በዓለ ደብረ ታቦር

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት መሠረት በወርሐ ነሐሴ ከሚከበሩ በዓላት መካከል አንዱ የደብረ ታቦር በዓል ነው፡፡ ይህንንም አስመልከቶ ቅዱስ ወንጌል ሲነግረን፡- ጌታችን ኢየሱስም ወደ ፊልጶስ ቂሣሪያ ሀገር በደረሰ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን “የሰውን ልጅ ማን ይሉታል?” ብሎ ጠየቃቸው፡፡ እነርሱም “መጥምቁ ዮሐንስ ነው የሚሉ አሉ፣ ሌሎችም ኤልያስ፣ ሌሎችም ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ” አሉት፡፡ እርሱም “እናንተስ ማን ትሉኛላችሁ?” አላቸው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም “አንተ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ ነህ” አለው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ደቀ መዝሙሩን ቅዱስ ጴጥሮስን   “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ አንተ ብፁዕ ነህ፤ በሰማይ ያለው አባቴ ነው እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህም፡፡” በማለት መለሰለት፡፡ (ማቴ. ፲፮÷፲፫-፳፤ ፲፯፥፩-፰)

ይህም በሆነ በስድስተኛው ቀን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሦስቱን ደቀ መዛሙርት ማለትም፡- ቅዱስ ጴጥሮስን፣ ቅዱስ ዮሐንስንና ቅዱስ ያዕቆብን ይዞ ሌሎቹን ደቀ መዛሙርት ደግሞ በእግረ ደብር (በተራራው ሥር) ትቶ ወደ ታቦር ተራራ ወጣ፡፡ በዚያም ሙሴን ከመቃብር፣ ኤልያስን ከብሔረ ሕያዋን ጠርቶ በፊታቸው ብርሃነ መለኮቱን ገለጠላቸው፡፡ ይህ ጌታችን መድኃኒታችን ብርሃነ መለኮቱን ክብረ መንግሥቱን የገለጠበት ዕለትም በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ከሚከበሩ ዐበይት በዓላት ውስጥ አንዱ ሆኖ በየዓመቱ ከነሐሴ ፲፫ ቀን በድምቀት ይከበራል፡፡ ከዋዜማው ነሐሴ ፲፪ ቀን ጀምሮ በሊቃውንቱ የሚቀርበው ስብሐተ እግዚብሔር ዕለቱን የሚያዘክር ነው፡፡

በዓሉ በምእመናን ዘንድ “ቡሄ” በመባል ይታወቃል፡፡ በሀገራችን ኢትዮጵያም ክረምቱ፣ ጭጋጉ፣ ደመናው ተወግዶ የብርሃን ወገግታ የሚታይበት ጊዜ በዚሁ በዓል አካባቢ ስለሆነ በዓሉ የ“ቡሄ” በዓል ተብሎ ይጠራል፡፡ በዓለ ደብረ ታቦር ጌታችን ምሥጢረ መለኮቱን የገለጠበት፤ ብርሃን የታየበትና ድምፀ መለኮቱ የተሰማበም ዕለት በመሆኑም “የብርሃን” በዓል ይባላል፡፡

የክረምቱ ጨለማነት አልፎ ብርሃን፣ ወገግታ የሚታይበት፤ ሰማይ ከጭጋጋማነት ወደ ብሩህነት የሚሸጋገርበት ወቅት በመሆኑ ከደብረ ታቦር በዓል በኋላ የጠነከረ ክረምት አይኖርም፡፡ “ቡሄ ከዋለ የለም ክረምት፤ ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት” እንዲሉ ኢትዮጵያውያን በብሂላቸው፡፡

ከላይ በጥቂቱ ለመግለጽ እንደሞከርነው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሦስቱን ደቀ መዛሙርት ወደ ተራራው ይዟቸው ከወጣ በኋላ “መልኩም በፊታቸው ተለወጠ፤ ፊቱም እንደ ፀሐይ አበራ፤ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ ሆነ፡፡ እነሆ ሙሴ እና ኤልያስም ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው፡፡” በማለት ብርሃነ መለኮቱን መግለጡን መጽሐፍ ቅዱስ ያስረዳናል፡፡ (ማቴ. ፲፯፥፪-፫) በዚህ ወቅት ብሩህ ደመና መጥቶ ጋረዳቸው፡፡ ከደመናው ውስጥም “የምወደው፤ በእርሱም ደስ የሚለኝ ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት” የሚል ቃል መጣ፡፡ ይህም የቅድስት ሥላሴን አንድነትና ሦስትነት በታቦር ተራራ ላይ መገለጹን ያመለክተናል፡፡

ለምን ወደ ተራራ ይዟቸው ወጣ?

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን ወደ ተራራ ይዟቸው የወጣው ስለ ሁለት ነገር እንደሆነ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ያስተምራሉ፡፡ የመጀመሪያው፡- በማርቆስ ወንጌል ላይ የእግዚአብሔር መንግሥት እስክትመጣ ድረስ ሞትን የማይቀምሱ እንዳሉ አስተምሯቸው ነበርና ይህ እውነት መሆኑን ለማሳየት ወደ ተራራ ይዟቸው ወጥቷል፡፡ “እውነት እላችኋለሁ በዚህ ከቆሙት ሰዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት በኃይል ስትመጣ እስኪያይዋት ድረስ ሞትን የማይቀምሱት አሉ” እንዲል ኤልያስን ከብሔረ ሕያዋን አምጥቶ አሳይቷቸዋል፡፡ (ማር. ፱፥፩) ሁለተኛው፡-  በዚህ ዕለት ምሥጢረ ሥላሴን እንዲረዱ የሦስትነት ምሥጢር ገልጦ ያሳያቸው ዘንድ ወደ ተራራ ይዟቸው ወጥቷል፡፡ ሌላው “ታቦር ወአርሞንኤም በስመ ዚአከ ይትፌሥሑ ወይሴብሑ ለስምከ፤ ታቦርና አርሞንኤም በስምህ ደስ ይላቸዋል፤ ስምህንም ያመሰግናሉ” ሲል ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት በትንቢት ተናግሮ ነበርና ይህ ይፈጸም ዘንድ ወደ ተራራ ይዟቸው ወጥቷል፡፡ (መዝ. ፹፰፥፲፪-፲፫)

ዘጠኙን ሐዋርያት ከተራራው ግርጌ ለምን ተዋቸው? 

ዘጠኙን ደቀ መዛሙርት ከታቦር ተራራ ግርጌ ትቷቸው ሦስቱን ብቻ ይዟቸው ወጥቷል፡፡ ለምን ቢሉ፡- ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ኢየሩሳልም ሄዶ ከሽማግለዎች፣ ከካህናትና ከጻፎች ብዙ መከራ እንደሚቀበል፣ እንደሚሞትና በሦስተኛውም ቀን እንደሚነሣ ለደቀ መዛሙርቱ ሲነግራቸው ቅዱስ ጴጥሮስ ግን ለጌታው ካለው ጽኑ ፍቅር፣ እንደዚሁም  በዚህ ምድር ላይ ሳለ ሹመት ሽልማትን ይሻ ነበርና “አቤቱ ይህ አይሁንብህ፤ ከቶም አይድረስብህ” አለው፡፡ (ማቴ.፲፮፥፳፪)፤ እንዲሁም ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ዮሐንስና  ማርቆስ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህንን ዓለም ለመግዛት የመጣ ስለመሰላቸው እናታቸው “እነዚህን ሁለቱ ልጆቼ በመንግሥትህ አንዱን በቀኝህ፣ አንዱን በግራህ እንዲቀመጡ አድርግልኝ” ብላ በተማጸነች ጊዜ ጌታችን “የምትለምኑትን አታውቁም፤ እኔ የምጠጣውን ጽዋ መጠጣት ትችላላችሁን? እኔስ የምጠመቀውን ጥምቀት ትጠመቃላችሁን?” አላቸው፡፡ እነርሱም “አዎን እንችላለን” ብለው መልሰዋል፡፡ (ማቴ. ፳፥፳-፳፫)

ይህም ልክ እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ ምድራዊ ሹመትን መሻታቸው፣ እንዲሁም ለጌታቸው ጽኑ ፍቅር እንዳላቸው ለመግለጽ ይህንን ብለዋልና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምድራዊ አምላክ ብቻ ሳይሆን ይህን ዓለም ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣ መሆኑን፣ በኋላም ይህን ዓለም እንደሚያሳልፋት፣ ምድራዊ ብቻ ሳይሆን ሰማያዊ አምላክ መሆኑን ለማሳየት ሦስቱን ወደ ተራራው ይዟቸው ወጥቷል፡፡ በዚያም ብርሃነ መለኮቱን ገለጠላቸው፡፡ ለሦስቱ የገለጠላቸውን ምሥጢርም ምንም የሚሳነው ነገር የሌለው አምላክ ነውና በእግረ ደብር ላሉት ለስምንቱ ሐዋርያትም ገልጦላቸዋል፡፡ ምነው ይሁዳን ተወው ስንል ደግሞ ይሁዳ አሳልፎ እንደሚሰጠው ያውቃልና ይህንን ምሥጢር ያይ ዘንድ ስላልፈቀደ ነው፡፡ ስለዚህም ይሁዳን ለመለየት ዘጠኙን ከተራራው ግርጌ አቆይቷቸዋል፡፡

ጅራፍ፡-

የደብረ ታቦር በዓል ከመድረሱ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ በገጠሪቱ የሀገራችን ክፍሎች ልጆች ባለ ሦስት ግምድ ጅራፍ ገምደው ከብቶች እየጠበቁ ማጮህ ይጀምራሉ፡፡ ይህም በዕለቱ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ መለኮቱን በገለጠበት ጊዜ አብ በደመና ሆኖ “የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት” ሲል የተናገረው ድምጽ ምሳሌ ነው፡፡ ከድምጹ አስፈሪነት የተነሣም ሦስቱም ሐዋርያት በግምባራቸው ወደ መሬት መውደቃቸውን ቅዱስ መጽሐፍ ያስረዳናል፡፡ “ደቀ መዛሙርቱም ሰምተው በግምባራቸው ወደቁ” እንዲል፡፡ (ማቴ. ፲፯፥፮) 

ሙልሙል ዳቦ፡-

የሙልሙል ዳቦ ትውፊታዊ አመጣጥ ጌታችን ብርሃነ መለኮቱን በገለጠበት ዕለት ደብረ ታቦርንና ዙሪያውን በብርሃን መልቶት ስለነበር በዚያ የነበሩ ሕፃናት እረኞች ቀኑ የመሸ ስላልመሰላቸውም ነበር፡፡ ከዚህም የተነሣ በዚያው ሆነው ከብቶቻቸውንና በጎቻቸውን እየጠበቁ ቆይተዋል፡፡ ይህ የልጆቻቸው ያለ ወትሮው መዘግየት ያሳሰባቸው ወላጆቻቸውም በፍጥነት የሚደርሰውን ያልቦካ ዳቦ ጋግረው ይዘውላቸው የመሄዳቸው ምሳሌ ነው፡፡

በዚህም ምክንያት ኦርቶዶክሳውያን ሙልሙል ዳቦ ጋግረው ልጆች ዕለቱን በማሰብ “ቡሄ በሉ” እያሉ በየቤታቸው ሲመጡ ሙልሙል ዳቦ ይሰጣቸዋል፡፡ ሕፃናቱም የጌታን በዓል ሊያበሥሩ እየዘመሩ ሲመጡ የምሥራች (ወንጌልን) ይዘው ወደ ምእመናን የተላኩት የደቀ መዛሙርት ምሳሌ ናቸው፡፡ ምእመናን ድምጻቸውን ሰምተው ለሕፃናቱ መስጠታቸውም ምእመናን የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት በክብር የመቀበላቸውንና በእነርሱ የተሰበከላቸውነ የክርስቶስን ቃል የመስማታቸው ምሳሌ ነው፡፡ ሐዋርያት በገቡበት ሀገር ሁሉ አስተምረው አጥምቀው የጸጋ ልጅነትን አሰጥተው እንደሚቆዩ ሁሉ ልጆችም ዘምረው አመስግነው መርቀው “ውለዱ ክበዱ የመንግሥተ ሰማያት ወራሾች ያድርጋችሁ” ብለው አመስገነው ይሄዳሉና ሕፃናቱ በሐዋርያት ይመሰላሉ፡፡

ችቦ

ችቦ የጌታችንን ብርሃነ መለኮት መገለጥ የሚያመለክት ነው፡፡ በመሆኑም ችቦ ለኩሰን በዓሉን እናከብራለን፡፡ የዚህ ችቦ ትውፊታዊ አመጣጥም በብርሃኑ ድምቀት የቀኑን መምሸት ያልተረዱ እረኞች በሜዳ መቅረታቸው ምክንያት ወላጆች ከየመንደራቸው ችቦ ለኩሰው ልጆቻቸውን ፍለጋ የሄዱበትን ታሪክ እያዘከርን በዓሉን እናከብራለን፡፡

በአጠቃላይ በታቦር ተራራ ላይ፡-

  • “ታቦርና አርሞንኤም በአንተ ስም ደስ ይላቸዋል” (መዝ. ፹፰፥፲፪) ተብሎ የተነገረው ትንቢት ተፈጸመ።
  • መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም አምላክነቱን ገለጠ።
  • ምሥጢረ ሥላሴ ተገለጠ/አብ በደመና ድምጹን በማሰማት፣ መንፈስ ቅዱስ በብርሃን፣ ወልድ በአካል/።
  • ሙሴ፦ “እኔ ጠላት ብገድልም፣ ደመና ብጋርድም፣ መና ባወርድም፣ እስራኤልን ከክፋታቸው መልሶ ማዳን አልተቻለኝም። ለአንተ ግን ሁሉ ይቻልሃል። ደግሞስ የእኔን ፈጣሪና ጌታ እንዴት ሙሴ ይሉሃል? የሙሴ ጌታ ይበሉህ እንጂ” በማለት የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነት መሰከረ።
  • ኤልያስ፦ “እኔ ሰማይ ብለጉም፣ እሳት ባዘንብም እስራኤልን ከክፋታቸው መልሶ ማዳን አልተቻለኝም። ለአንተ ግን ይቻልሃል። ደግሞስ የኔን ፈጣሪና ጌታ እንዴት ኤልያስ ይሉሃል? የኤልያስ ጌታ ይበሉህ እንጂ” በማለት የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነት መሰከረ።
  • ቅዱስ ጴጥሮስም በሕይወት፣ በእምነት፣ በቤተ ክርስቲያንና በአገልግሎት መኖር መልካም እንደሆነ ሲገልጥ “በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው” በማለት ተናገረ።
  • የእግዚአብሔር መንግሥት ሕጉን ጠብቀው ለሚኖሩ ለሁሉም መሆኑን ለማጠየቅ ሙሴን ከአገቡት፣ ኤልያስን ከደናግልና ሐዋርያትን ከዓለም አምጥቶ አሳየን።
  • ደብረ ታቦር የወንጌል፣ የመንግሥተ ሰማያት የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ መሆኗን፤ ነቢያት በትንቢትና በምሳሌ፣ ሐዋርያት በግልጥና በተግባር የሰበኳት መሆኗን ገለጠ።

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በነቢያትና በሐዋርያት መሠረትነት ላይ የጸናች (በነቢያት ትንቢት፣ በሐዋርያትም ስብከት ላይ ሳትናወጽ ጸንታ የቆመች) መሆኗን ለማጠየቅ የብሉይ ኪዳን ነቢያትንና የሐዲስ ኪዳን ሐዋርያትን ወደ ተራራው ጠርቶ ብርሃነ መለኮቱን ገለጠላቸው፡፡

ከበዓሉ ረድኤት በረከት ያሳትፈን። አሜን!

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *