“በጽዮን መለከትን ንፉ፤ ጾምንም ቀድሱ፤ ጉባኤውንም ዐውጁ” (ኢዩ. ፪ ÷፲፭)
በኃይለ ኢየሱስ ዘጼዴንያ
ክፍል ሁለት
የጾመ ነቢያት ሰንበታት መጠሪያ
ዘመነ ስብከት
በነቢያት ጾም ውስጥ ከታኅሣሥ ፯-፲፫ ቀን ያለው ዘመን ዘመነ ስብከት ይባላል፡፡ ዘመነ ስብከት የተባለበት ምክንያትም ነቢያት የጌታን በሥጋ መምጣት አምልተውና አስፍተው በትንቢትና በትምህርት መስበካቸውን ቤተ ክርስቲያን እያሰበች ሰውን ለማዳን ወደ ምድር የመጣውን አምላክ የምትሰብክበት ወቅት በመሆኑ ነው፡፡
የዘመነ ስብከት የመጀመሪያው ሰንበት (እሑድ) ስብከት ይባላል፡፡
በዚህ ሰንበት በኦሪተ ሙሴ፣ በነቢያትና በመዝሙራት አስቀድሞ ስለ ክርስቶስ ሥጋን ተዋሕዶ ሰው መሆኑ ትንቢት ተነግሮ፣ ምሳሌ ተመስሎ፣ ሱባኤ ተቆጥሮ እንደነበር ይነገራል፤ ይሰበካልም፡፡ ስብከት ማለት ሰውን ከእግዚአብሔር ጋር የሚያገናኝ ትምህርት ማለት ሲሆን በዚህ ሳምንት ከልደተ አብርሃም እስከ ልደተ ዳዊት ባለው ትውልድ ውስጥ ስለ ክርስቶስ ሰው መሆን የተሰበከው ስብከት ይታሰባል፡፡
በስብከት ሰንበት ወልደ እግዚአብሔር ከሙሴ ጀምሮ የተነሡ ነቢያት ስለ አምላክ ሰው መሆን የተናገሩትን ይነበባል፡፡ “ያም ቃል ሥጋ ሆነ፤ በእኛም አደረ፤ ለአባቱ አንድ እንደሆነ ልጅ ክብር ያለ ክብሩን አየን፤ ጸጋንና እውነትን የተመላ ነው፡፡” (ዮሐ. ፩÷፲፬)፤ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊትም “እጅህን ከአርያም ላክ አድነኝም” (መዝ ፻፵፫÷፯) በማለት ስለ ክርስቶስ ማዳን በትንቢት መነጽር ተመልክቶ የዘመረው የመዝሙር ክፍል እንዲሁ ይሰበካል፡፡
የዘመነ ስብከት ሁለተኛው ሰንበት ብርሃን ይባላል፡፡
ነቢያት ብርሃን ጌታ ይወለዳል ብለው ስለ መስበካቸው፣ እውነተኛ ብርሃን ይመጣል ብለው ሰለማስተማራቸው የሚታሰብበት ሲሆን በዚሁ ኢየሱስ ክርስቶስ አማናዊ ብርሃን መሆኑ ይሰበካል፤ ይዘመራልም፡፡ ከዚሁ ጋር ዘመነ ብሉይ መከራ ሥጋ፣ መከራ ነፍስ የጸናበት፣ የሰው ልጅ ብርሃን ከሆነው አምላክ ጋር የተራራቀበት ስለነበር ነቢያት ያሉበትን ያን ዘመን ጨለማ ብለው በመግለጥ የነፍሳችን ብርሃን ይወለዳል፣ እውነተኛ ብርሃን ይመጣል ብለው ስለመስበካቸው የሚታሰብበት ሳምንት ነው። በዚህ ሳምንት ከልደተ ዳዊት እስከ ፍልሰተ ባቢሎን የነበረው ፲፬ ትውልድ ይታሰብበታል፡፡
የዘመነ ስብከት ሦስተኛው ሰንበት ኖላዊ ይባላል፡፡
ኖላዊ ማለት “እረኛ” ወይም “ጠባቂ” ማለት ሲሆን በዚህ ዕለት ነቢያት የእግዚአብሔር ልጅ እውነተኛ ጠባቂ ሆኖ ይገለጣል ብለው መተንበያቸው እና ኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ጠባቂ መሆኑ ቤተ ክርስቲያናችን እያሰበች የምትዘምርበት፣ የምትቀድስበት፣ የምታመሰግንበት ዕለት ነው፡፡
ነቢያት ራሳቸውንና ሕዝበ እስራኤልን ብሎም ዓለምን እረኛቸው እንደተዋቸው በጎች በመቁጠር ስለ እውነተኛው እረኛ መምጣት ትንቢት ተናግረዋል። በዚህ ሰንበት ከፍልሰተ ባቢሎን እስከ ልደተ ክርስቶስ ድረስ ያለው አሥራ አራት ትውልድ ይታሰባል። በዚህ ዘመን እሥራኤላውያን ከሀገራቸው ተሰደው በባቢሎን ፸ ዘመን ከኖሩ በኋላ ዘሩባቤልን አንግሦላቸው ይዟቸው እንዲመለስ ተደርጓል፡፡ ከዚያ በፊት እሥራኤል ጠባቂ እንደሌለው መንጋ ተበታትነው ሲኖሩ ነቢያት ከኪሩቤል ላይ የሚገለጥ እረኛቸው እንዲገለጥ የእሥራኤል ጠባቂያቸው ሆይ፣ አድምጥ እያሉ የጠየቁበት መታሰቢያ ነው፡፡ (መዝ. ፸፱÷፩-፫)
መዝሙሩም “ኖላዊ ዘመጽአ ውስተ ዓለም ወልዱ ወቃሉ እግዚአብሔር ዘወረደ እምላዕሉ፤ የእግዚአብሔር ልጅና ቃሉ የሆነ ክርስቶስ ከላይ የወረደ ወደ ዓለም የመጣ እረኛ” የሚል ሲሆን የሚነበበው ደግሞ አንቀጸ አባግዕ የተባለው የዮሐንስ ወንጌል ክፍል ነው፡፡ (ዮሐ.፲÷፩-፳፪) እረኛ የሌለው በግ ተኩላ ነጣቂ እንዲበረታበት በበደሉ ከትጉኅ እረኛው የተለየው የሰው ልጅም በሲኦል አጋንንት በርትተውበት ሲጠቀጠቅ ኖሯል፡፡ እንዲሁም ከመንጋውና ከእረኛው የተለየ በግ እንዲቅበዘበዝ አምላኩን ዐውቆ አምልኮቱን ከመግለጽ የወጣው ሕዝብ በየተራራው መስገጃዎችን እየሠራ የሚታደገውን አምላክ በመፈለግ ሲንከራተት ኖሯል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ «እንደ በጎች ትቅበዘበዙ ነበር» እንዳለ፡፡ (፩ኛ ጴጥ፪÷፳፭) ነቢያት በዓለም ተበትነው የሚቅበዘበዙትን ሕዝቡን በቤቱ ሰብስቦ የሚጠብቃቸው እውነተኛ ቸር እረኛ እንዲወለድ ስለተናገሩ ያን ለማስታወስ ሳምንቱ ኖላዊ ተባለ፡፡
በአጠቃላይ በዚህ በገና ጾም ነቢያትም ሐዋርያትም ጾመው በረከት አግኝተውበታል፡፡ እኛ ምእመናንም እንደ እነርሱ በረከትን እናገኝ ዘንድ ይህንን ጾም መጾም እንደሚገባን የቤተ ክርስቲያን አባቶች ሥርዓት ሠርተውልናል፡፡ በዚህም መሠረት የነቢያት፣ የሐዋርያት፣ የጻድቃንና የሰማዕታት አምላክ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ከቅዱሳን ነቢያትና ሐዋርያት በረከት እንዲያሳትፈን፤ መንግሥቱንም እንዲያወርሰን ሁላችንም በዚህ በጾመ ነቢያት ወቅት በጾም በጸሎት ተወስነን እግዚአብሔርን ልንማጸነው ይገባል፡፡ ለዚህም አምላከ ቅዱሳን ይርዳን አሜን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ምንጭ-: ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፲፭፣
ቃኘው ወልዴ፣ ጾምና ምጽዋት፤ ፲፱፻፺፭ ዓ.ም፤
ተስፋዬ ምትኩ፣ ሰባቱ አጽዋማት፣ ፳፻፰ ዓ.ም
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!