“እናቴ ሆይ ገድላችን እንፈጽም ዘንድ ጨክኝ በርቺ አትጠራጠሪ”
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደም ላይ ተመሥርታለችና ዙሪያዋን በከበቧት ስፍር ቁጥር በሌላቸው ቅዱሳን መላእክት፣ ቅዱሳን ጻድቃን ሰማዕታት ተጋድሎና ጸሎት የታጠረች ናት፡፡ “እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ፤ በተራራ ላይ የተሠራች ከተማ መሰወር አይቻላትም” (ማቴ. ፭፥፲፬) እንዲል መጽሐፍ ቅዱስ ቅዱሳንን በብርሃን ይመስላቸዋል፤ ቅዱሳን ወንጌልን በመስበክ ዓለምን አጣፍጠዋታልና፡፡
ቤተ ክርስቲያን ለእነዚህ ዓለምን ድል ለነሱ ቅዱሳን ከዓመት እስከ ዓመት የተወለዱበትን፣ ተአምራት ያደረጉበትንና ያረፉበትን ቀን አስልታ መታሰቢያቸውን በድምቀት ታከብራለች፡፡ ከእነዚህ ቅዱሳን ጻድቃን ሰማዕታት መካከል ደግሞ ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስንና እናቱ ቅድስት ኢየሉጣ ንጉሡ ለሚያመልከው ጣኦት አንሰግድም በማለታቸው መከራ የተቀበሉበትና በእምነታቸው ጽናት እግዚአብሔርን ደስ በማሰኘታቸው መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ከነደደው እሳትና የፍላቱ ኃይል ዐሥራ ዐራት ክንድ ያህል ከፍታ ወደ ላይ ከሚዘል የፈላ ውኃ ያዳነበትን ቀን ሐምሌ ፲፱ ቀን አስባ በድምቀት ታከብራለች፡፡

በቤተ ክርስቲያን በየዕለቱ ከሚነበቡ መጻሕፍት መካከልም ስንክሳር ታሪኩን እንዲህ ይተርከዋል፡፡
ቅድስት ኢየሉጣ በሮም ግዛት በሚገኝ አንጌቤን በሚባል አገር በፈሪሃ እግዚአብሔር፣ በክርስትና ሃይማኖት እና በበጎ ምግባር ጸንታ ትኖር የነበረች ደግ ሴት ናት፡፡ በሥርዓት ያሳደገችው ቂርቆስ የሚባል የሦስት ዓመት ሕፃን ልጅም ነበራት፡፡ ይህቺ ቅድስት የዘመኑን አረማዊ መኰንን እለእስክንድሮስን በመፍራቷ ከልጇ ጋር ከሮም ወደ ጠርሴስ በተሰደደች ጊዜ መኰንኑ እነርሱ ከሚገኙበት አገር ገብቶ ክርስቲያኖችን እያሳደደ መግደል ጀመረ፡፡
የንጉሡ ወታደሮችም እግዚአብሔርን እንዲክዱ፤ ለጣዖት እንዲሰግዱ ቅድስት ኢየሉጣንና ቅዱስ ቂርቆስን አስፈራሯቸው፡፡ ቅዱሳኑ ግን ሃይማኖታቸውን ለመለወጥ ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡ በዚህም መኰንኑ ተቈጥቶ በዓይንና በአፍንጫቸው ውስጥ ጨውና ሰናፍጭ በመጨመር፤ በጋሉ የብረት ችንካሮች በመቸንከርና መላ ሰውነታቸውን በመብሳት በብዙ ዓይነት መሣሪያ አሠቃያቸው፡፡ እግዚአብሔርም የጋሉ ብረቶችን እንደ ውኃ ያቀዘቅዝላቸው፤ ሥቃያቸውንም ያቀልላቸው ነበር፡፡
በሌላ ጊዜም በገመድ አሳሥሮ ንጉሡ ሲያስጨንቃቸው ከቆየ በኋላ ራሳቸውን ከቆዳቸው ጋር አስላጭቶ እሳት አነደደባቸው፡፡ ዳግመኛም ከትከሻቸው እስከ እግራቸው ድረስ በሚደርሱ ችንካሮች ቸነከራቸው፡፡ በዚህ ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተልኮ ከሥቃያቸው አድኗቸዋል፡፡
አሁንም ቀኑን ሙሉ በልዩ ልዩ የሥቃይ መሣሪያዎች ቢያስጨንቃቸውም “እናቴ ሆይ! ገድላችን እንፈጽም ዘንድ ጨክኝ በርቺ አትጠራጠሪ” እያለ ቅዱስ ቂርቆስ እናቱን ቅድስት ኢየሉጣን እንድትጸና አበረታታት፡፡ የእግዚአብሔር ኃይልና የቅዱስ ገብርኤል ተራዳኢነት አልተለያቸውም ነበርና ምንም ዓይነት ጉዳት አልደረሰባቸውም፡፡ እንደ ገናም በመጋዝ ሰንጥቀው በብረት ምጣድ በቆሏቸው ጊዜ ጌታችን ከሞት አስነሣቸውና በመኰንኑ ፊት ድንቅ ተአምራትን አደረጉ፡፡ ከተአምራቱ መካከልም ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስ የመኰንኑን ጫማ በጸሎት ወደ በሬነት እንዲቀየር ማድረጉ ተጠቃሽ ሲሆን፣ መኰንኑ በተአምራቱ ተቈጥቶ የቅዱስ ቂርቆስን ምላስ አስቈርጦታል፤ ጌታችንም ምላሱን አድኖለታል፡፡
ዳግመኛም በፈላ የጋን ውኃ ውስጥ ቅዱስ ቂርቆስና እናቱን ቅድስት ኢየሉጣን ሊጨምሯቸው ሲሉ ቅድስት ኢየሉጣ በፈራች ጊዜ ቅዱስ ቂርቆስ “እናቴ ሆይ አትፍሪ፤አናንያ፣ ዓዛርያና ሚሳኤልን ከእሳት ነበልባል ያዳናቸው እግዚአብሔር እኛንም ከዚህ ከፈላ
ውኃ ያድነናል” እያለ ያረጋጋት፣ በተጋድሎዋ እንድትጸና ወደ እግዚአብሔር ይጸልይላት ነበር፡፡
ከዚህ በኋላ ተያይዘው ወደ ጋኑ ውስጥ ገቡ፡፡ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ውኃውን እንደ ውርጭ አቀዘቀዘው፡፡ ደግሞም ወታደሮቹ መንኰራኵር ባለበት የብረት ምጣድ ውስጥ አስገብተው ሥጋቸው እስኪቈራረጥ ድረስ በጎተቷቸው ጊዜ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል አድኗቸዋል፡፡ በመጨረሻም ከእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ተቀብለው በመንፈቀ ሌሊት አንገታቸውን ተቈርጠው በሰማዕትነት ዐርፈዋል፡፡ እስከ ሞት ድረስ በታመኑበት ተጋድሏቸውም ከእግዚአብሔር ዘንድ የሕይወትን አክሊል ተቀብለዋል፡፡
እኛም በሃይማኖታችን ምክንያት መከራ ባጋጠመን ጊዜ ቈራጥ ልብ ያለው ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስ “እናቴ ሆይ አትፍሪ” እያለ በእሳት ውስጥ ሊጣሉ ባሉበት ወቅት እናቱን እንድትጸናና ለሰማዕትነት እንድትበቃ እንዳደረጋት ሁሉ፣ ዘለዓለማዊውን የእግዚአብሔርን መንግሥት በአንድነት ለመውረስ እንድንችል “አይዞህ! አይዞሽ! አትፍራ! አትፍሪ” በመባባል በዚህ ዓለም የሚገጥመንን መከራ ታግሠን፣ እስከ ሞት ድረስ በሃይማኖታችን ጸንተን መኖር ይገባናል፡፡
ክርስትና ለብቻ የሚጸደቅበት መንገድ ሳይሆን በጋራ ዋጋ የሚያገኙበት የድኅነት በር ነውና፡፡ ከዚሁ ሁሉ ጋርም ቅዱስ ቂርቆስንና ቅድስት ኢየሉጣን የተራዳው የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ገብርኤል በአማላጅነቱ እንዲጠብቀን “በተአምኖ ንሴፎ ትንባሌ ዚአከ መዓልተ ወሌሊተ፤ በእግዚአብሔር ታምነን በቀንም በሌሊትም የአንተን ልመና ተስፋ እናደርጋለን” እያልን ዘወትር ልንማጸነው ያስፈልጋል፡፡ እርሱ ከፈጣሪው ከእግዚአብሔር በተሰጠው ቃል ኪዳን መሠረት ከሚደርስብን ልዩ ልዩ መከራና ሥቃይ ያድነናልና፡፡ “የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙርያ ይሠፍራል፤ ያድናቸውማል” ተብሎ እንደ ተጻፈ (መዝ. ፴፬፥፯)፡፡ ይህን እንድናደርግም የቅዱሳን ተራዳኢነት አይለየን፡፡ የቅዱስ ገብርኤል፣ ቅድስት ኢየሉጣ እና ቅዱስ ቂርቆስ ጸሎታቸውና ምልጃቸው ይጠብቀን፡፡
ስብሐት ለእግዚአብሔር
ምንጭ፡- ስንክሳር ዘወርኃ ሐምሌ
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!