“በወንድማማችነትም ፍቅርን ጨምሩ” (፪ኛጴጥ.፩፥፯)
በቀሲስ ኃይለሚካኤል ብርሃኑ
ክፍል ሦስት
ፍቅር የሁሉ ማሰሪያ ነው፡” የሺህ ፍልጥ ማሰሪያው ልጥ” “እንደሚባለው የምግባራት ሁሉ መደምደሚያ ፍቅር ነው፡፡ ስለዚህ በወንድማማችነት ፍቅር መጨመር እንደሚገባ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በመልእክቱ አስገንዝቦናል፡፡ “እርስ በርሳችሁ ከመዋደድ በቀር ለማንም ዕዳ አይኑርባችሁ ባልንጀራውን የወደደ ግን ሕግን ሁሉ ፈጸመ” (ሮሜ.፲፫፥፰) ብሏልና፡፡ የሕግ ሁሉ ፍጻሜው ፍቅር ነው፡፡ እሱም በሁለት መልኩ ይፈጸማል የመጀመሪያው ሕግ እግዚአብሔር አምላካችንን በፍጹም ልባችን፣ በፍጹም አሳባችን፣ በፍጹም ኃይላችን መውደድ ሲሆን ሁለተኛውም ባልጀራችንን እንደ ራሳችን አድርገን መውደድ ነው፡፡
በመሆኑም እነዚህ ከላይ ጀምሮ የዘረዘርናቸው ሁሉ በእኛ ቢሆኑ መንፈሳዊ ፍሬን ማፍራት እንደሚቻለን ቅዱስ ጴጥሮስ በመልእክቱ እንዲህ አስገንዝቦናል፡፡ ይህም ወጣትነት መንፈሳዊ ፍሬዎቻችን ጎልተው የሚታዩበት ተግተን ለአገልግሎት የምንሰማራበትን ሰፊ አገልግሎትን የምንፈጽምበት ስለሆነ ከፊት ይልቅ መትጋት ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡
ወጣትነት በእግዚአብሔር ቃል ካልበለጸገ ከውስጥ በሚመነጭ ፈቃደ ሥጋ ምክንያት ጥያቄ ውስጥ የሚከት ፈታኝ ወቅት ነው፡፡ ውጫዊውን ነገር ሁሉንም ለመጨበጥ የራስ ተነሣሽነት ሲያይል፣ ውስጣዊው ፈቃድ ደግሞ ዐይን ያየውን ልብ የተመኘውን ለመፈጸም በሚነሣሳበት ጊዜ የእግዚአብሔር ፈቃድ ምን እንደሆነ ፈትነን ከክፉ ምግባራት የምንርቅበትን የእግዚአብሔርን መንገድ ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ ይህን ለማድረግም የሚያስችሉን መንፈሳዊ ትጥቆችን መያዝ አስፈላጊ ነው፡፡ እነሱም በመንፈሳዊ ሕይወት ጠንካራ የሚያደርጉንና ፍቅረ እግዚአብሔርን የሚጨምሩልን ጾም፣ ጸሎት፣ ስግደት ሲሆኑ ቅዱሳት ገዳማትን መሳለምና የቅዱሳንን ታሪክ እንዲሁም የኑሮ ፍሬ መመልከት ወሳኝ ነው፡፡
ለዚህም ነው ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ “በነፍሳችሁ ዝላችሁ እንዳትደክሙ ከኃጢአተኞች በደረሰበት እንዲህ ባለ መቃወም የጸናውን እስኪ አስቡ” (ዕብ.፲፪፥፫) በማለት ያስተማረን፡፡
ስለዚህ በኑሮአችን መንፈሳዊ ፍሬ ማፍራት እንዲቻለን የቀድሞ ስንፍና ካለብን እሱን እየተውን በትጋት መንፈሳዊ ሩጫችንን ልንፈጽም ያስፈልጋል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሁሉንም በትጋት እንደ ፈጸመ ሲያስረዳን “መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ ሩጫዬንም ጨርሻለሁ ሃይማኖቴንም ጠብቄአለሁ እንግዲህስ የጽድቅ አክሊል ይቆየኛል ይህንም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው እግዚአብሔር በዚያ ቀን ለእኔ ያስረክባል ደግሞም መገለጡን ለሚወዱት ሁሉ እንጂ ለእኔ ብቻ አይደለም” (፪ኛጢሞ.፬፥፯) ብሏል፡፡
ያለንበት ዘመን መንፈሳዊ ሕይወታችንን፣ አገልግሎታችንን ብሎም እምነታችንን የሚፈታተን መሆኑ ይታወቃል፡፡ ለዚህ ደግሞ የመጀመሪያ ተፈታኝ ወጣቱ ክፍል እንደሆነ የማይካድ ሐቅ ነው፡፡ ወቅቱ ለመንፈሳዊ ሕይወት ፈተና የሚሆን ዓለማዊነት (secularism) በዘመናዊነትና በሥልጣኔ ሰበብ ተስፋፍቶ ትውልዱ ፈጣሪው እግዚአብሔርን እየተወ በሙት ፍልስፍና እየተመካ ወደ ጥፋት እየሄደ መሆኑ ላስተዋለው ሁሉ ግልጽ ነው፡፡ ይህም ዓለም ወደ አንድ መንደር (globalization) የመጣችበት፣ ቴክኖሎጂው እጅግ የመጠቀበት ወቅት ስለሆነ ሩቅ መሔድ ሳይጠበቅብን ባለንበት ሥፍራ ሆነን ዓለምን ስንቃኝ የባህል መወራረሶች እንዳሉ ልብ ይሏል፡፡ እነዚህ የየሀገራቱ ባህሎች ደግሞ የራሳቸውን ተጽእኖ በሃይማኖታችንና በሥነ ምግባራችን ላይ ያሳድራሉ፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያ የብዙ ባህሎች፣ ቋንቋዎችና ማኅበረሰቦች ባለቤት እንደሆነች ይታወቃል፡፡ በቀደሙት አባቶቻችን ሃይማኖታዊ ሆነ ባህላዊ ጥንካሬዎች ያላትን ሀብት ጠብቃ ያስቆየች ሀገር ናት፡፡ እስከ አሁንም ድረስ የራሷ ቋንቋ፣ የራሷ ፊደል፣ የራሷ ባህል ያላት ስትሆን ብዙዎች ባህሎቻችን ሃይማኖታዊ አንድምታ፣ ሃይማኖታዊ ምልከታ፣ ሃይማኖታዊ ትውፊት፣ ሃይማኖታዊ ይዘት አላቸው፡፡ በርግጥ በሀገራችን ስለነበረውና ስላለው ባህል ስናነሣ ጠቃሚና ጎጂ ብለን በሁለት መልኩ ማየቱ አስፈላጊ ነው፡፡ ስለዚህ ጎጂ ባህሎችን እያስወገድን ጠቃሚ የሆኑ ባህሎችን፣ ትውፊቶችን ግን ልናስቀጥላቸው ይገባል፡፡
ነገር ግን ዓለም ወደ አንድ መንደር በመጣችበት በዚህ ዘመን ከላይ እንዳየነው በተለያዩ መገናኛ ብዙኀን በሚታዩት፣ በሚሰሙትና በሚለቀቁት ነገሮች ጆሮአችን ብዙ ነገሮችን ይሰማል፡፡ ዐይናችንም ጠቃሚም የሆኑ ወይም በተቃራኒው ደግሞ ለክርስቲያናዊ ሕይወታችን ጎጂም የሆኑ ነገሮችን ያያል፡፡ ስለዚህ የራሳችንን ጠቃሚ ወጎችን ባህሎችን፣ ትውፊቶችን ሳንለቅ በምዕራቡ ዓለም የሚታዩትን ልቅ የሆኑ ተግባሮችንና እሳቤዎችን አለማስተናገድ ብልህነት ነው፡፡
እነዚህ ከውጪው ዓለም የምናያቸውና የምንሰማቸው ለሃይማኖታችንና ለበጎ ምግባራችን ጠቃሚ ለሆኑ ወጎቻችንና ትውፊቶቻችን ፀር ወይም ማደብዘዣ ብሎም ማጥፊያ የሆኑ በሥልጣኔ ስም ርኵሰትን የሚያስፋፉትን ፀረ ሃይማኖት ተግባራት ንቆና ተጸይፎ ማለፍ ከአሁኑ ትውልድ የሚጠበቅ ጥበብ ነው፡፡ በርግጥ በውጪው ዓለም የሚታዩና የሚሰሙ ሁሉም ጎጂ ናቸው ወይም ለሃይማኖታችንና ለመንፈሳዊ ሕይወታችን እንቅፋት ናቸው ማለት አይደለም፡፡ ምክንያቱም ቴክኖሎጂው ያፈራቸው፣ ሥልጣኔው ያስገኛቸው መልካም ነገርን በቀላሉ የምናስተላልፍባቸው፣ሃይማኖትን የምንሰብክባቸው፣መረጃ የምንለዋወጥባቸው በአጠቃላይ አገልግሎታችንን በቀላሉ የምንከውንባቸው ብዙ ጠቃሚ ነገሮችም አሉ፡፡
ዓለም አሁን ለደረሰችበት የሥልጣኔ ማማ ቅርብ የሆነ ወጣቱ ትውልድ እነዚህን ጎጂና ጠቃሚ ምንጮችን በማስተዋል በጥልቀት ሊመረምራቸውና ሊያጤናቸው ይገባል፡፡ ምክንያቱም የአሁኑ ዘመን በልማድና በየዋህነት ብቻ የምንኖርበት አይደለም፡፡ ብዙ ምርምርንና ጥናትን ይጠይቃል፡፡ ለዚህም ነው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን ወደ ዓለም ሲገቡ እንዴት ሆኖ ማገልገልና መኖር እንዳለባቸው ሲመክር “እነሆ እኔ እንደ በጎች በተኩላዎች መካከል እልካችኋለሁ እንግዲህ እንደ እባብ ብልሆች እንደ ርግብም የዋሆች ሁኑ” (ማቴ.፲፥፲፮ ) ብሏቸዋል፡፡
ስለዚህ ከፊት ይልቅ ዘመኑ እየከፋ ስለመጣ ያውም የዓለሙ ፍጻሜ ስለደረሰ ምልክቶቹም እየተፈጸሙ ስለሆነ አብዝተን ልንጾም፣ ልንጸልይ፣ ልንሰግድ ያስፈልጋል፡፡ አሁን የምንተኛበት ጊዜ ሳይሆን የምንነሣበት፣ የምናቀላፋበት ጊዜ ሳይሆን የምንነቃበት ወቅት ነውና ከፊት ይልቅ መትጋት ተገቢ ነው፡፡ ይህ ዘመን እጅግ ፈታኝ ነውና እናስተውል፤ እንትጋ፡፡
እግዚአብሔር ለሁላችን ትጋቱን ማስተዋሉን ያድለን አሜን፡፡
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!