. ትሕትና፡-
አንድ ክርስቲያን በክርስቲያንነቱ ሊያሟላቸው ከሚገቡ መልካም ምግባራት መካከል ትሕትና እጅግ አስፈላጊ ከሆኑት ውስጥ ይጠቀሳል፡፡ “ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ፣ ከእኔም ተማሩ፣ እኔ የዋህ ነኝና ልቤም ትሑት ነውና ለነፍሳችሁም ዕረፍትን ታገኛላችሁ፣ ቀንበሬ ልዝብ፣ ሸክሜም ቀላል ነውና” (ማቴ.፲፩.፳9) በማለት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳስተማረን እኛም ትሑታን ሆነን መገኘት ይገባናል፡፡
አምላካችን በሸላቾቹ ፊት እንደሚቆም በግ በትሕትና ቆሟልና እኛም ትሕትናን ገንዘብ ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ ትሕትና ዲያብሎስን ድል ማድረጊያ መንፈሳዊ መሣሪያችን ነው፡፡ በትዕቢት የሚመጣውን በትሕትና ማሸነፍ ስለሚቻል፡፡ ለዚህም ቅዳሳን፣ ፃድቃን ሰማዕታት አምላካችንን አብነት እንዳደረጉ ሁሉ እኛም እነርሱ በተጓዙበት መንገድ ልንከተላቸው ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ጸሎት እንዴት መጸለይ አለብን ስንል በእግዚአብሔር ፊት ስንቆም በፍጹም ትሕትና ሊሆን ግድ ይላል፡፡ በትሕትና የምንጸልየው ጸሎት ቅድመ እግዚአብሔር እንደሚደርስም ማመን ከእኛ ይጠበቃል፡፡
፬. አለባበስን ማስተካከል፡-
ለጸሎት በእግዚአብሔር ፊት ለመጸለይ በምንቆምበት ወቅት ልናደርጋቸው ከሚገቡን ነገሮች ሌላው ጉዳይ አለባበስን በተገቢውና ክርስቲያናዊ ሥርዓትን በተከተለ ሁኔታ መልበስ ነው፡፡ በእግዚአብሔር ፊት ስንቆም ነጠላችንን መስቀልያ አጣፍተን መልበስ ስንል ነጠላውን በቅድሚያ ከቀኝ ወደ ግራ፣ እንዲሁም ከግራ ወደ ቀኝ ማጣፋት ይገባል፡፡ ይህም ከቀኝ ወደ ግራ ማጣፋታችን አዳም አባታችን በበደሉ ምክንያት ከገነት ወጥቶ እንደነበር ሲያመለክተን፣ ከግራ ወደ ቀኝ ማጣፋታችንም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሰው ልጆች በመስቀል ላይ ተሰቅሎ፣ ሞቶ፣ ወደ መቃብር መውረዱን፣ መግነዝ ፍቱልኝ መቃብር ክፈቱልኝ ሳይል ሞትን ድል አድርጎ መነሣቱንና ዲያብሎስን አሥሮ፣ አዳምንና ልጆቹን ከሲኦል በማውጣት ወደ ገነት መመለሱን ሲያመለክተን ነው፡፡ ስለዚህ ለጸሎት በምንቆምበት ጊዜ ነጠላችንን መስቀለኛ አጣፍተን በተመስጦ ኅሊናችንን በመሰብሰብ፣ ለጸሎት በሁለት እግራችን ቀጥ ብለን በመቆም ልንዘጋጅ ይገባል፡፡
፭. የምንጸልየውን ማወቅ፡-
ለጸሎት ከመቆማችን በፊት ስለምንጸልየው ጉዳይ ማወቅና መረዳትም ያስፈልጋል፡፡ አንድ ክርስቲያን ዘወትር ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በደነገገችው ሥርዓት መሠረት የጸሎት ሰዓት ወስኖ መጸለይ እንደሚገባው የታወቀ ነው፡፡ ከጸሎት ተለይቶ ጽድቅ የለምና፡፡ ጸሎት የማይጸልይ ሰው በየቀኑ በውኃ እጦት እየጠወለገ እንደሚሄድ ዛፍ ነው፡፡ ለመጸለይ ደግሞ የምንጸልየውን ማወቅ አስፈላጊ ነው፡፡ አንድ ክርስቲያን ለምንድነው በእግዚአብሔር ፊት ለመቆም የፈለግሁት ብሎ ራሱን መጠየቅ፣ ለጥያቄውም ራሱ ምላሹን መስጠት አለበት፡፡
የምንጸልየውን ካወቅን እንዲደረግልን የምንፈልገው ላይ ብቻ ትኩረት ማድረግ ሳይሆን እስከ ዛሬ ውጣ ውረዱን አሳልፎ እዚህ ላደረሰን፣ እንዲሁም እንደበደላችን ሳይሆን በቸርነቱ ታድጎን ስላደረገልን መልካም ነገር ምስጋና ማቅረብን መዘንጋት የለብንም፡፡ ስለ ራሳችን ብቻም ሳይሆን ስለ ሀገር፣ ስለ ቤተ ክርስቲያን፣ ስለታመሙትና ስለ ተሰደዱት፣ . . . ሁሉ መጸለይ ተገቢ ነው፡፡
በተቃራኒው የምንጸልየውን አለማወቅ ከተግሣጽ አያድነንም፡፡ የዘብዴዎስ ልጆች እናት ማርያም ባውፍልያ ወደ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልጆቿን ያዕቆብና ዮሐንስን ይዛ በመቅረብ “. . . እነዚህ ሁለቱ ልጆቼ በመንግሥትህ አንዱ በቀኝህ፣ አንዱም በግራህ እንዲቀመጡ አድርግልኝ” አለችው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም “የምትለምኑትን አታውቁም፣ እኔ የምጠጣውን ጽዋ መጠጣት ትችላላችሁን? እኔስ የምጠመቀውን ጥምቀት ትጠመቃላችሁን?” ሲል ገሥጿቸዋል፡፡ እናታቸው የለመነችው ልመና ምድራዊ ንጉሥ መስሏት ምድራዊውን ሥልጣን ይሰጣቸው ዘንድ ጠየቀች፡፡ ነገር ግን በዕለተ ዐርብ በመስቀል ላይ በተሰቀለ ጊዜ በቀኝና በግራ ይሰቀሉ ብላ የመለመኗን ምሥጢር አልተረዳችም፡፡ ይህንን ሥጢር ባለመረዳትም ለልጆቿ ሕይወትን ሳይሆን ሞትን ለመነች፡፡ ይህም ለእኛ የማይገባና ያልተረዳነውን ልመና ወደ እግዚአብሔር ማቅረብ እንደሌለብን የሚያስተምረን ነው፡፡
፭. እንደ አቅማችን መጸለይ፡-
በመንፈሳዊ ሕይወታችን ውስጥ ልናየው ከሚገባን ነገር አንዱ ለመጸለይ ያለንን አቅም ነው፡፡ በእርግጥ ክርስቲያን የሆነ ሁሉ በእኩል መንፈሳዊ ብቃት ላይ ይገኛል ማለት አይቻልም፡፡ ከማይጸልዩ ክርስቲያኖች አንስቶ ግርማ ሌሊቱን፣ ጸብአ አጋንንቱን፣ ድምጸ አራዊቱን ታግሰው ጤዛ ልሰው፣ ድንጋይ ተንተርሰው፣ ቅጠል በጥሰው ወደ እግዚአብሔር ያለማቋረጥ እስከ ሚጸልዩት አባቶች ድረስ የተለያየ መንፈሳዊ ብቃትና ጸጋ ይኖራል፡፡ ስለዚህ ጸሎት ባለን መንፈሳዊ አቅም ይወሰናል፡፡
ገና ወጣኒ ሆኖ ይህንንም፣ ያንንም ሁሉንምየጸሎት መጽሐፍ ካላጸለይኩ ማለት ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡ ቀስ በቀስ ማደግ ሲገባ በስሜታዊነት የተጀመረ በመሆኑ እየቀነሱ፣ እየተሰላቹ በመምጣት ጨርሶ ጸሎትን እስከማቋረጥ ሊያደርስ ይችላልና፡፡ በሃይማኖት ጽናት የሚጸለይ ጸሎት እንደ ዛፍ ነው፡፡ ቀስ በቀስ የሚያድግ፣ ከራስ አልፎ ለሌሎች የሚተርፍ መንፈሳዊ ጸጋ ነው፡፡ ስለዚህ መንፈሳዊነት በራሱ ደረጃ አለውና ለታይታ ሳይሆን ለራሳችን ብለን እንደ አቅማችን ልንጸልይ ይገባል፡፡ “በምትጸልዩበት ጊዜ እንደ ግብዞች አትሁኑ፣ እነርሱ ለሰው ይታዩ ዘንድ በምኩራብና በአደባባይ መዓዘን መቆምና መጸለይን ይወዳሉና፣ እውነት እውነት እላችኋላሁ ዋጋቸውን ተቀብለዋል” እንደተባለ፡፡ (ማቴ.፮.፭)፡፡
፮. ከችኮላ መራቅ፡-
ለጸሎት በእግዚአብሔር ፊት በቆምን ጊዜም ራሳችንን አረጋግተን በተመስጦ ሆነን መጸለይ ያስፈልጋል፡፡ መቸኮል በማንኛውም የሕይወት ውጣ ውረድ ውስጥ ቢሆን ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡ የቆምነው በእግዚአብሔር ፊት እንደሆነና የምንነጋገረውም ከእግዚአብሔር ጋር መሆኑን በማሰብ ጸሎትን ሊያቋርጡ ከሚችሉ ነገሮች ከሥጋዊ ፍላጎትና ከንቱ ሐሳብ ርቀን ራስን መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡ ጸሎት በዘፈቀደ የሚፈጸም ሳይሆን ዓላማ ኖሮት መከናወን አለበት፡፡ የጀመሩትን ጸሎትም ሳይጨርሱ ጉዳይ አለብኝ፣ እንቅልፍ መጣብኝ፣ አሞኛል የመሳሳሉትን ምክንያቶች በመደርደር ለማረፍ መቸኮል ወይም ለሌላ ጉዳይ ተጣድፎ ማቋረጥ ተገቢ አይደለም፡፡ ይህንን ድርጊት ከመፈጸምም መቆጠብ ከአንድ ክርስቲያን ይጠበቃል፡፡ በችኮላ የምንገነባው ማንኛውም ነገር አወዳደቁ የከፋ ስለሚሆን ከችኮላ መራቅ አለበት፡፡
እነዚህ ከላይ ያየናቸው ነጥቦች ከብዙው በጥቂቱ ሲሆን በሚቀጥለው በክፍል ፭ ዝግጅታችን ደግሞ የጸሎት ሰዓታትን እንመለከታለን፡፡ ይቆየን፡፡
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!