በዓለ ክብሩ ለሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታኅሣሥ ፲፱ ቀን ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ከእግዚአብሔር ተልኮ ሠለስቱ ደቂቅን (አናንያ፣ አዛርያ እና ሚሳኤል) ከነደደ እሳት ያዳነበትን መታሰቢያ በዓል በድምቀት ታከብራለች፡፡
ቅዱስ ገብርኤል አብሣሪ መልአክ እንደሆነ ሁሉ ምእመናን እግዚአብሔርን በማምለካቸው ምክንያት ከአላውያን ገዢዎች ከሚደርስባቸው መከራም የሚታደጋቸው መልአክ ነው፡፡ የፋርስ ንጉሥ የነበረው ናብከደነፆር እግዚአብሔር አምላክ ምድሪቱን እና ሕዝቡን ያስተዳድር ዘንድ ቢፈቅድለት በትዕቢት ተሞልቶ “በኃይሌ አደርጋለሁ፣ በማስተዋል ጥበቤም የአሕዛብን ድንበሮች አርቃለሁ፣ ሀብታቸውንም እዘርፋለሁ፣ የሚቀመጡባቸውንም ከተሞች አናውጣለሁ፣ በእጄም ዓለምን ሁሉ እንደ ወፍ ቤት እሰበስባለሁ፣ እንደ ተተወ እንቁላልም እወስዳቸዋለሁ፤ ከእኔም የሚያመልጥ የለም፤ የሚቃወመኝም የለም” ብሎ በመታበይ የወርቅ ጣዖትን አሠርቶ በባቢሎን አውራጃ ቁመቱ ስድሳ ክንድ፣ ወርዱም ስድስት ክንድ የሆነ የወርቅ ምስል አሠርቶ በዱራ ሜዳ ላይ አቆመው፡፡ (ኢሳ. ፲፥፲፫-፲፬፤ ዳን.፫፥፩)፡፡
መኳንንትንና ሹሞቹን እንዲሁም ሕዝቡን አስጠርቶ በዐዋጅ ነጋሪ “ንጉሡ ናቡከደነፆር ላቆመው ለወርቁ ምስል ስገዱ፤ ወድቆም የማይሰግድ በዚያን ጊዜ በሚነድ እሳት እቶን ውስጥ ይጣላል” ሲል ዐዋጅ አስነገረ፡፡ ይህን ዐዋጅ የሰሙ የንጉሥ ሹማምንት ሁሉ ተደፍተው ለወርቁ ምስል ሰገዱ፡፡ ነገር ግን በመካከላቸው አናንያ፣ አዛርያ እና ሚሳኤል ንጉሡ ላቆመው ምስል አልሰገዱም፡፡
ነገር ሠሪዎችም ይህንን ወሬ ለንጉሥ ባደረሱ ጊዜ ንጉሡ እጅግ ተቆጥቶ ካስጠራቸው በኋላ “… አምላኬን አለማምለካችሁ ላቆምሁትም ለወርቁ ምስል አለመስገዳችሁ እውነት ነውን?” ሲል ጠየቃቸው፡፡
አናንያ፣ አዛርያ እና ሚሳኤል ግን በንጉሡ ፊት ቆመው “ንጉሥ ሆይ፥ እኛ የምናመልከው አምላክ በሰማይ አለ፡፡ ከሚነድደው ከእቶኑ እሳት ያድነን ዘንድ ይችላል፤ ከእጅህም ያድነናል፡፡ ንጉሥ ሆይ! ይህም ባይሆን አማልእክትህን እንዳናመልክ ላቆምኸውም ለወርቁ ምስል እንዳንሰግድ ዕወቅ” አሉት፡፡ (ዳን.፫፥፬፫-፲፰)፡፡
የንጉሥ ናቡከደነፆር ቁጣ ከፊት ይልቅ እጅግ ነደደ፤ እሳቱንም ሰባት እጥፍ እንዲያቀጣጥሉና እነዚህን ሦስት ብላቴኖች እጅና እግራቸውን አስረው ከእቶን እሳት ውስጥ እንዲጨምሩአቸው አዘዘ፤ ጋሻ ጃግሬዎቹም ፈጥነው ወደሚነደው እሳት ጨመሯቸው፡፡ እግዚአብሔርም የሦስቱን ወጣቶች የእምነት ጽናት ተመለከተ፡፡ በፊቱ የሚቆመውን ባለሟሉን የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤልንም ከመጣባቸው መከራ ይታደጋቸው ዘንድ ላከላቸው፡፡ ቅዱስ ገብርኤልም ከእስራታቸው ፈታቸው፤ እሳቱንም እንደ ውኃ አቀዘቀዘው፡፡ ሠለስቱ ደቂቅም ከተጣሉበት ሆነው መልአኩን ልኮ ከዚህ እቶን እሳት ያዳናቸውን አምላክ አመሰገኑት፡፡
ንጉሡ ናብከደነፆርም ሠለስቱ ደቂቅ እሳቱ አንዳች ጉዳት ሳያደርስባቸው በእሳት ውስጥ ሲመላለሱ ተመለከተ፡፡ “እነሆ እኔ የተፈቱ በእሳቱም መካከል የሚመላለሱ አራት ሰዎችን በዚያ አያለሁ ምንም የነካቸው የለም፤ የአራተኛውም መልክ የእግዚአብሔርን ልጅ ይመስላል” ብሎ ፊቱን ጸፍቶ አፉንም ከፍቶ እንዲናገር አደረገው፡፡ ሠለስቱ ደቂቅ በእሳቱ ውስጥ ሆነው እግዚአብሔርን ሲያመሰግኑ ሰማቸው፡፡ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልም ከነደደው እሳት አዳናቸው፡፡ (ዳን. ፫፥፳፬-፳፮)
ናብከደነፆር የተደረገውን ተአምር ተመልክቶ ወደ እሳቱ በመቅረብ ለሦስቱ ብላቴኖች “እናንተ የልዑል አምላክ ባሪያዎች ሲድራቅ፣ ሚሳቅንና አብደናጎም ኑ ውጡ” ብሎ ተናገራቸው፡፡ (ዳን.፫፥፳፮) እነርሱም እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ወጡ፡፡ መሳፍንቱና ሹማምቶችም የሚያመልኩት አምላካቸው ቅዱስ እግዚአብሔር የሚነደው እሳት ሰውነታቸውን ሳይበላ፣ የራሳቸውም ጸጉር ሳይነካ፣ የእሳቱም ሽታ በላያቸው እንዳልነበረ አዩ፡፡ ንጉሡ ናቡከደነፆርም በሠለስቱ ደቅቅ ፊት ለእግዚአብሔር ሰገደ፡፡ እግዚአብሔርንም እያመሰገነ ሕዝቡን ሁሉ የብላቴኖቹ ሠለስቱ ደቂቅን አምላክ እንዲያመልኩ፤ አናመልክም በሚሉትና የስደብን ነገር በሚናገሩት ላይ ከፍተኛ ቅጣት እንደሚደርስባቸው ዐዋጅ አስነገረ፡፡ ሚሳቅን፣ ሲድራቅና አብደናጎምንም በባቢሎን አውራጃ ውስጥ ሾማቸው፡፡ ከፍ ከፍም አደረጋቸው፡፡
ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም ልጆቿን ከእነዚህ ብላቴኖች የእምነት ፍሬ ተምረው፣ የመልአኩ ቅዱስ ገብርኤልንም ተራዳኢነት ተረድተው እግዚአብሔርን በማምለክ እንዲጸኑ ታኅሣሥ ፲፱ ቀንን ትዘክራለች፤ በታላቅ ድምቀትም ታከብረዋለች፡፡
የመላእክት አለቃ የቅዱስ ገብርኤል ምልጃና ተራዳኢነት አይለየን፤ ለዘለዓለሙ አሜን፡፡
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!