ነገረ ጳጕሜን

በመ/ር ተስፋ ማርያም ክንዴ

በዚህም የመጽሐፍ ቃል መሠረት የኢትዮጵያ ሊቃውንት በዓመት ከ፲፪ቱ ወራት የተረፉትን ዕለታት ከወር ባነሱ ዑደቶች በዕለት፣ በኬክሮስ፣ በካልኢት፣ በሳልሲት፣ በራብኢት፣ በሐምሲትና በሳድሲት ሰፍረውና ቀምረው በዓመት ፭ ቀን፣ ከ፲፭ ኬክሮስ፣ ከ፮ ካልኢት አድርገው እነዚህ ዕለቶች ጳጕሜን ፲፫ኛ ወር አድርገውታል።

ኢትዮጵያዊያንና ግብፃዊያን ብቸኛ የባለ ፲፫ ወር መባላቸው ግን ዕለቷ በሌሎች አልኖር ብላ ሳይሆን ሌሎች እንዲሁ በዘፈቀደ ከሌላው ወር ጋር ደርበው ሲያከብሯት ኢትዮጵያና ግብጽ ግን ከላይ ከኬክሮስ እስከ ሳድሲት ባሉት ጥቃቅን የጊዜ መስፈሪያዎች ሰፍረን ቀምረን ስለምናውላት ነው። የዓለም ሀገራትም አንዳንዶቹ ከወራቸው ደርበው የወሩን ቁጥር አንዳንዴ ፴ አንዳንዴ ፴፩ እያደረጉ አሽባጥን (የካቲትን) ደግሞ ለይተው በ፫ቱ ዓመት ፳፰፣ በ፬ኛው ፳፱ እያደረጉ ጳጉሜን ደርበው ያውሏታል። እንደዚህ ከሚያከብሩ ሀገሮች መካከል ሮማዊያን (አፍርንጅ) እና ሶርያ እንዲሁም ይጠቀሳሉ፤ አንዳንዶቹ ደግሞ በ፰ኛው ወር መጨረሻ ስሟን ለዋህቅ ብለው ስለሚያከብሯት ነው።

በሌላ በኩልም ጳጕሜን ማለት ከህፀፅ ጋር ሲሰላ በዓመት የሚገኝ የፀሐይና የጨረቃ ዑደት ትርፍ ማለት ነው። ማክሰኞ ለረቡዕ አጥቢያ ጨረቃ በምሥራቅ በ፬ኛው ኆኅት በ፬ኛው ኬክሮስ ላይ የ፲፭ ዕለት ሙሉ ጨረቃ ሁና ስትፈጠር ፀሐይ ደግሞ በምዕራብ በኩል ልትገባ ፬ ኬክሮስ (፵፰ ደቂቃ) ሲቀራት ተፈጥራ ወዲያው ገብታለች፡፡  “ወይመይጦ ለብርሃን መንገለ መስዕ፤ ብርሃንን ወደ መስዕ(አቅጣጫ) ይለውጠዋል”  እንዳለ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በሰዓታት መጽሐፉ፡፡ ፀሐይ በሰሜን ዙራ በምሥራቅ ስትወጣ ጨረቃ ለመግባት አንድ ኬክሮስ ፶፪ ካልኢት ፴፩ ሳልሲት ፶፰ ራብዒት ፳፯ ሐምሲት ሲቀራት ደርሳባታለች። ራብዒቱንና ሐምሲቱን ደቃቅ ብሎ ትቶ ሌላውን በትናንሽ የብርሃን መስፈሪያዎች እየተጠቀለለ ሲደመር አንድ ኬክሮስ በዓመት ፮ ዕለት ይሆንና ህፀፅን ሲሰጥ ሌላው ደግሞ ጳጕሜን ያስገኛል።

እንዲሁም ጳጕሜን ማለት ከአንድ ዕለት የተገኘ ትርፍ ብርሃን በዓመት ተጠቅሎ ሲሰላ ማለት ነው። ፀሐይ በአንድ ቀን ወጥታ ፭ቱን ኬክሮስ በአንድ ሰዓት ፷ውን ኬክሮስ በ፲፪ ሰዓት አድርሳ ትገባለች፡፡ በቀን ውስጥ ከዚህ የተረፈ ከመውጣቷ በፊትና ከገባች በኋላ መጠኑ ያነሰም ቢሆን ብርሃን አለ፤ ጳጕሜን ማለት ይህ ብርሃን ነው። ይህም ብርሃን በትናንሽ መስፈሪያዎች ሲለካ ከመውጣቷ በፊት ያለው ፳፮ ካልኢት ፲፭ ነሳልሲት ፴ ራብኢት ከገባች በኋላም እንዲሁ ፳፮ ካልኢት ፲፭ ሳልሲት ፴ ራብኢት ሆኖ በድምሩ በቀን ፀሐይ ከመውጣቷና ከገባች በኋላ ያለው የብርሃን መጠን ፶፪ ካልኢት ከ፴ ሳልሲት ከ፷ ራብኢት ወይም ራብኢቱን ወደ ሳልሲት በመቀየር ፶፪ ካልኢት ከ፴፩ ሳልሲት ይሆናል። ይህንንም በአንድ ላይ እየሰበሰብን ስናሰላው በዓመት ፭ ጳጕሜን ይሰጠናል። ፶፪ቱን ካልኢት እስከ አንድ ወር ስንሰበስበው ወይም ስናባዘው ፲፭፻፷ካልኢ ይሆናል፤ እስከ ዓመት ደግሞ ፲፰ ሺህ ፯፻፳ ካልኢት ይሆናል፤ ይህን ወደ ኬክሮስ ለመቀየር በ፷ ሲገድፉት ወይም ለ፷ ሲያካፍሉት። ፫፻፲፪ ኬክሮስ ይሆናል፤ ይህን ወደ ቀን ለመቀየር በ፷ ሲገድፉት ፭ ቀን ከ፲፪ ኬክሮስ ይሆናል፡፡

ይህን ባለበት እናቆየውና ሌላውን እናስላ ፴ውን ሳልሲት እስከ ወር ሲሰበስቡት ፱፻ ሳልሲት ይሆናል፤ እስከ ዓመት ሲሰበስቡት ደግሞ ፲ሺህ፰፻ ሳልሲት ይሆናል፤ ይህን ወደ ካልኢት ለመቀየር በ፷ ሲገድፉት ፻፹ ካልኢት ይሆናል፤ ወደ ኬክሮስ ሲቀይሩት ፫ ኬክሮስ ይሆናል። ይህን ከመጀመሪያው ጋር ስንደምረው ፭ ዕለት ከ፲፭ ኬክሮስ ይሆናል። እንዲሁም ፷ውን ራብኢት ወደ ካልኢት ሲቀይሩት አንድ ሳልሲት ይሆናል፤ ይህን እስከ ወር ቢወስዱት ፴ ይሆናል፣ እስከ ዓመት ቢወስዱት ደግሞ ፫፻፷ ሳልሲት ይሆንና ወደ ካልኢት ሲቀየር ፮ ካልኢት ይሆናል። ሁሉንም በአንድ ላይ እንሰብስበው፡- ከመጀመሪያው ፭ ቀን ከ፲፭ እና ከመጨረሻው ያገኘነው ፮ ካልኢት በዓመት ፭ ዕለት ከ፲፭ ኬክሮስ ከ፮ ካልኢት ያልነው ይህ ነው።

፲፭ቱ ኬክሮስ በ፬ ዓመት ፷ ኬክሮስ ሆኖ አንድ ዕለት ይሆንና በአራተኛው ዓመት በዘመነ ዮሐንስ ጳጒሜን ፮ ዕለት ትሆናለች። ይህችም ዕለት ሰግረ ዮሐንስ ትባላለች፤ ምክንያቱም የዮሐንስን ዓመት የወር መባቻ እያሰገረች ስለምታውል ነው። ፮ቱ ካልኢት ደግሞ እስከ ፮፻ ዓመት ቢሰበሰብ ፴፮፻ ካልኢት ሆኖ በዕለት አንድ ዕለት ይሆንና በ፮፻ ዓመት ጳጒሜን ሰባት ዕለት ትሆናለች፡፡ ይህችም በቁጥር መምህራን ዘንድ እሪና ዕለት ትባላለች። እሪና መንገዱ ብዙ ነው የቀን እሪና አለ፣ የወር እሪና አለ፣ የዓመት ዕሪና አለ። ዓለም የተፈጠረው በዕሪና ነው የሚያልፈው ግን በእሪና ነው የሚሉ አሉ እሱን ግን ወንጌል ዕለቲቱን የሚያውቅ የለም ስለሚል በዚህ ቀን ምጽአት ይሆናል እያሉ ሰውን ከማደናገር የሰው ዕለተ ምጽአቱ ዕለተ ሞቱ ነውና ሁሌም ተዘጋጅተው እንዲጠብቁ ማስተማር የተሻለ ይሆናል።

ከባንዲራዋ ጋር ነጻነቷንና ሉአላዊነቷን የምታሳይበት መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት አድርጋ በራሷ ሊቃውንት እየቀመረች ለዘመናት ይዛው የመጣችው የራሷ የዘመን ቆጠራ ያላት ኢትዮጵያ በራሷ የዘመን ቆጠራ ሃይማኖታዊ ሥርዓቷን ባህሏንና ማንነቷን ስታከናውን ኑራለች፤ ወደፊትም ትኖራለች። ይህን የማያውቁና የማይረዱ አንዳንድ ግለሰቦችና ድርጅቶች ግን ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ኢትዮጵያ ጳጕሜንን እንደ ሌሎች ሀገሮች ከወሯ ደርባ ማክበር አለባት ወይም መተው አለባት ሲሉ መደመጥ ጀምረዋል።

ለመሆኑ ኢትዮጵያ እነሱ እንዳሉት ጳጕሜን ከሌሎች ወራት ደርባ ብታከብር ምን ነገር ይፋለሳል? ብለው ለሚጠይቁ ሰዎች የሚከተሉትን ጥቂት ማሳየዎች እናቀርባለን።

፩ኛ. ቤተ ክርስቲያናችን በጳጕሜን ወር በርካታ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶችን የምታከናውን ሲሆን ከእነዚህም አንዱ ዕለተ ምጽአትን ታከብራለች። መምህራን ጳጕሜን ከክረምት ወደ በጋው የምንሸጋገርባት ናት፡፡ ክረምት ደግሞ ከላይ ዝናብ ከታች ጎርፍ ነጎድጓድ መብረቅ ወዘተ የሚበዛበት ነውና የዚህ ዓለም ምሳሌ፣ በጋው ደግሞ ክረምቱ የሚያልፍበት ብርሃን የሚወጣበት አዝመራው የሚያፈራበት ነው ብለው ከምጽአት በኋላ በምንወርሰው መንግሥተ ሰማያት ይመስሉና በዚህ ወር ዕለተ ምጽአትን እንድናስብ አድርገውናል። እኛ ክርስቲያኖች ደግሞ ዕለተ ምጽአትን በዚች ወር ብቻ ሳይሆን ዘወትር እሱን እያሰብን ክፉ ከመሥራት እንድንጠበቅ መጽሐፍ ያስተምረናል፡፡ (ማቴ. ፳፬ እና ፳፭) ስለዚህ ጳጉሜን ወር አታክብሩ ማለት ሃይማኖታችሁን፣ ባህላችሁን፣ ታሪካችሁን ተዉ እንደማለት ይቆጠራል፤ ሰው ደግሞ ይህን ማንነት ትቶ እንደ እንሰሳት ሊኖር አግባብ አይደለም።

፪ኛ. በዚህ ወር ከመልአኩ ሩፋኤል በዓል በተጨማሪ በቤተ ክርስቲያን ተሰባስበን ርኅዎ ሰማይን (የሰማይ መከፈት) እናከብራለን። ርኅዎ ሰማይ ጳጕሜን ሦስት ይከበርና ከዚያ ማግስት ያለውን ቀን አንድ ብሎ ቆጥሮ በየ ፶፪ ቀኑ በዓመት ሰባት ጊዜ ይከበራል። ርኅዎ ሰማይ ማለት የሰማይ መከፈት ማለት ነው። በሰማይ መከፈትና መዘጋት ኑሮበት ሳይሆን ጸሎት የሚያርግበት ያልታየ ምሥጢር የሚታይበት እንደሆነ በ(ማቴ. ፫፥፩) ላይ ተጽፎ እናገኘዋለን። ከዚህ በተጨማሪ በጳጕሜን ወር ብዙ ምእመናን በመጾም ጸበል በመጠመቅ ከመንግሥት ሥራ ጀምሮ በነጻ መንፈሳዊና ሥጋዊ ትሩፋቶችን በማከናወን አዲሱን ዓመት ለመቀበል የሚዘጋጁባት ዕለት ናት።

፫ኛ. የጨረቃ ወርኃዊ ልደትና የወቅቶች መፋለስ፡- ጨረቃ የራሷ የቀን፣ የ፲፭ ቀን የወርና የዓመት ዑደት አላት፡፡ ለማሳያ ያህል የያዝነውን ዓመት የ፳፬፲፯ ዓ.ም የዓመት ዑደቷን የምትጨርሰው በፀሐይ ነሐሴ ፲፰ ቀን ነው። ይህ ማለት የመስከረም ጨረቃ ነሐሴ ፲፱ ቀን ትወለዳለች ከነሐሴ ፲፪ ከጳጕሜ ፭ ስናመጣ ፲፯ ይሆናል፡፡ የመስከረም ወር ጨረቃ የምትቆየው ፳፱ ዕለት ስለሆነ ይህን ለመሙላት ከመስከረም ፲፪ እናመጣና በሚቀጥለው ቀን የጥቅምት ጨረቃ ትወለዳለች፤ ስለዚህ ጳጕሜን የለችም ማለት ግን የመስከረም ወር ጨረቃ መስከረም ፲፪ ቀን መጨረሷን ትታ ወደ ፲፯ ትሄዳለች ማለት ነው። ይህ ደግሞ መምህራን ከሠሩት የጨረቃ የወር መንገድና የዓመት መንገድ ጋር የተፋለሰ ይሆናል። አራቱን ወቅቶችንም ብናይ እንደዚሁ መፋለስ ይፈጥራል፡፡ አንድ ቀን ስንል የራሱን ኬንትሮስ ከኬንትሮሱ ጋር የራሱን ፊደል ከፊደሉ ጋር የራሱን የፀሐይ ኆኅት እንዲሁም በመራሒ ወተመራሒ ሕግ የራሱን የቀን የወር የ፲፪ ወርና የዓመት ከዋክብትን ይዞ የሚጓዝ ነው እንጂ እንደፈለገ አንዱን ዕለት ከአንዱ የምንጨምረው አይደለም፡፡ በጥቅሉ በቁጥር መምህራን ዘንድ አንዱን ዕለት እንደፈለግን ከአንደኛው ዕለት ጋር ደርበን እናውል ማለት አንዱን እጅ ከአንዱ እጅ አንዱን እግር ከአንዱ እግር ጋር እንጨምር እንደማለት እንደሚቆጠር ልብ ማለት ይገባል። ሲጠቃለል ኢትዮጵያ የራሷ ባህል ታሪክ ሃይማኖት ያላት ይህንም በትውፊትና በመጽሐፍ ቅዱስ ይዛ የቆየች ሀገር ናት ስለዚህ አንድ ሰው ውሸት ቢናገርና በውሸታሞች መካከል ቢደገፍ ሌሎችም ውሸት ይናገሩ እንደማይባል ኢትዮጵያም ሌሎች በንጉሣቸው በጣኦታቸው ስም በየጊዜው እየቀያየሩ የዘመን ቆጠራን ቢያከብሩ የራሷን እውነት ትታ የእነሱን ውሸት ትቀበል እንደማይባል መረዳት ያስፈልጋል።

ስብሐት ለእግዚአብሔር

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *