ነገረ ቅዱሳን
መ/ር መስፍን ምትኬ
ክፍል ሦስት
፫. ቅዱሳን የሚባሉት ምን የፈጸሙ ናቸው?
ቅዱሳን እንደየገድላቸውና ትሩፋታቸው በተለያየ አከፋፈል ሊከፈሉ ቢችሉም በአጠቃላይ ግን ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን የፈጸሙ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡
ሀ. ያላቸውን ሁሉ ትተው አምላካቸውን የተከተሉ ናቸው፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ “እኛ ሁሉን ትተን ተከተልንህ እንግዲህ ምን እናገኛለን?” አለው፡፡ ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፡- እውነት እላችኋለሁ የተከተላችሁኝ እናንተ በዳግም ልደት የሰው ልጅ በክብሩ ዙፋን በተቀመጠ ጊዜ እናንተም በዐሥራ ሁለት ዙፋን ትቀመጣላችሁ፤ በዐሥራ ሁለቱም ነገደ እስራኤል ትፈርዳላችሁ፡፡” (ማቴ. ፲፱፥፳፯-፳፰፤ ማር. ፲፥፳፱-፴፩)
ለ. ሕይወታቸውን በተጋድሎ ያሳለፉ ናቸው
➢ “መከራን የሚታገሥ ሰው ብፁዕ ነው፤ ተፈትኖ እግዚአብሔር ለሚወዱት ተስፋ ያደረገላቸውን የሕይወት አክሊል ይቀበላልና፡፡” መንፈሳዊ ሰው ረቂቅ ጠላት ያለበት ስለሆነ ሁል ጊዜ የተዘጋጀ ሆኖ መኖር አለበት፡፡ ቅዱሳንም ይህን ጦርነት ዐውቀው በፈተና የጸኑና እስከ ሞት ድረስ የታመኑ ናቸው” (ያዕ. ፩፥፲፪)
“ገና አልጸናችሁምና ደማችሁን ለማፍሰስ እስክትደርሱ ኀጢአትን ተጋደሉአት፤ አሸንፏትም፤ ተስፋችሁን የምታገኙባትን ትምህርትም ውደዱአት” (ዕብ. ፲፪፥፬)
➢ መጋደላቸውም ከውስጣዊ እና ውጫዊ (አፍአዊ) ፈተናዎች ጋር ነው፡፡
- ውስጣዊ ፈተና፦ ይህ ፈተና አንድ ሰው “ሰው” በመሆኑ የሚፈተነው ፈተና ነው፡፡ ይኸውም ከሰዋዊ ባሕርይ ጋር የተያያዘ በመሆኑ ከዚህ ፈተና የሚሸሹት ሜዳ፣ የሚሸሸጉበት ጓዳ የለም፤ ሰው የነፍሱና ሥጋ ተዋሕዶ ውጤት በመሆኑ በዚህ ዓለም ሕይወት ሲወጣና ሲወርድ ይኖራል፡፡ ሰው በዚህ ዓለም ሕይወቱ ራሱን ለፈጣሪ ለማስገዛት ከራሱ ጋር ብርቱ ተጋድሎ ማድረግ ግድ ይለዋል፡፡
➢ ቅዱስ ጳውሎስ “ሥጋ በመንፈስ ላይ መንፈስ በሥጋ ላይ ይመኛል፡፡ እነዚህም እርስ በእርሳቸው ይቀዋወማሉ፡፡ ስለዚህም የምትወዱትን ልታደርጉ አትችሉም” (ገላ. ፲፥፲፯) ብሎ የገለጸው ይህንን የሰው ሕይወት ያለበትን ብርቱ ጦርነት ለማስገንዘብ ነው፡፡
➢ ስለዚህ “ሰውነቴን እየጎሰምኩ አስገዛዋለሁ” እንዳለ ሐዋርያው ፍቃደ ሥጋችን ለነፍሳችን በጾም በጾሎት በስግደት ልናስገዛ ይገባናል፡፡ (፩ኛ ቆሮ. ፱፥፳፯፤ መዝ. ፷፰፥፲)
- አፍአዊ (ውጫዊ) ፈተና፡- ሰው የሚፈተነው በውስጣዊ ብቻ ሳይሆን በውጫዊውም ፈተና ጭምር ነው፡፡ ይኸውም በቤተሰብ፣ በጓደኛ፣ በዘመድ፣ በሥራ ቦታ፣ በልማድና ጎጂ ባህል፣ … ነው፡፡
ሐ. እግዚአብሔርን በራሳቸው (በፍጹም ሰውነታቸው) ያገለገሉ ናቸው፡፡
ጌታችን “እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ” (ማቴ. ፲፮፥፪) በማለት የፍጹምነት መንገድ ተናግሯል፡፡
➢ ሰው በዚህ ዓለም ሲኖር በሕግ ተወስኖ ቤተሰብ መሥርቶ ጌታውን እያገለገለ ይኖራል፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔርን በማገልገልና ይህን ዓለም በማሰብ ልቡ ይከፈልበታል፤ ለዚህ ነው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ያገባ ግን ሚስቱን ደስ ሊያሰኝ የዚህን ዓለም ኑሮ ያስባል፡፡” (፩ኛቆሮ. ፯፥፴፫) በማለት የልቡን መከፈል ይገልጻል፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምሳሌ ሲያስተምርም “አንድ ሰው ታላቅ ምሳን አደረገና ብዙ ሰዎችን ጠራ፡፡” ይለናል፡፡ ነገረ ግን በመልእክተኛው የተጠሩት ሁሉ ምክንያት እየፈጠሩ ቀርተዋል፡፡ ወደ ግብዣ ከተጠሩት ውስጥ ሦስተኛው ሰው እንደ ምክንያት ያቀረበው “ሚስት አግብቼአለሁ ስለዚህም ልመጣ አልችልም በለው” አለው መልእክተኛውን። (ሉቃ. ፲፬፥፳)
➢ ስለዚህ ቅዱሳን ምክንያት ሳያደናቅፋቸው ይህን ዓለምን በመናቅ በምናኔ የኖሩ ናቸው፡፡
መ. ሩጫቸውን በድል የተወጡ ናቸው
➢ መንፈሳዊ ተጋድሎ በሩጫ ይመሰላል፡፡ “በእሽቅድምድም ስፍራ የሚሮጡት፥ ሁሉ እንዲሮጡ ነገር ግን አንዱ ብቻ ዋጋውን እንዲቀበል አታውቁምን? እንዲሁም ታገኙ ዘንድ ሩጡ።” (፩ኛ ቆሮ. ፱፥፳፬) በማለት መንፈሳዊውን ሕይወት በሩጫ መስሎ ተናግሯል፡፡
“በፈተና የሚጸና ሰው የተባረከ ነው፤ ከተፈተነ በኋላ ለሚወዱት ተስፋ ስለ እርሱ የሰጣቸውን የሕይወትን አክሊል ይቀበላልና።” (ያዕ. ፩፥፲፪)
➢ መጋደላችንም ከማን ጋር እንደሆነ ሲገልጽ፦ “መጋደላችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለምና፥ ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር በሰማያዊም ስፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር ነው እንጂ።” በማለት እንደተናገረው፡፡ (ኤፌ. ፮፥፲፪)
➢ ይህንን ተጋድሎ በትዕግሥት ያጠናቀቁትም፦
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ቅዱሳን ተጋድሎና በኋላም የሚያገኙትን ክብር ሲናገር “መልካሙን ገድል ተጋድዬአለሁ፥ ሩጫውን ጨርሼአለሁ፥ ሃይማኖትን ጠብቄአለሁ፤ ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል፥ ይህንም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው ጌታ ያን ቀን ለእኔ ያስረክባል፥ ደግሞም መገለጡን ለሚወዱት ሁሉ እንጂ ለእኔ ብቻ አይደለም“ ብሏል፡፡ (፪ኛጢሞ. ፬፥፯-፰)
➢ ብዙ ሯጮች ሩጫውን አብረው እንደሚጀምሩ ሁሉ ከሐዋርያት ጋር ጀምረው ሩጫቸውን ያቋረጡም አሉ፡፡ ለምሳሌ ይሁዳ፤ እንዲሁም ዴማስ ከሉቃስና ጢሞቴዎስ ጋር መንፈሳዊ ሕይወቱን መምራት ጀምሮ ሳያጠናቅቁ አቋርጠዋል፡፡ በዚህም ምክንያት የተዘጋጀላቸውን አክሊል አጥተዋል።
ሠ. በፍጹም መንፈሳዊ ጥበብ የኖሩ ናቸው
አምላክችንና ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “እንደ እባብ ልባሞች እንደ ርግብ የዋሆች ሁኑ” በማለት በመንፈሳዊ ጥበብ መኖር እንዲገባ አስታምሯል (ማቴ. ፲፥፮) ምክንያቱም ጠላታችን ረቂቅ አመጣጡም ረቂቅ ነውና ይህንን ረቂቅ ጠላት ለመመከት ጥበብ መንፈሳዊ ያስፈልጋል፡፡
በአጠቃላይ ቅዱሳን፦
ሀ. እስከ ሞት ድረስ የታመኑ ናቸው።
“እስከ ሞት የታመንክ ሁን” (ራእ. ፪፥፲) እንደተባለ እስከ ሕይወታቸው ፍጻሜ ድረስ በጾም በጸሎት ተወስነው በፍጹም ተጋድሎ በአምልኮተ እግዚአብሔር የጸኑ ናቸው።
ለ. በጌታችን በአምላካችንና በመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደም ላይ የተመሠረተችውን ቤተ ክርስቲያን እምነትና ሥርዓት ጠብቀው በማስጠበቅ በአገልግሎት የተጉና የተጋደሉ ናቸው።
ሐ. የእግዚአብሔርን ቃል ንባብ፣ ትርጓሜና ምሥጢር ሳያፋልሱ በማስተማር በሃይማኖት የጸኑ እና ምእመናንንም ያበዙ ናቸው።
መ. በሕይወታቸው ነውር በሃይማኖታቸው ነቀፌታ ያልተገኘባቸው ናቸው።
ሠ. ከዓለም ተለይተው በበረሃ ወድቀው፥ ድንጋይ ተንተርሰው፣ ጤዛ ልሰው፣ ዋሻ ዘግተው፣ ጸብአ አጋንንትን ድምፀ አራዊትን እና ግርማ ሌሊትን ሳይሰቀቁ የኖሩ፤ ስለ ሃይማኖታቸው በመመስከር በሰማዕትነት ያረፉ ናቸው።
ረ. ምትሐት ያይደለ እውነተኛ ተአምራትን በማድረግ የሚታወቁ ናቸው።
ሰ. ከፍጹምነት መዓርግ የደረሱ ናቸው።
“እንግዲህ የሰማዩ አባታችሁ ፍጹም እንደ ሆነ እናንተ ፍጹማን ሁኑ” (ማቴ. ፭፥፵፰)
ስለዚህ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን፦
➢ ቅዱሳንን እግዚአብሔር እንዳከበራቸው ታከብራቸዋለች
➢ በቅድስና ስም ትጠራቸዋለች፡፡
➢ ከእነርሱ በፊት የቅድስና መዓርግ በተሰጣቸው ሰዎች መዝገብ ስማቸውን በክብር ታኖራለች
➢ ተአምራቸውን ወይም ገድላቸውን ጽፋ በክብር ታስቀምጣለች።
➢ ዐጽማቸው ያለበት ቦታ የሚታወቅ እንደሆነ ሰብስባ በክብር ታስቀምጠዋለች፡፡
➢ በእነርሱ ስም ለጸሎት ለልመናና ለምስጋና የሚሆን መልክእ ትደርሳለች።
➢ ስማቸውንም እየጠራች ትማጸንባቸዋለች፡፡
➢ በእነርሱ ስም ጽላት ትቀርጽላቸዋለች፣ ቤተ ክርስቲያን ታንጽላቸዋለች፡፡
➢ የምእመናንም ስመ ክርስትናቸውን በስማቸው ትሰይማለች።
➢ የሚታሰቡበት ዕለት ትሰጣቸዋለች
➢ የመታሰቢያ ሥዕል ትሥልላቸዋለች፡፡
የቅዱሳን መታሰቢያ በቤተ ክርስቲያን
• ቤተ ክርስቲያን የቅዱሳንን ውለታ አትረሳም፡፡ በአፀደ ሥጋ ያሉትን በማገልገል ያረፉትን ቅዱሳንን ደግሞ በማክበር ገድላቸውን በመጻፍ መታሰቢያቸውን ታደርጋለች፡፡ (ዕብ. ፮፥፲)
“እነርሱ በእምነት ተጋደሉ፤ ነገሥታትን ድል ነሡ፤ ጽድቅን አደረጉ፤ ተስፋቸውን አገኙ፤ የአናብስትን አፍ ዘጉ፡፡ የእሳት ኀይልን አጠፉ፤ ከሰይፍ ስለት አመለጡ፤ ከድካማቸው በረቱ” (ዕብ. ፲፩፥፴፪)
• ቅዱሳንን ቤተ ክርስቲያን በማነጽ፣ ጽላት በመቅረጽ ታስባቸዋለች፡፡
“በቤቴና በቅጽሬ ውስጥ ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች ይልቅ የሚበልጥ መታሰቢያና ስም እሰጣቸዋልሁ፤ የማይጠፋም የዘለዓለም ስም እሰጣቸዋለሁ፡፡” (ኢሳ. ፶፮፥፭)
• ቤተ ክርስቲያን በቅዱሳን የልደትና የዕረፍት ዕለታት የመታሰቢያ በዓል በማድረግ በቅዳሴና በማኅሌት በማክበር በዓለ ንግሥ ታደርጋለች፡፡ በስማቸው ጠበል ጸዲቅ ታደርጋለች፡፡ (ማቴ. ፮፥፵-፵፪)
• ቤተ ክርስቲያን ቅዱሳንን የተጋደሉትን ተጋድሎ፣ የደረሰባቸውን ፈተና፣ ከጠላት ዲያብሎስ ጋር ያደረጉትን ጦርነት ድልና አክሊል እስካገኙበት ድረስ ያሉትን ገድላቸውን በመጻፍ ታስባቸዋለች፡፡
“መልካሙን የእምነት ገድል ተጋደል፥ የተጠራህለትንም በብዙም ምስክሮች ፊት በመልካም መታመን የታመንህለትን የዘለዓለምን ሕይወት ያዝ።” (፩ኛጢሞ. ፮፥፲፪)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!