“በዐዋቂ ልጅ ሀገር ትጸናለች” (ሲራ.፲፮፥፬)

የአንድ ሀገር ቋሚ ሀብቶቿ ልጆችዋ ናቸው፡፡ ሕዝብ ሀገር ወዳድና ጠንካራ ሲሆን አነዋወሩን ከመቀየር ጀምሮ የሀገሩን ታሪክ በወርቃማ ቀለም መጻፍ ይችላል፡፡ እንዲህ ያለው ተስፋ ብዙውን ጊዜ በአዳጊ ሀገሮች ለወጣቶች ይሰጣል፡፡ ይህ የሚሆነው በብዙ ሀገሮች ውስጥ ከፍተኛውን የነዋሪ ቁጥር ከሚይዙት ውስጥ ሕፃናትና ወጣቶች በመሆናቸው እና በአባቶች ፈንታ አገር የሚረከቡም ጭምር በመሆናቸው ነው፡፡

በሀገራችን ኢትዮጵያም ይህን ከፍተኛ ቁጥር የያዙት ሕፃናትና ወጣቶች ናቸው፡፡ እንደ ሌሎች አዳጊ ሀገራት ሁሉ የሀገሩቱ አስከፊ ገጽታ በመቀየሩ ረገድ ሰፊ ሚና ያላቸው እነዚህ ወጣቶች ናቸው፡፡

ቤተ ክርስቲያንም ሀገር ወዳድ፣ ታሪክ ሠሪና ታታሪ ትውልድ የማፍራት ሥራዋን ስትሠራ ኖራለች፡፡ የሀገራችንን ሕዝብ ከፊደል ቆጠራ እስከ ሥርዓተ መንግሥት ቀረጻ አስተምራና የሀገሪቱን ታሪክ በሕዝቡ ቋንቋና ፊደል ጽፋ ያቆየች ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ በዚህ ትውልድም ውስጥ የለውጥ አርአያ የሚሆን ዜጋ ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ውስጥ የበኩሏን አስተዋጽኦ እያደረገች ትገኛለች፡፡

ትውልድ መፍትሔ ፈላጊ ሊሆን የሚችለው አዋቂ የሆነ እንደሆነ ብቻ ነው፡፡ የዕውቀት ብርሃን የያዘ ትውልድ የድህነትና የበሽታ፣ የጦርነትና የርኃብ ጨለማ አያሰጋውም፡፡ የዕውቀት ብርሃን የችግር መፍቻ ቁልፍ ነውና፡፡ ቤተ ክርስቲያን ከማይነጥፍ ማሕፀኗ ልትወልደውና ልታሳድገው የምትሻው እንዲህ ያለውን ነው፡፡ ለዚህ ነው ጠቢቡ “ከሺህ ልጆች አንድ አዋቂ ልጅ ይሻላል፤ ክፉ ልጅም ከመውለድ ሳይወልዱ መሞት ይሻላል፤ አዋቂ በሆነ በአንድ ልጅ ሀገር ትጸናለችና” በማለት የገለጸው፡፡ (ሲራ.፲፮፥፬)፡፡

ሰው ሁሉ በሙያ ዘርፉ ተሰማርቶ እየሠራ ያለው ዕውቀት ቢኖረው ነው፡፡ ታዲያ ለምን ውጤታማ መሆን አልተቻለም? ብዙ መንፈሳውያን የሆኑና በዕውቀት የበሰሉ ባሉባት ኢትዮጵያ ለምን ሥጋዊ ችግሮች ሰለጠኑ? የሚሉ በርካታ ተመሳሳይ ጥያቄዎች በማኅበረሰባችን ዘንድ የመወያያ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ ዕውቀቱም፣ ጉልበቱም፣ ገንዘቡም፣ ጊዜውም ተደምረው ለምን ለውጥ አላመጣም? የለውጡ መሠረት ምንድው? የቅዱሳት መጻሕፍት መጻፍ ቀዳሚ ዓላማ የለውጥን መንገድ መጠቆም ነውና ጠቢቡ በቅዱስ መጽሐፍ የሰጠንን ምክር እንመርምር፡፡ “በአዋቂ ልጅ ሀገር ትጸናለች” ብሎናልና፡፡

ዕውቀት ማለት በአንድ ዘርፍ ያለን ክህሎት አይደለም፡፡ ሁለቱን ዓይነት የዕውቀት ዘርፎች ይዞ መገኘት እንጂ፡፡ ዕውቀት ሁለት ዓይነት ነው፡፡ ዕውቀት ሥጋዊና ዕውቀት መንፈሳዊ፡፡ አዋቂነትም ሁለቱንም ዓይነት አጣምሮ መያዝ ነው፡፡ በአንድ ጎን ወይም ዘርፍ ማደግ ብቻውን የሰው ልጆችን ፍሬያማ አያደርግም፡፡ ለሀገር ለወገን ለቤተሰብና ለራስ መሆን የሚችል ዜጋ ለማፍራት በትክክል “በሁለት ወገን የተሣለ ሰይፍ” መሆን ያስፈልጋል፡፡ ይህ ነው በዕውቀት ሥጋዊ፣ በዕውቀት መንፈሳዊ፣ መታነጽ ማለት፡፡

ዕውቀት ሥጋዊ ከቤተሰብና ከአካባቢያዊ ሁኔታዎች ጀምረን በየደረጃው በትምህርት ማእከላትና በልዩ ልዩ መንገዶች የምናገኘው የተግባርና የቀለም ትምህርት ነው፡፡ ይህ ዕውቀት በተለይም በምድራዊ ኑሮአችን የሚኖረንን የግልና የማኅበር ሕይወት መልካም ለማድረግ ካለው ፋይዳ ባሻገር ለማኅበረሰባችንና ለሀገራችን ያለንን የምናካፍልበት የምድራዊ ኑሮ ክፍል ነው፡፡

ዕውቀት መንፈሳዊ የሰው ልጅ ከምድራዊ ኑሮው በኋላ ያለውን ሰማያዊ አነዋወር /አኗኗር/ የሚዋጅበት ዕውቀት ነው፡፡ ሁለቱም የዕውቀት ዓይነቶች ተፈላጊ ናቸው፡፡ ሰው የሁለት ነገር ውሕድ ፍጥረት ነው፡፡ የሥጋና የነፍስ፡፡ ሁለቱን ባሕርያት ማጣጣም ማዋደድና ማስታረቅ የመንፈሳውያን ሰዎች ዕውቀት መመዘኛ ነው፡፡ የሰው ልጅም ይህን ይይዝ ዘንድ ግድ ይለዋል፡፡

“ያልተገራ ፈረስ ገራገር ይሆናል፣ ያልተማረ ልጅም አውታታ ሆኖ ያድጋል፡፡ /ሲራ.፴፥፰/፡፡ ፈረስን መግራት ካልቻሉ ወይም አሥረው መያዝ ካልቻሉ አደጋ እንደሚያስከትል ሁሉ ከዕውቀት ሥጋዊ እና ከዕውቀት መንፈሳዊ ያልተማረ ልጅም አውታታ፣ ባተሌ፣ ባካና፣ ቀማኛ፣ ሥራ ፈት እየሆነ ያስቸግራል፡፡ ይህ ሁሉ የጨለማ ሥራ የሚሠራው ከዕውቀት ብርሃን የራቀ በመሆኑ ነው፡፡ ዕውቀት የሰው ልጅ ብርሃን ናትና፡፡

የሀገርን ሀብት የሚበዘብዝና የሚሠርቅ፣ ጉቦ የሚቀበል ዜጋ ምንም እንኳን በወረቀት ያስደገፋቸው የዕውቀቱ ማስረጃዎች /የምሥክር ወረቀቶች/ በዝተው የሥልጣንን እርከን እንዲቆናጠጥ ቢያስችሉትም ገና የዕውቀት ብርሃን ያልበራለት የእናት ጡት ነካሽ ነው፡፡ በአዋቂ ልጅ ሀገር ትጸናለች እንጂ አትፈርስም፣ ትለመልማለች እንጂ አትመዘበርም፡፡

አዋቂ የሆኑ የኢትዮጵያ ልጆች ሀገራቸው ከሰሜን ጫፍ እስከ ደቡብ፣ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ ያላትን የቀደመ ታሪክ የሚያውቁ፣ ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ያላቸውን የታሪክ አንድነት ነጥለው የማያዩና በዚህም የሚኮሩ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ የኢትዮጵያ ታሪክ የሚሆነው በሰዎች ስምምነት አይደለም፤ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዘመናት አብረው የተሻገሯቸው ዘመናት እንጂ፡፡ ለዚህም የኢትዮጵያ ታሪክ እውነተኛ ምንጮች የቤተ ክርስቲያናችን መዛግብት መሆናቸው ብቻውን ምሥክር ነው፡፡ ትውልዱን አዋቂ የሚያሰኘውም ዕድሜ ብቻ ሳይሆን እውነትንም ጭምር ከጠገቡት መዛግብት እውነቱን መረዳት ማወቅና ማሳወቅ ሲችል ነው፡፡

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ለኢትዮጵያ ሀገራችን ያበረከተቻቸውን አስተዋጽኦዎች ዘርዝሮ መጨረስ አይቻልም፡፡ በጥቅሉ ያየናቸው እንደሆነ ግን በርካታ ሥነ ጥበባት፣ ማኅበራዊ አንድነትን /በሕዝቦች ዘንድ ተዋሕዶና ተፋቅሮ የመኖር ባሕል/ ወዘተ… ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ይህ ሁሉ በአዋቂ ልጆቿ ትጋት የተገኘ ነው፡፡

በልዩ ልዩ ደረጃዎች የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች የሀገሪቱን ማንነት በግልጽ የተረዱ ሊሆኑ ይገባል፡፡ በዚህ ዕውቀት ላይ ተመሥርተው የሚሠሩት የአገር ግንባታ ሥራ ውጤታማ ብቻ ሳይሆን አኩሪ ታሪክም ይሆናልና፡፣ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የምትገኝ ሀገር ብቻ አይደለችም፡፡ በሕዝቦቿ ዘንድ አኩሪ ታሪክ ያላት የነጻነት ምልክት፣ በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ተደጋግሞ ስሟ በበጎ የተጠቀሰ መንፈሳዊት ሀገርና የክርስትና ደሴትም ጭምር ናት፡፡ /መዝ.፷፯፥፴፩፤አሞ.፱፥፯/ አዋቂ ልጅ በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ኢትዮጵያን የሚያውቃት ነው፡፡ ማንነቱን በትክክል መረዳት ያልቻለን ሰው እንዴት አዋቂ ልንለው እንችላለን?

በሁለት ወገን የተሳሉ ሰዎች ልበ ብርሃን በመሆናቸው አስተዋይነት ገንዘባቸው ነው፡፡ “አስተዋይነት ያልታከለበት ዕውቀት ለውድቀት” እንደሚባለው ከመውደቅ በፊት አስተዋይነትን ገንዘብ ልናደርግ ይገባል፡፡ አስተዋይነት አዋቂ ነን ከሚሉ ሰዎች መካከል በሁለት ወገን የተሳሉ ሰዎችን ለይታ የምታሳይ የመንፈሳውያን ሰዎች መለያ ናት፡፡

የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነጾር በከፈተው ት/ቤት እንዲማሩ የተመረጡ ተማሪዎች ከመስፈርቶቹ መካከል ብልሃተኝነት አንዱ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ተመርጠው ወደ ትምህርት ማእከሉ ከገቡ በርካታ ተማሪዎች መካከል በአስተዋይነት ተለይተው የወጡት በዕውቀትና በመንፈሳዊ ትጋት የበሰሉት ሠለስቱ ደቂቅ ነበሩ፡፡ /ዳን.፩፥፬/ የሦስቱ ሕፃናት በስደት አገር እየኖሩ ለሕዝባቸውና ለሀገራቸው ታሪክ መሥራት፣ ሕዝባቸውን መጽናትና በስደት አገር ሀራቸውን በበጎ ማስጠራት የቻሉት በአስተዋይነት ነው፡፡

የአስተዋዮች ጸሎት ሁልጊዜ በማስተዋል ይመላለሱ ዘንድ ነው፡፡ ዕውቀትና ጥበብን፣ ገንዘብንና ጉልበትን አስማምቶ ውጤት ማምጣት የሚቻለው በማስተዋል ነውና፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞን ወደ አባቱ የንግሥና ዙፋን ሲመጣ በጸሎቱ አስተዋይነት ገንዘብ እንዲያደረግ መለመኑ ለዚህ ነው፡፡ /፩ነገ.፫፥፱/፡፡ “በአዋቂ ልጅ ሀገር ትጸናለችና፡፡”

በጠቢቡ ሰሎሞን ዘመን አንድ እስራኤል ነበር፡፡ ጠቢቡ አዋቂ ልጅ ነበርና ለመጀመሪያ ጊዜ ለእግዚአብሔር ታቦት ማደሪያ ቤት /ቤተ መቅደስ/ አነጸ፡፡

አስተዋይነት ያለንን ዕውቀት በአግባቡ መጠቀም መቻል ነው፡፡ በየደረጃው የተማርናቸውን ትምህርቶች በአግባቡ በሥራ መተርጎም ከቻልን አስተዋይነታችን በውጤታማነታን ይገለጻል፡፡ የቤተ ክርስቲያን ልጅነታችንን በቅዱሳን አሠረ ፍኖት የምንጓዝ መሆናችንን ለሕግጋተ እግዚአብሔር የምናረጋግጠው በምግባራችን ነው፡፡ ይህ ነው አዋቂ የሚያሰኝ ተግባር፡፡

ታማኝነት ሌላኛው የአዋቂዎች መገለጫ ነው፡፡ ሀገርን ለማጽናት የሕዝብን ኑሮ ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ታማኞችን ማግኘት ካልተቻለ ከንቱ ድካም እየተደከመ ነው፡፡ በቤተሰቡ መካከል ጠብን የሚዘራ ሰው ለሀገር ሰላም ያመጣል ማለት እንዴት ይቻላል? የእናቱን መሀረብ የሚፈታ፣ የአባቱን ኪስ የሚያወልቅ ልጅ ነገ በሚሠማራበት የሥራ መስክ በታማኝነት ያገለግላል ማለት ያስቸግራል፡፡ አዋቂነት ታማኝነት ነው፣ ሀገርን ማጽናትም ከታማኝነት ይጀምራል፡፡

የልጆችን ሰብእና እንዴት ወደዚህ ደረጃ እናምጣ? በልጅነት ዕድሜው ወላጆቹ የሚያወጡለት የትምህርት ቤት ክፍያ፣ ስለሚለብሰው ልብስና ስለ ሌሎች ተመሣሣይ ወጪዎቹ ኃላፊነት የማይሰማውና ግድየለሽ አድርጎ ልጆችን መቅረጽም በነገ ሕይወታቸው ንዝህላልና በአሠራር ዝርክርክነት የሚታወቁ ያደርጋቸዋል፡፡ ስለዚህ የታማኝነትና የኃላፊነት መልካም ሥነ ምግባራትን በልጆች ሥነ ልቡና ውስጥ ከልጅነት ዕድሜ ጀምሮ ማስረጽ አለብን፡፡ በአዋቂ ልጅ ሀገር ትጸናለችና፡፡ ወላጆች በእግዚአብሔር ፈቃድ ልጆችን ወደዚህ ምድር እንዳመጡ ሁሉ ለልጆቻቸው ሕይወት ስኬታማነት ሊጠበቡ ያስፈልጋል፡፡ አልሚም አጥፊም ትውልድን  ይፈጥራሉና፣ አዋቂም አጥፊም ልጅ ያስገኛሉና፡፡

ሀገርን የሚጠብቅ፣ የሚገነባና የሚያጸና ትውልድ መቅረጽ ካልተቻለ የሚያፈርስ፣ የሚሸጥና የግል ጥቅሙን የሚያስቀድም ዘር/ትውልድ/ ያስቀራሉና ታማኝነትን፣ ሀገር ወዳድነትንና የእምነት ጽናትን ከልጅነት ዕድሜ ጀምሮ ልጆችን ማስተማር አለብን፡፡

የልጆች በቅዱሳት መጻሕፍት ምክር፣ በወላጆች ተግሣጽ ማደግ የሚያስገኘው ጥቅም ብዙ ነው፡፡ ጠቢቡ “እናንት ልጆች የአባትን ተግሣጽ ስሙ፣ ማስተዋልንም ታውቁ ዘንድ አድምጡ” /ምሳ.፩፥፬/ በማለት ልጆች የወላጆቻቸውን ምክር ያደምጡ ዘንድ ይመክራል፡፡ ልጆችን በምክር በማሳደግ አስቀድሞ ወላጆች ታላቁን አደራ ተወጥተዋል ማለት ነው፡፡ ልጆች ከእግዚአብሔር እጅ የተቀበልናቸው የከበሩ ሥጦታዎች ናቸው፡፡ በመሆኑም ልጆችን መንከባከብና በሥነ ምግባር ማሳደግ የእግዚአብሔርን ሥጦታ መጠበቅ ነው፡፡ /መዝ.፩፻፮፥፫/፡፡ ከወላጆችም በላይ ግን ልጆች የታማኝነት፣ የትሕትናና የዐዋቂነት ሥነ ልቡና እያዳበሩ የሚያድጉ ከሆነ ተወዳጅና ተመራጭ ያደርጋቸዋል፡፡ በዚህም አብዝቶ ተጠቃሚዎች ልጆች ይሆናሉ፡፡ የልጆች ጥቅም የወላጆችም ጥቅም ነው፡፡ የልጆች መልካምነት ለወላጆች ኩራት ነው፡፡ ለልጆችም አስፈላጊና ጠቃሚ ነው፣ በወላጆች ዘንድ ተወዳጅ ያደርጋልና፡፡ /ምሳ.፬፥፫/፡፡ በዚህ ብቻ አይበቃም በሥነ ምግባር በሃይማኖት ተኮትኩተው በሚያድጉ ልጆች ቤተ ክርስቲያንም ሀገርም ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡ “በአዋቂ ልጅ ሀገር ትጸናለች” እንደተባለ፡፡

በአጠቃላይ ሀገራችንም ቤተ ክርስቲያናችንም በርካታ “አዋቂዎች” የሚሹበት ዘመን ቢኖር ዛሬ ነው፡፡ አስተዋዮች ብቻ ሳይሆኑ በመንፈስ ቅዱስ ፀጋ የሚሠሩ የሃይማኖት ልጆችን በዕቅድና በሥርዓት ማሳደግ አለብን፡፡ ካለፈው ተምረው መጻኢውን የሚተነብዩ ለፈቃዳቸው፣ ለሐሳባቸውም እግዚአብሔርን በማስቀደም የሚሠሩ ልጆችን ማዘጋጀት የሚጀምረው ደግሞ በልጅነት ዕድሜአቸው ነው፡፡ እነዚህ ናቸው ሀገርን የሚያጸኑ፣ ቤተ ክርስቲያንን የሚጠብቁ፡፡

ቤተ ክርስቲያን የምትፈልገው አዋቂ ልጅ መስቀሏን በገንዘብ የማይለውጠውን፣ ቅርሶቿን የማይሸጠውን፣ ሃይማኖቷን የማይክደውን ነው፡፡ በከፋ ፈተና ውስጥ እያለፈ እንኳን “የማመልከው አምላክ ያድነኛል፣ ባያድነኝ እንኳ እንዲህ ያለውን አላደርግም” የሚለውን ነው፡፡ /ዳን.፫፥፲፯/፡፡

ሀገራችን ብዙ ጠበብት፣ ብዙ አዋቂዎችን ትሻለች፡፡ ፊደል የቆጠሩ፣ እንግሊዝኛ የሚናገሩ ብቻ ሳይሆን ወደተሻለ የዕድገት ደረጃ የሚያሸጋግሯትን ቅን ልቡና ያላቸውን አዋቂዎች ትሻለች፡፡ ሀገራችን የታሪኳ መበረዝ፣ የዕድገቷ ኋላ ቀርነት፣ የድህነቷ መብዛት፣ የሕፃናቷ ሞት፣ የሥነ ምግባር ውድቀት፣ የጠላቶቿ መብዛት፣…. የሚያስቆጫቸው፣ የሚያቃጥላቸውና ለለውጥ የሚሠሩ አዋቂ ልጆች ያስፈልጓታል፡፡

“ሮም በአንድ ቀን አልተገነባችም” እንደሚባለው የኢትዮጰያን ዕድገት በአንድ ጀምበር አናመጣውም፡፡ ይልቁንም አዋቂ ልጅ መርሐ ግብር ነድፎ የድርሻውን ጠጠር ይወረውራል፡፡ ያኔ ኢትዮጵያን እንደ ጥንቱ ሁሉ ከታላላቅ ሀገሮች ተርታ የምናይበት ዘመን ይመጣል፡፡

አዋቂዎችን አያሳጣን፡፡ አሜን፡፡

ምንጭ፡- ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ፣ ጥር፲፭-፴፣ ፳፻፩ ዓ.ም

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *