“በጊዜውም ያለ ጊዜውም ጽና” (፪ኛጢሞ. ፬፥፪)

በእንዳለ ደምስስ

ጊዜ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ከሰጣቸው በረከቶች አንዱ ነው፡፡ ቀኑንም በሴኮንድ፣ በደቂቃ፣ በሰዓት፣ ሰዓቱንም በቀን ለክቶና ሰፍሮ እንጠቀምበት ዘንድ ሰጥቶናል፡፡ ነገር ግን የተሰጠንን ጊዜ በአግባቡ የምንጠቀም ስንቶቻችን ነን? ሁሉንም ነገር ለማከናወን ጊዜ አስፈላጊ መሆኑን ጠቢቡ ሰሎሞን ሲገልጽም “ለሁሉ ጊዜ አለው፤ ከፀሐይ በታችም ስለሆነ ነገር ሁሉ ጊዜ አለው …” በማለት ጊዜ ለፍጥረታት ሁሉ አስፈላጊ መሆኑን ይነግረናል፡፡

የጊዜን አስፈላጊነት ከተረዳን ማንኛውም ነገር በጊዜ ውስጥ የተለካና የተወሰነ እንደመሆኑ መጠን በሰው አእምሮ ወይም ፍላጎት አሁን ይከናወን ዘንድ የምንፈልገው ነገር በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ገና ከሆነ የእግዚአብሔርን ጊዜ በጽናት መጠበቅ እንደሚያስፈልግ ሐዋርያው ይነግረናል፡፡ “በጊዜውም ያለ ጊዜውም ጽና” (፪ኛጢሞ. ፬፥፪) በማለት፡፡የእግዚአብሔርን ጊዜ መጠበቅ ደግሞ ዋጋ ያሰጣልና በጊዜውም ያለ ጊዜውም መጽናት ይገባል፡፡

እግዚአብሔር ጊዜን ለክቶ እንደሰጠን ሁሉ የሚያስፈልገንን ሁሉ ይሰጠን ዘንድም ጊዜ አለው፡፡ ነገር ግን የሰው ልጆች ደግሞ በተቃራኒው የምንሻውን ነገር ለማግኘት እንቸኩላለን፤ ሁሉንም ነገር አሁን ካልተደረገልን ብለን ከእግዚአብሔር ጋር ክርክር የምንገጥም፣ ባይደረግልን ደግሞ ከአምላካችን ጋር ለመጣላት የምንሞክር ብዙዎች ነን፡፡ ነገር ግን በእግዚአብሔር ላይ ከማጉረምረም ይልቅ ያላደረገልን ከእኛ አንድ ነገር የጎደለ ነገር እንዳለ በመረዳት በጸሎት በመትጋት የምንሻውን ነገር እስኪሰጠን ድረስ በትዕግሥት እግዚአብሔርን ደጅ መጽናት ያስፈልጋል፡፡

ለእኛ ጊዜው ነው፤ አሁን ሊሰጠን ወይም ሊያደርግልን ይገባል ብለን እንደምንለምነው ሁሉ እግዚአብሔር ፈቃዱ ሲሆን ባልታሰበ ጊዜና ሁኔታ ውስጥም ወደ እኛ ሊቀርብና ሊያከናውንልን ይችላል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ጌርጌሴኖን መንደር በደረሰ ጊዜ ሁለት አጋንንት ያደሩባቸው ሰዎች ከመቃብር ቦታ ወጥተው አገኛቸው፡፡ ክፉዎች ናቸውና በዚያ መንገድ ማንም ደፍሮ ማለፍ እስከማይችል ድረስ በእነዚህ አጋንንት ባደረባቸው ሁለት ሰዎች ቁጥጥር ሥር የነበረ ቦታ ነው፡፡ ነገር ግን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ እነርሱ ቀርቦ ባዩት ጊዜ እየራዱና እየተንቀጠቀጡ “የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆይ ከአንተ ጋር ምን አለን? ጊዜው ሳይደርስ ልታሠቃየን ወደዚህ መጣህን?” እያሉ አጋንንቱ ጮኹ፡፡ በአቅራቢያቸው ወደሚገኙት እሪያዎች ይሰዳቸው ዘንድ ተማጸኑት፡፡ ጌታችንም እንደ ልመናቸው ይሄዱ ዘንድ ሰደዳቸው፡፡ አጋንነቱም በእሪያዎቹ ላይ እያደሩ ወደ ባሕሩ ወደቁ፡፡ (ማቴ. ፰፥፳፰-፳፱) እግዚአብሔር በራሱ ጊዜ ሁሉ ይቻለዋልና እንዲህም ያደርጋል፡፡

እኛ ያስፈልጉናል የምንላቸው ነገሮች ከእግዚአብሔር የሚለዩን፣ በሕይወታችን ውስጥ ትልቁን ጠባሳ ትተው የሚያልፉ ሆነው ሊገኙ ይችላሉና ስለምንለምነው ነገር ሁሉ በጸሎት የታገዘ ሕይወት ሊኖረን ይገባል፡፡ የምንሻው ነገር ሳይፈጸም ቢዘገይ የእግዚአብሔር ፈቃዱ አይደለምና ጊዜው ሲደርስ ያከናውንልን ዘንድ መጽናት ከእኛ ይጠበቃል፡፡ የምንሻውን መጠየቅ ብቻ ሳይሆን ለሕይወታችን እንደሚያስፈልግና እንደማያስፈልግ መለየት ከእኛ ይጠበቃል፡፡ የምንጠይቀው ነገር ከእግዚአብሔር ሊለየን፣ ከአምልኮት ሊያርቀን ይችላልና ስለምንጠይቀው ነገር ጥንቃቄ ልናደረግ ይገባል፡፡ እንደ ዘብድዎስ ልጆች ማለትም የዮሐንስ እና የያዕቆብ እናት “የምትለምኑትን አታውቁም” እስክንባል ራሳችንን ለተግሣጽ አሳልፈን እንዳንሰጥ ትዕግሥትን ገንዘብ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

የዮሐንስ እና የያዕቆብ እናት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አንድ ጥያቄ ጠይቃዋለች፡፡ በሰው ሰውኛው አስተሳሳብ በዚህ ዓለም ላይ ሊነግሥ የመጣ መስሏታልና በመንግሥቱ አንዱን ልጇን በቀኛዝማችነት በቀኙ፣ ሁለተኛውንም ልጇን በግራዝማችነት በግራው በጋሻ ጃግሬነት እንዲያቆምላት ጠየቀችው፡፡ “እነዚህን ሁለቱን ልጆቼን በመንግሥትህ አንዱን በቀኝህ፣ አንዱንም በግራህ እንዲቀመጡ አድርግልኝ” አለችው፡፡ እርሱም “የምትለምኑትን አታውቁም፣ እኔ የምጠጣውን ጽዋ መጠጣት፣ ትችላላችሁን? …” ሲል ገስጿታል፡፡ ይህ ታሪክ ከሚያስፈልገን ነገር ውጪ ለእኛ ስለመሰለን ብቻ መጠየቅ እንደማይገባን ትልቅ ማሳያ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሕይወትን የለመንን መስሎን ሞትን እንደነ ዮሐንስ እናት የምለምን እንኖራለን፡፡

እግዚአብሔር ሁሉንም በጊዜው የሚያከናውን አምላክ ነው፡፡ የምንለምነውን ባለማወቃችን፣ የራሳችንን ፍላጎት ብቻ በማስቀደማችን ከእግዚአብሔር አንድነት እንለያለን፡፡ “ለምንድነው እኔ በሚያስፈልገኝ ጊዜ እና ሰዓት የማያከናውንልኝ? እኔ አሁን ነው የምፈልገው!” እያልን ከእግዚአብሔር ጋር ሙግት የምንገጥም ብዙዎች ነን፡፡ ነገር ግን በጊዜውም ያለ ጊዜውም በመጽናት የእግዚአብሔርን ጊዜ መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡ በራሳችን ፈቃድ ብቻ ተመሥርተን የምናከናውናቸው ተግባራት ሁሉ ለውድቀት የሚዳርጉን ናቸውና፡፡

ለመሆኑ የእግዚአብሔር ጊዜ መቼ ነው? እግዚአብሔር እያንዳንዱን ነገር ሲያከናውን በዕቅድ ነው፡፡ እግዚአብሔር እንደ ሰው አይደለም አይቸኩልም፣ አይዘገይምም፡፡ ዘግይቶ ወይም ቸኩሎ የፈጠረው አንዳች ነገር የለም፡፡ ሁሉንም በጊዜው ውብ አድርጎ ሠርቶታልና የሠራውም ሁሉ መልካም ነው፡፡ “ነገርን ሁሉ በጊዜው ውብ አድርጎ ሠራው” (መክ. ፫፥፲፩) እንዲል፡፡ በዕቅድና ሁሉን በጊዜው ባያከናውን ኖሮ በስድስቱ ቀናት እያንዳንዱን ፍጥረት ባልፈጠረ ነበር፡፡ ስለዚህ ከሰው ልጆች የሚፈለገው የእግዚእሔርን ጊዜ በትዕግሥት መጠበቅ ነው፡፡ “ … ቢዘገይም በእርግጥ ይመጣልና ታገሠው፤ እርሱ አይዘገይም” (ዕንባ. ፪፥፫) እንደተባለ፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለሮሜ ሰዎች በላከው መልእክቱ “በበጎ ምግባር ጸንተው ለሚታገሡ ምስጋናና ክብርን፣ የማይጠፋ ሕይወትንም ለሚሹ እርሱ ለዘለዓለም ሕይወትን ይሰጣቸዋል” (ሮሜ. ፪፥፯) በማለት እንደገለጸው ለእግዚአብሔር የምንመች፣ እንደ ቃሉም የምንመላለስ ሆነን በመገኘት በጾምና በጸሎት በመትጋት እግዚአብሔር ሊያከናውንልን የምንሻውን ነገር በትዕግሥት ደጅ በመጥናት መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ በዚህ ብቻ አያበቃም ለዕብራውያን ሰዎች በላከው መልእክቱም “ነገር ግን የእግዚአብሔርን ፈቃድ አድርጋችሁ የተሰጣችሁን ተስፋ ታገኙ ዘንድ መታገሥ ያስፈልጋችኋል” ሲል በመታገሥና በጽናት በሃይማኖት ቀንቶ፣ በምግባር ታንጾ መኖር ከሰው ልጆች ሁሉ ይፈለጋል፡፡ እግዚአብሔር እያንዳንዳችን የምንሻውን ብቻ ሳይሆን እርሱ ያዘጋጀልንን ሁሉ ይሰጠን ዘንድ ፈቃዱ ነውና በጊዜውም ያለ ጊዜውም ጸንተን እንቁም፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *