ባልንጀራ
ክፍል አንድ
በእንዳለ ደምስስ
ባልንጀራ የሚለውን ቃል ደስታ ተክለ ወልድ በመዝገበ ቃላት መጽሐፋቸው፡- “እኩያ፣ ባልደረባ፣ አቻ፣ አብሮ አደግ ጓደኛ፣ እንጀራ አቋራሽ” በ ማለት ሲተረጉሙት ባልንጀርነትን ደግሞ “እኩያነት፣ ባልደረብነት” በማለት ይፈቱታል፡፡
ባልንጀራ ክፉም ሆነ መልካም ነገር ሲገጥመን አብሮ የሚያዝንና የሚደሰት የልብ ወዳጅ፣ መልካሙን መንገድ የሚያሳይ፣ … ማለታችን ነው፡፡ ባልንጀርነት አብሮ በማደግ፣ አብሮ በመማር፣ አብሮ በመሥራት እንዲሁም በሙያ አጋርነት በመሳሰሉት ሁኔታዎች ሊፈጠር ይችላል፡፡ ይህ የባልንጀርነት ቁርኝት እየዳበረ የሚመጣ እንደመሆኑ መጠን በተለያዩ ምክንያቶችም ሊፈርስ ወይም ሊከስም ይችላል፡፡
ክፉ ባልንጀራ የሌላውን ሕይወት ያጨልማል፣ መልካምን ከማሰብና ከማድረግ ክፉ ሐሳቦችን ያመነጫል፣ ተግባራዊም ያደርጋል፡፡ አባቶችቻን ለዚህ ነው “ክፉ ባልንጀራ አይግጠምህ፤ ከክፉ ባልንጀራ ራቅ” እያሉ የሚመክሩት፡፡ ክፉ ባልንጀራ መልካም የሆነውን ወዳጁን ጠባይ ቀስ በቀስ በመለወጥ በሄደበት እንዲሄድ፣ በዋለበት እንዲውል፣ ከመልካም ቦታዎች ይልቅ ኃጢአትን ወደሚሠራባቸው ስፍራዎች ማለትም መንፈሳዊ ቦታዎችን አስጥሎ ወደ ጭፈራ ቤቶች፣ ዝሙት ወደሚሠራባቸውና ልዩ ልዩ ያልተገቡና በማኅበረሰቡም በእግዚአብሔርም የተጠሉ ተግባራት ወደሚከናወንባቸው ቦታዎች በመሄድ ጠፍተው እንዲቀሩ ምክንያት ይሆናል፡፡
ለዚህ እንደ ምሳሌ የሔዋንና የዲያብሎስ ወዳጅነት ማየት ይቻላል፡፡ ሰይጣን ከነበረው ክብር አምላክነትን በመሻቱ ምክንያት ከተጣለ በኋላ ለክፉ ሥራው ተባባሪ ለማግኘት በእባብ ላይ አድሮ ወደ ሔዋን ቀረበ፡፡ የአዳምና ሔዋን በገነት ውስጥ በተድላ በደስታ መኖር አበሳጭቶታል፡፡ እኔ ወድቄ ሌላው ለምን ይኖራል? በሚል በእባብ ላይ አድሮ ከሔዋን ጋር ባልንጀርነትን መሠረተ፡፡ እባብም ሴቲቱን “እግዚአብሔር በገነት ካለው ዛፍ ሁሉ አትብሉ ያላችሁ ለምንድነው?” አላት፡፡ ሴቲቱም “በገነት መካከል ካለው ከሚያፈራው ዛፍ ፍሬ እንበላለን፤ ነገር ግን በገነት መካከል ካለው ከዛፉ ፍሬ፤ እግዚአብሔር አለ “እንዳትሞቱ ከእርሱ አትብሉ፣ አትንኩትም” አለን በማለት አስረዳችው፡፡ (ዘፍ.፫፥፫)
በእባብ ላይ ያደረው ሰይጣንም “ሞትን አትሞቱም፤ ከእርሱ በበላችሁ ቀን ዐይኖቻችሁ እንዲከፈቱ እንደ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው እንጂ፡፡” አላት፡፡ ሔዋንም እጅግ ለመብላት ጓጓች፤ ከዕፀ በለሱ ቀጥፋም ለአዳም ሰጠችው፤ ሁለቱም በመብላታቸው ዐይኞቻቸው ተከፈቱ፤ እግዚአብሔርንም አስቆጡት፤ ከገነት ወደ ምደረ ፋይድ ተጣሉ፡፡ ይህ ሁሉ ከክፉ ባልንጀራ ጋር ወዳጅነት መመሠረት ያስከተለው ጥፋት ነው፡፡
ባልንጀርነትን ከሚያበላሹ ነገሮች መካከል ጥቂቶቹን ብንመለከት፡-
በመንፈሳዊ ሕይወት መዛል፡- በመንፈሳዊ ሕይወት ስንዝል ለሥጋዊ ፍላጎት ተላልፈን እንሰጣለን፡፡ ነፍሳችን በሥጋችን ላይ ትሠለጥናለች፡፡ በተለይ በወጣትነት ዘመናችን ስሜታዊነት ስለሚያይልብን ይህንንም ያንንም ለመሞከር በምናደረግው ጥረት ውስጥ መንፈሳዊ ሕይወታችን ይጎዳል፡፡ በዚህ ወቅት መንፈሳውያን ወንድሞቻችንና አኅቶቻችንን ትተን ከማይመስሉን ጋር የሥጋን ሥራ ለመሥራት እንፈጥናል፡፡ ይህ ደግሞ በሕወታችን ውስጥ ከእግዚአብሔር ጋር እንኖራለን፣ እናሳካዋለንም ብለን ያሰብናቸው ነገሮች ሁሉ ከንቱ ሆነው ይቀራሉ፡፡ ቀድሞ የነበረንን ማንነት እያጣን መንፈሳዊነትን እርግፍ አድርገን እንድንተው ያደርገናል፡፡
ነገር ግን ከዚህ ይልቅ መንፈሳዊ ሕይወታችንን ሊያጠናክሩልን፣ ብንወድቅ የሚያነሡንን፣ ብንደክም የሚያበረቱንን መልካም ወንድሞችና እኅቶችን መጠጋት ይገባል፡፡
የአቻ ግፊት፡- በብዙ ወጣቶች ዘንድ በተለይም በግቢ ጉባኤት ተማሪዎች ዘንድ ጎልተው ከሚታዩ ችግሮች አንዱ የአቻ ግፊት ነው፡፡ ከመንፈሳዊው ሕይወት እንድንወጣ ብልጭልጩን ዓለም እያሳዩ ከእግዚአብሔር እንድንለይ ከሚያደርጉን አቻዎቻችን መራቅ ተገቢ ነው፡፡ በአቻ ግፊት ምክንያት አዲስ ጠባይ እንድንይዝና ለማይገቡ ክፉ ጠባይት ተላልፈን እንዳንሰጥ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ “ሁሉን መርምሩ፤ መልካም የሆነው ያዙ” ተብለናልና፡፡ (፩ተሰ.፭፥፳፩)
በወጣትነት ዘመናችን በተለይም በግቢ ጉባኤ ሕይወታችን ውስጥ መልካም እየመሰሉን ከእግዚአብሔር አንድነት ከሚለዩን በዙሪያችን ካሉ ባልንጀሮቻችን መራቅ ይጠበቅብናል፡፡ ለመንፈሳዊ ሕይወታችን እንቅፋት የሆኑትን በመራቅ መንፈሳዊ ወንድሞቻችንና እኅቶቻችንን መከተል፣ መንፈሳዊ መጻሕፍትን በማንበብና ከመንፈሳዊ ሕይወታችን ሊያርቁን ከሚችሉ አካባቢዎች መራቅና ጊዜያችንን በአግባቡ በመምራት በአቻ ግፊት እንዳንወድቅ ይረዳናል፡፡
የሚጠቅመንና የሚጎዳንን መለየት፣ አባቶችን ማማከር፣ ወደ መልካም መንገድ ሊመሩን የሚችሉ አርአያ የምናደርጋቸውን ወንድሞችና እኅቶችን መከተል፣ ዘወትር በመንፈሳዊ ሕይወታችን በመትጋት የአቻ ግፊትን ተጽእኖ በመቋቋም በራስ መተማመንን ማጎልበት ይጠበቅብናል፡፡
ከላይ ከተመለከትናቸው ውጪ ክፉ ባልንጀርነት የሚፈጥረብን ተጽእኖ ቀላል አይደለም፡፡ በዚህም ምክንያት ክፉ ባልንጀርነት አለመተማመንን፣ ክፉ ጠባያት እንድንለምድ፣ ራስን ብቻ እንደንወድ፣ … ከመንፈሳዊነት እንድንወጣ ሊያደርገን ይችላል፡፡
ሀ. አለመተማመን፡- በባልንጀሮች መካከል መልካሙን ግንኙነት ከማጠናከር ፋንታ የግል ጥቅምን በመሻት ወይም በባልንጀራ ላይ በመቅናትና የባልንጀራን የሆነን ሁሉ በመመኘት በሚፈጠሩ ያልተገቡ ጠባያትና ድርጊቶች ምክንያት ጤናማ የባልንጀርነት ግንኙነት ሊበላሽ ይችላል፡፡ ይህም በባልንጀሮች መካከል አለመተማመንን ይፈጥራል፡፡
ራስን ልዩ አድርጎ መቁጠር፣ በባልንጀራ ላይ የበላይ ሆኖ ለመታየት መጣር፣ ራስን ብቻ መውደድ፣ … ወዘተ በሁለቱ አካላት መካከል አለመተማንን ወደ ከፍተኛ ደረጃ ሊያደርስ ይችላል፡፡ ይህም እስከ ጠላትነት ሊያደረስ የሚችል አካሄድ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ በሥነ ምግባር ያለመታነጽ፣ ከመንፈሳዊ ሕይወት ማፈንገጥና ለሥጋ ምኞትና ፍላጎት ብቻ ማደር በጎውን መንገድ እንዳናስብ መንገዱን ስለሚዘጋ ባልንጀራን ወደ ሥጋዊ አስተሳሳብና ድርጊት እንዲመራ በር ይከፍታል፡፡
ለ. ክፉ ጠባያትን ማስለመድ፡- በባልንጀሮች መካከል መልካም ጠባያት እንዳለ ሁሉ ክፉ የምንላቸው ጠባያትን ሊንጸባረቁ ይችላሉ፡፡ በተለይም የጓደኛ አመራረጣችንና አያያዛችን ወደማንፈልገው አካሄድ ሊመራን ይችላል።፡ ይህም ሕይወታችንን በመልካም ሥነ ምግባር እንዳንመራ እንቅፋት ይሆንብናል፡፡ ለመሆኑ ባልንጀራችን ማነው? በሕይወት፣ በባህል፣ በእምነት እንመስለዋለን? ውሎውን እንውላለን? በሃይማኖት አንድ ነን? የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ዶግማ፣ ቀኖና፣ ትውፊትና ሥርዓትን ይጠብቃል? እነዚህንና ሌሎችንም መመርመር ያስፈልጋል፡፡
ቤተ ክርስቲያንን አስጥሎ ለሥጋ ብቻ በማድላት ከጸሎት ይልቅ ሙዚቃን፣ ከመንፈሳዊ አገልግሎት ይልቅ ሥጋን ለመስደሰት የሚፈጥን ከሆነ ይህ ክፉ የክፉ ባልንጀራ ጠባይ ነውና መራቅ ያስፈልጋል፡፡ ሁል ጊዜ ከመልካም ይልቅ እግዚአብሔርንና አገልግሎትን የሚያስጥሉ ክፉ ጠባያትን የሚያስለምደን በመሆኑ ከዚህ ጋር ከመተባበር ልንቆጠብ ያስፈልጋል፡፡ ከማይመስሉን ጋር በክፉ መጠመድ አይገባም፡፡ ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋልና፡፡ (፩ቆሮ.፲፭፥፴፫)
ሐ. ራስን ብቻ መውደድ፡- ራሳችንን ብቻ የምንወድ ከሆነ ለሌላው ግድ አይኖረንም፡፡ ሁል ጊዜ ራሳችንን በማስቀደማችን ለሌሎች እንዳንኖር፣ ለባንጀሮቻችን ትኩረት እንዳንሰጥና ባልንጀሮቻችን እኛ በቀደድነው መንገድ ብቻ እንዲጓዙ ተጽእኖ እናሳድራለን፡፡ ይህ አካሄድ ደግሞ “እኔ ብቻ” አስተሳሰብን በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጎለብት ስለሚያደርግ ከምናመልከው እግዚአብሔር ይለየናል፤ ወደ ክፋትም ይመራናል፡፡ ራሳችንን ብቻ በወደድን ቁጥር ለሌላው ክብር ለመስጠት እንቸገራለን፡፡ ስለዚህ ባልንጀራችን በተቸገረ ጊዜ ከአጠገቡ ከመቆም ይልቅ ውድቀቱ እንዲፋጠን ግፊት እናደርጋለን፡፡ በትምህርትም ይሁን በልዩ ልዩ ዕውቀት፣ በሀብት፣ … የሚበልጠን መስሎ ከተሰማን ከእርሱ ከመማር ይልቅ ለመጣል ጥረት እናደርጋለን፡፡ ይህ አካሄድ ደግሞ ከእግዚአብሔርም ከሰውም ሳንሆን እንድንቀር ያደርግናል፡፡
በግቢ ጉባኤያት ውስጥ የምንሳተፈው እርስ በእርስ ተደረዳድተን ስንሳተፍ አንዱ ያላወቀውን በማሳወቅ፣ በመረዳዳት መጓዝ እንጂ ሊበልጠኝ ይችላል በሚል ሰበብ በባልንጀራ ላይ ክፉ ማድረግን ልንጸየፍ ይገባል፡፡ ግቢ ጉባኤያት እግዚአብሔርን የምናውቅበት፣ በዕውቀት በጥበብ የምንበለጽግበትና መልካም ባልንጀርነትን የምንመሠረትበት ለሌሎችም አርአያ ሆነን የምንገኝበት መልካም አጋጠሚ መሆኑን በመረዳት ራስን ብቻ ከመውደድ አልፈን መንፈሳዊ ፍሬ ልናፈራ ይጠበቅብናል፡፡
ባልንጀራን መውደድ በረከትን ያሰጣል፤ ከእግዚአብሔርም ጋር ሕብረት እንድንፈጠር ይረዳናል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ ሲሆን የእኛን ሥጋ ለብሷልና እኛን ያድነን ዘንድ በቀራንዮ አደባባይ በመስቀል ላይ ተሰቅሏል፡፡ ሰውን በመውደዱ እስከ ሞት ድረስም የታመነ ሆነ፡፡ “ስለ ወዳጆቹ ሕይወቱን አሳልፎ የሚሰጥ ሰው ያለ እንደሆነ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር የለም” እንዲል (ዮሐ.፲፭፥፲፫) ቅዱስ ዮሐንስ፡፡
ክፉ ባልንጀርነት በተመለከተ እነዚህን ከላይ የጠቀስናቸውን ነጥቦች አነሣን እንጂ ሌሎችንም ማንሣት ይቻላል፡፡
በተቃራኒው ራስን ከክፉ ባልንጀራ በማራቅ መልካም ባልንጀርነትን መመሥረትና በምግባር በሃይማኖት ታንጾ መኖር ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት እንድናጠናክር ያደርገናል፡፡
ይቆየን
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!