“ተወልደ ኢየሱስ በቤተ ልሔም ዘይሁዳ” (ቅዱስ ያሬድ)

ውድ የግቢ ጉባኤ ተማሪዎቻችን እንኳን ለጌታችንና ለመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ አደረሰን!

በዲ/ን አብርሃም ባንቲሁን

የጌታችን ልደት በነገረ ድኅነት ትልቅ ስፍራ የያዘና እግዚአብሔር ሰው ሆኖ ዓለምን ያዳነበት ጥበቡ ፍጹም ልዩ መሆኑን ያሳየ ነው። በጌታችን ልደት ቤተ ልሔም ሰማይን የመሰለችበት፣ መስተፃርራን የነበሩ ሰውና መላእክት በአንድነት ለምስጋና የታደሙበት ነው። የእረኞች አንደበት ከመላእክት ጋር ለሰማያዊ ምስጋና ብቁ የሆነበት፤ ግዕዛን የሌላቸው እንስሳት “ሠራኢ መጋቢያችን፣ በዘባነ ኪሩቤል በሰማያት የምትገለጥ አንተ ነህ” ሲሉ እስትንፋሳቸውን የገበሩለት ነገሥታት “በመንግሠትህ ሽረት በባሕርይህ ህልፈት የሌለብህ የነገሥታት ንጉሥ አንተ ነህ” ሲሉ ወርቅን ለመንግሥቱ፣ ዕጣንን ለክህነቱ፣ ከርቤን ለሕማሙ እጅ መንሻን ያበረከቱለት፤ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በግብረ መንፈስ ቅዱስ ተፀንሶ በፍጹም ድንግልና በከብቶች በረት ተወለደ፡፡  ይህ ልደት በእውነት ልዩ ነው።

ይህን የጌታችንን ልደት አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በአርጋኖን (ዘሰኑይ) ላይ እንዲህ ሲል በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ በአድናቆት ያመሰግናል “ለዚህ ልደት መስገድ መገዛት ይገባል፤ ክብር ምስጋና ለዚህ ልደት ይገባል፤ ጌትነትና ገናንነት፣ ኀያልነት፣ እልልታ፣ ግርግታ ለዚህ ልደት ይገባል፡፡ ይህ ጥበብ ፍልስፍና ዕፁብ ድንቅ ነው፡፡ ለዚህ አንክሮ ይገባል፤ ይህም የሥጋዊ ምሥጢር ምን ይረቅ? ምን ይጠልቅ? ለዚህ አንክሮ ይገባል፡፡ ይህም ሰው መሆን ሥጋ መልበስ እጅግ ዕፁብ ድንቅ ነው!” ይላል።

ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊም በረቡዕ ውዳሴ ማርያም በጌታ ልደት የተደረገልንን ድንቅ የማዳን ሥራ በተናገረበት ድርሳኑ እንዲህ ነበር ያለው፦ “በጨለማና በሞት ጥላ ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች ታላቅ ብርሃን ወጣላቸው፤ በቅዱሳን የሚያድር እግዚአብሔር እኛን ለማዳን ልዩ ከሆነች ድንግል ሰው ሆኗልና ኑ ይህን ድንቅ እዩ፣ ስለተገለጠልን ምሥጢር ምስጋና አቅርቡ፤ ሰው የማይሆን ሰው ሆኗልና፤ ቃል ተዋሕዷልና፤ ቅድምና የሌለው ሥጋ ቀዳማዊ ሆነ፣ ዘመን የማይቆጠርለት መለኮት ዘመን ተቆጠረለት።” በማለት ሲያደንቅ፡-  ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ደግሞ “ይህች ቤተ ልሔም መንግሥተ ሰማያትን መሰለች” በማለት የጌታ ልደት ልዩ መሆኑን ይገልጻል።

ቤተ ልሔም ማለት ቤተ ኅብስት፣ የእንጀራ ቤት ማለት ነው። ይህም ካሌብ እስራኤል ዘሥጋ ምድረ ርስት፣ ኢያሪኮን “ኃይል ዘእግዚአብሔር ኲናት ዘኢያሱ” ብለው በኢያሱ መስፍንነት ሲወርሱ ከኢያሱ የተሰጠችው ምድር፣ ኬብሮን ነበረች። ይህችም የይሁዳ ምድር በኋላም የቅዱስ ዳዊት ከተማ የሆነች ናት። አስቀድሞ ካሌብ ከብታ የምትባል ሚስት አግብቶ በሚስቱ ከብታ አላት፤ ትርጓሜውም የምስጋና ቤት ማለት ነው፤ ይህም ካሌብ በመንፈሰ እግዚአብሔር በዚህች ምድር የሚገለጠውን የክርስቶስ የልደቱን ነገር እና የመላእክትን ምስጋና ስለተረዳ ነበር። በኋላም ካሌብ ኤፍራታ የምትባል ሚስት አገባ ቦታዋን በዚህች ሚስቱ እንደገና ኤፍራታ ብሎ ጠራት። ኤፍራታ ማለት ፀዋሪተ ፍሬ፣ ፍሬ በውስጧ ያለባት ማለት ነው።

ይህችውም የእመቤታችን ምሳሌ ናት የሕይወት ፍሬ ክርስቶስን ወልዳልናለችና፤ “አንቲ ውእቱ ዕፅ ቡሩክ ዕፀ ሕይወት ዕፀ መድኃኒት ህየንተ ዕፀ ሕይወት ዘውስተ ገነት ዘኮንኪ ዕፀ ሕይወት በዲበምድር ፍሬኪኒ ፍሬ ሕይወት ውእቱ፤ አንቺ የተባረክሽ ዕፅ ነሽ፤ የሕይወትና የደኅንነት ዕፅ ነሽ፤ በገነት ውስጥ ባለው ዕፅ ሕይወት ፈንታ በዚህ ዓለም የሕይወት ዕፅ ሆንሽ፤ ፍሬሽም የሕይወት ፍሬ ነው ” እንዳለ ቅዱስ ያሬድ በአንቀጸ ብርሃን።

ቤተ ልሔም ይህን ስያሜዋን ያገኘችው ካሌብ ከኤፍራታ ባገኘው ልጁ በልሔም ነው፤ ልሔም ማለት ኅብስት፣ እንጀራ ማለት ነው፡፡ ይህም ምሳሌነቱ የጌታ ነው፤ ይኸውም አማናዊ፣ እውነተኛ የሕይወት እንጀራ፣ ኅብስተ ሕይወት ክርስቶስ ሥጋውን ቆርሶ ደሙን አፍስሶ ሊያድነን በቤተ ልሔም እውነተኛ እንጀራ ሆኖ ተወልዶልናልና ነው። “ከሰማይ የወረደ ሕያው እንጀራ እኔ ነኝ፤ ሰው ከዚህ እንጀራ ቢበላ ለዘለዓለም ይኖራል፤ እኔም ስለ ዓለም ሕይወት የምሰጠው እንጀራ ሥጋዬ ነው።” እንዲል (ዮሐ. ፮፥፶፩)።

በክርስቶስ ልደት መላእክት ባልተለመደ ሁኔታ ከሰዎች ጋር ተባብረው “ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ሥምረቱ ለሰብእ፤ በሰማያት ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን ሰላምም ለሰው ልጅ በምድር እርሱ በሚፈቅደው” እያሉ ንጉሥ ክርስቶስን አመሰገኑ። (ሉቃ. ፪፥፲፬) በሰማያት በዘባነ ኪሩቤል የሚገለጥ፤ ፍጹማን ግሩማን በሚሆኑ መላእክት፣ ሊቃነ መላእክት፣ ሥልጣናት፣ አጋእዝት የሚመሰገን ሰማያዊው ንጉሥ ዛሬ ስለ እኛ ፍቅር ሲል ሊነገር በማይችል ፍጹም ትሕትና እንደ ሕፃናት ተወለደ፣ በእናቱ እቅፍ ሆኖ ከኃጢአት በቀር የእኛን ባሕርይ ባሕርዩ አድርጎ ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው ሆኗልና።

”ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኀያል አምላክ፥ የዘለዓለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል።” (ኢሳ. ፱፥፮) ተብሎ እንደተጻፈ።

ለዚህ ለክርስቶስ ፍቅር አንክሮ ይገባል፤ በሙሉ አፍአዊና ውሳጣዊ ኅሊናችን እርሱን ዘወትር እናመስግን። ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ዻውሎስ ይህን ፍጹም ፍቅር ለሰው ልጅ በኃጢኣት ተዳድፈን ለነበርን መደረጉን እያሰበ በአንክሮ “ታስበው ዘንድ ሰው ምንድር ነው? ወይስ ትጐበኘው ዘንድ የሰው ልጅ ምንድር ነው? ከመላእክት ይልቅ በጥቂት አሳነስኸው፤ የክብርና የምስጋና ዘውድ ጫንህለት፥ በእጆችህም ሥራ ላይ ሾምኸው፤ ሁሉን ከእግሮቹ በታች አስገዛህለት” (ዕብ. ፪፥፮) በማለት ይናገራል። እኛም በክርስቶስ የተጠራን ሁላችን ይህን የአምላክ ፍቅር ዘወትር በልቡናችን እንድንሥልና ከሰው ጋር ሁሉ በትሕትናና በፍቅር እንድንኖር ይመክረናል፡፡

“እያንዳንዱ ለራሱ የሚጠቅመውን አይመልከት፥ ለባልንጀራው ደግሞ እንጂ፤ በክርስቶስ ኢየሱስ ያለች ይህች ሐሳብ በእናንተ ዘንድ ደግሞ ትኑር፤ እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከሰው ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ አልቆጠረም ነገር ግን፥ የባሪያውን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ” (ፊል. ፪፥፭) ይለናል ።

ይህ የጌታ ልደት የቤተ ክርስቲያን አንድነት ነው። ሁሉ በአንድነት የተሰባሰቡበት በጋራ የዘመሩበት፤ በዚህች በበረት፣ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ምሳሌ በሆነችው ጌታችን ከመሐል ከእናቱ ጋር እንዲሁም አረጋዊ ዮሴፍ ከማኅበረ ጻድቃን፣ ሰማያውያን መላእክት፣ እረኞች፣ ሰብአ ሰገል፣ እንስሳትም ሳይቀሩ በአንድነት የተገኙባት የፍቅርና የአንድነት ቤት ናት። ስለዚህ እኛም የክርስቶስ አባግዓ መርዔቱ፣ የመንጋው በጎች፣ የቤተ ክርስቲያን ልጆች በፍጹም አንድነት መኖር እንዳለብን ያሳስበናል፡፡

“ወንድሞች ሆይ፥ ሁላችሁ አንድ ንግግር እንድትናገሩ፤ በአንድ ልብና በአንድ ሐሳብም የተባበራችሁ እንድትሆኑ እንጂ መለያየት በመካከላችሁ እንዳይሆን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እለምናችኋለሁ።” (፩ኛቆሮ. ፩፥፲) በማለት ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ዻውሎስ ያስተምረናል።

ውድ የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች፡- የጌታችን ልደት በጨለማና በሞት ጥላ ውስጥ ለምንኖር ለእኛ ታላቅ የብርሃን ቀን ነው። በዚህ የልደት ብርሃን ቀን እንደ ቤተ ልሔም እረኞች ከቤተሰባችሁ ርቃችሁ ትምህርታችሁን በመከታተል ላይ የምትገኙ ሲሆን በጌታችን ልደት ቀን አንድ በምታደረገን ቤተ ልሔም የተወለደው ንጉሥ ክርስቶስ ዕለት ዕለት የሚሰዋባት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንደ እረኞቹና እንደ መላእክቱ ከሊቃውንቱና ከምእመናን ጋር በምስጋና ልታሳልፉ ይገባል፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምና አረጋዊ ዮሴፍ ለመቆጠር፤ ቅዱሳን መላእክት ለምስጋና፤ እረኞች የተወለደውን መድኃኒት ለማየት፤ የጥበብ ሰዎች (ሰብአ ሰገል) ቁሳዊና መንፈሳዊ ስጦታን ለመስጠት፤ የሄሮድስ ወታደሮች ለመሰለል በጌታ ልደት በቤተልሔም ተሰበሰቡ።

ሰብአ ሰገል ወርቅ፣ ዕጣን፣ ከርቤን ሊሰጡት ይዘውለት ሄዱ፤ እናንተስ ለጌታችን ልደት ምን ይዛችሁለት ልትሄዱ ምን ልትሰጡት አስባችሁ ይሆን?

ለእግዚአብሔርስ ምንም የምንሰጠው ነገር አይኖረንም፤ ከእርሱ ሁል ጊዜ እንቀበላለን እንጂ፤ እርሱማ ሁሉ የርሱ የሆነ፤ ሁሉን ለእኛ የሰጠን፣ የሚሰጠንም፡ አንድያ ልጁን እስከ መስጠት የወደደን፡ የሚሰጥ እንጂ የማይሰጡት አምላክ ነው። እርሱ  ከእኛ የሚፈልገው አንድ ስጦታ አለ። ይህ ስጦታ ምንድነው? ያልን እንደሆነ መልሱ ቅዱሳን አርሱን እንደመሰሉት እኛም እርሱን እንድመስል ነው። “እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እናንተም እኔን ምሰሉ።” እንዲል (፩ኛ ቆሮ. ፲፩፥፩)

እርሱ ራሱን ለኛ እንደሰጠን እኛም ራሳችንን ለእርሱ እንስጠው። ለመንግሥቱም የምንገባ እንሆን ዘንድ በብርሃኑ እንመላለስ፦ ንስሓ እንግባ፤ የሰጠንም እንቀበለው፤ ሥጋውን እንብላ ደሙንም እንጠጣ።

እርሱ የሰላም አለቃ እንደሆነ እኛም የሰላም ሰዎች ሰላማውያን እንሁን። እምነታችንን፣ ተስፋችንን፣ ፍቅራችንን አጽንተን እርሱን መስለን በብርሃኑ (በትሕትና፣ በበጎነት፣…) እንመላለስ፤ መለያየትን ከእኛ እናርቅ የዚያን ጊዜ ከመላእክት ጋር ደስ እያለን፦ “ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ሥምረቱ ለሰብእ፤ በሰማያት ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን ሰላምም ለሰው ልጅ በምድር እርሱ በሚፈቅደው” (ሉቃ. ፪፥፲፬) እያልን እንዘምራለን። የጌታችንና የአምላካችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደቱ በዓል በረከት ከሁላችን ጋር ይሁን። አሜን።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር። አሜን!

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *