“ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል” (ዮሐ. ፲፩፥፳፭)

እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላም አደረሳችሁ

ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን……. በዐቢይ ኃይል ወሥልጣን

አሰሮ ለሰይጣን …….. አግዓዞ ለአዳም

ሰላም.. እምይእዜሰ

ኮነ……. ፍሥሓ ወሰላም

ትንሣኤ የሚለው ቃል “ተንሥአ፤ ተነሣ” ከሚለው የግእዝ ቃል የወጣ ሲሆን ትርጉሙ መነሣት ማለት ነው፡፡ ይኸውም የሰው ልጅ ሞቶ ሥጋው ፈርሶና በስብሶ እንደማይቀር እና በዳግም ምጽአት ጊዜ እንደሚነሣ የሚያመለክት ነው፡፡ የሰው ልጅ ከፈጣሪ የተሰጠውን ትእዛዝ ባለመጠበቁ ምክንያት የሞት ሞት ተፈርዶበት ነበረ፡፡ “እንዳትሞቱ ከእርሱ አትብሉ፣ አትንኩትም” ተብሎ ነበርና፡፡ (ዘፍ. ፫፣፫) በዚህም ምክንያት ከአቤል ጀምሮ እስከ ዕለተ ምጽአት ድረስ የሰው ልጅ በሥጋ የሚሞት ሆኗል፡፡ ነገር ግን እንደሞትን አንቀርም፡፡ ሁላችንም ትንሣኤ አለን፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ በመነሣት የትንሣኤያችን በኩር ሆኖናልና፡፡(፩ኛ ቆሮ.፲፭፣፳፩)፡፡

“ሞት በሰው በኩል ስለመጣ ትንሳኤ ሙታን በሰው በኩል ሆኗል” እንዲል፡፡ ፈርሶ በስብሶ መቅረት የቀረልን አካላዊ ቃል ሥጋችን ተዋሕዶ ሰው ሆኖ ሞትን በሞቱ ድል ከነሣልን በኋላ ነው፡፡ ሊቁ በሃይማኖተ አበው “ሞተ ክርስቶስ በሞተ ዚኣነ ከመ ይቅትሎ ለሞት በሞቱ፤ ሞትን በሞቱ ያጠፋልን ዘንድ ክርስቶስ በተዋሐደው ሥጋ የእኛን ሞት ሞተ” ብሎ እንደገለጠው፡፡ (ዮሐ. ፲፩፣፳፭)

“ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ” ያለ ጌታ በጥንተ ትንሣኤ መጋቢት ፳፱ ቀን በዕለተ እሑድ ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፡፡ መልአኩም (ማር. ፲፮፣፮) “አትደንግጡ የተሰቀለውን የናዝሬቱን ኢየሱስ ትሻላችሁን? ተነሥቷል” ብሎ ለቅዱሳት አንስት ነግሯቸዋል፡፡ (ሉቃ. ፳፬፣፮)፡፡

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ የተነሣው በታላቅ ኃይልና ሥልጣን ነው፡፡ የትንሣኤያችን በኩር የሆነው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱሰስ ክርስቶስ አዳምና ልጆቹን በገባው ቃል ኪዳን መሠረት አምስት ቀን ተኩል ሲፈጸም ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷም ነፍስን ነሥቶ በድንግልና ተፀንሶ በድንግልና ተወለደ፡፡ በዚህ ምድር ላይም እየተመላለሰ ሕይወት የሆነውን ወንጌልን እያስተማረ ድውያንን እየፈወሰ፣ የተራቡትን እያበላ፣ የተጠሙትን እያጠጣ ሠላሳ ሦስት ከሦስት ወራትን በምድር ላይ ቆየ፡፡

ነገር ግን ጊዜው ሲደርስ በአይሁድ እጅ በፈቃዱ ራሱን ለመከራ መስቀል አሳልፎ ሰጠ፡፡ ከሞተ በኋላም በመቃብር ውስጥ ሦስት ቀንና ሌሊት ቆይቶ ሞትን ድል አድርጎ ተነሣ፤ ቅዱስ ዳዊት፡- “ነፍሴን በሲኦል አትተዋትምና ቅዱስህንም መበስበስን ያይ ዘንድ አትተዋትም” ያለው ይኽንን ታላቅ ምሥጢር በትንቢት ቃል ሲናገር ነው፡፡ (መዝ ፲፭፥፲)፡፡ በትንሣኤውም ለሰው ልጆች ሁሉ ትንሣኤያችንን አበሠረን፡፡ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ለቆላሲስዩስ ምእመናን በላከው መልእክቱ “…እርሱም በሁሉ ፊተኛ ይሆን ዘንድ መጀመሪያ ከሙታንም በኩር ነው…” በማለት ገልጾናል፤ (ቆላ. ፩፥፲፰) አባታችን ቅዱስ ኤጲፋንዮስም እንዲህ አስተምሯል፤ “አንድ ሆነው የሚነሡትን ትንሣኤ ዛሬ ተስፋ ያደርጋሉ፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን የሙታን ትንሣኤያቸው በኩር ነው፤ ከእንግዲህ ወዲህም ሞት የሌለበትን ትንሣኤ አስቀድሞ የተነሣ እርሱ ነው፤ ዳግመኛ ሞት አያገኘውም፡፡ (ሃይ. አበ. ፶፯፥፭)

በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረው የሰው ልጅም ሞቶ በስብሶ የሚቀር ሳይሆን የክብር ትንሣኤን ያገኛል፡፡ ጌታችን መደኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “…ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል…” በማለት በአማናዊ ቃሉ አስተምሮናልና፡፡ (ዮሐ. ፲፩፥፳፭) የሚያምኑበት የሕይወት ትንሣኤ፣ ለማያምኑበትም ደግሞ የዘለዓለም ፍርድ እንደሚጠብቃቸው ሲገልጽ “በመቃብር ያሉ ሁሉ ቃሉን የሚሰሙባት ጊዜ ትመጣለችና ስለዚህ አታድንቁ፡፡ መልካም የሠሩ ለሕይወት ትንሣኤ፣ ክፉ የሠሩም ለፍርድ ትንሣኤ ይነሣሉ” እንዲል (ዮሐ. ፭፥፳፰)፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *