በዲ/ን አብርሃም

“ጽዮን” ማለት “ጸወን አምባ፣ መጠጊያ” ማለት ነው፡፡ ጽዮን የሚለው ስም በቁሙ ለቅዱስ ዳዊት ተራራና ለኪዳኑ ጽላት ሲያገለግል በትንቢታዊ ምሥጢሩ ግን ለድንግል ማርያም፣ ለቤተ ክርስቲያንና ለዘለዓለማዊት ርስት ያገለግላል፡፡

ምእመናንም በዓለ ልደትን በላሊበላ፣ ጥምቀትን በጎንደር፣ ኅዳር ጽዮንን በአኵሱም ጽዮን ተገኝተው ለማክበርና የበረከቱ ተሳታፊ ለመሆን በድምቀት ያከብራሉ፡፡ በዚህም መሠረት ኅዳር ፳፩ ቀን የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ዓመታዊ በዓል ነው ብለን በተለየ መልኩ የምናከብርበት ምክንያት፡-

፩. በብሉይ ኪዳን ታቦተ ጽዮን የፈጸመችውን ልዩ ልዩ ገቢረ ተአምራትን ለማሰብ፣

፪. ቀዳማዊ ምኒልክ ከዓሥራ ሁለቱ ነገደ እስራኤል የበኲር ልጆች ጋር ሊቀ ካህናቱን አዛርያስንና ታቦተ ጽዮንን ይዞ አኵሱም የደረሰበት ዕለት በመሆኑ፣

፫. በሦስት መቶ ሠላሳ ዓ.ም በአብርሃ ወአጽብሃ ዘመነ መንግሥት ክርስትና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሃይማኖት ይሁን ተብሎ ዐዋጅ የታወጀበት፣

፬. ነቢዩ ዘካርያስ በተቅዋመ ወርቅ ምሳሌ ራእይ ያየበት፣ ነቢዩ ሕዝቅኤል የተቆለፈች ቤተ መቅደስን፣ ዕዝራ የቅድስት አገር ምሳሌ ራእይ ያዩበት፣

፭. አብርሃና አጽብሃ በወርቅና በዕንቍ ያሠሩት ባለ አሥራ ሁለት ክፍል ቤተ መቅደስ ለመጀመሪያ ጊዜ ቅዳሴ ቤቱ የተከበረበት እና

፮. ኅዳር ፳፩ ቀን በታቦተ ጽዮን የተፈጸሙ ታላላቅ ተአምራት የሚታሰቡበት ቀን ነው፡፡

አኵሱም ጽዮን ማርያም በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚገኙት አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ መሠረታቸው ስትሆን ከተማዋም የኢትዮጵያ ሥልጣኔ መነሻ ናት፡፡ አኵሱም በሕገ ልቡና የጸናች፣ ሕገ ኦሪትን የፈጸመች፣ በሕገ ወንጌል ያመነች ናት፡፡ ቅዱስ ዳዊት “ሕግ ይወጽእ እምጽዮን፤ ከጽዮን ሕግ ይወጣል” ሲል ተናግሮላታል፡፡

በዚህ ቀን ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የታቦተ ጽዮንን ተአምራት እግዚአብሔር ቃል (አካላዊ ቃል) ቅድስት ድንግል ማርያምን ታቦቱ አድርጎ ከፈጸማቸው ታላላቅ የድኅነት ሥራዎች ጋር በማነጻጸር እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በነገረ ድኅነት ውስጥ ያላትን ድርሻ በስፋት ታስተምራለች፡፡

የታቦተ ጽዮንን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ታሪክ  ካየን በኋላ  የሐዲስ ኪዳኑዋን አማናዊቱዋን ታቦት ከብሉይ ኪዳኑዋ ታቦት ጋር በንጽጽር እንመለከት፡-

ነቢዩ ሙሴ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ጸልዮና ጹሞ ዐሥርቱ ቃላት የተጻፈበትን ጽላት (የቃል ኪዳኑ ታቦት ‘ታቦተ ጽዮን’ን ከእግዚአብሔር እንደተቀበለ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል፡፡ ታቦተ ጽዮን ከማይነቅዝ እንጨት የተቀረጸች፣ በውስጥም በውጪም በጥሩ ወርቅ የተለበጠች ስትሆን ይህቺ የቃል ኪዳን ታቦት በደብተራ ኦሪት በቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ የኖረች፣ የዮርዳኖስን ባሕር የከፈለች (ኢያ. ፫÷፲፬-፲፯)፤ ቅጽረ ኢያሪኮን ያፈረሰች (ኢያ. ፮÷፩-፳፩)፤ ዳጎን የተባለ የፍልስጥኤማውያንን ጣዖት የቆራረጠች (፩ሳሙ. ፭÷፩-፭)፤ በድፍረት ሊነካ የሞከረውን ኦዛንን የቀሰፈች (፩ኛሳሙ. ፮÷፮)፤ በአቢዳራ ቤት ሦስት ወር ተቀምጣ ቤቱን በበረከት የመላች (፪ኛሳሙ. ፮÷፲፪)፣ ዳዊት የዘመረላት ፪ኛሳሙ. ፮÷፲፬)፤ ጠቢቡ ሰሎሞን በቤተ መቅደስ በክብር ያኖራት (፩ኛነገ. ፰÷፩)፤ የእግዚአብሔር የክብር መገለጫ ናት፡፡

በታቦተ ጽዮን እና በዘመነ ሐዲስ በተገለጠችው በቅድስት ድንግል ማርያም መካከል ያለውን ረቂቅ እና ድንቅ ምሥጢራዊ ንጽጽር አስመልክቶ ሦርያዊው ሊቅ ቅዱስ ኤፍሬም፤ “ታቦት በወርቅ ልቡጥ እምኩለሔ ዘግቡር እምዕፅ ዘኢይነቅዝ፤ ከማይነቅዝ እንጨት የተቀረጸ በውስጥ በአፍአ በወርቅ የተለበጠ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ንጽሐ ጠባይዕ ሳያድፍባትና የቅድስና ባሕርይ ሳይጎድፍባት በማየት፣ በመስማት፣ በመዳሰሰ፣ በማሽተት አንዳችም እድፍ ጉድፍ ሳያገኛት በንጽሕናና በቅድስና ጸንታ በኃጢኣት ሳትለወጥ ኖራለች፡፡” ጠቢቡ ሰሎሞንም፤ “አልብኪ ነውር ወኢምንትኒ ላዕሌኪ፤ ምክንያታዊ ነውር ኃጢአት የሌለብሽ የኃጢአት ሸታ ያልደረሰብሽ ንጽሕት በድንግልና ሥርጉት በቅድስና ክብርት በልዕልና አንቺ ነሽ” /መኃ. ፬÷፯) ሲል ተናግሯል፡፡

ታቦተ ጽዮን የቃለ እግዚአብሔር ማደሪያ እንደሆነችው ቅድስት ድንግል ማርያምም ለአካላዊ ቃል ለእግዚአብሔር ወልድ ማደሪያ ሆናለች፡፡ ይህንንም ቅዱስ ኤፍሬም ሲያስረዳ፤ “ኮንኪ ታቦቶ ለፈጣሬ ሰማያት ወምድር ፆርኪዮ በከርስኪ ተሰዓተ አውርኃ አንቲ ማእምንት ለዘኢያገምርዎ ሰማያት ወምድር፤ ድንግል ማርያም ሆይ ሰማይና ምድርን ለፈጠረ አምላክ ለእርሱ ማደሪያ ሆንሽ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በማኅፀንሸ ቻልሽው ተሸከምሽው ሰማይና ምድር የማይወስኑትን ለመወሰን የታመንሽ አንቺ ነሽ” ብሎ ተቀኝቶላታል፡፡

የቃል ኪዳን ታቦት በደብተራ ኦሪት በቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ እንደኖረች እመቤታችንም በመቅደስ ለ፲፪ ዓመት በቤተ መቅደስ ኖራለች ።

ታቦተ ጽዮን የዮርዳኖስን ባሕር እንዲከፈል ምክንያት እንደሆነች ድንግል ማርያምም ዮርዳኖስ የተባለ ባሕረ ሲኦል እንዲከፈልልን ምክንያት ሆናልናለች። ታቦተ ጽዮን ቅጽረ ኢያሪኮ እንዲፈርስ ምክንያት እንደሆነች የዳቢሎስን ምክር ጌታ ያፈረሰው ከድንግል ማርያም ሥጋን ነሥቶ ነው።

ቅዱስ ዳዊት በደስታ ለታቦተ ጽዮን እንደዘመረ፣ እንደዘለለና እንደሰገደ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ  በደስታ በማኅፀን ዘሏል፤  ሰግዷል።

ስለሆነም ከብሉይ ኪዳን እስከ ሐዲስ ኪዳን እግዚአብሔር ራሱን የገለጠበትን የቸርነት በዓል እግዚአብሔር በፈቀደልን ቦታ ሆነን ስናከብር ከእኛ የሚጠበቀውን በጎ ነገር እያሰብን በተግባርም እየገለጥን ከበዓሉ ረድኤትና በረከት ተሳታፊ እንሆን ዘንድ የእግዚአብሔር ቸርነት የእናታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን፡፡ አሜን።