ነገረ ቅዱሳን

መ/ር መስፍን ምትኬ

ክፍል ሁለት

ቅዱሳንን ማወቃችን ምን ጥቅም አለው?

ሀ. ሰይጣን የብርሃን መልአክ መስሎ እንዳንታለል መከላከያ ይሆኑናል።

ለ. ተኩላዎች በጎችን መስለው እንዳይገቡ እውነተኛ እረኛ ይሆኑናል።

ሐ. ቤተ ክርስቲያን መታሰቢያቸውን ለይታ ለመፈጸምና ለእኛ ለማሳወቅ ያስችላታል።

መ. በክርስቶስ የወይን ግንድነት ላይ ቅርንጫፍ በመሆን ብዙ ፍሬ ያፈሩ የሃይማኖት አባቶቻችንን ዐውቀን ከአታላዮች፣ ከአስመሳዮች፣ ከሐሳውያን እንድንጠበቅ ይረዱናል፡፡

የቅዱሳን ሕይወት

የቅዱሳን ሕይወት የሚነበብ መጽሐፍ ነው፡፡ ይኸውም ለክርስቶስ ወንጌል እንደሚገባ በመኖራቸው (በሕገ ወንጌል በመጽናታቸው) ነው፡፡ (ፊልጵ. ፩፥፳፯) በሕገ ወንጌል ለመጽናት የቻሉትም አስቀድመው ይህን ዓለም በመናቅ ከዓለም በመለየታቸው ነው፡፡

ይህንን በተመለከተ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “እኔ ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መሰቀል እንጂ በሌላ አልመካም ፤ በእኔ ዘንድ ዓለሙ የሞተ ነው፤ እኔም በዓለሙ ዘንድ የሞትሁ ነኝ” እንዲል፡፡ (ገላ. ፮፥፲፬)

ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስም በበኩሉ “ዓለሙንና በዓለም ያለውን አትውደዱ፤ ዓለሙን የሚወድ ግን የአብ ፍቅር በእርሱ የለም፡፡ በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዐይን አምሮት፣ ስለ ገንዘብም መመካት ከዓለም እንጂ ከአብ አይደለም፡፡ ዓለሙ ያልፋል፤ ምኞቱም ያልፋል፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ሰው ግን ለዘለዓለም ይኖራል” ብሏል (፩ኛዮሐ. ፪፥፲፭-፲፯)  

ቅዱሳን ሃይማኖት በመያዛቸው፣ ምግባር በመሥራታቸው በጾም፣ በጾሎት፣ በስግደት በመወሰናቸው በአጠቃላይ ሰውነታቸውን ቅዱስ መሥዋዕት አድርገው ለእግዚአብሔር በመስጠታቸው ዓለምን አሸንፈዋል፡፡ “ልጆች ሆይ፥ እናንተ ግን ከእግዚአብሔር ናችሁ፤ ክፉውንም አሸንፋችሁታል፤ በዓለም ውስጥ ካለው ይልቅ ከእናንተ ጋር ያለው ይበልጣልና፡፡” (፩ኛዮሐ. ፬፥፬)

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “እነርሱ የክርስቶስ አገልጋዮች ቢሆኑም እኔም እንደ ሰነፍ ለራሴ እናገራለሁ፤ እኔ እበልጣለሁ፤ እጅግም ደከምሁ፣ ብዙ ጊዜ ተገረፍሁ፤ ብዙ ጊዜም ታሰርሁ፤ ብዙ ጊዜም ለሞት ተዘጋጀሁ፡፡ አይሁድ አንዲት ስትቀር አምስት ጊዜ ዐርባ ዐርባ ገረፉኝ፡፡ ሦሰት ጊዜ በበትር ደበደቡኝ፣ አንድ ጊዜ በድንጋይ መቱኝ፤ መርከቤ ሦስት ጊዜ ተሰበረች፤ በጥልቁ ባሐር ውስጥ ስዋኝ አድሬ ስዋኝ ዋልሁ፡፡ በመንገድ ዘወትር መከራ እቀበል ነበር፤ በወንዝም መከራ ተቀበልሁ፤ ወንበዴዎችም አሠቃዩኝ፤ … የቀረውን ነገር ሳልቆጥር ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው፡፡” በማለት ስለ ክርስቶስ መከራ መቀበሉን ይገልጻል፡፡ (፪ኛቆሮ. ፲፩፥፳፫-፳፰)

የቅዱሳንን ሕይወት በቅድስና በንጽሕና ያጌጠ በገድልም የተመላ ነው

ንጽሕናቸው፡- ”ከእግዚአብሔር የሚወለድ ሁሉ ኃጢአትን አይሠራም፤ ዘሩ በእርሱ ይኖራልና፤ ኃጢአትንም ለሠራ አይችልም፤ ከእግዚአብሔር ተወልዷልና” እንደተባለው ቅዱሳን  ከኃጢአት የተለዩ ናቸው፡፡ (፩ኛዮሐ. ፫፥፱)

ገድላቸው፡- “የገረፉአቸው፣ የዘበቱባቸውና ያሠሯቸው ወደ ወኅኒ ያገቡአቸውም አሉ፡፡ በመጋዝ የሰነጠቁአቸው፣ በድንጋይ የወገሩአቸው፣ በሰይፍም ስለት የገደሉአቸው አሉ፤ እስከ ሞት ድረስ ተደበደቡ፤ ለሌሎችም መዘበቻ በመሆንና በመገረፍ ከዚህም በላይ በወኅኒ፣ ማቅ፣ ምንጣፍና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ፤ ተጨነቁ፣ ተቸገሩ፣ መከራ ተቀበሉ፣ ተራቡ፣ ተጠሙም፡፡” (ዕብ. ፲፩፥፴፮-፴፰)

➢ኑ ተከተሉኝ ያላቸውን ክርስቶስን መስለውታል፡፡ “እኔ ክርስቶስን እንደምመስለው እኔን ምሰሉ” እንዲል፡፡ (፩ኛቆሮ. ፲፩፥፩)

➢ ቅዱሳን ክርስቶስን የሚመስሉበትን ሕይወት ያገኙት በጸጋ ነው፡፡ “እነዚህን ደግሞ ጠራቸው የጠራቸውንም እነዚህን ደግሞ አጸደቃቸው፤ ያጸደቃቸውን እነዚህን ደግሞ አከበራቸው” በማለት ቅዱስ ጳውሎስ ገልጾታል፡፡ (ሮሜ ፰፥፳፱-፴)

➢ ‘ቅዱሳን በጸጋ ከብረው ክርስቶስን መሰሉት’ ስንል ሥልጣን ተካከሉት በማለት አይደለም፡፡ ለምሳሌ፡- የሰው ልጅ በእግዚአብሔር መልክ ፈጣሪውን መስሎ በመፈጠሩ እግዚአብሔርን ተካከለው አያሰኝም፡፡ “እግዚአብሔርም አለ፡- ሰውን በአርአያችንና በአምሳላችን እንፍጠር” (ዘፍ. ፩፥፳፮)፡፡

➢ በመሆኑም እግዚአብሔር ቅዱሳንን በጸጋ አክብሮ እንዴት እርሱን እንደመሰሉት ጥቅሶች በማቆራኘት ጥቂቶቹን እንመለከታለን፡-

ሀ. “ኢየሱስ ክርስቶስ የጽድቅ ፀሐይ ነው።” (ሚል. ፬፥፪፣ ማቴ. ፲፯፥፪)

➢ ቅዱሳንን “በአባታቸው መንግሥት እንደ ፀሐይ ያበራሉ” ተብሎላቸዋል፡፡ (ማቴ. ፲፫፥፵፫) ይህን የተናገረላቸው ራሱ ጌታችን ነው፡፡

ለ. “ለሰው ሁሉ የሚያበራ እውነተኛ ብርሃን ወደ ዓለም ይመጣል” (ዮሐ. ፩፥፲፱)

“በጨለማ የሄደ ሕዝብ ታላቅ ብርሃን አየ፤ በሞት ጥላና በጨለማ ሀገርም ለነበሩ ብርሃን ወጣላቸው።” (ኢሳ. ፱፥፪

“እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ” (ዮሐ. ፱፥፭) እንዲል ቅዱሳንንም “እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ” ብሏቸዋል፡፡ (ማቴ. ፭፥፲፮)

“የሕይወትን ቃል እያቀረባችሁ እንደ ብርሃን ትታያላችሁ” (ፊል. ፪፥፲፭)

“የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ በጨለማ አይመላለስም” (ዮሐ. ፰፥፲፪)

ሐ. “ቸር ጠባቂ እኔ ነኝ፤ ቸር ጠባቂ ስለ በጎቹ ነፍሱን ይሰጣል” (ዮሐ. ፲፥፲፩)

➢ ቅዱሳንን ወክሎ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስን “… በጎቼን ጠብቅ፤ … ጠቦቶቼን አሰማራ፤ … ግልገሎቼን ጠብቅ፤ …” (ዮሐ. ፳፩፥፲፭-፲፯)

“በእናንተ ዘንድ ያለውን የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ … የእረኞቹ አለቃ በሚገለጥበት ጊዜ የማያልፈውን የክብር አክሊል ትቀበላላችሁ” (፩ኛጴጥ. ፭፥፪-፬)

መ. “እግዚአብሔር ከዓለም አስቀድሞ ንጉሥ ነው፤ በምድርም መካከል መድኃኒትን አደረገ” (መዝ. ፸፫፥፲፪)

➢ ቅዱሳንን “እውነት እላችኋለሁ የተከተላችሁኝ እናንተ በዳግም ልደት የሰው ልጅ በክብሩ ዙፋን በተቀመጠ ጊዜ እናንተም በዐሥራ ሁለት ዙፋን ትቀመጣላችሁ፤ በዐሥራ ሁለቱም ነገደ እስራኤል ትፈርዳላችሁ፡፡” (ማቴ. ፲፱፥፳፰)

“አስቀድማ በምትመጣው ትንሣኤም ዕድል ያገኘ ብፁዕና ቅዱስ ነው፤ ከእንግዲህ ወዲህ በእነር ላይ ሁለተኛው ሞት ሥልጣን የለውም፥ የእግዚአብሔርና የክርስቶስ ካህናት ይሆናሉና፤ ከእርሱም ጋር ሺህ ዓመት ይነግሣሉ።” (ራእ. ፳፥፮)

“ከእንግዲህም ወዲህ ሌሊት አይሆንም፥ ጌታ አምላክም በእነርሱ ላይ ያበራላቸዋልና የመብራት ብርሃንና የፀሐይ ብርሃን አያስፈልጋቸውም፤ ለዘላለምም እስከ ዘላለም ይነግሣሉ።” (ራእ. ፳፪፥፭)

ሠ. ቅዱሳን የጸጋ አማልእክት መባላቸው ሊሻር አይችልም።  “በኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ዘለዓለም ክብሩ የጠራችሁ የጸጋ ሁሉ አምላክ ለጥቂት ጊዜ መከራን ከተቀበላችሁ በኋላ ፍጹማን ያደርጋችኋል፤ ያጸናችኋል፤ ልባሞችም ያድርጋችኋል” (፩ኛ ጴጥ. ፭፥፲)

“የኀጢአት ትርፍዋ ሞት ነውና፣ የእግዚአብሔር ጸጋ ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የዘለዓለም ሕይወት ነው” (ሮሜ ፮፥፳፫)

“ነገር ግን ለምትበልጠው ጸጋ ቅኑ፤ ደግሞም የምትሻለውን መንገድ አስተምራችኋለሁ፡፡” (፩ኛ ቆሮ. ፲፪፥፴፩)

ይቆየን

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *