በዓለ ቅዱስ ጴጥሮስ ወጳውሎስ 

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከዐረገ እና ለሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ከላከላቸው በኋላ ሐዋርያት የአገልግሎታቸው መጀመሪያ ያደረጉት ጾምና ጸሎት ነው፡፡ በዚህም መሠረት በጾም በጸሎት በሱባኤ ቆይተው አንድ ጊዜ ለወንጌል አገልግሎት በጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠሩበትን ተልእኮ ለመፈጸም እስከ ሕይወታቸው ፍጻሜ ወደ አገልግሎት ተሰማርተዋል፡፡ በአሕዛብ እና በአረማውያን የሚደርስባቸውን መከራ በመቋቋም ከአንዱ ቦታ ሲያሳድዷቸው ወደ ሌላው እየተሰደዱ ወንጌልን ለዓለም አዳርሰዋል፡፡ በዚህ አገልግሎት ውስጥ ሳሉም በርካታ መከራና ሥቃይ ተቀብለዋል፡፡ ሕይወታቸውንም ለሞት እስከ መስጠት ታምነው ተገኝተዋል፡፡

በዚህም መሠረት ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን ሐምሌ አምስት ቀን በሰማዕትነት ያረፉትን የሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስና የቅዱስ ጳውሎስ መታሰቢያ በዓልን በድምቀት ታከብራለች፡፡ እኛም ዕለቱን በማስመልከት ስለ ሁለቱ ሰማዕታት ታሪክ በጥቂቱ እናቀርብላችኋለን፡፡   

ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስን እና ወንድሙ ሐዋርያው እንድርያስን ያገኛቸው በገሊላ ባሕር ዳር ዓሣ በማጥመድ ላይ ሳሉ ነው፡፡ ጌታችንም “ኑ ተከተሉኝ ሰውን የምታጠምዱ እንድትሆኑ አደርጋችኋለሁ” አላቸው፡፡ (ማቴ. ፬፥፲፱) ወዲያውም መረባቸውን ትተው ተከተሉት፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስ ለአገልግሎት ሲጠራ የ፶፭ ዓመት ሰው ሲሆን ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያቱን ሰብስቦ “የሰውን ልጅ ሰዎች ማን ይሉታል?” ብሎ በጠየቀ ጊዜ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ “አንተ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ ነህ” ብሎ መመስከር የቻለ የእግዚአብሔር ታማኝ አገልጋይ ነው፡፡ ጌታችንም መልሶ እንዲህ ብሎታል “እኔም እልሃለሁ አንተ ዐለት ነህ በዚያች ዐለት ላይም ቤተ ክርስቲያኔን እሠራታለሁ፤ የሲኦል በሮችም አይበረቱባትም፡፡ የመንግሥተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ …” (ማቴ.፲፮፥-፲፱) ይህም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ጴጥሮስ የሰጠውን ምስክርነት ተከትሎ የሆነ ነው፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን የሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ እምነት የጎደለው ሆኖም እናገኘዋለን፡፡ ሐዋርያት በታንኳ ሆነው በባሕሩ ላይ ይሻገሩ ዘንድ ጉዞ እንደጀመሩ ባሕሩን ማዕበል አናወጠው፡፡ በማዕበሉም ምክንያት ሐዋርያት እጅግ ታወኩ፡፡ በዚህ ጊዜ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ በባሕሩ ላይ እየተራመደ ወደ እነርሱ መጣ፡፡ ይህን የተመለከተው ቅዱስ ጴጥሮስ “… ወደ አንተ እንድመጣ እዘዘኝ” አለው፡፡ እንዲመጣ ባዘዘውም ጊዜ ፍርሃት እንዳደረበት እንመለከታለን፡፡ ጥቂት እንደተጓዘም ነፋሱን ባየ ጊዜ ፈራ፡፡ መስጠምም ጀመረ፡፡ ያን ጊዜም “አቤቱ አድነኝ ብሎ ጮኸ“ ወዲያውም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እጁን ይዞ አወጣው፤ እንዲህም አለው “አንተ እምነት የጎደለህ፤ ለምን ተጠራጠርህ?” ብሎ ጌታችን ገሥጾታል፡፡ ማቴ ፲፬፥፳፬-፴፫)

ቅዱስ ጴጥሮስ ለክህደት ቅርብም እንደነበር ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተናግሯል፡፡ ጌታችን ለሐዋርያት “እርስ በእርሳችሁ ተዋደዱ” ብሎ አዲስ ትእዛዝ ከሰጣቸው በኋላ ቅዱስ ጴጥሮስ አንተ ወደምትሄድበት እከተልሃለሁ ብሎ ጠይቋል፡፡ “ወደ ምሄድበት ልትከተለኝ አትችልም፡፡ በኋላ ግን ትከተለኛለህ” ብሎታል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ግን ዝም ብሎ አልተቀበለውም፡፡ “ጌታ ሆይ ስለምን አሁን ልከተልህ አልችልም? እኔ ነፍሴን እንኳ ቢሆን ስለ አንተ አሳልፌ እሰጣለሁ” ሲል መልሶለታል፡፡ ከጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰወረ ምንም ነገር የለምና የጴጥሮስንም ክሕደት ስለሚያውቅ “ነፍስህን ስለ እኔ አሳልፈህ ትሰጣለህን? እውነት እውነት እልሃለሁ ሦስት ጊዜ እስክትክደኝ ዶሮ አይጮህም” ብሎ እንደሚክደው ነግሮታል፡፡ (ዮሐ.፲፫፥፴፬-፴፰) ይህም ጌታችን በመስቀል ላይ ሲሰቀል ሸሽቶ ወደ መንደር ገብቶ አብሯቸው እሳት ሲሞቅ “ይህ ሰው ከእርሱ ጋር ነበር” ብለው በተናገሩ ጊዜ የእርሱ ደቀ መዝሙር እንዳልሆነ፣ ከእርሱም ጋር እንዳልነበር ክዶ መስክሯል፡፡ ወዲያውም ዶሮ ጮኸ፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ምንም እንኳን በክሕደት ቢታማም በጸጸት የሚመለስና የንስሓ አንብዕ የሚያነባ እንደሆነ መጽሐፍ ይገልጻልና ምርር ያለ የጸጸት ልቅሶን አልቅሷል፡፡ ይህም ጸጸቱ ንስሓ ሆኖ ተቆጠረለት፡፡ (ማር.፲፬፥፷፰-፸፪)

በሌላ በኩል ደግሞ በጽናት ወንጌልን ለመስበክ ሳይሰቀቅ በተዘዋወረባቸው ቦታዎች ሁሉ የሚደርስበትን መከራ ሁሉ ታግሶ አስተምሯል፡፡ በዚህም ምክንያት ጌታችን ካረገ በኋላም በአይሁድ ሸንጐ ድውይ ፈወስክ ተብሎ በተከሰሰ ጊዜ በድፍረት ስለ መድኃኔዓለም ክርስቶስ መሥክሯል፡፡ በፍልስጥኤም፣ በሶርያና በተለያዩ ሀገሮች እየተዘዋወረ ወንጌልን የሰበከ ሲሆን ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤውን ከገለጠ በኀምሳኛው ቀን በዕለተ ጰንጠቆስጤ ለሐዋርያት መንፈስ ቅዱስ እንደወረደላቸው ሦስት ሺህ ሰዎችን በአንድ ቀን ስብከት ማሳመንና ወደ ክርስትና መመለስ የቻለ ሐዋርያ ነው፡፡

 ወደ ፍልስጥኤም፣ ሶርያ፣ ጳንጦን፣ ገላትያ፣ ቀጰዶቅያ፣ ቢታንያ እና ሮሜም ሀገርም በመጓዝ ለአሕዛብ ወንጌልን አስተምሮ በማሳመን ወደ ክርስትና ብዙዎቸድን መልሷል፤ አስተማረ፤ ድውያንንም ፈውሷል፡፡ (ሐዋ ፭፥፲፭)

ዝናው በሮማ ባለሥልጣናት ዘንድ ተሰማ፤ ብዙዎችም ወደ ክርስትና ለመመለስ ቻለ፡፡ በዚህም ምክንያት ኔሮን ክርስቲያኖችን ማሳደድና መግደል ተያያዘው፡፡ በመጨረሻም የሮም ከተማን በእሳት አቃጠላት፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ከሮማ ወደ ኦፒየም ጎዳና ተጓዘ፤ በዚያም ጌታችን በሽማግሌ አምሳል ተገለጠለት፤ ሆኖም ግን ጴጥሮስ ጌታ እንደሆነ ዐውቆ በፊቱ ተደፋና “ጌታዬ ወዴት እየተጓዝክ ነው?” አለና ጠየቀው። “ዳግም በሮም ልሰቀል” አለው። ቅዱስ ጴጥሮስም ይህን ሲሰማ እጅግ አዝኖ ወደ ሮማ ተመለሰ። ሲፈልጉት ወደ ነበሩት የኔሮን ወታደሮች ሄዶ “እነሆኝ ስቀሉኝ” አላቸው፤ ቅዱስ ጴጥሮስንም ይዘው ካሠሩት በኋላ ሊሰቅሉት የመስቀያውን እንጨት ሲያቀርቡ “እኔ እንደ ጌታዬ ልሰቀል አይገባኝም” በማለት ቁልቁል እንዲሰቅሉት ለመናቸው። እነርሱም ቁልቁል ሰቀሉት ይህም የሆነው ሐምሌ ፭ ቀን ፷፯ ዓ.ም. ነበር፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ከፈሪሳውያን ወገን ሲሆን የሕግና ፍልስፍና ትምህርት ቤቶች በብዛት ይገኝባት በነበረችው በጠርሴስ ከተማ የተወለደ ነው፡፡ የዘር ሐረጉም ከነገደ ብንያም ነው፤  እርሱም ሮማዊ እንደሆነ ራሱ ተናግሯል፡፡ ነገር ግን አስተዳደጉ በአይሁድ ሥርዓት ነበር፡፡ የኦሪት መምህር የሆነው የገማልያል ተማሪም ስለነበር የሕግ ትምህርት ተምሯል፤ ድንኳን መስፋትም ተምሮ እንደነበር ታሪኩ ምስክር ነው፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሐዋርያ ከመሆኑ በፊት አስቀድሞ ሳውል ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ክርስቲያኖችን እያሳደደ የሚያሳድድ፤ ለኦሪት ሥርዓትና አስተምህሮ ቀናዒ ሰው ነበር፡፡ “ሳውል ግን አብያተ ቤተ ክርስቲያናትን ይቃወም ነበር፤ የሰውንም ቤት ሁሉ ይበረብር ነበር፤ ወንዶችንም ሴቶችንም እየጎተተ ወደ ወኅኒ ቤት ያስገባቸው ነበር፡፡” እንዲል (የሐዋ.፰፥፫) ደማስቆ ከተማ ሲደርስም በድንገት መብረቅ ከሰማይ ብልጭ ሲልበት መሬት ላይ ወደቀ፤ ወዲያውም “ሳውል፥ ሳውል፥ ለምን ታሳድደኛለህ?” የሚል ድምጽ ሰማ፤ ሳውልም “አቤቱ፥ አንተ ማነህ” አለው፤ እርሱም አንተ የምታሳድደኝ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነኝ፤ በሾላ ብረት ላይ ብትቆም ለአንተ ይብስብሃል” አለው፤ እርሱም እየፈራና እየተንቀጠቀጠ “አቤቱ፥ ምን እንዳደርግ ትሻለህ?” አለው፤ ጌታም፥ “ተነሣና ወደ ከተማ ግባ፤ በዚያም ልታደርግ የሚገባህን ይነግሩሃል” አለው፡፡

ሳውልም ከምድር ተነሥቶ በሚቆምበት ጊዜ ማየት ተሳነው፤ ዓይኖቹ ቢገለጡም የሚያየው ነገር ግን አልነበረም፡፡ ለሦስት ቀናት ያህል ሳይበላና ሳይጠጣ ከቆየ በኋላም ጌታ በራእይ ለሐናንያ ተገልጦ ባዘዘው መሠረት እጁን ጭኖ ዓይኖቹን ፈወሰለት፤ ስለመመረጡ ነገርም አስረዳው፡፡ “በአሕዛብና በነገሥታት፥ በእስራኤል ልጆችም ፊት ይሸከም ዘንድ ለእኔ የተመረጠ ዕቃ አድርጌዋለሁና፡፡” እንዲል፤ (የሐዋ.፱፥፬-፲፭)

ሳውልም ተጠመቀ፤ ከበላና ከጠጣ በኋላ ስለበረታ በደማስቆ ከደቀ መዝሙርቱ ጋር ሰንብቶ ወደ ምኵራቦቹ በመግባት ሰብኳል፡፡ ደማስቆም ከተመለሰ በኋላ አሕዛብን በማሳመን አጥምቋቸዋል፡፡ በዚህም ጊዜ በዚያ ይኖሩ የነበሩ አይሁድ ሊገድሉት በማሰባቸው ክርስቲያኖቹ እርሱን ለመደበቅ ወደ ኢየሩሳሌም ሰደዱት፡፡

እርሱም ማስተማሩን ሳያቋርጥ በአንጾኪያ፣ ኤፌሶን፣ ቆሮንቶስ፣ ሮም ከተሞች እየተዘዋወረ የእግዚአብሔርን ቃል ሰብኳል፡፡ በተአምራት ሙት አስነሥቷል፤ ድውይ ፈውሷል፡፡ ትምህርቱንም የሚያደርገው የነበረው ሰው በተሰበሰበበት በምኵራብ፣ በዐደባባይ፣ በገበያ ቦታዎች፣… ነበር፡፡ (ሐዋ.፱፥፩-፳፭)

ቅዱስ ጳውሎስ በቃል ካስተማራቸው ትምህርቶችም ይልቅ በመልክእት መልክ በጽሑፍ ያስቀመጣቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ተመዝግበው ከትውልድ ወደ ትውልድ ተላልፈዋል፡፡ በዚህም መሠረት ፲፬ መልእክታትን ጽፏል፡፡

በ፷፭ ዓ.ም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በኒቆጵልዮን ከተማ ያስተምር በነበረበት ወቅት ንጉሥ ኔሮን ይዞ ወደ ወኅኒ አስገብቶ ጽኑ ሥቃይን አሠቃየው፤ በ፸፬ ዓመት ዕድሜው በሮም ከተማ አንገቱን በሰይፍ ተቆርጦ ሐምሌ ፭ ቀን ሰማዕትነትን ተቀበለ፡፡ ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችንም በዚህ ቀን በየዓመቱ ሁለቱን ማለትም ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስንና ቅዱስ ጳውሎስን መታሰቢያቸውን በድምቀት ታከብራለች፡፡

በረከታቸውና አማላጅነታቸው አይለየን፤ አሜን!

 ምንጭ፡፹፩ መጽሐፍ ቅዱስ፣ መጽሐፈ ስንክሳር ዘወርኃ ሐምሌ ፭፣

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *