ኒቆዲሞስ

በዲ/ን ዮርዳኖስ ተክሉ

ኒቆዲሞስ መምህርና የአይሁድ መሪ ሆኖ ሳለ እውነትን ለማወቅ ከክርስቶስ ዘንድ ሊማር በሌሊት መጣ። ራሱን ዝቅ አድርጎ በመማር የትሕትና አርአያ ሆነ። ከዮሴፍ ጋር የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ቅዱስ ሥጋውን ገንዞ በሐዲስ መቃብር በጌቴሴማኒ ቀበረ። እኛስ..???

በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን ኢትዮጵያዊው ቅዱስ ያሬድ የዐቢይ ጾም የሳምንታት ስያሜዎች ከነሥርዐተ ማኅሌቱ በጾመ ድጓ መጽሐፍ ባዘጋጀው መሠረት የጾሙ ሰባተኛ ሳምንት ኒቆዲሞስ በመባል ይታወቃል።

በዚህ ሳምንት ከዋዜማው ቅዳሜ ጀምሮ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሚዘመረው ዝማሬ፣ የሚሰበከው ስብከት፣ የሚሰጠው ትምህርት፣ የሚነበበው ወንጌል “ኒቆዲሞስ”ን የሚያወሳ ነው። በዚህ ሰንበት በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ሦስት የተጻፈልን፦ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኒቆዲሞስ ለተባለ የአይሁድ አለቃ ያስተማረው ትምህርት፤ እንዲሁም የኒቆዲሞስ አስተማሪ መምህረ ትሕትና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኒቆዲሞስን ያስተማረው ትምህርት ይነበባል፣ ይተረጎማል፣ ይዜማል።

          ኒቆዲሞስ ግን ማን ነው?

ኒቆዲሞስ የሚለው ቃል የግሪክ ቃል ሲኾን፤ ትርጉሙም “ድል ማድረግ” ወይም “አሸናፊነት” ማለት ነው። ኒቆዲሞስ ፈሪሳዊ፣ የአይሁድ ሸንጎ አባል የነበረ ከአይሁድ አለቆችና መምህራን አንዱ ነው። (“ከፈሪሳውያንም ወገን የአይሁድ አለቃ የሆነ ኒቆዲሞስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤…” ዮሐ.፫፥፩)

ኒቆዲሞስ መምህር ሲሆን ራሱን ዝቅ አድርጎ የተማረ የትህትና አርአያ ነው። ኒቆዲሞስ ፈሪሳዊ ብቻ ሳይሆን የፈሪሳውያን አለቃ፣ የኦሪት መምህር ብቻ ሳይሆን የኦሪት ምሁርም ነበር። በእርሱ ደረጃ የነበሩ ታላላቅ የአይሁድ ምሁራን መንፈሳዊ ሥልጣናቸውና ሹመታቸው የእግዚአብሔር ስጦታ መሆኑን ረስተው በሕዝቡ ላይ የሚመጻደቁ ነበሩ። በዘመናቸው ዕውቀትን የሚገልጥ እውነተኛ አምላክ፣ የካህናት አለቃ ኢየሱስ ክርስቶስ ለቤዛ ዓለም ሲገለጥ የአይሁድ ምሁራን የጌታን መገለጥ አልወደዱትም። የእርሱ ትሕትና የእነርሱን ትዕቢት የሚያጋልጥ ነበርና ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚሄዱትን ሁሉ ይነቅፉ ይከስሱ ነበር። ጌታችንም የፈሪሳውያን አሳባቸው በግብዝነት የተሞላና ከንቱም እንደሆነ ነግሯቸዋል። ለደቀ መዛሙርቱም ከጻፎችና ከፈሪሳውያን ጽድቅ የሚበልጥ ሥራን እንዲሠሩ አስጠንቅቋቸዋል። (“እላችኋለሁና፦ ጽድቃችሁ ከጻፎችና ከፈሪሳውያን ጽድቅ ካልበለጠ፥ ወደ መንግሥተ ሰማያት ከቶ አትገቡም።” ማቴ.፭፥፳፤ “ኢየሱስም፦ ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠንቀቁና ተጠበቁ አላቸው።” ማቴ.፲፮፥፮) ኒቆዲሞስ ከእነዚህ ከፈሪሳዊያን መካከል የተገኘ ልዩ ምሁረ ኦሪት ነበር።

የሌሊቱ ደቀ መዝሙር ኒቆዲሞስ

ኒቆዲሞስ ፈሪሳዊና የአይሁድ ከፍተኛ ሸንጎ አባል ቢሆንም፣ በልቡ ግን እውነትን የማወቅ ከፍተኛ ጥማት ነበረው። ኒቆዲሞስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚያደርጋቸውን ተአምራት ሲያይ፣ እሱ ከእግዚአብሔር ዘንድ የመጣ መሆኑን አመነ። ነገር ግን የአይሁድ መሪዎችን በመፍራት በግልጽ ሊከተለው አልደፈረም። ስለዚህ በሌሊት ወደ ጌታ መጣ።

ኒቆዲሞስ ራሱን ለእውነት፣ ልቡን ለእምነት አዘጋጅቶ ከዅሉ ቀድሞ በሌሊት ክርስቶስን ፍለጋ የመጣ ከእነዚህ ፈሪሳዊያን ወገን ተለይቶ እንደ አባታችን አብርሃም ወደ ጽድቅ መንገድ የተጠራ ነው። ኒቆዲሞስ ሹመት እያለው፤ ዕውቀት እያለው፤ ሀብት እያለው ሁሉ ሳይጎድልበት እውነትን ለማወቅ እልቅናው ሳይታሰበው ከአካባቢው ጋር መመሳሰልን ሳይመርጥ ራሱን ዝቅ አድርጎ ከጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ሊማር በሌሊት መጣ። መምህረ ትሕትና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም የኒቆዲሞስን ትሕትናውን ተቀብሎ “ለምን በቀን አትመጣም?” ሳይለው እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ትውልድ ሁሉ የሚማርበትን ረቂቁን ምሥጢር “ምሥጢረ ጥምቀት”ን አስተማረው፦ “እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም” (ዮሐ.፫፥፫) አለው። ኒቆዲሞስ መጀመሪያ ነገሩ ግራ ገብቶት “ሰው ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወለድ ይችላል? ሁለተኛ ወደ እናቱ ማኅፀን ገብቶ ይወለድ ዘንድ ይችላልን?” (ዮሐ.፫፥፬) ብሎ ጠይቆ ነበር። ጌታም ልደቱ ከሥጋ ሳይሆን “ከውኃና ከመንፈስ” (በጥምቀት) መሆኑን አስረዳው፦ “እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም” (ዮሐ.፫፥፭)።

ለምን ይሆን ኒቆዲሞስ ከቀኑ ክፍለ ጊዜ ይልቅ የሌሊቱን ጊዜ ለትምህርት የመረጠው ?

ከፈሪሳውያን ወገን የአይሁድ አለቃ የሆነው ኒቆዲሞስ ቀን ቀን በአይሁድ ወንበር በሸንጎ እየዋለ ሌሊት ሌሊት ደግሞ ጌታችን ዘንድ እየመጣ ቃለ ወንጌልን ይማር ነበር። ከጌታችን ዘንድ ለመማር ሌሊቱን የመረጠበትም ምክንያት እነሆ፦

፩- የአይሁድ መምህር ስለነበር ስማር ብዙ ሰዎች ሲያዩኝ በውዳሴ ከንቱ መምህር መባል ይቀርብኛል ብሎ፤ እንዳያዩት ፈርቶ ሌሊት እየመጣ ይማር ነበር።

፪- ከቀን ልብ ይልቅ የሌሊት ልብ የተካተተ ስለሆነ በሙሉ ልቡ በማስተዋል ለመማር ስለፈለገ ከቀኑ ክፍለ ጊዜ ይልቅ የማታውን መረጠ።

፫- ሌሊት ጨለማ ነው፤ ብርሃን የለም ጨለማ የኃጢአት ምሳሌ ነው። ኒቆዲሞስ በሌሊት መምጣቱ በኃጢአት እንዳለ ንስሐ እንደሚፈልግ የሚያስረዳን ነው።

፬- ሌሊት የብሉይ ኪዳን ምሳሌ ነው። ኒቆዲሞስም “እኔ ምሁረ ኦሪት እንጂ ምሁረ ወንጌል አይደለሁም። ወንጌልን ካንተ እማር ዘንድ ያስፈልገኛል” ሲል በሌሊት ይመጣ ነበር።

ኒቆዲሞስ ከጨለማ ተማሪነት ወደ ብርሃን ምስክርነት

የኒቆዲሞስ ታሪክ አንድ ሰው ከጥርጣሬና ከፍርሃት ወጥቶ እንዴት የክርስቶስ እውነተኛ ምስክር ሊሆን እንደሚችል የሚያሳይ ትልቅ ትምህርት ነው።

ኒቆዲሞስ በልቡ ያደረው የጌታ ፍቅር እያደገ ሲመጣ፤ አይሁድ ጌታን ያለ ጥፋቱ ሊይዙትና ሊፈርዱበት በሚያሴሩበት ጊዜ፣ በሸንጎው መካከል በድፍረት ቆሞ፦ “ሕጋችን አስቀድሞ ከእርሱ ሳይሰማ ምንስ እንዳደረገ ሳያውቅ በሰው ይፈርዳልን?” (ዮሐ.፯፥፶፩) በማለት ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተሟገተ። ይህ የሚያሳየው ኒቆዲሞስ ቀስ በቀስ ከፍርሃት እየወጣና ለጽድቅ/ለእውነት መቆም እየጀመረ እንደነበር ነው።

የዕለተ ዓርቡ ታላቅ ምስክርነት

የኒቆዲሞስ እውነተኛ ፍቅርና ድፍረት በጉልህ የታየው ጌታችን በተሰቀለበት ዕለት በዕለተ ዓርብ ነው። ደቀ መዛሙርቱ በፈሩበትና በሸሹበት በዚያ አስጨናቂ ሰዓት፣ ኒቆዲሞስ ግን ፍርሃቱን አስወግዶ ማንነቱን በግልጽ አሳወቀ።

ኒቆዲሞስ ከጌታችን በተማረው ትምህርት ጸንቶ ለመኖር የበቃ ታላቅ አባት ነው። የሃይማኖቱ ጽናትም በተግባር የተፈተነ ነው። ለዚህም ማሳያ የሚሆነን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተሰቀለ ጊዜ የአርማትያስ ሰው ከሚሆን ከዮሴፍ ጋር በመሆን የአይሁድን ድንፋታ ሳይፈራ “እሱን ያገኘ ያገኘኛል” ሳይል በድፍረት የጌታችንን ቅዱስ ሥጋውን ከጲላጦስ ለምኖ፤ መቶ ንጥር የሚያህል የከርቤና የእሬት ቅልቅል ይዞ መጥቶ (በወቅቱ ይህ በጣም ውድና ለነገሥታት ክብር የሚቀርብ ሽቶ ነበር)፤ ከዮሴፍ ጋር የጌታን ቅዱስ ሥጋ በንጹሕ የተልባ እግር በፍታ ከሽቶ ጋር ገነዙት፤ በጌቴሴማኒም በአዲስ መቃብር ቀበሩት።

የጌታችንን ክቡር ሥጋ ገንዘው ሲቀብሩም በጸናች የተዋሕዶ እምነት ጌታችን እንደገለጠላቸው “ቅዱስ እግዚአብሔር፣ ቅዱስ ኃያል፣ ቅዱስ ሕያው ዘኢይመውት…” የሚለውን ጸሎት እስከ ፍጻሜው እየጸለዩ ነበር። በዚህም ኒቆዲሞስ ከሐዲስ ኪዳን ካህናት ቀድሞ ምሥጢረ ጥምቀትን ከጌታ እንደተማረ፣ የሐዲስ ኪዳንን የምሥጢራት አክሊል ምሥጢረ ቁርባንንም እንዲሁ ተማረ። ይህንንም በሚመለከት ሊቁ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም ድርሰቱ አብሮት ይቀድስ የነበረውን ንፍቅ ካህን በባረከበት አንቀጽ “በዚህ ምሥጢር እየተራዳኝ ከእኔ ጋር ያለ ይህንን ካህን እርሱንም እኔንም ሥጋህን እንደገነዙት እንደ ዮሴፍና እንደ ኒቆዲሞስ አድርገን” እንዲል (ቅዳሴ ማርያም ቁጥር ፻፲፭/115)።

በሌሊት ተደብቆ የመጣው ኒቆዲሞስ፣ በመጨረሻ በፀሐይ ብርሃን ለዓለም ሁሉ በሚታይ ሁኔታ የጌታ አገልጋይ መሆኑን በተግባር አረጋገጠ።

እኛስ ዛሬ እንደ ኒቆዲሞስ እውነተኛ የክርስቶስ ወዳጆች ለመሆን ምን ያስፈልገናል?

‎ከኒቆዲሞስ ታሪክ የምንማራቸው ሰባት(፯) ዋና ዋና ነጥቦች፦

፩- ፍርሃትን ማሸነፍ (ከሌሊት ወደ ብርሃን መውጣት)

ኒቆዲሞስ መጀመሪያ አካባቢ “ሰው ምን ይለኛል?” ብሎ በመፍራት በሌሊት ነበር የመጣው። እኛስ ዛሬ በጓደኞቻችን ወይም በቤተሰባችን ዘንድ ላለመናቅ ብለን የምንደብቀው በጎ ማንነት ወይም እምነት አለን?

ስለአንዲቱ ሃይማኖታችን ቆመን ለመመስከር መጀመሪያ በውስጣችን ያለውን የሰው ፍርሃት በእግዚአብሔር ፍቅር መተካት ያስፈልገናል (ከጨለማ ወደ ብርሃን እንውጣ)።

፪- ትኅትና፦ ኒቆዲሞስ ትልቅ ምሁርና መሪ ቢሆንም፣ ያላወቀውን ነገር ለመማር በጌታ እግር ሥር ተደፍቷል። እርሱ መምህር ቢሆንም ጣት ከጣት እንደሚበልጥ ከመምህር መምህር ይበልጣና ለመማር በትኅትና ወደ ክርስቶስ ሄደ በዚያች ትሕትናውም መምህር ፍለጋ ሄዶ አምላኩን አገኘ፤ የሕይወትንም ቃል ሰማ። ስለዚህ እኛም እንደኒቆዲሞስ የሕይወትን ቃል እንሰማ ዘንድ ትኅትናን ገንዘብ ልናደርግ ይገባናል።

፫- የማወቅ ፍላጎት (ለትምህርት ጊዜ መስጠት)

ኒቆዲሞስ ምንም እንኳን የቀኑ ክፍለ ጊዜ ባይመቸውም በሌሊቱ ሰዓት ለመማር ችሏል፤ እኛም  ከእሱ ተምረን “ከልብ ካለቀሱ ዕንባ አይገድም” እንዲሉ ምንም ሥራ ቢበዛብን ቅዱስ ቃሉን የምንማርበት ጊዜ አይጠፋምና ሕይወት ለሚገኝበት ትምህርት ጊዜ ልንሰጥ ይገባናል።

፬- እድገት/ለውጥ፦ ኒቆዲሞስ በእምነቱ እያደገ እንደሄደ ማለትም ከሌሊት/ ከፍርሃት ተነሥቶ እስከ ቀራንዮ አደባባይ/መስቀል ሥር እንደደረሰ፤ እኛም በእምነታችን ጠንክረን ባለንበት ቦታና ሁኔታ ሁሉ ያለፍርሃት እስከሞት ድረስ ስለአንዲቱ ሃይማኖታችን ልንመሰክር ይገባናል።

፭- እውነትን በድፍረት መናገር (በሸንጎው ፊት መቆም)

ኒቆዲሞስ አይሁድ ጌታን ያለ ጥፋቱ ሲከሱት “ሕጋችን አስቀድሞ ከእርሱ ሳይሰማ ምንስ እንዳደረገ ሳያውቅ በሰው ይፈርዳልን?” (ዮሐ.፯፥፶፩) ብሎ ተከራክሯል። እኛስ ጓደኞቻችን አንድን ሰው ያለአግባብ ሲያሙ ወይም ሲሳለቁ አይተን “ይህ ስህተት ነው” ብለን የመገሰጽ ድፍረት አለን?

እውነተኛ ክርስቲያን ማለት አብዛኛው ሰው ስህተት በሆነ መንገድ ሲጓዝ፣ እርሱ ብቻውን ቢሆንም እንኳ በእውነት መንገድ ላይ በመጽናት የሚጓዝ ነው።

፮- መሥዋዕትነት (ምርጥ ስጦታን መስጠት)፦ ለእግዚአብሔር ያለንን ፍቅር በንግግር ብቻ ሳይሆን በዕለተ ዓርብ እንደታየው በሕይወታችን፤ በጊዜያችንና በንብረታችን መስዋዕትነት ከፍለን መግለጽ ይገባናል። ኒቆዲሞስ ለጌታ ቀብር እጅግ ውድ የሆነ ሽቶ ይዞ መጥቷል። እኛ ለፈጣሪያችንና ለሰዎች የምንሰጠው “ውድ” የምንለው ነገር ምንድን ነው? ወይስ የተረፈንን ብቻ ነው የምንሰጠው?

እውነተኛ ሃይማኖት ከመሰጠትና ከመስጠት ጋር የተያያዘ ነው። ጌታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን እስከሞት ድረስ አሳልፎ በመስጠት እንደወደደን፤ እኛም በፍጹም ፍቅር ራሳችንን አሳልፈን ልንሰጠው ይገባናል። ለሰዎች/ለባልንጀሮቻችን ደግሞ እንደራሳችን አድርገን ወድደናቸው፤ ለእኛ የሚያስፈልገን ሁሉ ለእነርሱም ያስፈልጋቸዋልና ካለን ላይ ልንሰጣቸው ይገናባል።

፯- በመከራ ጊዜ አለመሸሽ (በመስቀሉ ሥር መገኘት)

ብዙዎች ጌታን ጥለውት በሸሹበት ሰዓት ኒቆዲሞስ ግን በግልጽ ወጥቶ ሥጋውን ተቀብሏል። እኛስ ነገሮች ሲበላሹና መከራ ሲመጣ በጽናት እንቆማለን ወይስ እንደ ደቀመዛሙርቱ እንሸሻለን?

እውነተኛ ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን የሚታወቀው በደስታ ጊዜ ብቻ ሳይሆን በፈተና ወቅት በሚያሳየው ታማኝነት፤ በመከራ ጊዜ ስለሃይማኖቱ በሚያደርገው ተጋድሎ (ሰማዕትነት)ነው።

‎‎ኒቆዲሞስ ጉዞውን በጥያቄ ጀምሮ በእምነትና በተግባር ጨረሰ። እኛም ዛሬ የክርስትና ሕይወታችን ከቃላት አልፎ በተግባር የተገለጠ እንዲሆን እነዚህን የኒቆዲሞስን ጠንካራ ጎኖች ልንላበስ ይገባል። ለዚህም አምላከ ኒቆዲሞስ ብርታቱንና ጽናቱን ያድለን፡፡

ስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *