በዓለ መስቀል
በመምህር ፈቃዱ ሣህሌ
ክፍል -፪
ከክፍል አንድ የቀጠለ……………..
፩. በትምህርት፦ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔር በገለጠላት መሠረት ነገረ መስቀሉን አጉልታና አምልታ በማስተማር ክብረ መስቀልን ስትመሰክር ኖራለችም፤ ትኖራለች። ይህን የምታስተምረውም በጉባኤ፣ በመጽሐፍና በተግባር ነው። አስቀድሞ ነቢያት ለምሳሌም (መዝ. ፳፩፥፲፮-፲፱ ፤፷፰፥፳፩፣ ኢሳ. ፶፫፥፬-፲) በኋላም ሐዋርያትና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ሁሉ በአንደበታቸውም ኾነ በመጽሐፋቸው ስለ መስቀሉ ክብር በሰፊው በመግለጽ ተገቢውን ትምህርት ሰጥተዋል። አሁንም እንደቀድሞው ሊቃውንቱ በአብነት ጉባኤያት፣ በማኅሌት፣ በዝማሬ፣ በሰዓታት፣ በመንፈሳዊ ኮሌጆች፣ በሰንበት ትምህርት ቤቶች፣ በዐውደ ምሕረት፣ በቅዱሳት መጻሕፍትና በአገልግሎቶች ሁሉ የመስቀሉን ክብር በመመስከር ላይ ትገኛለች።
፪. በመሳለም፦ ቅዱሱ አምላካችን መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ ለድኅነተ ዓለም በላዩ ላይ ስለ ተሰቀለበት ዕፀ መስቀልም የተቀደሰ መሆኑን ከላይ ከተገለጹት ማብራሪያዎች መረዳት አያዳግትም። ይህንን ቅዱስ መስቀል መሳም ወይም መሳለም መቀደስ (ቅድስናን ማግኘት)፥ መባረክ መሆኑም ግርታን የሚፈጥር አይደለም። ይህንን ምሥጢር የበለጠ ለመረዳት እግዚአብሔር አምላካችን በብሉይ ኪዳን ዘመን ካዘዛቸው ትእዛዛት አንዱን መመልከት መልካም ነው።
በኦሪት ዘፀአት እግዚአብሔር አምላካችን ለርእሰ ነቢያት ሙሴ ቅብዐ ቅዱስ የሚዘጋጅበትን መመሪያ ከሰጠ በኋላ በቅብዐ ቅዱሱ የሚከብሩትን ንዋያተ ቅድሳት ሲገልጽልን “የመገናኛውንም ድንኳን፥ የምስክሩንም ታቦት፥ ገበታውንም፥ ዕቃውንም ሁሉ፥ መቅረዙንም፥ ዕቃውንም፥ የዕጣን መሠዊያውንም፥ ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነውን መሠዊያና ዕቃውንም ሁሉ፥ የመታጠቢያውን ሰንና መቀመጫውንም ትቀባበታለህ። ሁሉንም ትቀድሳቸዋለህ፤ ቅድስተ ቅዱሳንም ይሆናሉ፤ የሚነካቸውም ሁሉ ቅዱስ ይሆናል።” በማለት ያትታል (ዘፀ.፴፥፳፮-፴።)
ይህንን አስገራሚ የእግዚአብሔር ጸጋ በማስተዋል ያነበቡ ሁሉ በአድናቆትና በደስታ ሆነው ቢያንስ ራሳቸውን እንዲህ ብለን ለመጠየቅ መገደዳቸው አይቀርም።
“የሐዲስ ኪዳን ጥላ በሆነ በዘመነ ኦሪት በነበረ ሥርዓት በቅብዐ ቅዱስ የከበሩት በመቀደሳቸው ምክንያት የሚነኳቸውን ሁሉ የመቀደስ ኃይል ካገኙ፥ ቅዱሱ ጌታ አማናዊ በኾነው ዘመነ ሐዲስ በቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ የቀደሰው መስቀልማ ምን ያህል ክብርና ቅድስና ይኖረው ይሆን? የሳሙትንና የተሳለሙትንስ እንዴት ያከብራቸውና ይቀድሳቸው ይሆን?” በዚህም መሠረት ክርስቲያኖች ቅዱስ መስቀሉን በመሳም ወይም በመሳለም ክብረ መስቀሉን እንመሰክራለን ።
፫. በመባረክ፦ ከላይ እንደገለጽነው በላዩ ላይ ከተሰቀለበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት የተነሣ መስቀሉ ቅድስናንና ኃይልን ተጎናጽፏል። ለዚህም ምስክሩ ከላይ እንዳየነው በመስቀሉ ዲያብሎስ ድል ተደርጎበታል፤ የገነትም ደጅ ተከፍቶበታል፤ ፈያታዊ ዘየማንም ወደ ገነት አስገብቷል። በዚህም ምክንያት ከላይ እንደገለጽነው የነካቸውንና በእምነት የነኩትን ሁሉ የመባረክ (የመቀደስ) ኃይል አለው። የጌታችን ቀሚስ ለ፲፪ ዓመታት ደም ሲፈሳት የነበረችው ሴት በእምነት በዳሰሰችው ጊዜ ደሟን በቅጽበት እንዳደረቀላት ማስታወስ ለዚህ ንዑስ ርእሳችን ጥሩ ማነጻጸሪያ ነው። (ማቴ.፱፥፳-፳፫።)
መስቀሉ ኃይለ እግዚአብሔር ያደረበት ከመኾኑም በተጨማሪ ለካህናት አባቶቻችን በተሰጣቸውም ሥልጣን እኛ ክርስቲያኖችና የእኛ የሆነው ሁሉ እየተባረክንበት ክፉ የኾነውን ሁሉ እናርቅበታለን፤ ጸጋ መንፈስ ቅዱስንም እንቀበልበታለን። በዚህ አጋጣሚ እስራኤል የተባለ አባታችን ያዕቆብ የልጅ ልጆቹን (የዮሴፍን ልጆች) በአባታቸው ዮሴፍ ጥያቄ የባረካቸው እጆቹን አመሳቅሎ (በመስቀል ምልክት) መሆኑን ልብ ይሏል። (ዘፍ.፵፰፥፲፪-፲፭።) ባራኪው እየባረከ፥ ተባራኪውም እየተባረከ ክብረ መስቀሉን ሲመሰክሩ ኖረዋል፤ እየመሰከሩም ይገኛሉ።
፬. በማማተብ፦ ክርስቲያኖች የሆንን እኛ በእንቅስቃሴዎቻችን ሁሉ ማለትም ከቤት ስንወጣ፣ ወደ ቤት ስንገባ፣ ሥራችንን ስንጀምር፣ ማዕዳችንን ስንጀምርና ስንፈጽም፣ መንገዳችንን ስንጀምር፥ በየመኻሉና ስናጠናቅቅ፣ ጸሎታችንን ስንጀምርና ስንፈጽም፣ አስደንጋጭ ነገር ሲገጥመን፣ በጸሎታችን የመስቀልን ስም ከሚያነሣ አንቀጽ ስንደርስ፣. . . ወዘተ ጣቶቻችንን አመሳቅለን (መስቀል ሠርተን) እንድናማትብ ኦርቶዶክሳዊት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ዘወትር ታስተምረናለች። “እኔ ግን በእግዚአብሔር ጣት አጋንንትን የማወጣ ከሆንሁ፥ እንግዲህ የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ ደርሳለች።” (ሉቃ. ፲፩፥፳) የሚለውን የእግዚአብሔር ቃል ከዚሁ ጋር አያይዞ ማየት፥ ምሥጢሩንም በማገናዘብ መረዳት ይቻላል። ይህም የመስቀሉን ፍቅርና ክብር የምንገልጽበት ሌላው መንገዳችን ነው።
፭. በአንገት በማሠር፦ ክብረ መስቀልን ከምንገልጽባቸው ክርስቲያናዊ የሕይወት ጉዞዎች አንዱ መስቀሉን በአንገት ማሰር ነው። ይህንን የምናደርገው ላመንበት ሃይማኖት፥ ለተቀበልነውም መንፈሳዊ አደራ ያለንን ታማኝነት ለመግለጽ ነው። “በሃይማኖቴ አላፍርም፥ አልደራደርም፤ አንገቴንም እንኳን ሳይቀር ለመስጠት ዝግጁ ነኝ፤” ለማለት ነው። በኦሪቱም እግዚአብሔር አምላካችን በሙሴ አማካኝነት የሰጠውን አምላካዊ ትእዛዝ መመልከት ቃሉን ይበልጥ ለመረዳት ይረዳናል።
ዳግመኛም “እኔም ዛሬ አንተን የማዝዘውን ይህን ቃል በልብህ ያዝ። ለልጆችህም አስተምረው፤ በቤትህም ስትቀመጥ፥ በመንገድም ስትሄድ፥ ስትተኛም፥ ስትነሣም ተጫወተው። በእጅህም ምልክት አድርገህ እሠረው፤ በዓይኖችህም መካከል እንደ ክታብ ይሁንልህ። በቤትህም መቃኖች፥ በደጃፍህም በሮች ላይ ጻፈው።” በማለት የተናገረው ይህንኑ የሚያስገነዝብ ነው ። ጠቢቡ ሰሎሞንም በተመሳሳይ የተናገረው ከዚሁ ጋር ሊመሳከር የሚችል ነው። እንዲህ ያለው፦ “ልጄ ሆይ፥ የአባትህን ትእዛዝ ጠብቅ፤ የእናትህንም ሕግ አትተው፤ ሁልጊዜ በልብህ አኑረው፤ በአንገትህም እሰረው። ስትሄድ ይመራሃል፤ ስትተኛም ይጠብቅሃል፤ ስትነሣ ያነጋግርሃል” (ምሳ ፮፥፳-፳፫)
፮. በሕዝቡ ባህልና የዕለት ተዕለት አኗኗር ውስጥ በመጠቀም፦ ቅዱስ መስቀል ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርነው የክርስቲያኖች የድኅነት ዓርማ ወይም ምልክት ነው። በዚህም ምክንያት ክርስቲያኖች ሁሉ ስለሚመኩበት በአንገታቸው በማሠር ብቻ ሳይወሰኑ በግንባራቸውና በእጆቻቸው በመነቀስ፣ በመኖሪያ ቤታቸው ጣሪያ ላይ በማድረግ፣ በልብሶቻቸው በመጥለፍና በመሳሰሉት ገላጭ ክንውኖች በመጠቀም ለአምላካቸው ለክርስቶስና ለተሰቀለበት መስቀል ክብር ያላቸውን ፍቅርና ታማኝነት በፊትም አባቶቻችን፥ ዛሬም ልጆቻቸው ሲመሰክሩ ኖረዋል፤ ይኖራሉ።
፯. በአባቶች እጅ ዘወትር በመያዝ፦ ከርእሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ጀምሮ እስከ ቀሳውስቱ ድረስ ያሉ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች በእንቅስቃሴዎቻቸው ሁሉ መስቀሉን ይዘው ነው የሚንቀሳቀሱት። የክርስቶስ ቤተሰቦች የሆኑትን ኦርትዶክሳውያን ምእመናንም በቤተ ክርስቲያንና በየቤቶቻቸው እንዲሁም በየመንገዱ ሁሉ ይባርኩበታል።
በተጨማሪም እንደሚታወቀው አባቶቻችን በአገልግሎት ሂደት ወቅት በተለየ ሁኔታ መስቀሉን ይጠቀማሉ። በቅዳሴና በምሥጢራት አጠቃቀም ጊዜ ዲያቆናትም የመጾር መስቀል በመባል የሚታወቀውን የሚጠቀሙ ሲሆን በጥቅሉ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ያለ መስቀሉ የምትፈጽመው ምንም ዓይነት ምሥጢርና አገልግሎት የላትም። ይህም ለመስቀሉ ያለንን አክብሮትና ፍቅር የምንገልጽበት ሌላው ማሳያችን ነው።
፰. በጥንታውያን ቅርሶቻችን ላይ በማድረግ፦ሀገራችን ኢትዮጵያ ክርስትናን ከኢሩሳሌም ቀጥሎ ከሌሎች ሀገሮች ቀድማ የተቀበለች ሀገር እንደመሆኗ ትእምርተ መስቀሉን ተቀብላ ያላትን ፍቅርና ክብር ለመግለጽ በልዩ ልዩ መገልገያዎቿ ላይ በመቅረጽ ስትጠቀምበት ኖራለች። ለማሳያ ያህልም፦ በመገበያያ ገንዘቦች (ሳንቲሞች)፣ በነገሥታት ዘውዶችና አልባሳት ላይ በመቅረጽ፣ በቤተ መንግሥት ቤቶች፣ አጥሮችና የመሳሰሉት ላይ የመስቀሉን ምልክት በማኖር ለመስቀል ያላትን ክብር ስትገልጽ ኖራለች፤ ዛሬም ስለ ክብሩ ትገልጻለች፡ትመሰክራለችም።
፱. በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጉልላት፣ በበሮቿ፣ በግንቦቿ፣ በአጥሮቿና በንዋየ ቅድሳቷ ሁሉ ላይ ትእምርተ መስቀሉን በመጠቀም፦ ከላይ የጠቀስነው እንደ ሀገር ሲታይ ሲሆን አሁን ደግሞ እንደ ቤተ ክርስቲያን የሆነውን እንመልከት በገሃድ እንደሚታየው ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከጉልላቷ ጀምሮ በሕንጻ ቤተ ክርስቲያኗ ሁለንተና ላይ የመስቀሉን ምልክት ተሸክማ ትታያለች። ክብረ መስቀሉን ከምትመሰክርባቸው መንገዶች አንዱ በውስጥና በውጭ አገልግሎት ሁሉ በንዋየ ቅድሳትና ላይ መስቀሉ ተቀርጾበት ለአገልግሎት ማዋል የተለመደና የታወቀ ነው።
፲. በስሙ በመሰየም፦ በመስቀሉ ስም ታቦት (ጽላት) ቀርፆና ቤተ ክርስቲያን ሠርቶ አክብሮ መገልገል የመጀመሪያው ማሳያ ነው። በተጨማሪም ካህናት ተጠማቂዎች ፡ ምእመናንን በመስቀሉ ስም ገብረ መስቀል፣ ወለተ መስቀል፣ ብርሃነ መስቀል፣ መስቀል ክብራ፣. . . እያሉ በመሰየም ነው።) ለመሰቀሉ ያላቸውን ክብርና ፍቅር ሲመሰክሩ ኖረዋል፤ይኖራሉም።
፲፩. በዓሉን በማክበር፦ እንደሚታወቀው ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በዓለ መስቀልን ከዘጠኙ ንዑሳት የጌታ በዓላት መካከል አንዱ እንዲሆን አድርጋለች። በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ መሠረት በተለይ ዓመታዊ በዓላቱን ክርስቲያኖች እንደ አቅማቸውና ዕውቀታቸው መታሰቢያውን እያደረጉ በማክበር ይማጸኑበታል። በይበልጥ ደግሞ በመስቀል ስም በተሰየሙ አብያተ ክርስቲያናት በልዩ ሥርዓት እያከበሩ በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስን እያገኙና እያደሉ ይኖራሉ። በተለይም ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን በመላው ዓለም ዘንድ በታወቀው የመስከረም ፲፮ የደመራ በዓልና የመስከረም ፲፯ በዓለ መስቀል በምትሰጠው አገልግሎትና በምትፈጽመው ምስክርነት ለሀገራችን ለኢትዮጵያ ታላቅ በረከትን ስታድል ኖራለች፤ ትኖራለችም። ለክብረ መስቀሉ ማክበሪያ ይሆን ዘንድም ቅድስት ቤተ ክርስቲናችን በመላው የሀገራችን ክፍሎች የመስቀል በዓል ማክብሪያ ዐደባባዮችን ተቀብላ ዓመታዊ በዓለ መስቀሉን በማክበር ላይ ትገኛለች።
፲፪. በልዩ ኹኔታ የተፈጸመ ምስክርነት፦ እግዚአብሔር አምላካችን በብሉይ ኪዳን ክብሩን የገለጸባትን ታቦተ (ጽላተ) ጽዮንን ከዓለም ሀገራት መርጦ በኢትዮጵያ ማኖሩ ይታወቃል። በተመሳሳይ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበትንና ክብሩን የገለጸበትን ቅዱስ መስቀል (ግማደ መስቀል) በአደራ ያኖረው በኢትዮጵያ መሆኑም ግልጽ ነው።
በዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመነ መንግሥት በ፲፭ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ወደ ኢትዮጵያ የመጣውን ግማደ መስቀል አባቶቻችንና እናቶቻችን በታላቅ ክብር ተቀብለው መስቀለኛ በሆነው ግሸን ደብረ ከርቤ ቅዱስ ተራራ አውጥተውና ለምድር አደራ ሰጥተው ዛሬም ድረስ በክብር ተቀምጦ ይገኛል። በዚህም መሠረት “አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል፤ መስቀሌን በመስቀለኛ ስፍራ አኑር፤” በማለት በቅዱስ ዑራኤል አማካኝነት ልዑል እግዚአብሔር የሰጠውን ትእዛዝ በመፈጸም በፈሪሀ እግዚአብሔር የሚመሩ እውነተኛ የወንጌል አማኞች መሆናቸውን ለዓለም አሳይተዋል። ከመስቀሉ ጋር በተያያዘም በዚሁ ቅዱስ ስፍራ በያመቱ መስከረም ፲፮ እና ፲፯ እንዲሁም ፳፩ ቀናትን በልዩ ክርስቲያናዊ ሥርዓት በማክብር ለመስቀሉ ያለንን ክብር በመመስከር ላይ እንገኛለን።
እንደሚታወቀው ሁሉ ከቅድስት ዕሌኒ ጋር በተያያዘ ተረክቦተ መስቀሉን (የመስቀሉን መገኘት) ያለውን ታሪክ የዓለም ማኅበረሰብ የሚያውቀው፣ የሚጽፈውና የሚናገረው ነው። በዓለም ላይ የሚገኙ አኃትና ኦርቶዶክሳውያን አብያተ ክርስቲያናት በየባህላቸው በዓለ መስቀልን የሚያከብሩበት የየራሳቸው መንገድ እንዳላቸውም ይታወቃል። ሌላው በክርስትና ስም የሚጠራው የምዕራቡ ዓለም ደግሞ እንኳን ሊያከብረው ይቅርና መስቀሉን በማጥላላትና በመንቀፍ የስህተት ትምህርት በማሠራጨት ተጠምዷል ፡፡በዚህ ሁሉ የተደበላለቀ ሁኔታ ውስጥ ከዓለም ሀገራት ተለይታ ለታወቀውና ለተገለጸው መስቀለ ክርስቶስ ተገቢውን ክብር በአፀደ ቤተ ክርስቲያን ሳትወሰን በዐደባባይ በዓልነት ወስና በደመቀ ሁኔታ ስትሰጥ የኖረችና በመስጠት ላይ ያለች ብቸኛ ቤተ ክርስቲያንና ሕዝበ ክርስቲያን ያሉባት ሀገር ኢትዮጵያ ብቻ ነች።
መ. ማጠቃለያ
ቅዱስ መስቀል እንደ ተቋም ለኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን፥ እንደ ኅብረትም ለአንዲቷ የምእመናነ ክርስቶስ ጉባኤ ሁለንተናዋ ነው። በተለይም ተጋዳዪቱ የክርስቶስ አካል ኦርቶዶክሳዊት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ኃይል፥ ጽንዕ፥ መመኪያ ትእምርት (ምልክት) ይሆናት ዘንድ ከጌታዋ በተሰጣት መመሪያ መሠረት ተሸክማውና ተመርኩዛው ነገረ ክርስቶስን ስትመሰክር ትኖራለች። “ከቀስት ፊት ያመልጡ ዘንድ፥ ወዳጆችህ እንዲድኑ፥ ለሚፈሩህ ምልክትን ሰጠኻቸው።” (መዝ. ፶፱፥፬።) ተብሎ በቅዱስ ዳዊት እንደተገለጸው፥ ከአምላኳ የተሰጣትን ቅዱስ መስቀል ተቀብላና አክብራ እንደ አስፈላጊነቱ ስትጠቀምበት ኖራለች፤ ትኖራለችም። በዓለ መስቀሉን አባቶቻችንና እናቶቻችን በአማረና በደመቀ ሁኔታ ሲያከብሩ ኖረዋል፥ እኛም እናከብራለን፤ ስንል ምን ማለታችን ነው? ጽኑዓን የሆኑት አባቶቻችንና እናቶቻችን የቻሉትን ማድረጋቸውና እኛም የቻልነውን ሁሉ ማድረጋችን ለመስቀሉ እነርሱ የጨመሩለት፥ እኛም ደግሞ የምንጨምረው ክብር ኖሮ አይደለም።
ይልቁንስ ለቅዱስ መስቀሉ ክብር የነበራቸውንና ያለንን ፍቅር ለመግለጽ ያህል እንጂ ዋናው ምሥጢር በመስቀሉ ከብረውበታል፤ እኛም እንከብርበታለን፤ ማለታችን ነው። በዓለ መስቀሉን ከላይ በገለጽናቸው ልዩ ልዩ መንገዶች ስናከብርም በቅዱስ መስቀሉ ያገኘነውን እና የተረጋገጠውን የመዳናችንን ምሥጢር እያወደስንና እያከበርን እየመሰከርንም መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል።በክፉዎች አይሁድ ተቀብሮና ጠፍቶ የነበረው ቅዱስ መስቀል በፈቃደ እግዚአብሔር በቅድስት ዕሌኒ አማካኝነት ወጥቶ ከተገኘበት ጊዜ ጀምሮ በዓለ መስቀል በልዩ ሁኔታ መከበር መጀመሩ ይታወቃል። በዚህ ዘመን የምንገኝ ክርስቲያኖችም በዓለ መስቀሉን ስናከብር ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀሉ ላይ በቆረሰው ቅዱስ ሥጋውና ባፈሰሰው ክቡር ደሙ የሰጠንን ሀብታት በማስታወስ መሆን እንደሚገባው መርሳት የለብንም። በመስቀሉ ሰላምን፣ ዕርቅን፣ አንድነትን፣ ሕይወትን፣ ፍቅርን፣ ደስታን፣ ክብርን፣ ርስተ መንግሥተ ሰማያትን ማግኘታችን ይታወቃል። ዛሬ ግን የመስቀሉን ስጦታዎች ወደ ጎን ገሸሽ አድርገናቸው በተቃራኒው የጥፋት መንገድ ውስጥ በመግባታችን ጦርነትን፣ ጸብን፣ መለያየትን፣ኅዘንን፣ ሞትን፣ ውርደትን፣ . . እያነገሥናቸው መሆኑም ግልጽ ነው።
ስለዚህ በዓለ መስቀሉን ስናከብር እግዚአብሔር አምላካችን አሁን ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? የሚለውን ቆም ብሎ ማስተዋል ይኖርብናል። ይህ በዓል የቅዱስ መስቀሉን ትሩፋቶች በማሰብ ከጥላቻ ይልቅ ፍቅርን፣ ከጦርነት ይልቅ ሰላምን፣ ከመለያየት ይልቅ አንድነትን፣ ከኅዘን ይልቅ ደስታን፣ ከሞት ይልቅ ሕይወትን፣ ከውርደት ይልቅ ክብርን፣ ከቂምና ከበቀል ይልቅ ዕርቅን፣ . . . ለማረጋገጥ አቅም የፈቀደውን ሁሉ የሚያደርጉ ምእመናንንና ምእመናትን ይፈልጋል። ከዚሀ ውጪ ሆነን ቀን ቆጥርን፣ ነጭ ለብሰን፣ ቤታችንን ጎዝጉዘን፣ ጠጅ ጥልን፣ ጠላ ጠምቀን፣ ፍሪዳ አርደንና አወራርደን፣ ታላቅ ድግስ በመደገስ መስቀሉን አጅበን፣ ሆ! ብለንና ዘምረን በማሳለፍ ብቻ በዓለ መስቀልን ያከበርን የሚመስለን ካለን የተሳሳትን መሆናችንን መገንዘብ ይኖርብናል።
በዓሉ ታሪኩን በመተረክ ላይ ብቻ ሳንወሰን እንደቀድሞው ሁሉ ዛሬም የጠፋውንና ያጣነውን ለኢትዮጵያ፣ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያንና ለሁላችንም በእጅጉ አስፈላጊ የሆነውን ነገር ሁሉ መፈለግንና ከተቀበረበት ቆፍሮ ማውጣትን ይፈልጋልና።
እንደ ደመራው እሳትም የፍቅርን፣ የሰላምን፣ የደስታንና የአንድነትን እሳት በሃይማኖት በማቀጣጠል (በማንደድ) ጥላቻን፣ መለያየትን፣ ዘረኝነትን፣ ኅዘንንና የመሳሰሉትን ጎጂ የሆኑ የሰው ልጅ ጠላቶች በተቀጣጠለው እሳት ማጥፋት ይጠበቅብናል። እያንዳንዳችን የመስቀሉ ወዳጆች የሆንን ሁሉ ራሳችንንም እንደ ዕጣኑ መዓዛ የተወደደ መሥዋዕት አድርገን እስከ ማቅረብም ደርሰን አስፈላጊውን ሁሉ መሥዋዕትነት ለመክፈል መዘጋጀት ተገቢ ነው። ከምንም በላይ እያንዳንዳችን ከእግዚአብሔር ጋር ሕጉንና ትእዛዙን በመጣስ መጣላት አለመጣላታችንን ማረጋገጥ አለብን። እኛው በድለን ከእርሱ ተጣልተንና ተለይተን ስንኖር ዕርቅ፣ ሰላምና አንድነትን የሰጠን ወልደ እግዚአብሔር ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑ ይታወቃል።
አሁን ራሳችንን መመርመር ያለብን በእኛና በእግዚአብሔር መካከል የጥል ግድግዳ አቁመናል ወይስ አላቆምንም? የሚለውን ነው። የጥል ግድግዳ አቁመን ከሆነ በዓለ መስቀልን ልናከብር የሚገባው በመጀመሪያ የጥሉን ግድግዳ አፍርሰንና በንስሓ ወደ ቤቱ ከተመለስን ከኃጢአት ከበደላችን ከነጻን በኋላ በመስቀሉ ላይ የተቆረሰውን ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን በመቀበል ነው። እንዲህ ባለ መንገድ ማክበር ከቻልን “መስቀል መልዕልተ ኵሉ ነገር ያድኅነነ እምፀር።ከጠላት የሚያድነን መስቀል ከሁሉ ነገር በላይ ነው።” በማለት ከቅዱስ ያሬድ ጋር ለመዘመርና በዓለ መስቀሉን በእውነት ለማክበር እንችላለን።
ልዑል እግዚአብሔር በኃይለ መስቀሉ ይጠብቀን ለዘለዓለሙ አሜን።
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!