በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻነት አወጣን (ገላ. 5÷1)
በዲ/ን ታደለ ፈንታው
በኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያናዊ አስተምህሮ ያሉት ምርጫ ሁለት ናቸው፡፡ እነርሱም የቅዱስ ጋብቻ ሕይወትና የምንኩስና ሕይወት ነው፡፡ የቅዱስ ጋብቻ ሕይወት ደግሞ የእጮኝነት ጊዜያት አሉት፡፡ አንድ ወደ ጋብቻ ለመምጣት የወሰነ ወይም የወሰነች ወጣት ሦስት ነገሮችን እንዲያሟላ (እንድታሟላ) ይመከራል፡፡ እነዚህም
- መንፈሳዊ ብስለት
መንፈሳዊ ብስለት እንዲህ ከሚለው የእግዚአብሔር ቃል ጋር ይስማማል፡ ፡ “ጎበዞች ሆይ ክፉውን አሸንፋችኋልና እጽፍላችኋለሁ” (1ዮሐ.2፥13) ተብሎ ስለተጻፈ ክፉ የሆነውን ወይም ኀጢአት የሆነውን ነገር ጽድቅ ከሆነው ለይቶ ማወቅ፣ ክፋት፣ ማስወገድና መልካም በሆነው በጽድቅ መንገድ መመላለስ ነው፡፡
መንፈሳዊ ብስለትን የተላበሰ ሰው በገላትያ መልእክት የተገለጡትን የእምነት ፍሬዎች ይዞ ይገኛል፡፡ እነርሱም “ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ እምነት፣ የዋሃት፣ ራስን መግዛት ነው” /ገላ.5፥22/ በመንፈስ ያልበሰለ ሰው ለራሱ ሕይወት የማይራራውን ያህል ለሰው ሕይወትም አይራራም ይህ ደግሞ ጭካኔ ነው፡፡ ‹‹ ስለ እነዚህ ነገሮች ምንም ብታውቁ በእናንተ ዘንድ ባለች እምነት /እውነት/ ምንም ብትጸኑ ሥራ እነዚህ ዘወትር እንዳሳስባችሁ ቸል አልልም” /1ኛ.ጴጥ.1፥12/፡፡ ስለሆነም መንፈሳዊ ብስለት ጽድቅን ከኀጢአት፤ ክፋትን ከበጎነት ለመለየት የሚያስችል ስለሆነ ወደ ትዳር ዓለም ለመግባት የሚያስቡ ሊይተገብሯቸው ከሚያስፈልጉ ነገሮች ዋነኛው ነው፡፡
- የሥነ ልቡና ብስለት
የሥነ ልቡና ብስለት በመንገዱ ላይ ያገኘውን የሚለክፍ /የምትለክፍ/ ጠይሟን ሲያይ ወደ ጠይሟ ቀይዋን ሲመለከት ወደ ቀይዋ የሚመለከት፤ ጥቁሯን ሲያይ በጥቁሯ ፍልቅልቅነት የሚሸነፍ ልብ፣ እንዲህ ዓይነት ልብ ኦርቶዶክሳዊ ልብ አይደለም። የእውነተኛ ክርስቲያኖች መታወቂያም አይደለም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሰይጣን ወይም አንዳንድ ክፉ ባልንጀሮች አጣኻት /አጣሽው /ቅጠፋት/ ቅጠፊው ሊሉን ይችላሉ፡፡ አምኖንን በባልንጀራው ተመስሎ እኅቱን ትዕማርን አጣኻት አለው፡፡ የማይሆን ሥራን ካሠራው ሕይወቷን ካበላሸው በኋላ ግን ጠላት፡፡ አሁንም በእኛ ዘመን በብዙ ተቋማቶቻችን እየሆነ ያለው ተመሳሳይ ነገር ነው፡፡ ክርስቲያን አንድ ትልቅ ነገር ማመን አለበት፤ ሊያስጨንቀው የሚገባው የእርሱ መልካም ሆኖ መገኘት ነው፡፡ ሰው መልካም ከሆነ መልካም የሆነ እግዚአብሔር የመልካም መገኛ እግዚአብሔር፤ መልካም የሆኑ ሴቶች ልጆቹን መልካም ለሆኑ ወንዶች ልጆቹ ያዘጋጃል ይጠብቃል፡፡ እግዚአብሔር ሲፈቅድ፣ ጊዜውም ሲደርስ ወረፋ መጠበቅ እንኳን አያስፈልገውም፡፡ ስለዚህ በስሜት ከመነዳት ይልቅ የሥነ ልቡናን ብስለት ገንዘብ ማድረግ ይገባናል፡፡ ይህም በተረጋጋ ልቡና የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ በመረዳት፤ ቅዱሳት መጻሕፍት በዚህ ላይ ምን ብለዋል እንዲሁም በዚህ ጉዳይ አበው እንዴት አስተማሩ በማለት በመጠየቅ ወደዚህ ስሜት በሥጋዊ ጥበብ ያይደለ በመንፈሳዊ ጥበብ መድረስ ይቻላል፡፡
- የኢኮኖሚ ብስለት
የሃይማኖት ብስለቱ የሥነ ልቡና መረጋጋቱ ቢኖርም እንኳን እንቅፋት በማይገጥመው መልኩ ለመጓዝ ከተጠቀሱት በተጨማሪ የኢኮኖሚ ብስለት መኖር መቻል አለበት፡፡ ክርስቲያን በስሜት በዘፈቀደ የሚነዳ አይደለም፤ ተስፋ የማይሆን ነገር ተስፋ አድርጎ ራሱንም አያታልልም፡፡ በተለይ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚገኙ ተማሪዎች ተማሪ እንደ መሆናቸው መጠን ገና የትምህርት ጊዜያቸውን ሳይጨርሱ ወይም ራሳቸውን በራሳቸው መርዳት ሳይጀምሩ ወደዚህ የሕይወት ጎዳና ለመግባት ማሰብ በትምህርታቸው ላይ የሚያሳድረው ተጽኖ በቀላሉ የሚገመት አይደለም፡፡ ስለዚህ በኑሮአችን መደርጀት መጀመራችንን ማረጋገጥ አለባቸው፡፡ አሁን በጊዜያችን ለምንመለከታቸው ፍቺዎች ምክንያት ናቸውና፡፡ እነዚህን ሦስት ነጥቦች ለአብነት አነሣን እንጂ ብዙ ነጥቦችን መዘርዘር ይቻላል፡፡ የግቢ ጉባኤ ሕይወት ወጣቶች ከቤተሰቦቻቸው በርቀት ያሉበት ስለሆነና ምናልባትም ከሚያውቃቸው ማኅበረሰብ ራቅ ብለው የሚኖሩበት ሕይወት ስለሆነ አስቀድመው የነበሩበትን የተዐቅቦ /መጠበቅ/ ዘመን እንደባርነት የመቁጠርና በዚያው መንገድ ራሳቸውን መጠበቅ ሲገባቸው ልቅ ሆነው የሚቆዩበትን ወራት ነጻነት ብለው ሊጠሩ ይችላሉ፡፡ ይህ ነጻነትን በተሳሳተ መልኩ ከመተርጎም የሚነሣ ነው፡፡ ሐዋርያው “በነጻነት እንድንኖር ክርስቶስ ነጻነት አወጣን” ያለው የነፍሳችንን ነጻነት ነው፡፡ ከእግዚአብሔር የሚለይ ልጅነታችንን የሚያስጥል ምንም ዓይነት ነገር ክፉ ባርነት ነው፡፡ ሰው ተሸንፎ ለተገዛበት ለዚያ ነገር ባሪያ ነውና፡፡ አንዳንዶች ለሥጋቸው አርነት ለመስጠት የወሊድ መከላከያን ተጠቅሞ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ማድረግን አሊያም የከፋ ርምጃን ሲወስዱ ይታያሉ፡፡ በክርስትና ሕይወት ዓለም የምታቀርበው ምርጫ መታቀብ፣ መወሰን፣ መጋባትና መጠቀም የሚሉ ምርጫዎች የሉም፡፡ እነዚህ ለክርስቲያን የባርነት መንገድ እንጂ የነጻነት መንገዶች አይደሉም፡፡ “ወዳጆች ሆይ አሁን የምጽፍላችሁ መልእክት ይህች ሁለተኛይቱ ናት በቅዱሳን ነቢያትም ቀድሞ በሐዋርያትም የተባለውን ቃል በሐዋርያቶቻችሁም ያገኛችኋትን የጌታንና የመድኀኒት እንድታስቡ እያሳሰብኋችሁ ቅን ልቡናችሁን ….›› /2ጴጥ.3፥1-2/፡፡ ‹‹የእግዚአብሔርን ስንወድ ትእዛዛቱንም ስናደርግ የእግዚአብሔርን ልጆች እንድንወድ በዚህ እናውቃለን ትእዛዛቱን ልንጠብቅ የእግዚአብሔር ፍቅር ይህ ነውና›› /1ኛ ዮሐ.5፥2/
ስለዚህ የእግዚአብሔር የሆነ ወጣት የእግዚብሔር ለሆነችው ኮረዳ ይራራል፣ ያዝናል፣ ይጠብቃል እንዲሁም ይንከባከባታል፡፡ እርሷም ሆነች እርሱ የእግዚአብሔር መልካምነት የሚገለጥባቸው ሰብአዊ ፍጡሮች ሊሆኑ ይገባቸዋል፡፡ ነገር ግን አንዳንዶች የነጻነትን ትርጉም በደንብ ካለመረዳት የተነሣ ለሥጋ ፋቃዳቸው ልቅ የሆነ ነጻነትን በመስጠት፤ ከክርስትና ሕይወት ጋር የማይሔድ፤ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹በሆነው ሁሉ ላይ ሥልጣን አለኝ፤ ግን ሁሉ የሚጠቅመኝ አይደለም፤ ሁሉም ይቻለኛል፤ ነገር ግን በእኔ ላይ እንዲሠለጥን የማደርገው ምንም የለም፡፡›› ያለውን በመዘንጋት ቀናውን መንገድ ስተው የሚጓዙ አሉ፡፡ ስለዚህም ‹‹የመዳን ቀን ዛሬ ነው›› እንዳለ መጽሐፍ፤ በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረ የሰው ልጅ ከጎኑ ለተገኘች ኮረዳ፤ እርሷም እንደዚሁ መልካም በመሆን በመንፈሳዊ መንገድ ይጓዙ ዘንድ ይገባል፡፡ የነጻነት ትርጉሙ ይህ ነው፡፡ ሐዋርያው “በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻነት አወጣን እንግዲህ ጸንታችሁ ቁሙ እንደገና በባርነት ቀንበር ደግማችሁ አትያዙ” ያለው ይህንን ነው፡፡