ተቀጸል ጽጌ

ተቀጸል ጽጌ ማለት የአበባ በዓል ማለት ነው፡፡ ክረምቱ አይሎ ምድር በዝናብ የምትረሰርስበት፣ ገበሬው ተስፋውን ለእግዚአብሔር ሰጥቶ ዝናቡን ድጡን ተቋቁሞ ሲያርስ ከርሞ የዘራው ለፍሬ ይበቃ ዘንድ ፀሐይ ብርሃን የምትፈነጥቅበትን ወር መስከረምን በጉጉት ይጠባበቃል፡፡ ምድርም በአበቦች አጊጣና አሸብርቃ ደምቃ በምትታይበት ወቅት ጠብቃ መስከረም ፲ በየዓመቱ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ተቀጸል ጽጌ (የአበባ በዓል)ን ታከብራለች፡፡

ታሪኩ በ፮ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያን ሲመሩ ከነበሩት ከዐፄ ገብረ መስቀል ዘመን ጀምራል፡፡ ይህ በዓል እስከ ፲ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ መስከረም ፳፭ ቀን ሲከበር እንደነበር መዛግብት ያስረዳሉ፡፡

በ፲ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በግብፅ ይኖሩ የነበሩ ክርቲያኖች ግን በእስላሞቹ ከፍተኛ ስቃይና መከራ ይደርስባቸው ስለነበር ለኢትዮጵያዊው ንጉሥ ዐፄ ዳዊት ከሚደርስባቸው ስቃይ እንዲታደጓቸው መልእክት ላኩ፡፡ ዐፄ ዳዊትም መልእክቱ እንደደረሳው ስለ ሃይማኖታቸው ቀንተው በእግዚአብሔር ፈቃድ ተመርተው ፳ሺህ ሠራዊት አስከትለው የግብፅ ክርስቲያኖችን ለመታደግ ወደ ግብፅ ዘመቱ፡፡

የግብፅ እስላሞችም ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነውን የዐፄ ዳዊት ሠራዊትን መቋቋም እንደማይችሉ ሲረዱ ከክርስቲያን ወንድሞቻቸው ጋር ዕርቅ አውርደው በሰላም መኖር ይጀምራሉ፡፡ ይህንን የተረዱት የግብጽፅ ክርስቲያኖች ግን ስላደረጉላቸው መልካም ውለታ ፲፪ ሺህ ወቄት ወርቅ ከምስጋና ጋር ወደ ዐፄ ዳዊት ይልካሉ፡፡ ነገር ግን የዐፄ ዳዊት ፍላጎት ክርስቲያኖቹ ከላኩት ወርቅ ይልቅ በኢትዮጵያ የገባውን ድርቅ እንዲታደግላቸው፣ እግዚአብሔርም ምሕረቱን እንዲልክ ለረጅም ዘመናት በግብፅ የቆየውን ጌታችን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበትን ግማደ መስቀል እንዲልኩላቸው ስለነበር የላኩላቸውን ወርቅ መለሱላቸው፡፡

የግብፅ ክርስቲያኖችም በጥያቄአቸው መሠረት ግማደ መስቀሉን፣ በዕለተ ዐርብ ለብሶት የነበረው ቀይ ልብስ (ከለሜዳው)፤ ሀሞት የጠጣበት ሰፍነግ (ጽዋ)፤ ዮሐንስ የሳለው ኩርዓተ ርዕሱ ሥዕል እንዲሁም የቅዱሳን አፅም ጋር ላኩላቸው፡፡ በንጉሡ እና በሠራዊቱ ታጅቦ ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡም ባለፉበት መንገድ ሁሉ ሕዝቡ፣ ካህናቱና ሊቃውንቱ በዝማሬ፣ በእልልታና በጭብጨባ በደስታ እያጀቡ መስከረም ፲ ቀን ተቀበሏቸው፡፡ ይህንንም ልማድ አድርገው በኢትዮጵያ የነገሡ ነገሥታት ሁሉ “የዐፄ መስቀል በዓል” ብለው ሰይመውታል፡፡ (መጽሐፈ ጤፉት ገጽ ፶-፶፩፣ የመስከረም ፲ ስንክሳር አርኬ)

የጌታችን ግማደ መስቀል ከአሌክሳንደርያ ወደ ኢትዮጵያ መስከረም ፲ ቀን በመግባቱ የተቀጸል ጽጌ በዓል የዐፄ መስቀል በዓል እየተባለ ቀኑም ከመስከረም ፳፭ ወደ መስከረም ፲ ተዛውሮ ሲከበር ኖሯል፡፡

ስለዚህ ጉዳይ ድርሳነ መስቀልም እንዲህ ይላል፤ “መስከረም ዐሥር ቀንም በንጉሥ ከተማ መካከል በመስቀል ምልክት ሰንደቅ ዓላማ ተተከለ ስለዚህም ያቺ ዕለት የዐፄ መስቀል ተባለች” ይላል፡፡ (ድርሳነ መስቀል ገጽ ፪፻፺፬)

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *