“እነሆ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኅን ተወልዶላችኋል” (ሉቃ. ፪፥፲፩)

አንኳን ለጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ!

በእንዳለ ደምስስ

አውግስጦስ ቄሳር የሮም ገዥ፣ ሄሮድስ የይሁዳ ንጉሥ፣ በነበሩበት ወቅት በሀገረ እስራኤል በቤተ ልሔም የሰውን ልጅ ሕይወት ወደ ድኅነት ያሸጋገረ ታላቅ ነገር ተከሰተ፡፡ ይህንንም ክስተት ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ እንዲህ ይገልጸዋል፡፡ “እነሆ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኅን ተወልዶላችኋል፤ ይኸውም ቡሩክ ጌታ ክርስቶስ ነው፡፡ ለእናንተም ምልክቱ እንዲህ ነው፡- ሕፃን አውራ ጣቱን ታስሮ፣ በጨርቅ ተጠቅልሎ በበረት ውስጥ ተኝቶ ታገኙታላችሁ፡፡” (ሉቃ. ፪፥፲፩)

ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ ወቅቱን በተመለከተ ሲገልጽ “በዚያም ወራት እንዲህ ሆነ፤ ሰው ሁሉ ይቆጠር ዘንድ ከአውግስጦስ ቄሣር ትእዛዝ ወጣ፡፡ … ዮሴፍም ከገሊላ አውራጃ ከናዝሬት ከተማ ወደ ይሁዳ ቤተ ልሔም ወደምትባለው ወደ ዳዊት ከተማ ወጣ፤ እርሱም ከዳዊት ሀገርና ከዘመዶቹ ወገን ነበርና፡፡ ፀንሳ ሳለች ከእጮኛው ከማርያም ጋር ይቆጠር ዘንድ ሄደ፡፡” (ማቴ. ፪፥፩-፭) በማለት ሂደቱን ይገልጻል፡፡

አዳም ትእዛዛትን በማፍረሱ ምክንያት ከገነት ከወጣ አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ሲፈፀም፣   በመንፈስ ቅዱስ ግብር በነቢያት ትንቢት፣ በመልአኩ በቅዱስ ገብርኤል ብስራት በኅቱም ድንግልና ተፀንሶ በኅቱም ድንግልና በቤተ ልሔም በከብቶች በረት ተወለዷልና ልደቱ ልዩ ነው፡፡ (ማቴ. ፩፥፲፯)፡፡

በዚያም (በቤተልሔም) የሚያርፉበት ቦታ አልነበረምና በከብቶች በረት እያሉ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርም የመውለጃዋ ወራት ደረሰ፡፡ የበኩር ልጅዋንም ወለደችው፤ አውራ ጣቱንም አሰረችው፣ በጨርቅም ጠቀለለችው፡፡ ወቅቱ የብርድ ወራት ነበርና ከብቶች በትንፋሻቸው አሟሟቁት፡፡ በዚህም በነቢይ “ድንግል ትፀንሳለች፣ ወንድ ልጅም ትወልዳለች” የተባለው (ኢሳ. ፯፥፲፬) ተፈፀመ፡፡

የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ በጨለማ የነበርነውን ወደ ብርሃን አወጣን፡፡ “በጨለማ የሄደ ሕዝብ ታላቅ ብርሃን አየ፤ በሞት ጥላና በጨለማ ሀገርም ለነበሩ ብርሃን ወጣላቸው” እንዲል፡፡ (ኢሳ. ፱፥፪) ዘመኑ ሲፈጸም አዳምና ልጆቹን ያድን ዘንድ፣ ሞትንም ይሽረው ዘንድ ወደዚህች ምድር ከእመቤታችን ከሥጋዋ ሥጋ፣ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ ፍጹም ሰው፣ ፍጹም አምላክ በተዋሕዶ ተወለደ፡፡

ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ የተበታተኑትን ሊሰበስብ፣ ተጣልተው የነበሩትን ሰውና እግዚአብሔር፣ ሰውና መላእክትን ያስታርቅ ዘንድ መምጣቱንም ሲገልጽ “ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኀያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል።” በማለት በትንቢት የተናገረው ደረሰ፡፡ (ኢሳ. ፱፥፮)

መዝሙረኛው ዳዊትም “እነሆ በኤፍራታ ሰማነው፤ ዛፍ በበዛበትም ቦታ አገኘነው፡፡ እንግዲህስ ወደ እግዚአብሔር ማደሪያዎች እንገባለን፤ የጌታችን እግሮቹ በሚቆሙበት ቦታ እንሰግዳለን” በማለት የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ልደት ከአንድ ሺህ ዓመታት በፊት የተነበየው ትንቢት ጊዜው ሲደርስ በቤተ ልሔም በከብቶች በረት ተፈጸመ፡፡ (መዝ. ፻፴፩፥፮)

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በቤተ ልሔም ልጇን (ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ) በወለደች ጊዜ እንስሳት ትንፋሻቸውን ገበሩለት፤ “በሬ ገዢውን አህያም የጌታውን ጋጣ ዐወቀ፤ እስራኤል ግን አላወቁኝም፥ ሕዝቤም አላስተዋሉኝም።” (ኢሳ. ፩፥፫) እንዲል፡፡

የሰማይ መላእክት ልደቱን በቤተ ልሔም በጎችን ይጠብቁ ለነበሩት እረኞች የምሥራች ተናገሩ፡፡   “በዚያ ሀገር እረኞች ነበሩ፤ ሌሊቱንም ተግተው መንጋቸውን ይጠብቁ ነበር፡፡ እነሆም፥ የእግዚአብሔር መልአክ በአጠገባቸው ቆመ፤ የእግዚአብሔርም ብርሃን በዙሪያቸው አበራ፤ ታላቅ ፍርሃትንም ፈሩ፡፡ መልአኩም እንዲህ አላቸው፣ “እነሆ፣ ለእናንተና ለሕዝቡ ሁሉ ደስታ የሚሆን  ታላቅ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፡፡ እነሆ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኅን ተወልዶላችኋል፤ ይኽውም ቡሩክ ጌታ ክርስቶስ ነው፡፡ ይህም ምልክት ይሆንላችኋል፤ ሕፃን ተጠቅልሎ በግርግምም ተኝቶ ታገኛላችሁ።” (ሉቃ. ፪፥፰-፲፫) በጌታችን ልደትም መላእክት ከሰው ልጅ ጋር አብረው አመሰገኑ፡፡

መልካም እረኛ የሆነው ጌታ ልደቱ ከዘመኑ ታላላቅ ነገሥታት ይልቅ ቀድሞ ለእረኞች ደረሰ፡፡ (ዮሐ. ፲፥፲፩) እረኞቹ አመስግነውም አልቀሩም፡፡ “እንግዲህ እስከ ቤተ ልሔም ድረስ እንሂድ፤ እግዚአብሔርም የገለጠልንን ይህን የሆነውን ነገር እንይ” ተባባሉ። ፈጥነውም ወደ ቦታው ደርስው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከሕፃኑ፣ እንዲሁም ዮሴፍ ጋር በግርግም ተኝቶ አገኙት። አይተውም አደነቁ፤ ያዩትንም ፈጥነው ሄደው የምሥራቹን ለሌሎች ተናገሩ፡፡

ሰብዓ ሰገል (የጥበብ ሰዎች) በኮከብ እየተመሩ ቤተ ልሔም ደርሰው በታላቅ ምስጋና የነገሥታት ንጉሥ ነውና ወርቅ ለመንግሥቱ፣ ዕጣን ለክህነቱ፣ ከርቤንም ለሞቱ ገበሩለት፡፡ በነቢይ “የተርሴስና የደሴቶች ነገሥታት ስጦታን ያመጣሉ፤ የሳባና የዓረብ ነገሥታት እጅ መንሻን ያመጣሉ” እንደተባለ፡፡ (መዝ. ፸፩፥፲)

ሄሮድስና ኢየሩሳሌም ግን “ንጉሥ ተወለደ” ሲባሉ ደነገጡ፡፡ ሄሮድስም የካህናት አለቆችንና የሕዝቡን ጻፎች ሁሉ ሰብስቦ “ክርስቶስ በየት ይወለዳል?” ብሎ ጠየቃቸው፡፡ እነርሱም “በይሁዳ ክፍል ቤተ ልሔም ነው፤ በነቢይ እንዲህ ተብሎ ተጽፏልና፡፡ የይሁዳ ምድር አንቺ ቤተ ልሔም ከይሁዳ አለቆች ከቶ አታንሺም፤ ሕዝቤን እስራኤልን የሚጠብቅ ንጉሥ ከአንቺ ይወጣልና፡፡”  ከዚህም በኋላ ሄሮድስ ሰብአ ሰገልን በስውር ጠራቸው፤ ኮከቡ የታየበትንም ዘመን ከእነርሱ ተረዳ፡፡ “ሂዳችሁ የዚያን ሕፃን ነገር ርግጡን መርምሩ፤ ያገኛችሁትም እንደ ሆነ እኔም መጥቼ እሰግድለት ዘንድ በእኔ በኩል ተመልሳችሁ ንገሩኝ” ብሎ ወደ ቤተ ልሔም ሰደዳቸው። (ማቴ. ፪፥፬-፱) ሄሮድስ ይህን ያለው እንደ ቃሉ ሊሰግድለት ሳይሆን ሊገድለው አስቦ ነበር፡፡ የሩቆቹ ነገሥታት ሰብአ ሰገል ሰሙ፤ ሄሮድስ እና መሰሎቹ ግን ሲሰሙ ተረበሹ፡፡ እነሆ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኅን ተወልዷልና፡፡ (ሉቃ. ፪፥፲፩)

ከልደቱ በረከት ረድኤት ያሳትፈን፡፡ አሜን፡፡

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *