“…ኒቆዲሞስ የተባለ አንድ ሰው ነበረ ”(ዮሐ.፫፥፩)

 በቀሲስ ኃይለሚካኤል ብርሃኑ

የዐቢይ ጾም ሰባተኛው ሳምንት ኒቆዲሞስ ይባላል፡፡ ይህም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሌሊት ወደ እርሱ እየመጣ ይማር ለነበረው  ኒቆዲሞስ ለተባለ ፈሪሳዊ ሰው የዳግም ልደትን ምሥጢር (ምሥጢረ ጥምቀትን) ያስተማረበት በመሆኑ ኒቆዲሞስ ተብሏል፡፡

ኒቆዲሞስ በሕይወት ዘመኑ ቅንናና መልካም ሰው እንደነበር ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በቀን ለመገናኘት ሁኔታው ባይፈቅድለትም በሌሊት እየመጣ የሕይወት ቃል በመማር ያልገባውንም በመጠየቅ ያሳየው ቁርጠኝነት ምስክር ነው፡፡ በሌላም መልኩ ስንመለከተው የኒቆዲሞስ የብሉይ ኪዳን መምህርነቱ የአይሁድም አለቅነቱ እንደ ሌሎች ጸሐፍት ፈሪሳውያን በምቀኝነትና በራስ ወዳድነት የተሸፈነ ስላልነበረ የክርስቶስን አምላክነት ለመረዳት ጊዜ አልወሰደበትም፡፡ ምክንያቱም በወቅቱ የነበሩ የአይሁድ ሹማምንት በተለያዩ ምክንያቶች በክሕደት ማዕበል የተዋጡበት ጊዜ ስለ ነበረ ነው፡፡

በዚህ ወቅት አይሁድ በክፋትና በምቀኝነት ተጠምደው የኢየሱስ ክርስቶስን አዳኝነት ለመሸፈንና አማላክነቱን ላለመቀበል እንኳንስ በአለቅነት መዓርግ ያለውን ኒቆዲሞስን ይቅርና ተራውን ሰው እንኳን ክርስቶስን እንዳይከተሉ ተጽዕኖ ያደርሱባቸው ነበር፡፡ ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ እንደ ጻፈው ፈሪሳዊው ኒቆዲሞስ የአይሁድ ዛቻና ማስፈራሪያ ሳይበግረው የሌሊቱ ጨለማ ሳያስፈራው በሌሊት የኢየሱስ ክርስቶስን ትምህርት ይከታተል ነበር፡፡

ኒቆዲሞስ የኢየሱስ ክርስቶስን የባሕርይ አምላክነት የሚያሳዩ የማዳን ሥራዎቹን የቃሉን ትምህርት፣የእጁን ተአምራት አይተው ካመኑበት ሰዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ ያልገባውን ጠይቆ በመረዳትም ጭምር ቅንነቱን እና የዋህነቱን አሳይቶአል፡፡ በተለይም ደግሞ ለጥያቄው መልስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሰጠው ትምህርቱ እስኪገባው ድረስ እንዴት፣ከየት፣መቼ፣ማን፣ እያለ በመጠየቅ እውነትን በመፈለግ የተጋ ብልህ ሰው ነው፡፡

ከትምህርት በኋላም ኢየሱስ ክርስቶስን በእግር ብቻ ሳሆን በልቡ አምኖ የተከተለ፡፡ ጌታችን ነፍሱን ከሥጋው በፈቃዱ አሳልፎ በሰጠም ጊዜ ሥጋውን ከመስቀል አውርደው የቀበሩት ዮሴፍና ይሄው መልካሙ ሰው ኒቆዲሞስ ናቸው፡፡ ለዚህም ነው በበዓለ ኀምሳ የቅዳሴ ሥርዓት ቀዳስያኑ ከቤተልሔም  ወደ ቤተ መቅደስ ሲገቡ  “ሃሌ ሉያ ዮሴፍ ወኒቆዲሞስ ገነዝዎ ለኢየሱስ በሰንዱናት ለዘተንሥኣ እሙታን በመንክር ኪን፤ ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ድንቅ በሚሆን ጥበብ ከሙታን ተለይቶ የተነሣውን ኢየሱስን በበፍታ ገነዙት” የሚለውን የምስጋና ቃል በዜማ እያሰሙ የሚገቡት (ሥርዓተ ቅዳሴ ዘበዓለ ኀምሳ)፡፡

በመሆኑም ኒቆዲሞስ እስከ መጨረሻው ድረስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የተከተለ የቁርጥ ቀን ባለሙዋሉ ነው፡፡ እምነቱ ፍርሀቱን አርቆለት በጽናት ሆኖ የጌታችን ቅዱስ ሥጋ ከመስቀል አውርዶ በአዲስ መቃብር ገንዞ በክብር በመቃብር ለማኖር የተመረጠ ቅዱስ ነው፡፡

ቅዱስ ያሬድም  በምስጋናው ውስጥ ይህን መልካም ሰው በመዘከር  ለዐቢይ ጾም ሳምንታት ስያሜን  ሲሰጥ ሰባተኛውን ሳምንት ኒቆዲሞስ በማለት በስሙ እንዲጠራ አድርጎአል፡፡ ኒቆዲሞስ አመጣጡ ከፈሪሳውያን ባለ ሥልጣናት ሲሆን ከማያምኑት የሚለይበትን እምነት ለማጽናት በጆርው የሰማውን እና በዐይኑ ያየውን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን የማዳን ሥራ  እየመሰከረ ያልገባውንም ቀርቦ በመጠየቅ እምነቱን ወደ ፍጹምነት አሳድጎታል፡፡ ለሚያነሣቸው ትያቄዎችም ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ የሚሰጡትን መልሶችና ማብራሪያዎችን በጥሙና ይሰማ ነበር፡፡ ጌታችንም በምሳሌ ጭምር እንዳስረዳው ወንጌላዊው  ቅዱስ ዮሐንስ እንዲህ ሲል በሰፊው ጽፎታል፡፡

“ከፈሪሳውያን ወገን የአይሁድ አለቃ የሆነ ኒቆዲሞስ የተባለ አንድ ሰው ነበረ፡፡ እርሱም በሌሊት ወደ ጌታችን ኢየሱስ መጥቶ እንዲህ አለው “መምህር ሆይ ልታስተምር ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ መጣህ እናውቃለን እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርገውን ይህንን ተአምር ሊያደርግ የሚችል የለምና፡፡ ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እውነት እውነት እልሀለሁ ዳግመኛ ያልተወለደ ሰው የእግዚአብሔርን መንግሥት ለማየት አይችልም” አለው፡፡ (ዮሐ.፫፥፩ )

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለኒቆዲሞስ በምሳሌ ጭምር እንዳስተማረው የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ (ለመዳን) የልጅነት ጥምቀት የግድ አስፈላጊ ነው፡፡  በዚያው የወንጌል ክፍል ዝቅ ይልና  “ኒቆዲሞስም ሰው ከሸመገለ በኋላ ዳግመኛ መወለድ እንደምን ይችላል? ዳግመኛ ይወለድ ዘንድ ወደ እናቱ ማኅፀን ተመልሶ መግባት ይችላልን? አለው ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፡፡ እውነት እውነት እልሀለሁ ዳግመኛ ከውሃና ከመንፈስ ቅዱስ ያልተወለደ ሰው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም፤ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፤ከመንፈስ የተወለደ መንፈስ ነውና›› (ዮሐ.፫፥፬) በማለት አስረዳው፡፡

ጌታችን እንዳስተማረን የሰው ልጅ ዳግም ከውኃና ከመንፈስ ሲወለድ የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ይሆናል፡፡ መንፈስ ቅዱስም ስለሚያድርበት የእግዚአብሔር ማደሪያ፣ ለእግዚአብሔር የተለየ ዙፋን፣የእግዚብሔር ቤተ መቅደስ ይሆናል፡፡ በዘመነ አበውም ሆነ በዘመነ ኦሪት ራሳቸውን ከርኲሰትና ከኃጢአት ለይተው ለእግዚአብሔር ክብር ከተለዩ ምእመናን ጋር እግዚአብሔር በረድኤት ነበረ፡፡ በሐዲስ ኪዳን ግን ዳግም ስንወለድ የእግዚአብሔር ልጆች ስለምንሆን የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያዎች ለመሆን እንሠራለን፡፡

ዳግም ልደት የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ማደሪያ ለመሆንና የመንግሥቱ ወራሾች መሆን የምንችልበት ምሥጢር ነው፡፡ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስም በመልእክቱ #እናንተ ግን ለመንፈሳዊ ሕግ እንጂ ለሥጋችሁ ፈቃድ የምትሠሩ አይደላችሁም፤የእግዚአብሔር መንፈስ በእናንተ አድሮ ይኖራልና፤የክርስቶስ መንፈስ ያላደረበት ግን እርሱ የእርሱ ወገን አይደለም፤ክርስቶስ ካደረባችሁ ግን ሰውነታችሁን ከኃጢአት ሥራ ለዩ፤መንፈሳችሁንም ለጽድቅ ሥራ ሕያው አድርጉ ጌታችን ኢየሱስን ከሙታን ለይቶ ያስነሣው የእግዚአብሔር መንፈስ ካደረባችሁ ኢየሱስ ክርስቶስን ከሙታን ለይቶ ያስነሣው እርሱ አድሮባችሁ ባለ መንፈሱ ለሟች ሰውነታችሁ ሕይወትን ይሰጣል$ (ሮሜ ፰፥፱) ይላል፡፡

ዳግም ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ የተወለደው የክርስቲያን አካል የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ የመንፈስ ቅዱስ ቤት፣የመንፈስ ቅዱስ ዙፋን ነው፡፡ ይህንን አካል በንጽሕና በቅድስና መያዝ የሚያድርበትን እግዚአብሔርን ማክበር ነው፡፡ እግዚአብሔር ንጹሐ ባሕርይ ነውና ያድርበት ዘንድ ንጹሕ ነገርን ይወዳል፡፡ በኃጢአትና  በበደል  በተጐሳቆለ አካል  ላይ  እግዚአብሔር አያድርም፡፡ የእርሱ ማደሪያ፣ለመሆን በኃጢአት ያደፈውን ማንነት በንስሓ ማጠብና ማንጻት ያስፈልጋል፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በላከላቸው መልእክቱ “ሥጋችሁ ከእግዚአብሔር ለተቀበላችሁት በእናንተ አድሮ ላለ ለመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደ ሆነ አታውቁምን? ለራሳችሁም አይደላችሁም በዋጋ ተገዝታችኋልና፤ስለዚህ እግዚአብሔርን በሥጋችሁ አክብሩ” (፩ኛቆሮ.፮፥፲፱) ይላልና፡፡

ሐዋርያው እንደገለጸው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ የተሰቀለውና ደሙን ያፈሰሰው በዲያብሎስ ግዛት ሥር ወድቆ የነበረውን፤ የሰው ልጅ ነጻ ለማውጣት ነው፡፡ በሲኦል የነፍስ መገዛትን፤ በመቃብር የሥጋን መበስበስ፣ አስወግዶ በፊቱ ሕያዋን አድርጎ ሊያቆመን

ስለ በደላችን የደሙን ዋጋ ከፍሎ ገዝቶናልና የራሳችን አይደለንም፡፡ በዋጋ የተገዛን የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ ቤተ መቅደስ ነን እንጂ፡፡

ይህንን የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የሆነ አካላችን በኃጢአት ብናቆሽሽ በዋጋ የተገዛ አካል ነውና ተጠያቂዎች ነን፡፡ “እናንተ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደሆናችሁ የእግዚአብሔር መንፈስም በእናንተ ላይ አድሮ እንደሚኖር አታውቁምን? የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ የሚያፈርሰውን ግን እርሱን ደግሞ እግዚአብሔር ያፈርሰዋል፤ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ነውና፤ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስም እናንተ ራሳችሁ ናችሁ እንግዲያስ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ አታርክሱ” (፩ኛቆሮ.፫፥፲፮)

በሐዲስ ኪዳን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወርቀ ደሙ ፈሳሽነት የዋጀን እያንዳንዳችን የእግዚአብሔር ማደሪያ ቤተ መቅደስ፣ የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ነን፡፡ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መሆን እጅግ የከበረ ማንነት ነው፡፡ ይህም የሚያሳየው እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ምን ያህል እንዳከበረውና እንደወደደው ነው፡፡ ለሰው ልጅ ወደር የሌለው ፍቅሩን የገለጠበትም ታላቅ ምሥጢር ነው፡፡ እግዚአብሔርን ያህል በባሕርዩ ቅዱስ የሆነ ጌታ በእኛ በደካሞችና በበደለኞች አካል ማደሩ እጅግ የሚያስደንቅ ቸርነት ነው፡፡ ይህንን ስንረዳ እግዚአብሔር ለእኛ ያደረገውን ምሕረት እናደንቃለን፡፡

በወንጌል እንደ ተጻፈው በእርሱ ሕይወት ይሆንልን ዘንድ የሚወደውን አንድያ ልጁን ወደ ጎስቋላዋ ዓለም ልኮታል፡፡ “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲያገኝ እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ቤዛ አድርጎ እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲህ ወዶታልና” እንዲል፡፡ (ዮሐ.፫፥፲፮)

እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍጹም ፍቅሩን ማስተዋል ከቻልን  የመንፈስ  ቅዱስ  ቤተ  መቅደስ  የሆነ  አካላችንን  የኃጢአት  መሣሪያ  ለማድረግ አንደፍርም፡፡ ምክንያቱም ቀደም ብለን እንዳየነው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “በዋጋ ተገዝታችኋልና የራሳችሁ አይደላችሁም” በማለት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዋጋ የገዛን ገንዘቡ እንደሆንን አስገንዝቦናል፡፡ ይኸው ሐዋርያ “ሥጋችሁ የክርስቶስ አካል እንደሆነ አታውቁምን? እንግዲህ የክርስቶስን አካል ወስዳችሁ የአመንዝራ አካል ታደርጉታላችሁን?   አይገባም››ይላልና፡፡ (፩ኛቆሮ.፮፥፲፭)

በክርስቶስ ክርስቲያን በመንፈስ ቅዱስ መንፈሳዊ የተሰኘን መሆናችንን ሁልጊዜም እያሰብን ሥጋዊ ፈቃድ ሳያሸንፈን ከኃጢአት ሥራ መራቅ ይኖርብናል፡፡ በኛ የሆኑ ሕዋሳቶቻችንን ሁሉ በማስተዋል መጠበቅና መቆጣጠር በተለይም ወጣቶች ያለንበት የዕድሜ ክልል በራሱ ፈታኝ መሆኑን ተረድተን ለስሜታችን ሳይሆን  ለሕገ እግዚአብሔር መገዛት እንደሚገባን ላፍታም መዘንጋት የለብንም፡፡ እንደ ኒቆዲሞስ ያልገባንን ወደ አባቶቻችን ካህናት እየቀረብን በመማርና በመጠየቅ ለመንፈሳዊ ሕይወታችን መትጋት ይጠበቅብናል፡፡

             የእግዚአብሐር ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን:: ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላም ያድርሰን አሜን፡፡

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *